>
6:16 pm - Friday August 19, 2022

ጥጋብና ንዴት የተቀላቀሉባት የለገጣፎዋ ከንቲባ!!! አቶ አብዱረህማን - (የቀድሞው የፓርላማ አባል)

ጥጋብና ንዴት የተቀላቀሉባት የለገጣፎዋ ከንቲባ!!!
አቶ አብዱረህማን – (የቀድሞው የፓርላማ አባል)
ከቅርቡ ጊዜ ትዝታችን ብንነሳ በሮማ ሀገረ ኢጣልያ – 800 ኢትዮጵያውያንን (እና ኤርትራውያንን) ለ4 ዓመታት ከኖሩበት ባዶ ህንፃ ከነዕቃቸው በፖሊስ ግብረኃይል እየመነጠረች መንገድ ላይ የጣለቻቸው አንዲት ቨርጂኒያ ራጊ የሚሏትን የሮማ ገዢ!! “ከመጠለያችን አስወጣሽን .. ግን እሺ የት እንውደቅ?” ላሏት ሀበሾች ፦
 
    “ከፈለጋችሁ የቤርጎ አልጋ ይዛችሁ ውደቁበት፣  ካሻችሁ ደሞ አውላላው አስፋልት ላይ ውደቁበት፣  የናንተ አወዳደቅ በምን መልክ ቢሆን እንደሚሻላችሁ የምታውቁት እናንተና እናንተ ብቻ ናችሁ!” 
 
የሚል ምላሿን – የፌብሯሪ 18፣ 2018 የዕለተ ሰኞ የዘጋርዲያን ጋዜጣ ለታሪክ አስፍሮላታል።
ነገሩ በወቅቱ ብዙዎችን አስለቅሶ አልፏል።

—-

ያ መፈናቀል ያ ልቅሶ በሰው አገር ነውና “ይሁን” ብለን እንቀበለው ፤ የእኛይቱን ቨርጂኒያ ራጊ ( ወ/ሮ ሐቢባ)ን የዘር መድሎ የታየበት ማፈናቀልስ ምን ይሉታል..?!?
—-
በፖለቲካ ጡንቻ የታገዘው የለገጣፎ ቤት ፈረሳ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልቆመም፡፡ በሜዲያ ያልቀረቡ ብዙ አሳዛኝ ሁኔታዎችን እያየን/እየሰማን ነው፡፡ በአረብ ሀገር በበርሃ ተጠብሳ ባፈራችው ሳንቲም የሰራቺው ቤት በደቂቃዎች ውስጥ እንዳልነበር የሆነባት አንዲት ከርታታ ወጣት ራሷን ማጥፋቷን ስሰማ ወፈጠሬን ነው ያስጠላኝ፡፡
እነዚህ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ለኦሮሚያ መንግሥትና ለከንቲባዋ እንደ ስደተኛ የሚታዩ “መጤዎች” እንጂ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆናቸው አልታያቸውም፡፡ ከስደተኛ ካምፕ ነዋሪዎች ጋር እያነጻጸሩ መግለጫ እስከ መስጠት የደረሱት ለዚሁ ነው፡፡
የሚገርመው ነገር ቤታቸው ከፈረሰባቸው ዜጎች ይልቅ አካባቢውን የማታውቀውና የአካባቢውን ማህበረሰብ ስነ-ልቦና ያልተገነዘበቺው “መጤ” ራሷ ከንቲባዋ ናት፡፡
ሁሉም አካባቢ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ በለገጣፎ ከንቲባ መሆን የሚችል ሰው የሌለ ይመስል ስለከተማ ማስተዳደር ምንም ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ሁልጊዜ ከሌላ አካባቢ እየመታ የሚጫንብን እስከመቼ ነው? ወ/ሮ ሐቢባ የለገጣፎ ተወላጅ ብትሆን ኖሮ በህዝቧ ላይ ያን ያህል አትጨክንም ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር በምክክር ትሰራ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ቤት ማፍረስ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ የህይወታችን አካል ከሆነ 27 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እናም በለገጣፎ ቤት መፍረሱ አላስገረመኝም፡፡ የገረመኝ ነገር ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2011 የከተማው ከንቲባ በአራት ፖሊስ ታጅባ ወደ ፈረሰው መንደር መጣች፡፡ እኔም በአቅራቢያው ነበርኩ፡፡ ምን ልታደርግ ነው ብለን ስንጠብቅ በአቅራቢያው ወደ ነበረው ቤተክርስቲያን ገባች፡፡ እዚያ ተጠልለው ለነበሩ ዜጎች አንዳች ማበረታቻ ልታደርግ ነው ብለን ስንጠብቅ “እነዚህ ሰዎች እዚህ መጠለላቸው የከተማችንን ገጽታ እያበላሸ ስለሆነ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ አንድ ሰው እዚህ አካባቢ እንዳይታይ አስወጡ…” የሚል ቀጭን ትእዛዝ መስጠቷን ሰማን፡፡ ከዚህ በላይ ባልተፈጠርኩ የሚያስብልና ልብ የሚያቆስል ነገር የለም፡፡
የለገጣፎ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ሐቢባ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠቻቸው ቃለ ምልልሶች በርካታ ተገቢ ያልሆኑ አስተዛዛቢ ሃሳቦችን ተናግራለች፡፡ ወ/ሮ ሐቢባ ቤት ማፍረሷ ሳያንስ ቤተክርስቲያን አትጠለሉ ማለቷ ግን እጅግ የከፋ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ነው፡፡ ወ/ሮ ሐቢባ ከትናንት ጓዶቻቸው የተማሩ አልመሰለኝም፡፡
ዛሬ በየሜዲያው “በዜጎች ላይ ሰብአዊ መብት በመጣስ” ክስ እንደተመሰረተባቸው እየተነገሩ ያሉ ሰዎች እኮ ትናንት እንደ ወ/ሮ ሐቢባ ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ሐቢባ ይህንን ልብ ሊሉት ይገባ ነበር፡፡ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላጠፉት ጥፋት ኦዴፓም ኢህአዴግም አያድኗቸውምና!
Filed in: Amharic