>
10:24 pm - Tuesday July 5, 2022

ቪቫ ምንሊክ!!! (ዘመድኩን በቀለ) 


ቪቫ ምንሊክ!!!
ዘመድኩን በቀለ 
የዓድዋን ድል ሊቀብሩት ያሉ ሁሉ ተቀበሩ። ሊያጠፉት ያሉ ሁሉ ብን ብለው ጠፉ። ሊያፈርሱት የነበሩት ሁሉ በቁማቸው ፈረሱ። እምዬ ሚኒልክና የዓድዋ ድል ግን እንደ ደቦል አንበሳ በከፍተኛ ድምጽ እያገሳ ተነሳ!!!
• 7 ጦር
• 5 ጎራዴ
• 23 ጠብ መንጃ
• 42 ጎራዴ የእንጨት
• 10 ጋሻ
• 17 ዝናር
• 850 ቀልሀ የእንጨት
• 6 መድፍ በአዲስ አበባ ልጆች ተዘጋጅቷል።

ኢትዮጵያ
| ~ አዲስ አበባ • ሸገር • አዱገነት
ነገ ልጆችሽን የአብራክሽን ክፋይ አዲስ አበቤዎችን ከሜክሲኮ አደባባይ ጀምሮ አጅበሽ ተከተያቸው። ወስልተህ የቀረህ እንደሆን ማርያምን ምሬ አልምርህም ብለውሃል። እምዬ ምኒሊክ ጊዮናውያኑ።
•••
እኔ ዘመዴ ስለ ተሃድሶ መጻፍ ያቆምኩት ሀገር ምድሩ ስለ ተሃድሶ መጻፍ ስለጀመረ ነው። ደስ ይላል። ስለ ዓድዋ መጻፍ ያቆምኩት ሀገር ምድሩ ስለ ዓድዋ መጻፍ አይደለም ራሱ ዓድዋን መሆን በመጀመሩ ነው። ስለ ዓድዋ ዛሬ የማይጽፍ፣ የማይናገር፣ የማይሰብክ፣ የማይዘምር የለም።
•••
አይደለም ስለ አጼ ሚኒልክ ስለ ታላቁ ድል ስለዓድዋና በአል አከባበር መናገር ይቅርና ስለ ሂደቱ ማውራትና አፍ አውጥቶ መናገር በራሱ የሚያስቀስፍ በሚመስልበት ዘመን፤ ያ ዘመን ተቀይሮ በዚያው በእምዬ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተሾመው 7ተኛው ንጉሥ ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ስለ ዊዝደማቸው የምንሰማበት ዘመን መጣ። ኦነጉ ታከለ ኡማም የዓድዋን በዓል አድማቂ ሆኖ አረፈው። ይሄ ለኦሮሞ ራሱ ታላቅ ድል ነው።
•••
እናም ወዳጄ ዛሬ የዓድዋ ድል ሀገር አቀፍ ሆኗል። ከህጻን እስከ አረጋዊው ቀና ብሎ መናገር ጀምሯል። እነ ሁሉም ኬኛ ሳይቀር ሳይወዱ በግዳቸው ዓደዋ ኬኛ ለማለት ተገደዋል። የቀራቸው ከሚኒልክ ጋር ያላቸው ጠብ ነው እሱም የተስፋዬ ገብረ እባብ የፈጠራ ዲስኩር በሊቃውንቱ፣ በኦሮሞ ልጆች ሲደበደብ ፍርስርሱ ይወጣና ሚኒሊክ ኬኛ ባይ ትውልድ ይፈጠራል። ቱ ምን አለ በሉኝ ዘመዴ ሩቅ አይደለም። በጣም ቅርብ ጊዜ ነው።
•••
ወዳጄ እግዚአብሔር አምላክ ሲጣላህም ሆነ ሲታረቅህ አንተን የሚቀጣበትም ሆነ የሚታረቅበት አርጩሜውንም ሆነ ቅቤውን ከሩቅ አያመጣውም። እዚያው ከመሃልህ ከጉያህ ከብብትህ ስር ነው የሚያወጣልህ።
•••
መለስ ዜናዊ የተባለ ክፉ ኢህአዴግ የተባለ በህወሓት ተጠፍጥፎ የተሠራ ፓርቲ ከዚያው ከጭንህ ስር ዱብ አለና ህይወት ዘርቶ፣ በሜዳህ ድሆ፣ ከምንጭህ ጠጥቶ፣ አየርህን ተንፍሶ፣ እህልህን በልቶ፣ አንተኑ መስሎ፣ አንተኑ አህሎ ተሯሩጦ ከማማው ከዙፋኑ ከአናትህም ላይ ወጥቶ ያለ አቅሙ ይህቺን ታላቅ ሀገር እመራለሁ ብሎ የውርደት ካባ አልብሶ፣ እሱ ተዋርዶ እኛንም አዋርዶ በመጨረሻ ፈጣሪ በሚያውቀው እኛ በማናውቀው በኪነጥበቡ እንደጢስ ተንኖ፣ እንደ ጉም በንኖ ከፊታችን እልም ብሎ ጠፋ። ህልም ዕልም ሆነ።
•••
ላለፉት ድፍን 26 ዓመታት የዓድዋ ድል በደመቀ ሁናቴ እንዳይከበር የዓድዋው የባንዳ ልጆች ስብስብ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። የዓድዋ ጉዳይ ሲነሳ ጣልያንና ህወሓት እኩል ይናደዳሉ። ይበሳጫሉ። ይነስራቸዋልም። አሁን ደግሞ በተለይ የአክራሪው ኦነግ ኃይል በፊት በፊት ዓድዋን ጭምር አታንሱብኝ ይሉ የነበሩት አሁን አሁን እየበሰሉ ሲመጡ ዓድዋን ኬኛ ጠላታችን ግን ምኒልክ ነው ባይሆነው አርፈውታል። ቡድኑን ያለ አምበል፣ ጦር ያለ አዛዥ፣ ሀገር ያለ መሪ፣ ቤተሰብ ያለ አስተዳዳሪ ይሆናል እንዴ? ቀበሌ እንኳን ያለ ሊቀመንበር፣ ዕድር ያለ ዳኛ፣ የማይታሰብ እኮ ነው። የምን ከሥጋው ጦመኛ ነኝ ከመረቁ ስጡኝ ነው። ዓድዋን ያለ እምዬ ምኒሊክ ማሰብ አይቻልም።
•••
ሲሚንቶ በጢኒጢዬ አካፋ ቤኒሻንጉል ክልል የህዳሴው ግድብ መሠረት ላይ ስላስቀመጠ ብቻ “ዓባይን የደፈረ መሪ” እያለ አታሞውን ሲደልቅ የሚውል የባንዳ የልጅ ልጅ ሁላ ጣልያንን አፍር ከድሜ ያበላውን የኢትዮጵያን ጦር እየመራ ሺ ኪሎ ሜትር አቋርጦ ዓድዋ ድረስ የተመመውን ኢትዮጵያዊ ሙሴ የእምዬ ምኒልክ ስም ሲነሳ ግን ወባ እንደያዘው ሰው ያንቀጠቅጠዋል። አረፋም ያስደፍቀዋል። እንቁላል ከመቀቀል፣ ሴቶቹን ለነጭ ከመገበር የታደገውንና ነጻ አውጥቶ በስሙ ሀጎስ ገመቹ ተብሎ እንዲጠራ ያደረገውን መሪውን ማየት ያስጠላዋል።
•••
ብዙዎች ሊቃውንት የዓድዋን በዓል ሀገር አቀፋዊ ለማድረግ በብርቱ ጥረዋል። ነገር ግን በህወሓት ሴራና ተንኮል ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ነገርግን የዛሬ ስድስት ዓመት እንደ ድንገት የተጀመረው ጉዞ ዓድዋ የሌለ መነቃቃትን ፈጥሮ የተቀበረውን የዓድዋ ክብር ከመቃብር ቆፍሮ ፈንቅሎ አውጥቶታል። ዕድሜ ለያሬድ ሹመቴና ለጓደኛው መሃመድ ካሳ። ዕድሜ ለጉዞ ዓደዋ ቀደምት መስራቾች ለእነ ብርሃኔ ንጉሤ፣ ዕድሜ ለጉዞ ዓድዋ አባላት በሙሉ። ይኸው የጦሩ መሪ እምዬ ምኒልክም ክብራቸው ከፍ አለ። የዓደዋ በዓልም ሀገር አቀፍ ሆነ። ካርኒቫል መሰለ።
•••
የዓድዋን ድል ሊቀብሩት ያሉ ሁሉ ተቀበሩ። ሊያጠፉት ያሉ ሁሉ ብን ብለው ጠፉ። ሊያፈርሱት የነበሩት ሁሉ በቁማቸው ፈረሱ። እምዬ ሚኒልክና የዓድዋ ድል ግን እንደ ደቦል አንበሳ በከፍተኛ ድምጽ እያገሳ ተነሳ። ቪቫ ምንሊክ።
•••
አሁን ደግሞ በእነ ወጣት በረከት ጋሻው የሚመራውና ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ልጆች የተመሰረተው “ግዮናውያን የኪነጥበብ ቡድን” “ከሕብረ ቀለምና የጥበብ በልጆቿ የኪነ ጥበብ ቡድን ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የቴአትር ተማሪዎች አስተባባሪነት ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄድና ከአርቲስት ሚካኤል በፊት ዝግጅት የጀመሩ ልጆች ዘንድሮ በኃይለኛው ለዓደዋ በአል መዘጋጀታቸውን ገልጸውልኛል።
•••
ነገ ከንጋቱ 11:30 ከሚክሲኮ ተግባረድ ትምህርት ቤት ጋር ይነሱና በእግራቸው ተጉዘው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በነፃነት እየፎከሩ፣ እያቅራሩ፣ እየሸለሉ፣ ጉዞ ወደ ሚኒልክ አደባባይ ያደርጋሉ። በዚያም ያዘጋጁትን ፉከራ ካሳየዩ በኋላ እንደገና ጉዞ ወደ አድዋ ድልድይ ያደርጋሉ። ከዓድዋ ድልድዩ ዝግጅት በኋላ ግብር (የምሳ) ግብዣ በሜክሲኮ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እናደርጋለን ብለውኛል።
•••
ለዚህ በአል ድምቀት ብዙ ድካም፣ ብዙ ላብ፣ ብዙ ገንዘብ ያፈሰሱ ኢትዮጵያውያን የድል ልጆች ስምም ተሰጥቶኛል።
አስተባባሪው በረከት ጋሻው፣ ናትናኤል ከተማ፣ አስጠራው ከበደ፣ ዳዊት ዳምጤ፣ ሲኞር፣ ብርሃኑ፣ ዳዊት፣ አዳሙ ተጠቅሰዋል።
•••
በዘንድሮው ጉዞ ከሜክሲኮ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ከጊዮናውያኑ ጋር የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር አባላት፣ የአንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ዳጋፊዎች፣ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች፣ የባህርዳር ከነማና የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች አብረዋቸው እንደሚጓዙ ነግረውኛል።
እናት አዲስ አበቤዎች ዘር ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለያችሁ፣ እንቅልፍም ሳያታልላችሁ ነገ በጠዋት ሜክሲኮ አደባባይ ይሁን ቀጠሮአችሁ።
ዓድዋ የዐማራ ነው።
ዓድዋ የኦሮሞ ነው።
ዓድዋ የትግሬ ነው።
ዓድዋ የአፋሩ ነው።
ዓድዋ የቤኒሻንጉሉ ነው።
ዓድዋ የሶማሌው ነው።
ዓድዋ የወላይታው ነው።
ዓድዋ የሲዳማው ነው።
ዓድዋ ጉራጌው ነው።
ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ነው።
ዓድዋ የአፍሪካውያን ነው። 
በአጠቃላይ ዓድዋ በዓለም ላይ ላሉ ለነፃነት ፈላጊዎች ሁሉ በዓላቸው ነው። ይሄው ነው።
ሻሎም!  ሰላም  ! 
የካቲት 22/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic