>

የተፋጠጡ ወጣቶች!  (ልጆቻችን ወይስ ልጆቻቸው?!?) (ደረጄ ደስታ)

የተፋጠጡ ወጣቶች!  (ልጆቻችን ወይስ ልጆቻቸው?!?)
ደረጄ ደስታ
ምናልባት ሥራም ሆን መዋያ ብሎም ምንም ተስፋ የሌላቸው እንደሆኑስ? ምናልባት እስከዛሬ የተደከመባቸው የብሔር ፖለቲካ ሥራ ውጤትና ፍሬዎች ሆነው ከሆኑስ? ምናልባት ልጅነታቸውን ታስረውና ተንገላተው፣ አስታዋሽ አጥተው የኖሩ፣ አገርና ተስፋን የቀበሩ፣ ትኩስ ተበዳዮች ሆነው እንደሆነስ? ያውም ነግ በኔን ሳናውቅ ራሳችን በማንነታችሁ ተጎድታችኋል ተበድላችኋል ብለን ተበዳይነትን የጠመቅናቸው እንደሆነስ?
ምናልባት የአክቲቪስቶች የፖለቲካ መሳሪያ፣ ጡንቻ ማሳያ፣ ዱላ የያዙ ሳይሆን ራሳቸው ዱላ ሆነው እንደሆነስ?
ምናልባት በማንነታቸው፣ በከተሜነታቸው፣ በአዲስ አበቤነታቸው ብቻ ተጠቃሚ ናችሁ መባላቸው የግፍ ፌዝ ሆኖባቸው ከሆነስ?
ምናልባት ሊጠሉ ቀርቶ ሊታሰብላቸው፣ ሊታዘንባቸው ቀርቶ ሊታዘንላቸው እሚገቡ ወገኖቻችን እንደሆኑስ?
ጣትህን መገለ ብለህ ቆርጠህ ትጥለዋለህ? አዲስ አበቤውም ቄሮውም ወንድምህ ባይሆን ልጅህ እንደሆነስ?
ወላጆቼ አይደላችሁም ብሎ የካደን ልጅ፣ ምላሹን ፈጥኖ የካደ ወላጅ፣ ቀድሞውንስ የወላጅ አንጀት ይኖረው ይሆን ያሰኘ እንደሆነስ? ኢትዮጵያ ውስጥ የበቀለ ሳርም ሆነ ሙጃ የኢትዮጵያ ነው ብንባልስ? አገር ኢሳያስን “ኢሱ” ያላቸው እሳቸው ኢትዮጵያዊ ነኝ ስላሉ አይደለም። አገር ኢትዮጵያዊ ናቸው ብሎ ስለሚያምንም ጭምር እንደሆነስ?
ለማንኛም ውሏቸውን አደባባይ ያደረጉ ወጣቶችን ግራና ቀኝ ሆናችሁ፣ የውክልና ፍልሚያ ያቀጣጠላችሁ አዋቂዎች እስኪ አስቡበት!
ፖለቲካው ተወሳስቧል። ህዝብ ቁጥር ጨምሯል። የአገሪቱ ህዝብ አማካይ እድሜ 19 ግድም ነው ተብሏል። ሥራ አልነበረም። አሁን ደግሞ የበለጠ አልተፈጠረም። ኢኮኖሚው አሃዙ አከራካሪ ቢሆንም ከ10 ከመቶ ወደ 7.7 ከመቶ ወድቋል ተብሏል። የውጭ ምንዛሪ እሚያስገኝ ነገር ጠፍቷል። የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በ2006 ዓ.ም 430 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው የወርቅ ማዕድን ባለፈው ዓመት 32 ሚሊዮ ዶላር ብቻ አስገኝቷል፡፡ ለአገሪቱ ከፍተኛውን (እንደሳቸው ገለጻ) 85% እሚሆነውን ብድር የሰጠቸው ቻይና ትንሽ የራራች ሆና ብድር የመክፈያውን ጊዜ ባታራዝመው ዘንድሮ ጉድ ፈልቶ ነበር እየተባለ ነው። ጊዜውም ብድር መበደሪያ ጊዜ ሳይሆን የመክፈያ ጊዜ ስለሆነ መንግሥት ካለችውም ላይ ነጥቆ ለመክፈል በመገደዱ እጁ ታስሯል እየተባለ ነው። ትንሽ እፎይ የተባለው ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ከዓለም ባንክ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከሳዑዲ አረቢያ 500 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም አንዳንድ አገሮች ትንሽ ትንሽ እርጥባን ጣል በማድረጋቸው ነው ተብሏል። 8.ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑም እየተሰማ ነው። ውጥረትና ግጭት በመላ አገሪቱ ነግሷል።
በዚህ መካከል ልንጥለው እምንሮጠው መንግሥት አለ። ችግሩ መጣል አለመጣላችን አይደለም። እንጣለው ብለን የተጣደፍንበት መንግሥት ራሱ ወድቆ ቢቆየን ምን እናደርጋለን እሚለው ነው:: አሁንስ በነፍስ ይኖር ይሆን? እሚለውን ጥያቄ አቆይተን ማለት ነው። ለማንኛውም ግን ተቃዋሚውንም- መንግሥትንም ደርቦ ደራርቦ የመጣል አደጋው ታይቶን ይሆን? እኔ መፍትሔውን አላውቅም። ማድረግ እምፈለገው ምሁራን ጥያቄውን መልክ አስይዘው በማቅረብ ማሰብና መተሳሰብ እንዲኖር እንዲረዱን መጎትጎት ነው። ፖለቲካው ቁጣ መቀስቀሱ ጥሩ ነው። ጫፍ መያዙ – ጫፍ የያዘውን ሚዛን አስጠብቆ መሃል ያመጣል ማስባሉም ጥሩ ነው። ችግሩ መሃል ቢመጣስ ምን እንሰጠዋለን ነው። ተመልሶ ጫፍ መውጣቱ አይቀርም። ናፖሊዮን እንደሚለው- በጦርነት ውስጥ ምንም ሊያጡና ምንም ነገር ሊቀርባቸው ከማይችሉ ሰዎች ጋር ከመዋጋት የበለጠ ሽንፈት የለም። ወይ አላበላነው ወይ አላስተማርነው፣ ያልዘራነውን ማጨድ ወይም ማጭድ ማዋስ ያዋጣን ይሆን? ለይቶለት ሲያበቃ – ይለይለት ብሎስ ነገር ምንድነው? አደጋው ታይቶን ይሆን?
Filed in: Amharic