>

አዲስ አበባ ከማኅጸኗ ነዳጅ ፈልቆ ወይንም በተአምር የበለጸገች ከተማ አይደለችም!!! (አቶ ሙሼ ሰሙ)

አዲስ አበባ ከማኅጸኗ ነዳጅ ፈልቆ ወይንም በተአምር የበለጸገች ከተማ አይደለችም!!!
አቶ ሙሼ ሰሙ
 
አዲስ አበባ አቅም ያለው በእውቀቱና በሃብቱ ያልቻለው ደግሞ በጉልበቱና በሙያው የገነባት የሁሉም ዜጋ መናሕርያ ነች፡፡ አዲስ አባባ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ስታልፍ የአንድ ብሔር ወይም የአንድ ክልል መገለጫነት ይዛ የዘለቀች አልነበርችም፡፡ አዲስ አበባ በ125 ዓመት ታሪኳ ውስጥ የራሷን እሴቶች የፈጠረች ከተማ ነች፡፡ እሴቶቿም የኦሮሞ፣ የአማራ ወይም የትግራዋይ አሊያም የቀሪዎቹ ከ80 በላይ የሚቆጠሩት ብሔርና ብሔረሰቦችም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከሁሉም ተቀይጦና ተዳቅሎ የተወለደ፣ ሁሉንም ያቀፈና  ያጣመረ አዲስ አበባዊ ባህል፣ የቋንቋ ዘይቤ፣ ስነልቦና፣ የአኗኗር ዘዴ፣ ማህበራዊ መስተጋብር ፈጥራለች፡፡
አዲስ አበባ የተቀበለችውን ሁላ ያስተናገደችው በቀላሉ እራሱን እንዲሆን ፈቅዳ አልነበረም፡፡ ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ማንነቱን፣ ማህበራዊ መስተጋብሩን እያዋሃደች፣ እያጣጣመች፣ እየዋጠችና እየሰለቀጠች ቅድመ ሁኔታ እየፈጠርችና የራሷ ልዩ ገጽታ እያላበሰች ነበር፡፡ አዲስ አበባ፤ በአዲስ አበቤነት ቅድመ አያቶቻቸውን ለመጥራት የደረሱ ነዋሪዎቿን ቀርቶ ራቅ ካለ ዘምን ጀምሮ የተቀላቀሏትን ግሪኮች፣ አረቦች፣ አርመኖች፣ ባንያኖች አፍሪካዊያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቀላቀሏትን ቻያናውያን፣ ህንዳውያንና አውሮፓዊያንን አንዲሁም ሌሎችን በማጣጣም ከፈጠረችው አዲስ ስነልቦናና ማህበራዊ መስተጋብር ጋር ያዋሃደች የሁላችንም የተስፋ መዲና (Land of opportunity) ነች፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸው ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች በሂደት የተፈጠሩና በሰነድ ያልሰፈሩ በጋራ መግባባት የተደረሰባቸው እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች ከእምነት ባሻገር ምን ሕጋዊ መሰረት አላቸው፡፡ የትኛውም ክልል ቅጥያ ላድርግሽ ሳይላት አዲስ አባባ  የራሷ ህልውና አስጠብቃ ለመኖር ምን ሕጋዊ መሰረት ማጣቀስ ትችላለች፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49  ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ ንዑስ አንቀጽ 5 ደረስ ስለ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር (Self Administration) በማያሻማ መልክ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ንዑስ አንቀጽ 3 የአዲስ አበባ ከተማ ተጠሪነት ለኦሮሞ፣ ለአማራ ለደቡብ ወይም ለሌላ ክልል ሳይሆን በተለይ ለፌደራል መንግስት መሆኑንም እንዲሁ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፊደራሉ መንግስት ውስጥ እንደማንኛውም ብሔር ብሔረስብ (በ23 ድምጽ) እንደሚወከሉ በዚሁ አንቀጽ፣ በተለይ በንዑስ አንቀጽ 4 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ሕገ መንግስቱ ከላይ የተዘረዘሩትን ልዩ ባህሪያት በማጤን አዲስ አበባ ከ11ዱ ክልሎች (ድሬድዋን ጨምሮ) ከግማሽ በላይ ሊባል በሚችል ደረጃ የላቀ፣ የተናጠልና የድምር ውክልና እንዲኖራት አድርጓል፡፡
ሱማሌ——– 24
አዲስ አበባ— 23
ቤንሻናጉል ጉሙዝ ——-9
አፋር ————————8
ጋምቤላ——————3
ሐረሪ ————————2
ድሬዳዋ—————— 2
ድምር ———————-24
ከላይ እንደምንመለከተው አዲስ አበባ ከግምሽ በላይ ከሚሆኑት ክልልች በቁጥር የሚልቅ የተናጠል ውክልና በቁጥር 23 መቀመጫ አላት፡፡ አዲስ አበባ ከሱማሌ ክልል በ 1 መቀመጫ ብቻ የምታንስ ሲሆን የአምስቱ ክልሎች አጠቃላይ ውክልና ተደምሮ 24 መቀመጫ ነው፣ ከአዲስ አበባ ጋር ሲነጻፀር የከተማዋ ውክልና ከአምስቱ ክልሎች መቀመጫ በአንድ ድምጽ ብቻ ይሆናል ያሚያንው፡፡……
…… እነዚህ በሕገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች እስካልረጉ ድረስ ለአንዱ ክልል ሃቅ ለሌላው ክልል ሐሰት ሆነው በማግባባት ሊያገለግሉ አይችሉም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ ማንኛውም የመብራት፣ የቴሌ፣ የውሃና ሌሎቹም መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በደረቅ ወደብ ላይ እስከ ተከማቸው የገቢና የወጪ ንብረት ወይም በባንኮች እስከተቀመጠው ጥሬ ገንዘብ ድረስ፣ ሁሉም ክልሎች የመሬት በባለቤትነትን እያነሱ ንብረቱን፣ ገንዘቡንና ሃብቱን የራሳቸው ንብረት ማድረግና መውረስ ይቻላሉ እንደማለት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር  በኮየ ፈጪ ላይ የተሰሩ ጋራ መኖርያ ቤቶች ጉዳይም ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ ሊታይ አይችልም፡፡……..
Filed in: Amharic