>

ህገ ወጦቹ ስራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች (አሸናፊ ብርሃኑ)

ህገ ወጦቹ ስራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች

አሸናፊ ብርሃኑ

ወደ ውጪ ሀገር ለመሄድ ፍላጎቱ ያላቸው በርካታ ስራ ፈላጊ ሰራተኞች ዘወትር ቢሮቸውን ያንኳኳሉ፡፡ የተሻለ ስራና ደመወዝ ለማግኘት በመጓጓትም ሰርክ ይመላለሳሉ ወደ ስራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች፡፡ ይሁንና ስራና ሰራተኛን በህጋዊ መንገድ በማስተሳሰር ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ ማጭበርበር በተሞላበት ተግባር የሚያፍሱት ረብጣ ገንዘብ የሚያማልላቸው እነዚህ ተቋማት ግን የተጣለባቸው ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው በተቃራኒ መልኩ እየሰሩ ናቸው ፡፡
ከአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ አዲሱ የአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ ስራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ፈቃድ አውጥተው በአገልግሎቱ ዘርፍ የተሰማሩት 317 ተቋማት ተመዝግበዋል፡፡ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ከሠራተኛ ጋር የሥራ ውል ስምምነት በማድረግ ሠራተኛን በውጭ አገር ለአሠሪ የማቅረብ አገልግሎት እንዲሰጡ ሃላፊነት የተሰጣቸው ድርጅቶች ናቸው ፡፡ ግን ከጥቂቶቹ በቀር አብዛኛዎቹ ህግን ጥሰው እና የተሰጣቸውን ሀገራዊ ሀላፊነት ውደ ጎን ትተው የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም እየሰሩም ነው ፡፡ ለዙህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከ1ሺህ በላይ ህገ ወጥ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ላይ እገዳ መጣሉን የከተማ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ማስታወቁ ነው፡፡ ቢሮው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጸሙ ደርሸባቸዋለው ያላቸውን 239 አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ የዕገዳና የእሸጋ ዕርምጃ ወስዶል፡፡ ከእነዚህም መካከል 150 ያህሉ የዕገዳና የእሸጋ፣ የቀሩት 89 ኤጀንሲዎች ደግሞ የታገዱ ናቸው ፡፡ የዕገዳና የእሸጋ ዕርምጃ የተወሰደባቸው በልደታ፣ በቦሌ፣ በቂርቆስ፣ በአራዳ፣ በየካ፣ በአዲስ ከተማ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 84 ኤጀንሲዎች ሲሆኑ፣ ዕርምጃ የተወሰደባቸውም ከሥራ ፈላጊዎች ገንዘብ በመቀበል ሕገወጥ ድርጊት የፈፀሙ በመሆናቸው ነው ፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 66 አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ደግሞ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖራቸው በመሥራታቸው መታሸጋቸውን ተነግሮል ፡፡ 20 አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በየአደባባዩና ሕዝብ በሚተላለፍባቸው አካባቢዎች አማላይ የውሸት ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ከሥራ ፈላጊዎች ገንዘብ በመቀበል ተጠርጥረዋል ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡
አለም አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ ህግ ድርጅቶች ለሚሰጡት አገልግሎት ተገቢውን ጥቅም እና ገንዘብ እንዲያገኙ እንዲሁም ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ይደነግጋሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከሀገሯ አልፋ በውጭ የሚሰሩ ዜጎቿ የሚያፈሱትን ጉልበት የሚመጥን ክፍያ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገችና በዚህም ጥቅም እያገኘች ነው፡፡
ከሰሞኑ በአዲስ አባባ የተደረጉት አስሳዎች የሚያመላክቱት ስራ አጥተው ወይም የተሻለ ስራ ፍለጋ በሚተጉ ዜጎቻችን ላይ የሚፈጸመው ማጭበርበር እና ስርቆት የተሞላበት ድርጊት እየተበራከተ መምጣቱን ነው ፡፡ ስራ እናስቀጥራችኋለን በማለት የመመዝገቢያ ገንዘብ የሚሰበስቡ፤ ከስራ ቀጣሪዎች ጋር በሚደረግ ምስጢራዊ ውል ለራሳቸው ዳጎስ ያለ የኮሚሽን ክፍያ በየወሩ የሚቀበሉ እና ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ የሚሰማሩ ኤጀንሲዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ነው ፡፡
በእኛው በገዛ ወገኖቻቸው ላይ በስራ ማስቀጠር ስም ግፍና በደል የሚፈጽሙት ኤጀንሲዎች ህገ ወጥ ተግባር ለመቆጠጠር የተጀመረው ጥብቅ ክትትል መጠናከር ለነገ የሚተው ስራ መሆን የለበትም፡፡ አሰሪና ሰራተኛ በማገናኘት በአስቀጣሪ ኤጀንሲ ስም በህገወጥነት ብር የሚያጋብሱት አካላት በፍጥነት ማስቆም ይገባል፡፡ አማላይ ማስታወቂያዎችን በተለያየ መንገድ እያስነገሩ እና ስራ ታገኛላችሁ የሚሉ አማላይ የሃሰት ዜናዎችን እያሰራጩ ገንዘብ ሰብስበው እብስ የሚሉትንና ኤጀንሲዎች ሌብነት ይቅር የማይባል ነው፡፡ በኤጅንሲዎች ተጭበርብረው ህይዎታቸው ለአደጋ የሚጋለጡት አብዛኛዎቹ ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውን ስናስብ ደግሞ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል ፡፡ ስራው ህጋዊ መንገዶች ቢበጁለትም በህጋዊ ሰበብ ህገ ወጥ ኤጀንሲዎች ትርፍ እያጋበሱበት እና የዜጎቻችን ህይዎትም አደጋ ላይ እየጣሉ ያለበት ሁኔታ ከወዲሁ ሊገታ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የስራ ሥራ ስምሪት አዋጁ ኤጀንሲዎች የሁለትዮሽ ስምምነት ከተፈፀመበት ሃገራት ውጭ ሠራተኞችን ለሥራ እንዳይመለምሉ እና እንዳይልኩ እንዲሁም የሥራ ስምሪት አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ ከሠራተኛ ገንዘብ በጥሬም ሆነ በዓይነት እንዳይልኩ ያግዳል ፡፡ የሠራተኛ እና ማህበሪዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኤጀንሲዎች ከሠራተኞች ያለአግባብ የተቀበሉትን ገንዘብ የማስመለስ ጥያቄን ጨምሮ አዋጁን መሠረት አድርገው የወጡትን ደንብና መመሪያያዎች በሚጥሱት ላይ ፈቃዳቸውን የማገድ እና የመሰረዝ ስልጣን አለው ፡፡ኤጀንሲወችም ይህንን የሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ስልጣን አውቀው እና ተረድተው ህግ እና ህግን ብቻ ተከትለው ሊሰሩ ግድ ይላቸዋል እንላለን ፡፡

Filed in: Amharic