>

“ የዓድዋው ድላችን ወደ ሌሎች ድርብ ድርብርብ ድሎች መሻገሪያችን፤ የድካም መርቻ ጉልበታችን፤ በዝለት ጊዜም መበርቻችን ነው” ጠ/ ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

“ የዓድዋው ድላችን ወደ ሌሎች ድርብ ድርብርብ ድሎች መሻገሪያችን፤ የድካም መርቻ ጉልበታችን፤ በዝለት ጊዜም መበርቻችን ነው” ጠ/ ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

 

 

በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ

ለመላው አፍሪካውያንና ለዓለም ነጻነት ወዳድ ሕዝቦች ሁሉ

በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት ለምናከብረው ለ123ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን፡፡

ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን እናቶቻችን እና አባቶቻችን በወራሪው የጣልያን ጦር ላይ በዓድዋ የተቀዳጁት ታላቅ ወታደራዊ ድል፣ በኢትዮጵያ ምድር የኢትዮጵያ እንጂ የቅኝ ገዢ ሮማ ባንዲራ እንዳይውለበለብ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፥ ፖለቲካዊ ነጻነታችንም ከዘመን ዘመን ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር ያስቻለ ደማቅ የታሪክ አሻራ ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ላይ በደምና በአጥንት የከፈሉት መሥዕዋትነት የዛሬው እና የነገው ትውልድ ቀኝ ግዛት ቀንበር ትከሻው ጎብጦ አንገቱን ደፍቶ እንዳይኖር አስችሎታል፡፡ የዓድዋው ድላችን ቀንተንም – ነቅተንም በዓለም ፊት ለመቆማችን አባቶቻችን ያቀናኝጁን አክሊል ነው፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፥፣ በወራሪውና በተስፋፊው የኢጣልያ ጦር ላይ ጀግኖቹ እናቶቻችንና አባቶቻችን የተቀዳጁት ድል ከራሳችን ነጻነት ባሻገር ለመላው አፍሪካ ብሎም በባርነት ቀንበር ይማቅቁ ለነበሩ መላ የዓለማችን ሕዝቦች ሁሉ ተስፋ የፈነጠቀ እና ወኔ ያሰነቀ ታሪካዊ ክሥተት ነው፡፡ ይህን በውል ለመረዳት መቻል ትናንታችንን ዘክረን፤ ዛሬን መርምረን፤ ነጋችንን ለመቃናት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የዓድዋው ድላችን ወደ ሌሎች ድርብ ድርብርብ ድሎች መሻገሪያችን፤ የድካም መርቻ ጉልበታችን፤ በዝለት ጊዜም መበርቻችን ነው፡፡ ለዚህም ከዓድዋ ድላችን ወዲህ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የተቀዳጀናቸው ስኬቶቻችን ህያዋን ምስክሮች ናቸው፡፡ የዛሬው ትውልድም እንደ አባት እናቶቹ – እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ ሁሉ የሚገጥሙትን ፈተናዎች እና የሚያደናቅፉትን ተግዳሮቶች በድል በመወዛጣት የአባቶቹና የእናቶቹ ልጅ መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥበት ታሪካዊ የዘመን አንጓ ላይ ቆሟል፡፡

ዓድዋ ከትግል እና ድል የሚሻገር የተጨቋኞች ረቂቅ ኃይል ነው፡፡ ዓድዋ መልከ ብዙ ትርጓሜና ሕይወታዊ አስተምህሮ በውስጡ አቅፎ የያዘ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ፍልስፍና ነው፡፡ በፈተና ጊዜ፣ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ፣ የመደመር መንፈስና ንቅናቄ አንድን ሕዝብ ሊያደርስበት የሚችለውን የልዕልና ጫፍ ያየንበት ነው፡፡ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ከመሐልና ከዳር እንዲሁም ከምሥራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጫፍ፣ ከሰሜን ጫፍ እስከ እስከ ደቡብ ጫፍ: አብረውና ተባብረው የማንነታቸውን ልክ ያሳዩበት የመሥዋዕትነታቸው ውጤት ነው፡፡

ዓድዋ እኛ ነን፡፡ አትንኩኝ ባይነት – ጸዳላችን፣ የሀገረ ፍቅር ስሜት – ጥበባችን፣ ለአንድ ዓላማ መጽናት – ጥለታችን፡ ጀግንነትና ነጻነት ወዳድነት ደግሞ – የራስ ቁራችን ሆኖ የዋልንበት – እኛ ማለት ዓድዋ ነን፡፡ የሀገር መሪዎቻችን ሕዝብን የማስተባበር ችሎታ፡፣ የጦር ጄኔራሎቻችን የጦር አመራር ጥበብ፡ የዲፕሎማቶቻችን የዲፕሎማሲ ልቀት የታየበት የጥቁር ሕዝቦች የፀረ ኮሎኒያሊዝም ገድል ነው – ዓድዋ፡፡

የዓድዋ ድል የሴት ኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ተጋድሎና የላቀ ሚና መገለጫ ነው፡፡ እህቶቻችንና እናቶቻችን ከስንቅ ዝግጅት እስከ ጦር መሪነት፣ በግጥምና ዜማ አርበኞቹን ከማጀገን እስከ ቁስለኛ ተንከባካቢት ከትጥቅ አቀባይነት እስከ ምርኮ ሰብሳቢነት፣ የተሰለፉበት ደማቅ አደባባይ ነው – ዓድዋ፡፡ የዓድዋን ድል የሚያከብር ሕዝብ የሴቶች ክብር የገባው መሆን አለበት፡፡ ዓድዋ መሪ እና ተመሪ – አስተዳዳሪ እና ተዳዳሪ ሲደማመጡ፥ ሲግባቡና ለአንዲት ሀገር ሲሠሩ የሚበግራቸው ነገር እንደማይኖር አስተምሮን ያለፈ ታሪክ ነው፡፡

የክብርህ መመኪያ- ደስታ እና ሕይወትህ የሆነችውን ውብ ሀገር ከወራሪ ትታደግ ዘንድ የምሥራቅ – የምዕራብ- የሰሜን እና የደቡብ ሰው ፊትህን ወደ ዓድዋ አዙረህ ወረኢሉ ላይ ቆየኝ ያለውን የመሪውን የአፄ ምኒልክን ቀጠሮ አክብሮ ለነፍስ ቀጠሮ በነፍስ የደረሰ ሳተና ሕዝብ፣ የድል አክሊል የተቀዳጀበት ታሪካዊ ቀን ነው – ዓድዋ፡፡

በዛሬው ዕለት የዘንድሮውን የድል በዓል ስናከብር እንደዚህ ዘመን ነዋሪና እንደ አዲስ ትውልድ፣ በድሉ ውስጥ የተካተተውን ሰምና ወርቅ፣ ምሥጢርና ቅኔ በጥልቀት በመረዳት መሆን ይኖርበታል::

በትክክል ታሪክን ለሚመረምር ትውልድ ዓድዋ ውስጥ – ህልውናን አጽንቶ የመኖር፤ ዓድዋ ውስጥ – ዲፕሉማሲ፡፡ ዓድዋ ውስጥ – ወታደራዊ ስትራቴጂ፡ ታላቅ ውስጣዊ የሕዝቦች ኀብረትና አንድነት፣ ጥበብ እና ተግባቦት፣ ፍቅር እና መስጠት፣ ክብር እና ጀግንነት ሞልቶና ሰፍቶ የነበረ መሆኑን እናያለን፡፡ አንድን ሀገራዊ ድል ለማስመዝገብ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የግድ እንደሚል እንማራለን፡፡ የሀገር መሪዎች፣ የጦር አበጋዞች፣ ቃፊሮች፣ ወታደሮች፣ ስንቅ አዘጋጆች፣ ሐኪሞች፤ አዝማሪዎች፤፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እንጨት ፈላጮች፡፣ ውኃ ቀጅዎች፥ የጥበብ እድ ባለሙያዎች፡ ታሪክ መዝጋቢዎች፤ ሌላው ቀርቶ ከብቶችና አጋሠሶች እንኳን ሳይቀሩ ለድሉ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አድርገዋል፤ መደመር ማለት ይሄ ነው፡፡ በጦር መግሪያ አቅም፤ በሀብት፣ በወታደራዊ አደረጃጀት እና በዘመናዊ የጦር ስልት በወቅቱ ታላቅ ደረጃ ደርሻለሁ ብሎ ያሰበውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ከዚያ በፊት ባልታየና በታሪክ ውስጥ ባልተስተዋለ ጀግንነት፣ አርበኞች እናቶቻችንና አባቶቻችን ድል የመቀዳጀታቸው እና የማሸነፋቸው ቁልፍ፡: ምሥጢር ውስጣዊ ልዩነታቸውን አቻችለው በኅብረትና በአንድነት ተደምረው፤ ለአንድ ሀገራዊ ግብ፣ በፍቅር መቆማቸው ነው፡፡ ብልህ ትውልድ ከዓድዋው የድል መሠዊያ ላይ ሊጭር የሚገባው ቁም ነገርም ይሄው ነው፡፡

የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንቶቹ ኢትዮጵያውያን በሕይወት መሥዋዕትነት ብቻ ሳይሆን እየኖርን በመሥራት፣ በደም የተቀበልናትን ሀገር ነጻነቷን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን መታገል ይገባናል፡፡ በልዩነት ተቆራቁሰን እርስ በርስ የምንጫረስና የምንጠፋፋ ሳይሆን የውዲቷ ሀገራችንን ችግሮች ለመቅረፍ እንድንችል በኅብረትና በአንድነት፡ በፍቅርና በይቅርታ ወደፊት መራመድ ይጠበቅብናል፡፡ መሪና ተመሪ በሁሉም ጉዳዮች ባይግባቡ እንኳን የሀገርን ነጻነት፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ዴሞክራሲን በተመለከቱ ጉዳዮች ግን ተግባብተውና አንድ ሆነው ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ድል ያስመዘግባሉ ዓድዋ ያስተማረን ይኽንኑ ነው፡፡ ዓድዋ ያስተማረን ሌላም ነገር አለ፡፡

በደምና በአጥንት የተጠበቀው ነጻነት ከሥነ ልቡናና ከክብር ትሩፋትነት አልፎ ለኢኮኖሚ ጸጋነት እንዲተርፍ በደም ሳይሆን በላብ፤ በአጥንት ሳይሆን በጉልበት የምንከፍለው የመጪው ትውልድ ዕዳ እንዳለብን ዓድዋ ያስተምረናል፡፡ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ይላሉ ቀደምቶቻችን፡፡

የዓድዋ ድል ሀገራችንን የምናዘምንበትን ፍልስፍና የምናገኝበት፣ ሀገራችንን ወደ ከፍታ ለማድረስ የሚያስችለንን ዐቅም የምንሸምትበት፥ በየዘመናቱ እየመነዘርን እንደ ታዳሽ ኃይል የምንስፈነጠርበት ሕዝባዊ አቅም  ነው፡፡ ዓድዋን ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ፥ እንኳን የድሉ ትሩፋት የደረሰን ኢትዮጵያውያን ቀርተን፡ ስንቅ ያጓጓዙት እንስሳት እንኳን ሳያውቁት አይቀሩም፡፡ ይህ የተጋድሎ ታሪካችን በዓለም ፊት ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ፣ በነጻነት ፊት ብቻውን ተነጥሎ የቆመ አንድ የዛፍ ጭራሮ ሳይሆን በልምላሜ የተከበበ ጫካ እንዲሆን፣ በሳይንሳዊ ምርምርና በጥበባዊ ሥራችን ማረጋገጥና ማድመቅ ይኖርብናል፡፡ ነገረ ዓድዋን በጥበብ፣ በአካዳሚያዊ ፈለግ እና በማኅበረ ባሕላዊ አውድ መመርመር- ማክበር እና ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ ይህ የሀገራችን ዕምቅ ሀብት የሆነ ታሪካዊ ድል ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ግጥሞችን የገጠሙ፥ ድርሳናትን የሰነዱ፣ ተውኔቶችን የደረሱ፣ ዜማዎችን የቀመሩ፣ መጣጥፎችን የከተቡ፣ የመድረክ ዝግጅቶችን ያቀናበሩ፣ የእግር ጉዞዎችን ያዘጋጁ፥ በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኙ፣ ኢትዮጵያውያን፥፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ብዙ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ያለኝን ላቅ ያለ ክብርና ምስጋና በዚሁ አጋጣሟ አቀርባለሁ፡፡

ዓድዋ በውስን ፊልሞች፣ በጥቂት ድርሳናት)፣ በጣት በሚቆጠሩ ዜማዎች) እፍኝ በማይሞሉ የታሪክ ምርምር ጽሑፎች፤፡ በእግር ጉዞ እና በመድረክ ትወና ብቻ ተዘርዝሮ እና ተዘከሮ የሚታለፍ አይደለም ፡፡ በፍፁም ያገባናል የምንል አካላት ሁሉ ከሥነ ጥበብ፣ ከእምነት፣ ከፍልስፍና፥ ከታሪክ፡ ከሴቶች ተሳትፎ፣ ከመሪነት ጥበብ፣ ከሀገራዊ አንድነት፥ ከውትድርና ሳይንስ፤ በኢኮኖሚ ራስን ከመቻል፤ ብሎም ከጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እና የትግል ታሪክ ፋና ወጊነት ጋር በማስተሣሠር ዓለም አቀፋዊ ሥራ መሥራት ገና ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ምሁራንና የጥበብ ሰዎች ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለው ሥራ እንዲሠሩ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ መንግሥትም የበኩሉን  ድርሻ ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፈራና ተከብራ  በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን  ይባርክ!

አመሰግናለሁ፡፡

የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Filed in: Amharic