>
5:18 pm - Thursday June 15, 2367

...የሰሞኑ የኦዲፓ አሰልቺ ክርክሮች (ኤፍሬም የማነብርሐን)

 

“እኔ ማንን ጠላሁ፣ …” የሰሞኑ የኦዲፓ አሰልቺ ክርክሮች

ከኤፍሬም የማነብርሐን

ሰሞኑን ባፍ ወለምታ ይሁን በተተመነ ስልት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ለኦሮሞ ጎሳ እየሰሩ ስላለው አድሏዊ እንቅስቃሴ ከገለጹ በኋላ በይዘቱ አንድ የሆነ ድግግሞሽ ማብራሪያ በኦዲፒ ተወካዮች መሰጠቱ ቀጥሏል። የክርክሮቹ ጋጋታ፣ ነፍሳቸውን ይማርና፣ የባለቤቴ እናት የጅሩይቱ ወይዘሮ ዘነበች ይነግሩኝ የነበረውን ተረት አስታወሰኝ። እንዲህ ነው ያጫወቱኝ። በጣም ወደሚያከብራቸው ወንደላጤው ጎረቤቱ ባሻ ገበያው ቤት ደጋግማ መመላለስ ያበዛችበትን ባለቤቱን፣ “የት ነበርሽ” ብሎ በጠየቀ ቁጥር “ባሻ ገበያው ቤት ነበርኩ፤ባሻ ገበያው ቤት ነበርኩ” የሚለው መልሷ ሰላም የነሳውና ጥርጣሬም የገባው ባል፣ አንድ ቀን እንደተለመደው ከሄደችበት ቦታ ስትመለስ በንዴት “ደግሞ ዛሬ የት ነበርሽ” ሲላት “ባሻ ገበያው ቤት ነበርኩ” ስትለው፣ “እኔ ማንን ጠላሁ፣ ባሻ ገበያውን“ አለ ይባላል። ሰሞኑን እነ ክቡር ኦቦ ለማ መገርሳ፤ አቶ ታከለ ኡማ፣ የኦዲፒው ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋና፣ የቀድሞው የወያኔ እስረኛ ግን ከተፈቱ ም በኋላ ከዘረኝነት እስር ያልተላቀቁት የኦዲፓ ቃል አቀባይ ታዬ ደንዴአ ደግመው ደጋግመው የሚነግሩን መከራከርያ ይህንኑ የወይዘሮ ዘነበችን ተረት ያስታውሰኛል።

ያለሕዝብ ፈቃድና የአብዛኛውን አዲስ አበቤ ፍላጎት በሚቃረን፣ በኦሮሞ የሰሞኑ ጡንቻ የም/ከንቲባ (ሰሞኑን ደግሞ ከንቲባ እያሉ ይጠሯቸው ጀመር ልበል?) ቦታ የያዙት አቶ ታከለ ኡማ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመንገድ ተዳዳሪነት የሚኖሩ በሺሆች የሚቆጠሩ ሕጻናትና ወጣቶችን ከጎዳና ለማንሳት በግላጭ ያቀረቡት አንዱ አማራጭ፣ “የጎዳና ተዳዳሪዎቹን እየለቀምን ወደመጡበት ክልል እንመልሳቸዋለን” ማለታችው “ወቸ ጉድ! ምን ዓይነት ዘመነ ከይሲ ውስጥ አመጣኸን! በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለበት ቦታው ከፈቀደ አገሩ መስሎኝ። ደግሞስ እነኚህስ ልጆች ከስደስት ወር ወይ ካንድ ዓመት በላይ ባንድ ቦታ ከቆዩ፣ እንደማንኛውም ነዋሪ አዲስ አበቤዎች ሆኑ ማለት አይደለም እንዴ? እንደው ቤት መጠጊያ ስላጡ እንጂ መታወቂያስ ሊሰጣቸው አይገባም እንዴ? ቢማሩኮ ሲያያድጉ ለአዲስ አበባ ከንቲባነትም የመወዳደር መብቱ ሊጠበቅላቸው ይገባል” ብዬ አዘንኩ።

ሰሞኑን ደግሞ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳቡት፣ በጣም የምናከብራችውና እግዜር የላከልን “የዘመኑ ሙሴ” ብለን ያሞካሸናቸው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አቢይ አህመድ “ታናሽ ወንድም” እና በ”ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ንግግራችው ያሰከሩን አቶ ለማ መገርሳ፣ ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብና አዲስ አበቤ የተደበቀ በሚመስል ስብሰባ ላይ ከጎሳ አባላቶቻቸው ፊት ቀርበው በኩራት የአዲስ አበባን ዴሞግራፊ ለመቀየር በአፋጣኝ እየሰሩ መሆኑንና እስከ 500ሺ ከሐረር አካባቢ የተፈናቀሉ “የኦሮሞ” ተወላጆችን በአዲስ አበባ አካባቢ እስካሁን ያሰፈሩ መሆኑን ሲዘረዝሩ፣ “እኝህ ሰው ሸወዱን እንዴ” ወደሚል ጥርጣሬ ገባሁ። “ኸረ አንድ በሉን እንጂ፤ በአንድ አገር እየኖረ አንዱ እየተመረጠ ሁሉም አለችን በሚላት ብርቅዬ አዲስ አበባ ላይ “በድብቅ” ቤት እየተሰራለት እንዲሰፍር፣ የመንገድ ተዳዳሪው “የሌላ ጎሳ” ልጅ ወደ “ክልሉ” እንዲመለስ ሲደረግ፤ ሌላው የ86 ብሔረ ሰብ አባላት ግን ያለችው አንድ አዲስ አበባ ብትሆንም እየተገለለና እየተዘነጋ የሚኖርባት ኢትዮጵያ ተፈጥራለች ለካ” ብዬ አዲስና ያልገመትኩት ግንዛቤ ወሰድኩ። እርኩሱ መለስና ሕውሓት ያዘጋጁልን ወጥመድ የጣጣ ስፋቱን ተገነዘብኩ ። በተለይ ደግሞ በለገጣፎ አካባቢ በከፊልም ቢሆን የመኖርያነት መስፈርቶችን ያሟላ (እስከ ሃያ ዓመታት የቤት መሬት ግብር፣ የውሃና የመብራት ወርሃዊ ክፍያ ማስረጃ በእጁ የያዘ ወዘተ) ብዛት ያለው ኢትዮጵያዊ ሲፈናቀልና፣ በOMN ቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ የለገጣፎና የሰበታ “ከንቲባ” ነን ባዮች ቀርበው የሚሰጡትን የየጎጠኝነት ቃለ ምልልሶች ካዳመጥኩ በኋላ አገሪቱ ወደከፍተኛ ጥፋት እያመራች መሆኑን ተገነዘብኩ።

ብዙዎቻችን አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ናት እያልን ስላደግን፣ እንዴ የሱማሌውም፤ ከምባታውም፤ ትግሬውም፤ አማራውም፤ ጋምቤላውም፤ ዶርዜውም፤ ወዘተ ተፈናቃይኮ እድሉን ቢያገኝ አዲስ አበባ አካባቢ መጥቶ ቤት መሬት ተሰጥቶት መኖር ይፈልጋል። አዲስ አበባን ለኦሮሞ ብቻ ያረገው ማነው? እንዴት እንዲህ ያመናቸው ሰው የወያኔ “የምርጥ ዘር፣ የወርቅ ዘር፣ ጥቁር አይሁዶች ነን” ትዝታው ገና ላልለቀው ኢትዮጵያዊ ይህን የመሰለ አስከፊ አድልዎ ከጀርባው ይፈጽሙበታል? “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ብሎ ሥልጣን የያዘ ሰው እንዴት ይህን ሸፍጥ ይፈጽማል? የሚል ረባሽ ሀሳብ የመጣበታል። ለኦቦ ለማ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር አሁንም ስላለኝ፣ “የንግግራቸውን አሰከፊ ጥልቀት ስላላገናዘቡ ነው” ብዬ ያው ሰሞኑን ምናልባትም በሳሉና አዋቂው ብዙ ያነበቡት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዕውቅቱን ያካፍሏቸውና አለያም “ቆንጠጥ” ያረጓቸዋና ያብራሩልናል ብዬ ስጠብቅ፣ ኦቦ አዲሱ አረጋ መልሰው ደገሙልኝ። “የኦሮሞ ሕዝብ በገጠሬነት ብቻ ሳይሆን በከተመኛነትም መገለጽ አለበት። ወደከተማ በማምጣትም ከተመኛነትን ለኦሮሞውች ማስለመድ ያስፈልጋል። የኦሮሞ አርሶ አደር ልጆች ወደ ከተማ ኢንዲገቡና እንዲሰባጠሩ እየተደረገ ይገኛል። የኦሮሞ ዴሞግራፊ በገጠር ሳይወሰን በከተማም ኢንዲሆን እያደረግን እንገኛለን። ኦዲፒም ለዚህ ጠንክሮ ይሰራል። ለዚህም የማንንም ፈቃድ አንጠይቅም” በማለት የበለጠ አጠጡን። አቶ ታየ ደንዴአም “ሰፊው ምሕዳር” በተሰኘው የኤል ቲቪ ፕሮግራም ላይ ተመሳሳይ የኦሮሞን ጎሳ ብቻ ዕድገት የሚያራምድ የሌላውን ግን የሚያገልና፣ የሚደፈጥጥ፣ “የኔ፣ የኔ” ብቻ የሚለውን የጎጠኝነት መርህ በድጋሚ ሰማኋቸው። ያን ጊዜ “እኔ ማንን ጠላሁ …” ይሕንን “ለኦሮሞ ብቻ፣ ለኦሮሞ ብቻ” የሚለውን አስልቺ ከርከር ነው መስማት የሰለቸኝ ብዬ ይህችን መጣጥፍ መጻፍ ጀመርኩ።

የአቶ ለማ መገርሳ፣ አዲሱ አረጋ፣ ወዘተ ምኞት የኦሮሞ ብቻ ምኞት አይደለም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለእያንዳንዱ የአገሩ ዜጋ የሚመኘው ምኞት ነው። እንዲያውም ከሌላ አካባቢ ገበሬ የአዲስ አበባ ዙሪያ ገበሬዎች የተሻለ የከተሜነት ዕድሉ አላቸው። ለአዲስ አበባ ከመቅረባችው የተነሳ ቤት፣ ንብረትና መሬታቸውን ሌላው የኢትዮጵያ ገበሬ ከሚሰጠው በተሻለ ዋጋ እያገኙ ላዲሳባ ከተሜው መሸጥ መለወጥ ይችላሉ። ልጆቻቸው ከሌላው የኢትዮጵያ ገበሬ ሰፋ ያለ ትምሕርት ቤት የመማር እድል በቅርበት አላቸው። የሃብት መጠናቸውም ከሌላው አካባቢ ገበሬ የተሻለ ነው። እንዲያውም እውነቱ በአመዛኙ የሀብት መጠን ፍላጎታቸው ለከተማዋ የቀረቡ በመሆናቸው የአዲስ አበባ አካባቢ ገበሬዎች ክሌላው ገበሬ የተሻለ ሀብት ለመፍጠር እድሉ (opportunity) አላቸው። የትኛው ሌላ አካባቢ ነው ከአዲስ አበባ እኩል ያደገ ወይም በትንሹም የሚወዳደር ከተማ ያለው? ሁሉም ዓይኑ አዲስ አበባ ላይ ሆኖ ሳለ፣ የኦሮሞ ገበሬ የበለጠ ከተመኛ ሊደረግ ልጆቹም ከተማ እንዲያድጉ የተለየ ርብርቦሽ ያሰፈልገዋል ብሎ ለመደምደም የሚያስችል የተለየ ክስተት ከየት መጣ? አፋሩስ፣ ሱማሌውስ፣ አማራውስ፣ ከምባታውስ፣ የሚገኝበት የድህነትና ገጠሬነት ደረጃ ኢንዳያዩ አይናቸውን ያሳወረውና፤ ያለሀፍረት አድሏዊ አሰራራቸውን በጥብቅና እንዲከራከሩለት ያደረገው፣ ከጎጠኝነት በቀር ምን ሊሆን ይችላል?

ሁሉን ነገር በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የተሳሳተ የዘር አመለካከት ስላላቸው እንጂ፣ አዲሳበባ እኮ በዘሩ ቢታሰብ 60 አስከ 70 ፐርሰንቱ ድብለቅ የአማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፤ ከምባታ፤ ወላይታ፤ ሶማሌ፣ ወዘተ ዘር ውጤት ነው። አማርኛን የሚናገረው እኮ “ንጹሕ አማራ” ስለሆነ አይደለም። የከተሞች የመግባቢያ ቋንቋ ስለሆነ እንጂ። ይሕም የሆነበት ታሪካዊ ምክንያት አለው። በትንሹ ለማንሳት እኳን በአፍሪቃ አጠቃላይ እኮ በጽሑፍ ላይ የተመሰረተ ባሕል የተለመደው በኢትዮጵያ ብቻ ነው ለምን እንደሆነ ባላውቅም። የዳበረ ጽሑፍን መፍጠር ምን ያህል ከባድ መሆኑን የሚያስገነዝበን ይህን የመሰለ ግኝት በዓለምም ቢሆን ጥቅት ቦታዎች ብቻ ናቸው ጀምረው ማቆየት የቻሉት። በዚሕም በታሪክ ተሳታፊነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ ብሎ ሊኮራበት ይገባዋል። ይህም በጽሑፍ የመግባቢያ ዘዴ ቀድሞ ለያዘው ኃይል የመንግስት ምስረታን፣ የወታደር አመራርን፣ በጋራ ሰርቶ ውጤት የማምጣትን ቅድሚያ እድል (comparative advantage) ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ይሰጠዋል። ብራና ማዘጋጀት እንኳን ምን ያህል ድርጅታዊ መዋቅር ይፈልጋል። በቀደመው ዘመን ደግሞ ምስጢር ለመላላኪያም ሆነ ዕውቀትን ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ይህች ቁንቋን በጽሑፍ የማስተላለፍ ልምድ፣ ትንሽ ብትመስልም በረጅም ታሪክ ድግግሞሽ ግን ለውጥ ታስከትላለች።

አብዛኛው በአዲስ አበባ የሚኖረው ሰው ሆነ በ ሸዋ የሚኖረው ሰው ወደኋላ ቢቆጥር በብዛት የኦሮሞ ቅድም፣ ቅም አያት ያለው መሆኑን ይገነዘባል። በኢትዮጵያ ውስጥ የቤተሰብ ስም አጠራር (family name; surname) ስለሌለና ከራሱ ስም (first name) ሌላ ሁሉም በአባቱ ስም ስለሚጠራ የአያት የቅድም አያት ስሙን አየተወ አዲስ ስሞችን እየያዘ ይመጣል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ግኝቶች ልምዶች የአብዛኝው በትለይ የሁለቱ ትላልቆቹ ጎዳዎች ግኝቶችና ልምዶች ናቸው ሕዝቡ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ በደም ተዋህዷል ተሳስሯልና። የማንም ሞኖፖሊ አይደሉም። ሰሞኑን ጄነራል ኃይሉ ጎንፋ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ “ስሜ ለምን ኅይሉ የሆነ ይመስልሃል፤ የአማራ ጭቆና ውጤት ስለሆነ እኮ ነው” ብለው ያዙኝ ጥለፉኝ ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ አባባላቸው በቋንቋ ብሔረተኝነት ያስከተለው የዕብደት መጨረሻ ነው ቢዬ አስባለሁ። የመለስ ምልምሎች ምን ያህል የኢትዮጵያውያንን አብሮ የመኖር እሴት በእኩይ መንፈስ እንደበረዙት የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። በኢትዮጵያዊነታቸው ከሙሉ መብቱ ጋር የኔ ብለው መውሰድ ሲችሉ ራስን ማግለልና ሌላውንም እኩይ መንፈስ ማስተማር አድርጌ ነው ያየሁት። እንደሰማሁት ግን እንዳላረጋገጥኩት በአባቴ ከምንጃሪቱና ክትግራይ አያቶቼ፤ በእናቴ ደግሞ ከሰላሌ ኦሮሞና ወለዬዎች አያቶቼ ስብጥር በይርጋለም ሲዳሞ ክፍለሐገር የተፈጠርኩና ኢትዮጵያን አገሬ አዲስ አበባን ደግሞ የሁሉ የአገሬ ሕዝብ መናኸርያ አድርጌ ሳምን የኖርኩት ሰው፤ በፈረንሳይ ሌጋሲዮን፤ በጌጃ ሰፈር፣ በጉለሌ፤ በሱማሌ ተራ፤ በካዛንቺስ፣ በሰንጋ ተራ፤ በቦሌና ለገዳዲ፤ በኮተቤና ኮርያ ሰፈር “ሁሉም የኔም የሁሉም” ብዬ በፍቅር የማስባትን አዲስ አበባ ጎጠኞች እንዳያጨልሙብኝ እፈራለሁ ። ጎጠኞቹም እንደኔው መጀመርያ አሶሳ፤ ባሌ፣ አርሲ፤ አምቦ፤ መንዲና ጊምቢ፤ ወዘተ ተውልደው ነው ወደ አዲስ አበባ የመጡት። ገና ለገና ኦሮሞ አዲስ አበባን ከቧል ከሚል የተሳሳተ ክርክር በመነሳት አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት በሚል የተዛባ ትርከት ይዘው የዘርን ስብጥር ለመቀየር የሚረባረቡትን ፣ሞኛችሁን ፈልጉ ከማለት ሌላ ምንም ማለት አይገባንም።

ጀዋር የሚባለው የዲሞክራሲ አገራት ስለኖርኩ በቂ ልምድ አለኝ አያለ የሚደስኩረውና የሚኩራራው ሰው፣ እስክንድር ነጋ በረቀቀና በዲሞክራሲ አገሮች በተለመደ የአነጋገር ዘይቤ “ታከለ ኡማን በምርጫ እነቀጣቸዋለን” (“We will punish [ታክለ ኡማ] by our vote”)፣ ስላለ፤ ጃዋር “በምርጫ ከተሸነፍንማ ሥራ ቀለለልን፤ በአዲስ አበቤ ላይ ይህን ቄሮ ጃስ ብለን እናስዘምትበታለን፤ ምርጫኮ የሚያስከትለው ጣጣ አለው” በማለት የዲሞክራሲን መሰረት ላንዴም ለመጨረሻም ገደል በከተተ መልኩ ወደለየለት ዛቻና ማስፈራራት ገብቶ የዘር ጦርነት አዋጅ እንደሚያስጎስም ገለጸ። ለመሆኑ ቄሮ ጀዋር ዪድ ተናከስ ሲለው ህግን ጥሶ ሄዶ ሊናከስ ነው እንዴ? የቄሮ መሪዎችስ እንዴት ዝም ትላላችሁ ለማስፈራሪያነት ሲጠቅምባችሁ። እነኦዲፓስ እያስብነው ያለነውን ዲሞክራሲ የሚያጨናግፍ ቱልቱላማ ልትነፋ አትችልም ብሎ ደፍሮ እንዴት አበግልጽ አይነግረውም? የመናገር መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ሕዝብን ወደጦርነት የሚቀሰቅስ ንግግር (fighting words) እኮ በዲሞክራሲ በሰለጠኑ አገሮችም ይወገዛል።

በዚህ በታላቁ 123ኛ የአድዋ በዓል አስተዋዩና አዋቂው መሪ ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ፣ ነገሮችን ያዩ የነበረበት መነጽርና ያሁኖቹ ያጠለቁት መነጽር የስፋት ልዩነቱ በጣም ይታያል። አጼ ሚኒልክ መሰረታችው ሸዋ ሲሆን፣ ሸዋ ደግሞ ትላላቆቹ የኢትዮጵያ ጎሳዎች ከአጼ ሚኒልክ በፊት ከአስራ አራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ አማራ እና የተለያዩ የአካባቢው ጎሳዎች፤ ከዚያም ከአስራ ስደስተኛው መቶ ዘመን በኋላ ደግሞ በኦሮሞዎች መምጣት በጋራ የመሰረቷት የዚሕ ሁሉ ሕዝብ የደም ውጤት የሆነች አካባቢ ናት። አማራም ከኦሮሞ ጋር ባይጋባና ባይዋለድ ደግሞ ብዙም ከትግራይ ሕዝብ በቋንቋው የማይለይ ሕዝብ ነበር የሚሆነው። አማራውና ኦሮሞው አብሮ በመሆን ራሱ የግእዝን ቋንቋ አጻጻፍ በመቀየር በግእዝ ቀድሞ የማይታወቁ ቃላቶችን በመጨመር አሁን በስፋት የሚሰራበትን የአማርኛ ፊደል ፈጥሯል። አሁን ያሉት እነጀዋርን የመሰሉት የሚሉት፣ ለምን ሙሉ ኦሮምኛ አልነበረም? ለምን ግዕዝ መሰረቱ የሆነው አማርኛ በሰፊው ይሰራበታል? ለምን በአማርኛ ሲጻፍ ስለኦሮሞ ገድል አልተጻፈም? ወዘተ የሚሉ ሟች ፍጡራን (ordinary mortals) ሊመልሱ የማይችሏቸውን ጥያቄዎች ያዥጎደጉዱታል። ጨረቃ ላይ የወጣው ፈረንጅ በአውሮፓም ሰሜን ደቡብ አሜርካም ያላደረገውን ምስኪኖቹ የአማራ ገዢዎችና የቤተ ክህነት ደራሲዎች ላይ ሊቆጠር የማይችል የክስ ዓይነት ይዘረዝሩባቸዋል። እነኝያ የቀድሞዎቹ የቤተ ክህነት ምሁራን በወቅቱ በሚገባቸው ያዩትን የሰሙትን ጽፈው አልፈዋል። ሁሉም የዓለም ታሪክ ጸሐፊ ካለው ውሱን የዘመን አሰራር የሚያቀርበውን ሰርቶ ሄዷል። የአሁኑ ትውልድ ያን ታሪክ ቀዝቀዝ ባለ አዕምሮ መርምሮ ለሚያስፈልገው ታሪካዊ ምርምር ማቅረብ እንጂ የራሱን የመሰለውን ታሪክ ዛሬ ተቀምጦ ሊፈጥረው አይገባም፤ አይፈቀድለትምም።

ግን የሚጠብቁት መልስ ከባድነቱ ጠፍቷችው አይደለም። “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” አንዲሉ መልሱንም አይፈልጉትም። የጥቂት የኦሮሞ ኤሊት ዓላማቸው በብዙ ዘመናት አብሮ በመኖር የተፈጠረውን የኦሮሞ፤ የአማራና፤ ሌሎች ብዛት ያላቸውን ሕዝቦች የደም ትስስር ብቀዶ ጥገናዊ (surgical) ማሕበራዊ ምህንድስና (social engineering) ዝዴ እንዴት ማለያየት ይቻላል የሚል ሙከራ (experiment) ውስጥ ነው የሚገኙት። ደርግና የቀድሞ ማርክሲዝም አቀንቃኞች የመደብ ልዩነት ብለው ሕዝቡን ላይ ታች ሲያደርጉት ከረሙ፤ ስንቱም ሳይገባው ለሞት፣ እስራትና ስደት ተዳረገ። ሕወሓት ቀጥሎ በተባባሰ ሁኔታ ይህንን ኤክስፐሪመንት በወልቃይትና ራያ ሕዝብ ላይ ለመተግበር አማርኛ አትናገሩ አትዝፈኑ ትግርኛ ብቻ እንጂ፤ የትግራይ ነጋዴ ይበረታታ፣ የአማራ ነጋዴ እንዲከስር ይደረግ፤ ሕዝቡ የትግራይ ስነ ልቦና እንጂ የአማራ ስነ ልቦና እንዳያሳይ፤ ወዘተ እያለ ለ27 ዓመታት ሲገድል፣ ጥፍር ሲነቅል፣ በውጭ ጉድጓድ ቆፍሮ ሲያስር (እስካሁንም አለ ይባላል ይህማ ግፍ በትግራይ፣ በወልቃይትና ፣በራያ የበጌምድር ግዛቶች ውስጥ)፤ የአማርኛ ተናጋሪውን ሞራል ለማኮላሸት ላይ ታች ሲል ከረመ። ግን ውዱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምናልባት ለጊዜውም ቢሆን ይህንን አስከፊና አስጸያፊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን እንደ ናዚ ወንጀለኞች መታደን የነበረባቸውን የሕወሓት ነፍሰ በላ የቅን ጅቦች በመቀኤ እንዲመሽጉ ትተዋቸዋል። የዚሕን መጨረሻ የምናየው ይሆናል። ግፈኞች ግን ሁሌ ሮጠው አይዘልቁም።

ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ የአማራ ብሄር አቀንቃኝ የነበሩ ቢሆን አዲስ አበባን አንኮበር ላይ፣ ወይ ምንጃር ሜዳ ላይ፣ ወይ ደብረ ብርሐን ላይ፣ ወዘተ ይገነቡ ነበር። እሳቸው ግን ራሳቸውንና ሌላውን የሚያዩት ለጎሰኝነት እውር (ethnic blind) በሆነ አመለካከት ስለነበረ፣ የኦዴፓ መሪዎች ኢትዮጵያውያንን ከሚመለከቱበት ጠባብ መነጽር አንጻር ሊያዩም አይታሰባቸውም። ለአጼ ሚኒልክ ባልቻ አባነፍሶ፣ ጎበና ዳጨው፤ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ፊታውራሪ ሐብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፤ ወዘተ ኦሮምዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ እንደራሳቸው አጼ ሚኒሊክ ከሁሉ ዘር የተዋለዱ የብርቅዬ ኢትዮጵያ ልጆች ነበሩ። ሚኒሊክ በጦር ሜዳ ያሸነፉትን የሌላ ጎሳ ሰው ደጃዝማች ራስ አድርገው የአገር ገንቢ የሚያረጉ መሪ ነበሩ። የአጼ ሚኒልክ ገጽታ ውቢቱን ኢትዮጵያ እንጂ የሴም ዘር ነን ብሎ አያስጠረጥራቸውም። የሴም ዘር ሊባል የሚችል ገጽታ የነበራቸው ቀዳማዊ ኅይለሥላሴ እንኳን በቅርቡ ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ እንዳጫወቱን በኦሮሚኛ “ሁላችንም እኮ አንድ ነን” ብለው የሚያምኑ ሰው ነበሩ። ያለምክንያት አይደለም። የመኮንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ የልጅ ልጅ መሆናቸውን በመጥቀስ መሆኑ አያጠራጥርም። መቼም ሁሌም አንድ ንጉስ ነው በዙፋን የሚኖረው። የቀድሞ ንጉሳውያን አገዛዝም የዲሞክራሲ አይጠበቅበትም። የኦሮሞ አሊቶች የታሪክን ጎማ ወደኋላ የመዘወር አባዜቸውን ቢይቆሙ ይበጃችዋል። አለዚያ የሚመኙትን በሥራ መተግበር ከፍተኛ ለሆነ የሕዝብ እልቂት ይዳርጋል።

በዚሕ በአገረ አሜሪካ የዜግነት መብት ያለው ሰው ክሃምሳ አንዱም የአሜሪካ ግዛቶች በአንዱ ውስጥ ስድስት ወር በላይ ከኖረ የግዛቱ ነዋሪነትን መታወቂያ ማግኘት መብቱ ነው። የመምረጥ የመመረጥ መብቱ ይጠበቅለታል፤ በዜግነት ዘጠኝ ዓመት ከኖረ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ሴኔተር ሆኖ የመመረጥ መብት ያገኛል። በአገሪቱ በማንኛውም ግዛት ውስጥ ከተወለደ ደግሞ ለአሜሪካ ፕሬዝደንትነት ዘር፣ ሐይማኖት፣ ጾታ፤ ዕድሜ፤ ብሔር፣ ወዘተ ሳይለይ መወዳደር ይችላል። እርግጥ ከባድ ፉክክር አለ። መሰረታዊው መመሪያ ግን ቦታ ይዞ ተቀምጧል። በአሁኒቱ ኢትዮጵያ ግን የመለስ ከፋፍለህ ግዛ መርህ ለነሱም የሚሰራ መስሏቸው ጠባብ ብሔረተኝነት ያነገቡ መለስ ከሞተ ሕውሓትም ከተቀበረ በኋላ ሕዝቡን ቁም ስቅሉን ያሳዩታል። ናዝሬት/አዳማ፣ ሐረር ድሬዳዋ፤ አዋሳ ጅማ፤ አሰላ ነቀምቴ፣ ውዘተ ድርሽ እንዳትሉ አያሉ ዲሞክራሲን በእንጭጩ ሊያስቅሩት እየተረባረቡ ይገኛሉ። አዲስ አበባና አካባቢዋን የኦሮሞ ናት ኦሮሞ ብቻ ከተሜነትን ይልመድ ወዘተ እያሉ ብዛት ባላችው ቦታዎች የአጥር ግንብ እየገነቡ ይገኛሉ። መሪያችን ድልድይ እንገነባለን ሲሉ መጀመርያ ኦዲፒ በኦሮሞ ላይ የገነባውን ግንብ ማፍረስ ይጠበቅባቸዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚኖርበት ማንኛውም አካባቢ ባለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለምንም ተጽእኖ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ ተከብሮለት፤ ወይ አብላጭ (majority)፤ አለያም አናሳ (minority) ቡድን አባል ሆኖ ያለፍርሐት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሕዝብ ማሕበራት ውስጥ በነጻ የመሳተፍ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። ከቀዶ ጥገናዊ ማሕበራዊ ምህንድስና (social engineering) አራማጆች ተጠብቆ አንዱ ለሁሉ፣ ሁሉ ለአንዱ የሚተሳሰቡባትን ኢትዮጵያን እንድንፈጥር ሊረዳን ባለፉት አስር ወራት አምላክም ፊቱን ወደኛ ሊያዞር ያሰበ ይመስላል።

የካቲት 23 1911 (March 2, 2019) ዓመተ ምሕረት አሌክሳንድሪያ፣ ቨርጅኒያ

Filed in: Amharic