>
5:18 pm - Friday June 15, 1663

"ኢትዮጵያ ላይ የኦሮሞ አገዛዝ እናሰፍናለን" በሚል  የጀመራችሁትን አጉል ጉዞ ግን ዛሬውኑ አቁሙ!!! (ያሬድ ጥበቡ)

 

“ኢትዮጵያ ላይ የኦሮሞ አገዛዝ እናሰፍናለን” በሚል  የጀመራችሁትን አጉል ጉዞ ግን ዛሬውኑ አቁሙ!!!

ያሬድ ጥበቡ
የገባሮቿ ልጆች ያገኙትን ነፃነትና እኩልነት በማጣጣም፣ በጎደለው እየሞሉ ለመሄድ ከመሰናሰል ይልቅ በየጎራው የዘረኝነት ልክፍት በሽተኛ በመሆን ካደጉበት የሮብና አርብ ገበያ አርቀው ለማየት የማይችሉ እየሆኑ መምጣታቸውን አዲስ እየታዘበች ነው!!!
ከታች የምትመለከቱት ሆቴል ክፍሌ በረንዳ ላይ የወሰድኩት የአዲስአበባ (ቅፅበቴ) ሰልፊ ነው። አዲስ አበባ ዝም ብላ ከተማ አይደለችም ። አዲስ አበባ ለፍትህ በመቆም ታሪኳ ነው የምትታወቀው። ገና ዳዴ በምትልበት የህፃንነት እድሜዋ “የአፍሪካን ጥቁር ሆኖ የመቆየት ቀለሟን የወሰነውን” የአድዋን የክተት አዋጅ ያዋለደች ከተማ ናት አዲስ። በግራዚያኒ ላይ በደረሰው የእጅ ቦምብ ጥቃት የተነሳ የተደናበረው የጣሊያን ፋሺዝም ባደረገው ጭፍጨፋ 19 ሺህ ዜጎቿን የገበረች ናት አዲስ።
አዲስ አበባ የጣሊያንን ፋሺዝም መቋቋም ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያን ገባሮች እንባ ለማበስ በወጣት ተማሪዎቿ አንደበት በ1957 ዓም “መሬት ላራሹ” የተዘመረባት፣ አርሶአደሩ ሰብእናውን ተረድቶ ለመብቱ እንዲቆም ትግሉ የተጀመረባት ናት አዲስ ። የአባቶቻቸውን የመሬት ባለቤትነት የተቃወሙና፣ ንብረቱንም ወራሽ ከመሆን ለድሃው ለማካፈል ልቦናቸው በሸፈተ ወጣቶችና ምሁራን ያበበች ከተማ ነበረች አዲስ። ይህን የሚወዳደር የፍትህ ታሪክ በዓለም ላይ ብርቅ ነው። ለአዲስ አበቤዎች የተሰጠ።
አዲስ አበባ፣ ታላቁን የ66ቱን የየካቲት አብዮት የለኮሰች፣ የ15 ሳንቲም የቤንዚን ዋጋ ጭማሪን በመቃወም የተነሳ የሥራ ማቆም አድማዎች፣ በመቶ ሺዎች የሚሰለፉባቸው የሰላማዊ ሰልፎች ትእይንቶች፣ የወሎን ረሃብ በመቃወም የተማሪዎች የረሃብ አድማዎች የተደረጉባት፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች “የሃይማኖት እኩልነት” ብለው ከሞስሊም ወንድምቻቸው ጎን የቆሙባት፣ ሁሌም ከራሷ አልፋ በዙሪያዋ ላሉ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የመቆም ሃላፊነት ያሳየችና መስዋእትነት የከፈለች ነበረች እኔ የማውቃት አዲስ ። በዚህ የመስዋእትነት ታሪክ በመሳተፌም ደስተኛ ነኝ።
አዲስ አበባ በነዚህ ተጋድሎዎቿም የባላባታዊና ጉልተኛ ሥርአት እንዲያከትም ወሳኙን ሚና ተጫውታለች። ዘውዳዊ አገዛዝ በህዝባዊ መንግስት እንዲተካ ቀን ከሌት ቧግታለች። የብሄረሰቦች እኩልነት እንዲሰፍን ተከራክራለች። ትምህርት ለሁሉምና ያለአድልኦ እንዲደርስ ብዙ መርሃግብሮችን በመዘርጋት ፣ በነዚህ ተግባራቷ ሃገራዊ አንድነቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ችላለች ።
ሆኖም የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ የተሟገተችላቸውና ቆማ ያከፋፈለቻቸው ገባሮቿ፣ ትምህርት ለሁሉም በሚለው እምነቷ በየማእዘኑ በተስፋፉት ከፍተኛ ተቋማት ያስተማረቻቸው የገባሮቿ ልጆች ያገኙትን ነፃነትና እኩልነት በማጣጣም፣ በጎደለው እየሞሉ ለመሄድ ከመሰናሰል ይልቅ በየጎራው የዘረኝነት ልክፍት በሽተኛ በመሆን ካደጉበት የሮብና አርብ ገበያ አርቀው ለማየት የማይችሉ እየሆኑ መምጣታቸውን አዲስ እየታዘበች ነው ። ይህን ሁሉ ነፃነት ያጎናፀፈቻቸውን መዲናቸውንም በመቀራመት ሊያወድሟት ማሰፍሰፋቸውን በአንክሮ ትመለከታለች ።
አሁን ግን ከተመልካችነት ወጥታ አዲስ አበባ ራሷን ወደመከላከልና፣ ለህልውናዋ አለመስነፍን መምረጥ ትችላለች። የአቢይን የምርጫ ሰሌዳ ሳትጠብቅ አዲስ አበባ በአንድ ሰንበት በየቀበሌዎቿ ጊዜያዊ የአስተዳደር አካሎቿን ማቆም ትችላለች ። እነዚህ በየቀበሌው የተቋቋሙ ህዝባዊ ኮሚቴዎች በየወረዳው ተሰብስበው፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎቻቸውን መምረጥ ይችላሉ። ለየወረዳው የተመረጡ አካላት ተሰብስበው የከተማዋን ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት ይችላሉ። መብትን ለማስከበር መንግስትን አንጋጦ መጠበቅ ነውር ነው። ሁሌም መንግስትና የህዝብ መብት ተፃርረው ነው የሚቆሙት። በተለይ ኦዴፓ/ኦህዴድ የራሱን ካድሬ በህገወጥ መንገድ በጎለተበትና፣ ወያኔ እንኳ ሲሠራበት ከቆየው በራሱ ድርጅቶች መሃል ሚዛን የመጠበቅ አሠራርን በመጣስ፣ የከተማዋን ወሳኝ ሥልጣኖች በኦሮሞዎች ለመሙላት ያደረገውን ደባ የሚያይ የአዲስ አበባ ህዝብ፣ ይህ ሃይል በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ይለቃል ብሎ ራሱን ማሞኘት የለበትም። ዘዱስ፣ ፈጥኖ ራሱን ማደራጀት፣ ፈጥኖ ራሱን መከላከል፣ ፈጥኖ ለዘረኝነት አልንበረከክም የሚል ቁርጠኝነት ለመያዝ መጣደፍ አለበት። ኦሮሙማ የተደረገ አዲስ አበባ ማለቂያው መፈናቀልና ስደት መሆኑን ለቅፅበትም መርሳት በራስ ላይ ወንጀል መፈፀም መሆኑን አዲስ አበቤው ሊረዳው ይገባል። አዲስ ፈፅሞ ለህልውናህ አትስነፍ! የሚሻልህን ምከር፣ ዘክር፣ ተወያይ፣ ተከራከር፣ ዘረኝነትም ተፀየፍ፣ አብረህም ቁም!
እነዚህን ቃላት ስተይብ ማህበራዊ ሚዲያው የአዲስ አበባ ወጣቶች የታላቁን እስክንድር ንግግር ሰምተው በሰላም ወደየቤታቸው በመመለስ ላይ ሳሉ የፌዴራል ፖሊስ የማእረግ ልብስ በለበሱ፣ ሆኖም ለመደብደብና ማሰር በተዘጋጁና፣ በአንዲት የማህበራዊ ሚዲያ ዘጋቢ አባባል “ጥላቻቸው በዓይናቸው ላይ በሚነበብ ቅጥረኞች” እየታፈሱ ነው። ለምን? ትናንት ባሌ፣ ናዝሬት፣ ሻሸመኔ ወዘተ ቆመጥ ዱላና ገጀራ ይዘው የተሰለፉ የኦሮሞ ወጣቶችን ለመናገር ያልደፈረ መንግስት፣ ባዶ እጃቸውን ተሰብስበው ተወያይተው በሚመለሱ ወጣቶች ላይ እንዲህ ዓይነት እብሪት መፈፀም ለምን አስፈለገው? መንስኤውስ “እኛና እነሱ” የሚለው ዘረኛ አስተሳሰብ አይደለምን? እንዲህ ዓይነት ዘረኛ አስተሳሰብ ተይዞስ እንዴት ነው ኢትዮጵያን የምታህል ህብረ ብሄር ሃገር መምራት የሚቻለው?
ኦዴፓ/ኦህዴድ ከወያኔ ውድቀት ለመማር አለመቻሉና በ10 ወራት ውስጥ ራሱን ዘርጥጦ ለመጣል መጣደፉ ትርጉሙ ምን ይሆን? ሃገር ለማስተዳደር አለመቻል ወይስ ሌላ? ሃገር ማስተዳደሩን ሳትጀምሩ ሰለቻችሁ ይሆን? እስቲ ከራሳችሁ ጋር ቁጭ ብላችሁ ምከሩ። ምንድን ነው የምትፈልጉት? የኦሮሞ አገዛዝ ከሆነ፣ ተስፋ ቁረጡ! ኦሮሞ ከቁመናው ጋር የሚመጣጠን ተሳትፎ ማድረግ ከሆነ፣ ባለፉት ወራት በንግድ ባንክ አመራር ምደባ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ አመራር ተዋፅኦ፣ ነጋዴዎችን በከፍተኛ ኪራይና ቀረጥ ለማፈናቀል ከምታደርጓቸው ደባዎች ተመለሱና፣ መሳሳታችሁን አምናችሁ፣ ከኦሮሞ ቁመና ጋር የሚመጣጠን ሚናችሁን ተጫወቱ። ሃገር የሚያረጋጋ ሥራ ስሩ። ሃላፊነት ይሰማችሁ! እኛና እነሱ ከሚል እሳቤ ወጥታችሁ ኢትዮጵያዊነታችሁን ተቀበሉ!
እኛ ኢትዮጵያውያን በቅን ልቦና ተቀብለን፣ ጓዳችንን፣ ማጀታችንን፣ የገንዘብ ቦርሳችንን፣ ልቦናችንን ከፍተን የሰጠናችሁ ኢትዮጵያችንን ትወዳላችሁ ብለን ነው። ቃልኪዳናችሁን ሰብራችሁ ኢትዮጵያ ላይ የኦሮሞ አገዛዝ እናሰፍናለን ብላችሁ የጀመራችሁትን አጉል ጉዞ ግን ዛሬውኑ አቁሙ። ላይሆንላችሁ ደክማችሁ እኛንም አታድክሙን! ታከለ ኡማን በማንሳትና ከኦዲፒ ያልሆነ፣ አዲስ አበባ ሊቀበለው የሚችል ጊዜያዊ ከንቲባ ሹሙና ለሰላም ያላችሁን የወይራ ዝንጣፊ ላኩልን። አለበለዚያ ትግሉ ይቀጥላል። እባካችሁ ተመከሩ፣ የዓለሙም መሳቂያ አታድርጉን፣ ፈጣሪ ቀናውን ያሳያችሁ!
Filed in: Amharic