ውብሸት ሙላት
ማኅበረሰብ ሲረጋ እና አዲስ የልቡና ዉቅር (paradigm shift) ዉስጥ መግባት ካልቻለ ወይም ወደ አዲስ የልቦና ዉቅር እንዲገባ ሲፈለግ shock ዉስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ መሪዎች አሉ፡፡ ከዚያ ወደሚፈልጉት የለዉጥ አቅጣጫ ይከቱታል፡፡ ይሔ በብዙ አገራት ተፈጽሟል፡፡ ስለ shock doctrine ማንበብ ነዉ፡፡
ኢትዮጵያም ዉስጥ ከባለፈዉ ዓመት ጀምሮ የተለያዩ የ shock ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ወደ 1 ሚሊዮን ገደማ ኦሮሞ ከሶማሊያ ክልል በጥቂት ጊዜያት ተፈናቅለዉ፣ በታቀደ እና በተጠና ስልት ትራንስፖርት ሁሉ በአናት በአናቱ እየመጣ፣ ወደ ኦሮሚያ ክልል መጥተዉ እነዲሠፍሩ ተደርጓል፡፡ የማፈናቀል ድርጊቱ ሰቅጣጭ ነበር፡፡ ያስደነግጣልም፡፡ ግን ማን አፈናቀላቸዉ? እንዴት ያሁ ሁሉ መኪና በዚያ ፍጥነት በአካባቢዉ ተገኘ? ለምንስ ወደ ሶማሊያ እንዲመለሱ አልተፈለገም?
ሌላ shock… ዶ/ር አቢይ ላይ የተደረገዉ የመግደል ሙከራ?!?
……………….
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. መስቀል ዐደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የመግደል ሙከራ ተደረገ፡፡ በማግስቱ ከአሜሪካ፣ የፎረንሲክ ባለሙያዎች እርዳታ ለማድረግ መጡ ተባለ፡፡ (በምን ፍጥነት እርዳታ ተጠይቆ፣ ባለሙያ ተመርጦ፣ ከአሜሪካ ተነስተዉ ኢትዮጵያ እንደደረሱ እግዜር ይወቅ)፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሁሉንም ነገር ያቀነባበረዉ አቶ ጌታቸዉ አሰፋ ነዉ ተባለ፡፡ ይሁን እንጂ የእስር ትእዛዝ ስለመዉጣቱ እንኳን አይታወቅም፡፡ እንደዉም የሕወሃትም የኢሕአዴግም የሥራ አስፈጻሚ አባል ነዉ፡፡ የዶ/ር ደብረጽዮን አማካሪም ነዉ፡፡ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገዉን ጥረትም አይታወቅም፡፡ ብቻ ጌታቸዉ አሰፋ ነዉ ተብሏል፡፡ ኬንያ ሆና አቀነባበረች የተባለችዉ ሴት ተላልፋ እንድተሰጥ መጠየቁን አናዉቅም፡፡ የእነ ተስፋዬ ዑርጌም ክስ ምን ላይ እንደደረሰ አይታወቅም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርን ያህል የመግደል ሙከራ ተደርጎ ክሱም ሁሉም ከአጀንዳት ወጥቷል አሁን፡፡
የኢንጅነር ስመኘዉ ግድያ?!?
………………
ኢንጂነር ስመኘዉ መስቀል ዐደባባይ ሞቶ/ተገድሎ ተገኘ፡፡ መኪናዉ ዉስጥ ሆኖ ራሱን በራሱ አጠፋ ተባለ፡፡ ጥይቷ ከስመኘዉ ጭንቅላት አልፋ መኪናዉን አልመታች፤ መኪናዉ ከዉጭ ሆኖ ሊቆለፍ ቢችልም የፖሊስ ኮሚሽነሩ ዐይኔን ግንባር ያድርገዉ ብለዉ መኪናዉ ከዉስጥ ነዉ የተቆለፈዉ አሉ፡፡ (የኢንጂነር ስመኘዉ መኪና ዓይነት እንዴት ከዉጭ ሆኖ፣ ቁልፉ ከዉስጥ እያለ ሊቆለፍ እንደሚችል ስመኘዉ የሞተ ገደማ ጽፌያለሁ፡፡)
የጅግጅጋዉ ዘግናኝ ቃጠሎ…ሌላዉ Shock ?!?
……………
አብዲ ሙሃመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ያዘጋጃቸዉ ሄጎ የሚባሉ የወጣቶች ስብስብና የክልሉ ልዩ ኃይል ጅግጅጋ የተፈጸመዉን ግዲያ፣ ቃጠሎና ዝረፊያ እንደፈጸሙ ሁላችንም አወራን፡፡ ግን ያ አሰቃቂ ክስተት መፈጸም እንደጀመረ አብዲ ኢሌ ቤተክርስቲያን ተገኝቶ እያለቀሰ ሕዝቡን አጽናንቷል፡፡ ከሰዓት በኋላ ቄሶችን ቤተመንግሥቱ ጠርቶ ኮሚቴ እንዲያዋቅሩ፣ ለደረሰዉ ጉዳት ካሳ እንደሚከፍል፣ ነገር እየተፈጸ ያለዉ ዘግናኝ ጭፍጨፋና ቃጠሎ ከእሱ ቁጥጥር ዉጭ እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱም ድርጊቱ መከሠት እንደጀመረ ወደ ጅግጅጋ ከገባ በኋላ ተመልሶ ወጥቷል፡፡ ከሁለት (ሦስት?) ቀናት በኋላ ከእንደገና ገብቷል፡፡ የጅግጅጋዉ ክሥተት ጥልቅ ጥናት ይጠይቃል፡፡ አብዲ ኢሌ ክፉ ነዉ፡፡ ግን ከአብዲ ኢሌም የከፉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚቸሉ መጠርጠር ነዉ፡፡ ለማረጋገጥ ማጥናት ነዉ፡፡
የጌዲዮ ሕዝብ መፈናቀል….
~~~~~~~~~~
ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ የጌዲዮ ተወላጆች ከጉጂ ዞን ተፈናቀሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሁኑ ሌላ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዘወር ብሎ አላያቸዉም፡፡ ስምንት ወራት ገደማ ሊሆናቸዉ ነዉ፡፡ በምን ምክንያት የጉጂ ኦሮሞ ያለወትሮዉ በማን አቀነባባሪነት ያን ያህል ሕዝብ አፈናቀለ ለምንስ በመንግሥት ተረሱ
የለገጣፎዉ የማፈናቀል shock
———-
በቁጥር ሲታይ ከሶማሌ ከተፈናቀሉት ኦሮሞዎች፣ ከጉጂ ከተፈናቀሉት ጌዲዮዎች ዝቅተኛ ሊሆን ነዉ፡፡ ግን በሕገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ስለሆነ ቤታቸዉ መፍረስ አለበት ተብሎ የፈረሰዉ በወቅቱ ለገጣፎ ብቻ ነዉ፡፡ አብዝኃኛዎቹ ደግሞ አማራ ናቸዉ፡፡ በዚያን ወቅት ኮንዶሚኒየም ዕጣ ሊወጣ የጭቅጭቅ ወቅት ነበር፡፡ ለምን በዚያን ጊዜ እንደ ቀብር አፈር ማጣደፍ ሁሉ አስፈለገ?
የኮንዶሚኒየም ዕጣ እና ሿሿዉ
———-
ተገንብተዉ ያለቁ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ሊወጣ ሲል ኢንሳ ሲጠቀምበት የነበረዉ ሶፍትዌር ችግር ነበረበት ተባለና ቆመ፡፡ ከዚያ የሶፍትዌሩ ነገር ዉሃ በላዉ፡፡ ማንም አንስቶት አያዉቅም፡፡ ተስተካክሎ ይሁን ሌላ ሶፍተዌር ይዘጋጅ ሳይታወቅ ዕጣ ወጣ፡፡ ቀድሞ ዕጣ ሊወጣባቸዉ የነበሩት ቤቶች ስንት ነበሩ? ለምን ቁጥሩ ቀነሰ? ታከለ ኡማ የኮየ ፈጨ ኮንዶሚኒየም ዕጣ እንዳይጣባቸዉም ታግሎ ነበር፡፡ በትዕዛዝ ዕጣዉ ወጣ ተባለ፡፡ ከዚያ ጃዋር ሰልፍ ጠራ አሉ፡፡ የክልሉ መንግሥት ደግፌያለሁ አለ፡፡ ሿሿ!
አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመሬት ተነስተህም ቢሆን ለጥጠህ ይገባኛል በል፡፡ ቢያንስ የተወሰነ አታጣም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሕግና ሥርዓት ሳይሆን እንደ ከብት ነጋዴ ቀንስ ጨምር እያሉ በመደራደር ብቻ ሆኗል፡፡ ይህንንም የድርድር ፖለቲካ እያሉት ነዉ!