>

ተነሳ ተራመድ ... በጎርፍ ሳትወሰድ ... !!! (አሰፋ ሀይሉ)

ተነሳ ተራመድ … በጎርፍ ሳትወሰድ … !!!
አሰፋ ሀይሉ
 
ኢትዮጵያዊ ነኝ። ነፃነት ደሜ ነው። ፍቅር ምርጫዬ ነው። ፀብ ያስጠላኛል። ግፍ ያንገበግበኛል። ዘረኝነትና መድልዎ ያንጨረጭረኛል። ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይን ሲሰብር ያንቀጠቅጠኛል!
*  “ቄሮ – ጥረህ-ግረህ ብላ!” … ፣ “ቄሮ – ጥረህ-ግረህ ብላ!” …፣ “ቄሮ – ጥረህ-ግረህ ብላ!”
መንፈቅ አልሞላኝም። ስድስት ወር። በሥልጣን ገግሜ እቆያለሁ ብሎ ምሎ የተገዘተ በሚመስለው በመሐን-ዲስ ታከለ ኡማ የአስተዳደር ዘመን ነው። ከአዲሳባ ወገኖቼ ጋር የስቴዲየሙን ሠላማዊ ሰልፍ ማልጄ ተቀላቀልኩ። የቡራዩን ዘግናኝ ዕልቂት ተቃውሜ። ግፍን እጃቸውን አጣጥፈው የተመለከቱ የመንግስት ቅልብተኞችን ተቃውሜ። “ፍትህ ለወገኔ” ብዬ። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ማተቤን በአንገቴ አስሬ።
ሠልፋችን ፍፁም ሠላማዊ ነበር። ድንገት ግን ለገሀርን ስናልፍ አድማ በታኝ ፖሊሶች የፋሺስቶችን ጦር እንደሚከላከል ሠራዊት ደም ለብሰው፣ ደም ጎርሰው አረንጓዴ ጎርፍ ጋር ከሀይፋ መኪኖቻቸው እየተራገፉ ተንጋጉብን። ባለንበት ቆመን በጭብጨባ ድምፃችንን ማሰማት ቀጠልን። “ቄሮ – ጥረህ-ግረህ ብላ!” … ፣ “ቄሮ – ጥረህ-ግረህ ብላ!” …፣ “ቄሮ – ጥረህ-ግረህ ብላ!”።
ያ በነፃነት ቀሚዎች ፊት ያልተቆራረጠ የአዲሳቤ ሠላም ወዳድ ወጣቶች ታላቅ የነፃነት ድምፅ አሁንም በዓይነ ህሊናዬ ያቃጭላል። የሞባይሌ ቪዲዮም አሁን ድረስ በእጄ አለ። ለታሪክ።
በመጨረሻም አድማ በታኞቹ ሳይጠሩ መጡ። እንደተራበ ተኩላ በእኛ በወገናቸው ላይ እያጉረጠረጡ። እያፈጠጡ። ደማቸው እየተንተከተከ። እና መንገድ ዘጉ። ለመግደል ተዘጋጁ። እኛም አስፋልቱ ላይ ቆመናል። በጭብጨባችን ድምፃችንን አጅበን።
ጅቦቹ አመነቱ። ተንቆራጠጡ። በመጨረሻም ፈጣሪ በመገናኛ ሬዲዮኖቻቸው ትዕዛዙን በአለቆቻቸው ልሳን ነገራቸው። ትልቅ ዕልቂት ነበረ የሚሆነው። ማናችንም በታንክ ካልደፈጠጡን ንቅንቅ አንልም ባዮች ነበርን። ወይም እንደዚያ ባዮች የነበርን ይመስለኛል። እና እነርሱም አወቁት መሠል። ጥለውን ሄዱ።
ይመስገነው ፈጣሪ – የዚያን ዕለት – ማናችንም በስቴዲየሙ አልፈን – ወደ መስቀል አደባባይ ያመራነው ሠላማዊ ሠልፈኞች ሁሉ – በህይወት – ለቤታችን በቃን።
የዚያኑ ዕለት ግን – በአምባሳደር አቅጣጫ አምርተው – እኛን በመስቀል አደባባይ “ፍትህ ለወገኔ” በሚል ጩኸታቸው ለመቀላቀል ማልደው ከቤታቸው “ሠላም አውለኝ” ብለው የወጡ – በቁጥር አምስት የሆኑ ያዲሳባ ልጆች – በእነዚያ እኛን አጉረጥርጠው ባለፉን ፋሺስታዊ ፖሊሶች እጅ – በመሐል አደባባይ ተነጣጥሮ በተተኮሰባቸው የስናይፐር ጥይት –  በሞባይል “ላይቭ” እየተቀረፀ ህይወታቸው እንደ ወይራ ቅጠል ረገፈች።
እነዚህ ምስኪን ያዲሳባ ወገኖቼ እናቶች ለቤታቸው ሳይበቁ እንደወጡ በቀሩት ልጆቻቸው የተነሳ እስካሁን የሀዘን ማቃቸውን እኖደማያወልቁ ሳስብ እሳቀቃለሁ። የዕጣፈንታ ጉዳይሰ ካልሆነ በቀር – እኔስ – እነርሱን ልሆን እችል እና እናቴን ሳስለቅስ ልኖር እችል አልነበር ወይ?።
ያሳዝናል ብቻ። እና የተገደለም ተገደለ። የተተኮሰበትም ወደቀ። የተደበደበም ተረሳ። የፖሊስ አዛዡም የሚኒስትርነት ማዕረግ ተሰጠው። እርሱ ክቡር ሚኒስትር እየተባለ፣ እናቶቻችንም እያለቀሱ አብረን እንኖራለን። እንዲህ ነው የግፍ ትርጉሙ። ሌላ ትርጉም የለውም። የተገፋም ተገፋ። የተረሳም ተረሳ። ይኸው አሁንም በዘረኞቹ ጅቦች እየተገፋ እንዳለ አለ ያዲሳባ ወጣት።
ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦችን አሳፍሮ እንደወጣ ቀረ። ሰው የጊዜ ምርኮኛ ነውና በሠላም ወጥተው በሞት ተመለሱ። ያሳዝናል። ልብ ይነካል። እሺ ይህስ አደጋ ነው። ምን ታረገዋለህ? – አደጋ ነዋ።
አደጋ ሆኖ ይቅርና -*አደጋ ያልሆነውንስ፣ ሆነ ብሎ የተደረገውንስ ቢሆን፣ እርሱንስ መከራውን ጭኖ ካመጣብህ ምን ታረገዋለህ??! “ዋ ኦሮማይ!” ነበር ያለው በዓሉ ግርማ?! አዎ። ምን ያረጋል ጊዜ በሰው ሰው እጅ ሲጥልህ??????
ዛሬ በፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ የሆነው ከቢሾፍቱው አደጋ ባልተናነሰ ያሳዝናል። ያኛው አደጋ ነው። ይሄኛው እኮ የጥጋበኞች እጅሥራ ነው። ታዲያ የቱ ይበልጥ ያናድዳል? የቱ ይበልጥ ያስቆጫል?? ዛሬም መንፈቅ ሳይሞላ በሠላም ከቤታቸው ወጥተው፣ በሠላም ተሰብስበው፣ በሠላም ተወያይተው፣ በሠላም እየዘመሩ ወደቤታቸው የሚመለሱ ያዲሳባ ወጣቶችን – እነዚያ ባለፈው ወንድሞቻችንን ሲገድሉ እየተንጨረጨርኩ ያስተዋልኳቸውን የመሠሉ ደም የጎረሱ አጉራዘለል መለዮ ለባሾች – አሁንም ወጣቶቻችንን – በገዛ ሀገራቸው፣ በገዛ ሰፈራቸው – ያለከልካይ እንደ አህያ ሰውን ሲራገጡና ያለከልካይ እንደከብት ሰውን ሲደበድቡ በሞባይል ቪዲዮ ተመለከትኩ።
ጉዳችንን ትናንት በዓይኔ በብረቱ፣ ዛሬ በሞባይል ቪዲዮ ተመለከትኩ። ተመለከትን ዛሬ። እና ምን ይሉታል ይሄን ግፍ? ይህ ከአደጋ ካልከፋ ምን የከፋ ነገር ይገኛል?? … እነዚህ ሰውን እንደ ጅብ ለመዋጥ ያሰፈሰፉ ወሮበላ መለዮ ለባሾች – የ1928ቶቹ የግራዚያኒ ፋሺስቶች አይደሉም። እነዚህ – በአካል እኛኑ የመሠሉ፣ መለዮ የለበሱ፣ አዕምሯቸው በመድልዎ የተንሸዋረረባቸው የቀን ጅቦች ናቸው። ዘረኛ የቀን ጅቦች። ይቅርታ ይደረግልኝ። ሌላ ቃል አልመጣልህ ስላለኝ ነው።
እና ይሄንንስ የመለዮ ለባሾች አደጋ – እንደ አውሮፕላን አደጋ – ፈጣሪ ያመጣብን ፍርጃ ነው ብለን በፀሎት እያሰብን  እንለፈው??? ወይስ ምን…????!!!
በበኩሌ – የፋሺስቶችን እብሪት በነፍሱ የከፈለ መላው የአዲሳባ ነዋሪ – እና ግፍ የሚያንገፈግፈው መላው የሚያስብ አዕምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ – እነዚህን ዓይነቶቹን የግፍ ዘቦች ከነጨካኝ አረመኔያዊ ክንዳቸው –  ከሀገራችን ምድር ጠራርጎ እስኪያመክን ድረስ – የኢትዮጵያ ነፃነት ወዳድ ሕዝብ በአንድ የተባበረ ክንድ ነቅቶ ሳይዋጋቸው – ዝንተዓለም እየሰገደላቸው ወጥቶ – እየተቀወረ ይገባል የሚል – የከንቱ ከንቱ ዕምነት ከቶውኑም የለኝም።
ስደተኞች አይደለንም። ሁለተኛ ዜጎች አይደለንም። ሁላችንም ሙሉ ነፃነት ያለን ሙሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ነን። ማንም ላይ አንደርስም። አጥቂነትን አንወድም። ግፍን አንቀበልም። ለዘረኞች እጅ አንሰጥም። እኛ ያ ነን። ሁሌም።
እና ያገሬ ሰው ንቃ። ያገሬ ሰው ግፍ ሲጠራቀም ሁሉንም ጠራርጎ ይወስዳል። ሁላችንም በግፍ ተገፋፍተን እስክንወሰድ እስክንጠራረግ አንጠብቅ። ያገሬ ሰው ግፍን ዝም አትበል። ያገሬ ሰው ግፍን ለመላተም ተባበር። ተነሳ ለክብር። ተራመድ ለእኩልነት። ለዜግነትህ መብት ክንድህን አበርታ። ለባንዲራህ ለወገንህ ለኢትዮጵያዊነትህ ክብር ስትል ንቃ ያገሬ ጀግና። ግፍን ተቃወም ያዲሳባ ህዝብ።
ምክንያቱም… እስከዛሬ … በሰው ልጅ አጠቃላይ ታሪክ – በግፈኞች በትር ፊት በፅናት የሚቆሙ እውነተኞች እስካሉ ድረስ – ግፈኞች ሣይወድቁ የቀሩበት ጊዜ የለምና።
ምክንያቱም – በመጨረሻ – ሀቅ እና ለሀቅ የቆሙ – ሸፍጠኞችና ነፍሰበላዎችን ድል ይነሳሉና!!
ምክንያቱም – አምላክ – ለኢትዮጵያውያን የፅድቅ ፍርዱን ሳይሰጥ አይቀርምና።
በፈርዖን ፊት ህዝቡን ያጀገነ ፈጣሪ አምላካችን ለመላው ነፃነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በግፈኞች ፊት በፅናት የመጀገን ፅናቱን ይስጠን!!
አምላክ ኢትዮጵያን እና ልጆቿን አብዝቶ ይባርክ!
እምዬ ኢትዮጵያ – በፍቅር – በነፃነት – በብልፅግና – ከትውልድ እስከ ትውልድ ፀንታ – ለዘለዓለም ትኑር!
ክብር ለሰው ልጅ በሙሉ!
“እያልኩ ተሰናበትኩ ፤
ኩሩ ኢትዮጵያዊ – ባንዲራ የለበስኩ ።”
ቸር ይግጠመን።
Filed in: Amharic