>

የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዝነት [Hypocrisy]! [ክፍል ፫] (አቻሜለህ ታምሩ)

የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዝነት [Hypocrisy]! [ክፍል ፫]
በአቻሜለህ ታምሩ
የኦሮሞ ብሔርተኞች ሕገ መንግሥት ተብዮውን  ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን በሚለው አቋማቸው ይታወቃሉ። የኦሮሞ ብሔርተኞች ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉት ሕገ መንግሥት ግን  አዲስ አበባን  እንኳን  የኦሮሞ  ሊያደርጋት  ኦሮምያ የሚባለው ክልል ዋና ከተማውን አዲስ አበባ የማድረግ  መብት  እንኳን አይሰጣቸውም።
በሕገ መንግሥት ተብዮው  መሠረት አዲስ አበባ የምትታወቀው  የኢትዮጵያ ዋና ከተማና ኦሮምያ ከሚባለው ክልል የተለየች  ራሷን የቻለች  የከተማ አስተዳደር  እንደሆነች  ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ የኦሮምያ ዋና ከተማ የሆነችው ያለ ምንም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ነው። በሕግ ያልተከለከለ ነገር ወንጀል አይደለም  የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። በሌላ አነጋገር  ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባ የኦሮምያ ክልል ዋና ከተማ ናት ባይልም አይደለችም ብሎ  እስካልከለከለ ድረስ አዲስ አበባ የኦሮምያ ዋና ከተማ ልትሆን ትችላለች የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል።
ይህ መከራከሪያ ግን ኦሮምያ ለሚባለው  ክልል ብቻ የሚሰራ አይደለም። ኦሮምያ ለሚባለው ክልል ያልተከለከለው የአማራ ለሚባለው ክልልም የተከለከለ አይደለም። ስለዚህ በሕገ መንግሥት ተብዮው እስካልተከለከለ ድረስ አማራ ክልል የሚባለውም፣ ትግራይ ክልልም፣ አፋር ክልልም፣ ሶማሌ ክልልም፣ ወዘተ ልክ ኦሮምያ እንደሚባለው  ክልል ሁሉ አዲስ አበባን ዋና ከተማቸው የማድረግ እኩል መብት አላቸው።
ባጭሩ  አዲስ አበባ ኦሮምያ ለሚባለው  ክልል በተለየ ሁኔታ ዋና ከተማ የምትሆንበት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለም!  ሕገ መንግሥቱን ካላስከበርን ሞተን እንገኛለን የሚሉን የኦሮሞ ብሔርተኞች ግን  ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን በሚሉን ሕገ መንግሥት ያልተሰጣቸውን መብት አዲስ አበባ የኦሮምያ ዋና ከተማ ናት ይሉናል።
ኦሮምያ  የሚባለው  ክልል  ከሌሎች ክልሎች የተለየ መብት በአዲስ አበባ ላይ  ስላልተሰጠው  አዲስ አበባን ኦሮምያ የሚሉት ክልል ዋና  ከተማ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት የለውም። እንዴውም ሕገ መንግሥት ተብዮው ይከበር ከተባለ ኦሮምያ ክልል ከአዲስ አበባ ክልል መውጣት አለበት።
በሕገ መንግሥት ተብዮው እስካልተከለከለ ድረስ ያልረከለከለን ነገር ማድረግ ወንጀል አይደለም ከተባለ ብአዴን የሚባለው ድርጅትም  ነስፍ የለውም እንጂ   የአማራ ባለጉዳይ ቢሆን  አብዛኛው ኗሪ  አማራ የሆነባትን አዲስ አበባን ኦሮምያ የሚባለው ክልል በሕገ መንግሥት ተብዮው  ያልተከለከን ነገር የማድረግ መብቱን ተጠቅሞ ዋና ከተማው እንዳደረጋት ሁሉ  አማራ በሚል የተዋቀረው ክልል ዋና ከተማ በማድረግ  በሕገ መንግሥት ተብዮው ያልተከለከለ መብቱን መጠቀም ይችል ነበር።   ምክንያቱም ኦሮምያ የሚባለው ክልል አዲስ አበባን ዋና ከተማው ያደረጋት በሕገ መንግሥቱ ተብዮው መሠረት አዲስ አበባ የኦሮምያ ዋና ከተማ ስለሆነች ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባን የማንም ክልል ዋና ከተማ አትሆንም የሚል ክልከላ ስለሌለው ያንን ተጠቅሞ ነውና። ይህ  አማራና ኦሮምያ  ለሚባሉት  ክልሎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክልሎች ይሰራል።
ኦሮምያ የሚባለው ክልል በአዲስ አበባ ጉዳይ ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ  ከአዲስ አበባ ጋር የሚተሳሰርበትና የአዲስ አበባ ባለቤት የሚሆንበት  ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደሌለው ሕገ መንግሥት ተብዮው ተጠቅሶ እስካሁን አልተነገረውም። ይህ የልብ ልብ የሰጣቸው ግብዞቹ የኦሮሞ ብሔርተኞች ባንድ በኩል ሕገ መንግሥት ተብዮውን  ካላከበርን ሞተን እንገኛለን እያሉ በሌላ በኩል ሕገ  መንግሥት ተብዮውን  አናቱን እያፈረሱ በሕገ መንግሥት ተብዮው ያልተሰጣቸውን አዲስ አበባን የኛ ነው ይሉናል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት አዲስ አበባ የኦሮሞ አይደለችም፤ ኦሮምያ የሚባለው ክልል ዋና ከተማም አይደለችም!
ሲጀመር ሕገ መንግሥት ተብዮው እንኳን አዲስ አበባን  ኦሮምያ የሚባለውንም ክልል የኦሮሞ አድርጎ አያውቀውም። በሕገ መንግሥት ተብዮው መሠረት የትም ቦታ ያለው የኢትዮጵያ  መሬት ባለቤት  መንግሥት እንጂ  የትኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ አይደለም!  ሕገ መንግሥቱን ካላስከበርን  ሞተን እንገኛለን የሚሉን የኦሮሞ ብሔርተኞች ግን ከክልላቸው አልፈው ክልላቸው ባልሆነው አዲስ አበባ ውስጥ በመግባት  ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን  የሚሉት ሕገ መንግሥት ያልሰጣቸውን ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥት ተብዮውን ባፍጢሙ በመድፋት አንድ መሬት  የኦሮሞ ለማድረግ እንደሚሰሩ ይነግሩናል። እስቲ የትኛው ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉን  ሕገ መንግሥት  አንቀጽ ነው  ይህንን ወይንም ያንን መሬት የኦሮሞ ነው የሚለው?  በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ  የአገዛዝ አገልጋይ እንጂ ለሕገ መንግሥት ተብዮውም ሆነ ለኅሊናው የሚታዘዝ ዳኛ ባለመኖሩ   ኦሮምያ የሚባለው ክልል ሕገ መንግሥት ተብዮውን አፍርሶ  መሬትን የኦሮሞ ለማድረግ ሲነሳ ሕገ መንግሥት  እየተጣሰ ነው  ብሎ ትንፍሽ የሚል የለም!
Filed in: Amharic