>

ደመቀ ያቺን ሰአት!!! ክፍል ሁለት - (ያሬድ ጥበቡ)

ደመቀ ያቺን ሰአት!!!
ክፍል ሁለት – ያሬድ ጥበቡ
(አቶ ደመቀ የአማራ ክልል ተፈናቃዮችን ለመርዳት የተደረገው ቴሌቶን ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የሞቀ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ ደስ የሚል የሰላም እንቅልፍ ቢተኙም፣ የአዲስ አበባ ውጥረት አልፎ አልፎ በእንቅልፋቸው መሃል እየገባ ሲያገላብጣቸው አድሮ ዛሬ በማለዳ ለውይይት ወደ ምንሊክ ቤተመንግስት ደርሰው ከዶክተር አቢይ ቢሮ ሲገቡ አቢይ፣ ለማ፣ ሙፍሪያትና ወርቅነህ በጠረጴዛ ዙሪያ ከበው ሲያወሩ ደረሱ።)
አቢይ፣ ደሜ እንደምን አደርክ! እዚህ ጋ ቁጭ በል ።  በአዲስ አበባም በዳያስፖራም የለውጥ አመራሩ ተቀባይነት እያሽቆለቆለ መምጣት ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መወያየት እንደጀመርን ነው የደረስከው፣ ሃሳብ እንደሚኖርህ እርግጠኛ ነኝ ምን ትላለህ። ከዚያ በፊት ግን ሻይ ወይስ ቡና ምን ላቅርብልህ?
ደመቀ፣ አጋፋሪው የት ሄዶ ነው አንተ የምታቀርበው፣ ጥራው እንጂ።
አቢይ፣ ውይይታችን ጥብቅ ምስጢር ስለሆነ ረዳቶች እንዳይኖሩ አዝዤ ነው።
ደመቀ፣ ይሁን፣ እንግዲያው አንድ ስኒ የአጋሮ ቡና አቅርብልኝ።
አቢይ፣ በደስታ፣ እናንተ ውይይቱን ቀጥሉ፣ ይሰማኛል።
ደመቀ፣ ይሄን ቲም ለማ ፣ ቲም ለማ፣ አቢይ ፣ አቢይ እያለ አርፎ የተኛ ሰው ቆስቁሳችሁ ፣ ቆስቁሳችሁ ከአደባባይ አወጣችሁት አይደል፣ እንግዲህ ደስ ይበላችሁ።
ለማ፣ ለምን የህግ የበላይነትን አስከብራችሁ፣ ህገወጦችን ከለገጣፎ አስወጣችሁ ብሎ የሚሰለፈውን ነው ቆስቁሳችሁ፣ ቆስቁሳችሁ የምትለን?
ደመቀ፣ የቱን ህግ ነው የምታስከብሩት? የማንን ህግ ነው የምታስከብሩት? ከ10 ና 15 ዓመታት በፊት መሬት  ከገበሬ ላይ ገዝተው፣ በባድማ መሬት ላይ ከተማ ገንብተው፣ ቤት ሠርተው፣ ትምህርት ቤት አቋቁመው፣ ታክስ ከፍለው፣ መንግስት ውሃና ኤሌክትሪክ አስገብቶላቸው የአገልግሎት እየከፈሉ የኖሩትን ዜጎች ነው ህገወጥ የምትላቸው? ምን በደሉህ? በባዶ መሬት ላይ ከተማ ስለገነቡ? ለክልልህ የታክስ መሠረት የሆነ ልማት ስላመጡልህ? ከቶ ምን ሃጢያት ተገኘባቸው?
ለማ፣ አንተ የለገጣፎ ሲገርምህ፣ የክልሉ ምክርቤት በሰጠኝ መመሪያ መሠረት በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ሁሉ ነው የህግ የበላይነትን እንዳስከብር ትእዛዝ የተሰጠኝ። እኔ በግሌ የማደርገው አንድም ነገር የለም፣ የምክርቤቱን ውሳኔዎች ማስፈፀም ደግሞ ግዴታዬ ነው። ይህን ሥልጣን እኮ ያያዝኩት የማርያም ፀበል ልጠጣበት አይደለም።
ደመቀ፣ (ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አየተመለከተና ዝም ትላለህ የሚል ጥያቄ ዓይነት በገፅታው ላይ እየተነበበ)፣ አሁን ለማ የሚነግረኝ እውነት ነው? በየክልሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን መጠለል፣ መመገብ ያልቻልን ሰዎች፣ አሁን በህግ የበላይነት ስም ተጨማሪ መቶ ሺዎችን በአዲስ አበባ ዙሪያ ማፈናቀሉ ይጠቅማል ብለህ ታስባለህ? እረ ተው አቢይ ውሾችህን እሰር? እረ ተው ኋላ ይቆጭሃል?
አቢይ፣ ደሜ እጄ ታሰረ እኮ፣ ምን አድርግ ነው የምትለኝ። ጨፌ ኦሮሚያ ክልሉን በሚመለከት የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ላግድ? ወይስ ከማስተላለፋቸው በፊት በደህንነትና ስለላ ላስፈራራ? እስቲ በእኔ ቦታ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?
ደመቀ፣ መጀመሪያ መች አሰብክበት? ጉዳዩ አስጨንቆህ ቢሆንማ ኖሮ ገና ጨፌ ኦሮሚያ አጀንዳ ይዞ ሳይወያይበት ቢሮህ ጠርተህ ታማክረኝና መላ እንፈልግለት ነበራ። የታል ያን ሃላፊነትህን የተወጣኸው? ምን ይሻላል ብለህ አማክረኸኝ ታውቃለህ? ከተወሰነ በኋላ ለማ ዛሬ ነግሮኝ ሳይሆን፣ አጀንዳው ለጨፌው ከመቅረቡ በፊት ነበር መመካከር  የነበረብን።
አቢይ፣ ይህ የነፃነት ዘመን ነው፣ የየክልሉን ሸንጎ አጀንዳ አስቀድሞ እንዲቀርብልን እየጠየቅን አቅጣጫ መስጠት አንችልም።
ሙፍሪያት፣ በትክክል
ወርቅነህ፣ በዚህ ጉዳይ ደመቀ ትክክል ይመስለኛል። ሁሉም የክልል ፓርቲ የየራሱን ፍላጎት ብቻ የሚያይ ከሆነና የክልሉ ምክርቤት የክልሉን ፓርቲ አመራር ተከትሎ የሚወስን ከሆነ ጭልጥ ያለ የርስበርስ መፋጠጥ ሊከሰት ይችላል ። ደመቀ እንዳለው የክልሎቹ አጀንዳ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አመራር ሊሰጠው ይገባል፣ አለዚያ ተያይዘን ገደል ነው።
ለማ፣ (ወደ ወርቅነህ እየተመለከተ) አንተ ዝም ብለህ መገላበጥ ሥራህ ነው፣ መቼ ነው በመተክል ላይ የምትቆመው? እንዴት ነው በዚህ የነፃነት ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልል ፓርቲዎችን ወይም ምክርቤቶችን አጀንዳ አቅጣጫ መስጠት የሚችለው? ምን ሥልጣንና አቅም አለው?
ደመቀ፣ ምን ማለትህ ነው ለማ? አቅሙም ሥልጣኑም አለው እንጂ። የአቢይን ያህል ፍቅርና ድጋፍ ከህዝቡ ያገኘ መሪ በኢትዮጵያ ታሪክ አለ? አቢይ ወጥቶ “ምርጫ አካሂደን በህዝብ ፍለጎት የተመረጡ የክልልና የከተሞች ምክርቤቶች እስኪቋቋሙ ድረስ ህዝብን ከያዘው ይዞት የሚያፈናቅሉ አዲስ ውሳኔዎች ታግደዋል” ቢል የትኛው የክልል ምክርቤት ወይም ከንቲባ ነው ያንን ሲጥስ የሚገኘው? እነ ለማ በህግ ማስከበር ስም የምትገፉት “ኦሮሞ ጊዜው አሁን ነው፣ ዛሬ ካልጠቀለልነው መቼም አናደርገውም” ከሚል እሳቤ እንደምትንደረደሩ እያንዳንዱ ፀሀይ እያጋለጣችሁ ነው።
ለማ፣ ደሜ፣ ምንም የሚጋለጥና የማይጋለጥ ነገር የለውም። ኦሮሞ ሁሉንም ነገር በጠራራ ፀሀይ በግልፅ ነው የሚያደርገው፣ በጭለማና በድብቅ የሚሠራው የለም። በነገራችን ላይ አልሰማህ እንደሆን የክልሉ ፖሊስና ልዩ ሃይል ዋና ፅህፈትቤቶች ከነሙሉ ሃይላቸው ወደ ፊንፊኔ እንዲዘዋወርም ጨፌ ኦሮሚያ ወስኗል።
ደመቀ፣ አዲስ አበባ የራሱ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ አለው፣ የናንተ መደረብ ለምን አስፈለገ? ለምን ሽግግሩ እስኪያልቅ ባለበት አይቆይም? ይህ እርምጃችሁ ከምታነሱት የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ጋር ተዳምሮ አዲስ አበቤውን ወደ አመፅ እንደሚገፋው ጠፍቷችሁ ነው? ወይስ በልዩ ሃይላችሁና በፖሊሳችሁ አስፈራርታችሁ ፍላጎታችሁን ልትጭኑበት አቅዳችኋል?
ሙፍሪያት፣ በሰላም ሚኒስቴሩ ግምገማ ከሆነ አዲስ አበባ ተጨማሪ የፀጥታ ሃይል ማግኘቷ ሰላሙን ያጠናክረዋል ብለን ነው የምናስበው
ወርቅነህ፣ እንዲህም አድርጎ የሰላም ሚኒስቴር የለም። ራሴን በራሴ ላስተዳድር ብሎ ተገቢ ጥያቄ የሚያነሳን አዲስ አበቤ፣ በራሱ ከንቲባና በራሱ ፖሊስ እንዲተዳደር ከመተው ይልቅ፣ የተለየ የባለቤትነት ጥያቄ አለኝ የሚል ክልል የሚልክበትን ልዩ ሃይልና ፖሊስ በሰላም ይቀበላል ብለሽ ማሰብሽ ለቦታው እንደማትመጪኚ ብቻ ነው የሚያሳየው። እንደ እውነቱ ከሆነ የዚህን የኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ሃይል ወደ አዲስ አበባ መግባት የሰላም ጠንቅነት አስቀድመሽ መቃወም የነበረብሽ አንቺና መሥሪያቤትሽ መሆን ነበረባችሁ። የፖሊስ ኮሚሽነር ስለነበርኩ ይህ ውሳኔ የሚያስከትለው የሰላም መቃወስ ኮለል ብሎ ነው  የሚታየኝ። አቢይ! ይህን እብደት ማስቆም የምትችለው አንተ ብቻ ነህ በዚህ ሰአት።
ለማ፣ ወርቄ ምን እያልክ ነው? ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ ሃይል ሲገባ እንዴት ነው የበለጠ ሰላሙ የሚደፈርሰው? ሎጂክህ አልገባኝም።
ወርቅነህ፣ ምኑ ነው የማይገባህ? በአዲስ አበባና አላማጣ መሃል ስንት ኪሎሜትር እንደሆነ ታውቃለህ? 757 ኪሎ ሜትር ነው። የህወሓት ጦር ከአላማጣ ተነስቶ አዲስ አበባ ለመግባት ስንት ሰአት እንደሚወስድበት ታውቃለህ? 10 ሰአት ብቻ። አዲስ አበባን ካንቀላፋበት ለመቀስቀስ የምታደርጉት ሁሉ የወሎን በር ለወያኔ ብርግድ አድርጎ እየከፈተለት መሆኑ አይታያችሁም አይደል!
ሙፍሪያት፣ ለካስ ያለምክንያት አይደለም የዳያስፖራ ነፍጠኞች በትግሬነት ሲከሱህ የኖሩት። አሁንም ወያኔ ይመለስ ይሆናል በሚል ፍርሃት ውስጥ ነው የምትኖረው?
ወርቅነህ፣ ለምን አልፈራም። ለራሴ እንዳይመስልሽ ፍርሃቴ። እኔማ እድሜ ለአንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ናይሮቢ ማቅናቴ ነው። የዚህ የታናሽ ወንድሜ የአቢይ እጣ ነው የሚያሳዝነኝ። ለኖቤል ሽልማት የታጨ ታላቅ ሰው፣ በራሱ ብሄርተኛ ፓርቲ ስግብግነት ተጠልፎ ሲወድቅ ማየት ያሳዝነኛል።
ለማ፣ የተመድን ሥራ ካገኘህ ወዲህ ባሉት ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የኢትዮጵያ አርበኝነትህ ደም ፍላት ከየት የመጣ ነው? የት ነበርክ እስከዛሬ?
ሙፍሪያት፣ የዲቃላ ችግር ነዋ፣ አሁን እኮ አማሮቹ ኢትዮጵያዊነታቸውን ሲሰናበቱ ኢትዮጵያን የሙጥኝ ብለው የቀሩት እኮ የአባታቸውን ወይም የእናታቸውን ዝርያ መምረጥ ያልቻሉት ዲቃላዎች ብቻ እኮ ናቸው ። ድንቄም ኢትዮጵያዊነት!
ደመቀ፣ ሙፊ፣ አሁን አንቺ ዲቃላ ብለሽ ያዋረድሻቸው የመሰለሽ ከተለያዩ ብሄረሰቦች መስተጋብር የተፈጠሩ ዜጎች፣ አርሶአደር ቅድም አያቶቻችን ተነጣጥለው ይኖሩባቸው ከነበሩ የገጠር አምባዎች ወርደው ከተማ ሲመሰርቱ ከየብሄሩ የከተማ ህይወት ጠርቶት የመጣው ሰው አብሮ ሲኖርና ሲዋሰብ የፈጠራቸው ናቸው። ከአባት ወይም ከእናታቸው ዝርያ መምረጥ አይገደዱም። ሁለቱንም የሚያዋድድ ኢትዮጵያዊነት አላቸው። በዚያ ላይ ማፌዝ ወይም መቀለድ የሚቻል አይመስለኝም። በሚሊዮኖች ስለሚቆጠር ህዝብ ነው የምናወራው። አዲስ አበባ ማለት ያ ህዝብ ነው። ማንነቱና ኢትዮጵያዊነቱ ሊከበር ይገባዋል። አዲስ አበባ የማንም ሳትሆን የነዋሪዎቿና የመላው ኢትዮጵያዊ የጋራ ሃብት ናት። ኢትዮጵያችን በዘመናዊ ታሪኳ ከመቶ አመታት በላይ በአዲስ አበባ ላይ ከዓለሙ የተበደረችውን፣ የተለገሳትን፣ ከየክፍለሃገሩ የመረጠችውንና የሳበቸውን ክህሎት፣ ወርቅ፣ እንቁ፣ ላብና እምባ፣ ባህልና ቋንቋ ለንቁጣና አዋህዳ አዲስ ኢትዮጵያን የፈጠረች ብርቅዬ ናት። የሚሻለን ሁላችንም ይህን ብርቅዬ አውቀን ማክበርና መንከባከብ እንጂ፣ ለማ እንደሚደሰኩረው በኦሮሞ ልዩ ሃይል መውረር አይደለም። ያ የሆነ ቀን ወሎ ብቻም ሳይሆን አፋርም ለወያኔ ሰራዊት ክፍት ይሆናል፣ ሚሌ 300 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደሚርቅ ታውቃላችሁ? ተው የተያያዝነው እልህና የማግበስበስ ፍላጎት ሁላችንንም ያጠፋናል፣ እረ ተው ተመከሩ!
አቢይ፣ እንዲህ የውስጣችንን አውጥተን መወያየታችን መልካም ነው። ሃሳብ ሳልሰጥ የቆየሁትም ጭንቅ ስላለኝ ነው። ቀላል መልስ የለውም። የኦሮሞ ብሄርተኝነት እድሌ ዛሬ ነው ብሎ ክተት ብሏል። በአንፃሩ ደግሞ አዲስ አበቤው ለህልውናው ፈርቷል። ዛሬ በኦሮሚያ ከተሞች የሚካሄዱትን መፈናቀሎች እያየ ነግ በኔ ብሎ ስጋት አሳድሯል። ይህ ላልታሰበ ግጭትና የህዝብ እልቂት ሊዳርገን ይችላል። በዚህ ላይ የህወሓቶች ወታደራዊ ግፊት ከተጨመረበት ለራሳችንም ህልውና አስጊ ሊሆን ይችላል። መላ መፍጠር አለብን። ከዚህ በፊት በአሜሪካ ጉብኝቴ ወቅት “ባለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ሁሉ ቆሻሻ ነበር” ብዬ በመናገሬ ህወሓቶች ቂም ይዘውብኛል። ያን የሚያስታግስ ንግግር ለማድረግ ስለተገደድኩ፣ ባለፈው ቀን በተካሄደው የፓርቲዎች ቃልኪዳን ፊርማ ሥነሥርአት ምክንያት በማድረግ “በመከላከያውና ደህንነቱ ላይ ፍፁም ቁጥጥር የነበረው ህወሓት ለሃሳብ ትግል ቦታ ሰጥቶ ሲረታም ሥልጣኑን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆኑ ከዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ የመነጨ ነበር” በማለት ወደሰላማዊ ፖለቲካ እንዲመለሱ የዘንባባ ዝንጣፊ ልኬላቸዋለሁ። ያ ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ የሰላም አማራጭ እንዲያዩ ያደርጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። በተጨማሪም የእጅ አዙር ንግግር እየሞከርኩ ነው።
ወርቅነህ፣ በመጀመሪያም ቃል ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሄር ሆነን ተቀብያለሁ፣ እቀበላለሁም። አቢዬ ግን በቃልህ ብዙ የምትመካ መስሎ ይሰማኛል። በተግባር የኦሮሚያ ልዩ ሃይል አዲስ አበባ እንዲገባ እየፈቀድክ ወያኔዎች በቃልህ ብቻ ስለደለልካቸው ለምን የሚያምኑህ ይመስልሃል? ቱሪስት ብላ ሊሉህ እኮ ይችላሉ።
አቢይ፣ መቼ ነው የፈቀድኩት? ፊርማዬ ያለበትን ማዘዣ አንብበሃል?
ደመቀ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፈፅሞ ያልገባህ ነገር አለ። አዲስ አበባ የፌዴራል ከተማ ናት፣ በኦሮሚያ ልዩ ሃይል ሲወረር ዝም ብለህ የምታይና እንዲወጡ ማዘዣ፣ እምቢ ካሉም ጡጫ እንዳለ ካልተናገርክ በዝምታህ ወረራውን የተቀበልክ ያህል ይቆጠራል። በዚህም ብቻ ሳይሆን የጌዶኦ ተፈናቃዮችን ረሃብ ለህዝብና ከአቅም በላይ ከሆነም ለዓለምአቀፍ ማህበረሰብ አለማስታወቅና ለተጎዱ አለመድረስ በጭካኔ ያስከስስሃል።
አቢይ፣ ደሜ እኔን በጭካኔ? ልቤን እያወቅከው? መንፈሳዊነቴን እያደነቅከው? ከቶ እንዴት ተስማማልህ?
ደመቀ፣ እኔማ አውቅሃለሁ ቀናና ጥሩ ሰው ነህ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ተወዳጅና መንፈሳዊ ሰው ነበሩ። ሆኖም የወሎን ረሃብ መደበቃቸው ለመንግስታቸው ውድቀት ምክንያት ሆኗል። ቅንነት ብቻውን ከውድቀት አያድንም ። በመጨረሻ የምትመዘነው በተሰጠህ ሥልጣን ምን አደረግክበት ተብለህ ነው። ያለበለዚያ እነዚህ ሁሉ የምእራብ አድናቂዎችህና ለኖቤል ሽልማት የሚያጩህ ሁሉ “በአጭር የተቀጨው ረጅም ጉዞ” ን ይፅፉልሃል። እንደምታውቀው ያ ለታላቁ ምሁር ለሃይሌ ፊዳም አልጠቀመው። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይሉ ነበር  እንደሚባለው “ጊዜን ሥራበት እንጂ አይሥራብህ!”። አቢይ ከልቤ ነው።
ለማ፣ ኤጭ! የነዚህን ፊውዳሎች ተረብ እንደ እውቀት አታመንዥግብኝ። ተጋግዘን ይሄን ሰው እንርዳው እንጂ አንዴ በወያኔ መጣብህ፣ አንዴ በታሪክ ማደንዘዝ ምን ይጠቅማል ብለህ ነው?
ደመቀ፣ እውነቱን ከእኔ ካልሰማ ከማን ይስማ ትላለህ? ተጋግዘን ላልከውም ተግባርህ እንደ ቃልህ በሆነ ጥሩ ነበር። ምንሊክ ቤተመንግስት ስትመጣ ትለሰልሳለህ፣ ጨፌ ኦሮሚያ ስትሄድ የኦነግን ተገንጣይ ዓላማ ታስወስናለህ ። እኔ እንዳንተ ወደባህርዳር በሄድኩ ቁጥር በአማራ ብሄርተኛው ግፊት አዴፓ የሚወስንበትን ሁኔታ ፈጥሬ ቢሆን ገና ዱሮ ከትግራይ ክልል ጋር በወልቃይትና ራያ ጉዳይ መታኮስ በጀመርን ነበር። ሆኖም የፓርቲዬን አመራር ገርቼ፣ ምንቆጣውን ተቆጥተን፣ ምናስፈራራውን አስፈራርተን፣ አንዳንዴም ተጎድተን ነው በሰላም ያለነው። እናንተ ለጃዋርና ቄሮ ሃገሩን እንደለቀቃችሁት ለቀን ቢሆን ኖሮ እኮ ዛሬ ይሄን የምናወራበት ቅፅበትም ባላገኘን ነበር። ለማ ውሾችህን ያዝ!
ለማ፣ አሁንስ እያስፈራኸኝ መጥተሃል፣ ለምንድን ነው እንደዚህ ያመረርከው?
ደመቀ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነዋ፣ አንድምታው ጭራሽ አልገባችሁም። ባለፉት 45 ዓመታት ኢትዮጵያ በየማእዘኑ ስትሸራረፍና የየብሄረሰቡ ነፃአውጪ ነኝ ባይ አውድማውን በባሩድ ሲለቀልቀው፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያን ወክላ ስለቆመች ነው፣ እስከዛሬም ሃገር ያለን። ይህ አልገባችሁ ብሎ፣ የኛ ጊዜ አሁን ነው ብላችሁ አዲስ አበባን ልትውጡ ስታሰፈስፉ፣ የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተናችሁ መሆኑ እንኳ አይገባችሁም። ሲበዛ ራስ ወዳድ ሆናችኋል።
ለማ፣ (መነፅሩን እያወለቀና ላቡን ከግንባሩ ላይ በመሃረብ እየጠረገ) ደሜ፣ ምንድን ነው የምትለው? ታዲያ ፖሊሳችንና ልዩ ሃይላችን ፊንፊኔ የገባ እንደሆን ምን ይጠበስ? የክልላችን ዋና ከተማ እኮ ናት።
ደመቀ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ጓደኛህን አንድ በልልኝ። ህገመንግስቱን ለመከላከል ቃለመሃላ ወስደን ሥልጣን ተረክበን በህገመንግሥቱ ስለማትታወቅ ፊንፊኔ ልናወራ አንችልም። እኔ እስከማውቀው ፊንፊኔ ፍልውሃ አካባቢ ያለች ቀበሌ ነች። ስለፊንፊኔ ለማውራት ክብሬና ቦታዬ አይመጥነኝም።
አቢይ፣ ደመቀ አታክርር እንጂ። ለማ ደግሞ ቃለመሃላ ለፈፀመበት ለኦሮሚያ ህገመንግስት አዲስ አበባ ፊንፊኔ ናት፣ ስለሆነም እንደ መኢሶንና ኢህአፓ በእናቸንፋለንና በእናሸንፋለን ባትጣሉ ጥሩ ነው።
ወርቅነህ፣ አቢይ ያልከው እንደተጠበቀ ሆኖ ሃገሪቱን የሚመለከት ጉዳይ ስንወያይ በሃገሪቱ ህገመንግስት መሠረት ውይይታችን መቃኘት ይኖርበታል። ነገ ደግሞ የአማራ ብሄርተኞች መጥተው በረራ እያሉ ማውራት ቢጀምሩ እንደነዚያ ፈጣሪያቸውን ለመውጋት የባቢሎን ግንብን እንደገነቡት ሰዎች ሳንግባባ እንፈርሳለን።
ደመቀ፣ (ወደ ለማ እየተመለከተ) አየህ ለማ በህገመንግስቱ መሠረት አዲስ አበባ የፌዴራል ከተማ ናት። በራሷ በመረጠችው ከንቲባና ከእቅፏ በወጡ ልጆቿ ፖሊስነት እንድትተዳደር ነው ህገመንግስቱ የደነገገው። የኦሮሚያ ክልል ፖሊስና ልዩ ሃይል መቀመጫ ናት የሚል አንቀፅ የለም። መለስ በ97 ምርጫ ሽንፈቱ በመብሸቁ የተነሳ የኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ማድረጉ ህገወጥ ነበር። እናንተንም አልጠቀማችሁም። እስኪ አስበው አዲስ አበባን ኦሮሞ እናደርጋለን ብላችሁ ስትማስኑ፣ ደቡብ ከኋላችሁ ተነስቶ የመሠረተውን የአዋሳን ከተማ እስቲ ተመልከት። ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት አምቦን ወይ ጅማን ወይም ነቀምትን የክልላችሁ ከተማ አድርጋችሁ ተቀብላችሁ ቢሆን ኖሮ፣ የኦሮሞ ቋንቋና ባህል የራሱን መዲና አግኝቶ የት በደረሰ ነበር። ያልሆነ የአቀበት ውድድር ነው የተያያዛችሁት። ሌላው ኢትዮጵያዊ ፈቅዶላችሁ አዲስ አበባ ብትገቡ እንኳን፣ በቋንቋና ባህላዊ ውድድሩ ትሸነፋላችሁ። ያንን ላለመቀበል መንግስታዊ ሥልጣንን ከለላ በማድረግ ትርፍ ጥቅም በማግኘት ለማሸነፍ ትገደዳላችሁ፣ ይህም ይበልጥ ከሌላው ኢትዮጵያዊ እየተገለላችሁ ተነጥላችሁ፣ ኦሮሞው ራሱ የሚያፍርባችሁ ቀን ይመጣል ። ከዚህ ይሰውራችሁ። በእኔ ይሁንባችሁ እልሁን ተውት፣ አዲስ አበባንም ለኢትዮጵያ ተውላት፣ ለኦሮሚያ አዲስ ከተማ ሁሉም ክልሎች ተባበረው ቢያስፈልግ ከበጀታቸው ደጉመውም ቢሆን ያቁሙላት። እስቲ እናንተም ቀልባችሁን ሰብስቡ። ምከሩበት። የኦነግን አጀንዳ ለመንጠቅ በሚል እየሄዳችሁበት ያለው እብደት ወያኔን ከነሚሊሺያው ሰገሌ ሜዳ ድረስ አንደርድሮ የሚያመጣ ነው የሚል ፍርሃት አለኝ። ግዴላችሁም በጉዳዩ አልቅሱበት። ቄሮአችሁን ምከሩ እንጂ በሱ አትመሩ፣ አለበለዚያ እኛም ፋኖአችንን መስማት የጀመርን ቀን ጉሮሮ ለጉሮሮ እንያያዛለን፣ ከዚህ ይሰውረን በሉ! አይዞን
ክፍል ሦስት ይቀጥላል።
Filed in: Amharic