>
11:42 am - Sunday May 22, 2022

ባላብዙ ስሟ አዲስ አበባ (የዳዊት ከተማ ፥ ሸገር፥ እንጦጦ፥ በረራ ፥ ፊንፊኔ) [ሀብታሙ ተገኘ]

ባላብዙ ስሟ አዲስ አበባ (የዳዊት ከተማ ፥ ሸገር፥ እንጦጦ፥ በረራ ፥ ፊንፊኔ)
ሀብታሙ ተገኘ
አንዳንድ የኢትዮጵያ ከተሞች ከአንድ በላይ ስያሜ አላቸው። አዲስ አበባም እንዲሁ በኦፊሳላዊ ደረጃ ከሚታወቀው በተጨማሪ ሸገር በሚል ስያሜ የሚጠሯት ሰዎች አሉ። ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባን ፊንፊኔ ብለው ኢንደሚጥሯት የሚታወቅ ነው። የኦሮሞ አክራሪ ፖለቲከኞች ፊንፊኔ ከሚለው ቃል ላይ ሙዝዝ ያሉበት ቃሉ ኦሮምኛ መስሏቸው ነው። በተመሳሳይ ብዙ ሰወች ሸገር የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል ይመስላቸዋል። ለንገር ገን ሸገርም ሆነ ፊንፊኔ የኦሮሞኛ ቋንቋ ፈጽሞ አያውቃቸውም። ፊንፊኔም ሸገርም እጅግ ጥልቅ መሰረት ያላቸው ፍጹም የአማርኛ ቃላት ናቸው።የዳዊት ከተማ፣ ሸገር፣ እንጦጦ እና ፊንፊኔ ስለተባሉት ስያሜዎች ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ነው። ቀጥሎ ያለው ጽሁፍ የዳዊት ከተማ፥እንጦጦ (በታሪክ ሁለት እንጦጦ ነበረ)፥ፊንፊኔ እና ሸገር የሚሉትን ስያሜዎች ታሪክ ይዳስሳል። የዳዊት ከተማ ከሚለው ስያሜ እንጀምር።
የዳዊት ከተማ
ከተቃጠለም በኋላ ሆነ ከመቃጠሉ በፊት በራራ ከአንድ በላይ ስያሜ እንደሚኖረው አያጠያይቅም። ከተሞችን በመስራቹ ስም መጥራት የተለመደ ስለነበረ በረራ ከመቃጥሏ በፊት የዳዊት ከተማ ተብላ እንደምትታወቅ መገመት ይቻላል። ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ጎንደርን የፋሲል ከተማ ብለው ይጥሩታል። በተመሳሳይ ብዙ ሰዎች መተማን የዮሃንስ ከተማ ብለው ይጠሩታል። ቋራ ውስጥም የቴዎድሮስ ከተማ የሚባል ስያሜ ያለው ከተማ አለ። በራራም የዳዊት ከተማ የተባለበት በዚሁ ምክንያት መሆን አለበት። ከተማው ከተቃጠለ በኃላ ግን ሰወች በራራን የሚያስታውሱት በመስራቹ ስም የዳዊት ከተማ በሚለው ብቻ ነው። ይህ ስለመሆኑ ጸሀፌ ትዛዝ ገብረ ሥላሤ የጻፉት ታሪከ ነግስት ያስረዳል።
በተጨማሪም ከተሞች ከተቆረቆሩ በኋላ ከአንድ ጊዜ በላይ የስም ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ። የደብረ ብርሀን እና የደብረ ማርቆስ ከቶሞች የስያሜ ለውጦች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ደብረ ብርሀን ቀዳሚ ስሟ ኢባ ነበር። ከተማዋ የስም ለውጥ ያደረገቸው በአጼ ዘርአ ያቆብ ዘመን ኢባ በተደረገ የኃይማኖት ጉባዔ ምክንያት እና ይህን ተከትሎ በታየ የተፈጥሮ ክስተት እንደሆነ በዘመኑ የተጻፉ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በተመሳሳይ የደብረ ማርቆስ ከተማ ቀዳሚ ስሙ መንቆረር ነው። መንቆረር እና ዘና በአካባቢው የንበሩ የጋፋት አባቶች ናቸው። ንጉሥ ተክለኃይማኖት ከመንቆረርም ከዘናም ይወለዳሉ። መንቆረር ከደጃዝማች ተድላ ዘመን ጀምሮ የጎጃም ከተማ በመሆን አገልግሏል፡ በኋላ የደብረ ማርቆስ ቤተ ክርስትያን ሲሰራ የጋፋት አባቶች ከሆኑት ባንዱ በመንቆረር የተሰየመውን የጥንቱን ቦታ በአዋጅ የስም ለውጥ አድርገው ደብራ ማርቆስ አሉት። ሆኖም ግን ከደብረ ማርቆስ ውጭ በሰፊው ባይታወቅም ደብረ ማርቆስን የአካባቢው ሰወች እስካሁን ድረስ መንቆረር ኢያሉ ይጠሩታል። የበራራም ታሪክ እንዲሁ ነው። የዳዊት ከተማም ተባለ በራራ ከተማው አንድ ነው።
ፊንፊኔ (ፍል ውሀ)
ፊንፊኔ ሰለሚባለው የቦታ ስም ከቀዳሚ የጽሁፍ መረጃዎች ውስጥ የእግሊዛዊው የሻለቃ ኮርንዋሊስ ሃሪስ መጽሀፍ አንዱ ነው። ሀሪስ በ1840ዎቹ መጀመሪያ ወደ ሸዋ የመጣው ከሽዋው ንጉስ ከሣህለ ሥላሴ ጋር የንግድና የወዳጅነት ስምምነት ለመፈራረም በእንግሊዝ መንግስት ተልኮ ነው። በዚህ ዘመን ንጉስ ሳህለ ስላሴ እንጦጦን፣ወጨጫን እና የአሁኑን አዲስ አበባን እስከ ጉራጌ እና ዝዋይ ሀይቅ ድረስ ያለውን አገር በቁጥጥራቸው አድርገውት ንበር። ሌላው ቀዳሚ መረጃ የጀርመኑ የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ሚስዮናዊ ዮሀንስ ክራፍ ነው። ወደሸዋ መጥቶ የነበረው በ1840ዎቹ ነው። ክራፍ በአሁኑ አዲስ አበባ አካባቢ ያሉትን ቦታወች ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ወደ አካባቢው በሄዱበት ጊዜ አብሮ በመሄድ ለማየት ችሏል። ወጨጫን፥ እንጦጦን፥ ፊንፊኔን እና ሌሎችንም በዙሪያው ያሉትን አካባቢዎች አይቷል። ፊንፊኔን በጎበኘበት ወቅት ሶስት ቦታ ላይ ፍል ውሃ እንዳየ ውሃውም ሰልፈር የሚበዛበት እና በጣም የሚያቃጥል መሆኑን ጽፏል።
ዮሀንስ ክራፍ እንደሚለው ፊንፊኔ አካባቢ በወቅቱ ይኖሩ የነበሩ ሰወች ከንጉሡ ጋር ለረጅም ዓመታት የዘለቀ የቅርብ ግንኙነት ነበራቸው። ጸሀፌ ትዛዝ ገብረ ሥላሤ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ከፊንፍኔ ጋር ስላለው የቀረበ ግንኙነት ተመሳሳይ መረጃ ይሰጣሉ። ንጉሡ ፊንፊኔ ላይ ቤት ሰርተው እጥር አሳጥረውበት እንደነበረ ገብረ ሥላሴ ጽፈዋል። በኋላም ንግስት ጣይቱ አዳሲ አበባን ሲቆረቁሩ በምኒልክ ፈቃድ ቀደም ሳህለ ሥላሴ እጥር ካሳጠሩበት ቦታ መኖሩያ ቤት እንዳሰሩ ጸሀፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ የሚከተለውን ጽፈዋል፣
የእንጦጦ፡ከተማ ቤቱም ዕድሞውም ስላማረ ብርዱ እጅግ የበረታ ነው። ነገር ግን ከእንጦጦ በታች ካለው ፍል ውሀ ለመታጠብ አጼ ምኒልክም ወይዘሮ ጣይቱም ወርደው ነበር። በዚያ ጊዜ ወይዘሮ ጣይቱ ከድንኳኑ ደጃፍ ሁነው ሙቀቱን ማማሩን ሀገሪቱን ተመለከቱ። ከዚች ሀገር ቦታ ይስጡኝ እና ቤት ልስራ ብለው ለመኑ። ንጉሱም ፊት ቤት አሠሪና ኃላ አገሩን እሰጥሻለሁ አሉዎ። ወይዘሮ ጣይቱም የት ልስራ ብለው ጠየቁ ። ንጉሥም አባቴ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ እጥር ያሳጠሩበት ይህ ነው ከዚህ ላይ ይሁን ብለው የሚያሰሩበትን ቦታ አሳዩዎ። በዚችም አገር ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ እንደ ነቢዩ እንደ ሚኪያስ ትንቢት ተናግረውባታል። ከትልቁ ዛፍ ከማዎቱ አጠገብ ተቀምጠው ጠጅ በቀንድ ቀርቦ ሰንጠረዥ እየተጫወቱ አንች አገር ዳዋ ሰፍሮብሻል ኃላም የልጅ ልጄ ቤት ይሰራብሻል ከተማ ያደርግሻል ብለው ተናግረው ነበር አልዎ። [138]
ቦታው ሌላ የኦሮምኛ ስያሜ ስላልነበረው ፍልውሃን ለመጀመሪያ ጊዜ ፊንፊኔ ብለው የሰየሙት ከቦታው የነበሩ የሸዋ የመንግስት ሹማምንት እና ኗሪዎች ናቸው። የሸዋ መንግስት የፊንፊኔን አካባቢ ከመቸ ጀምሮ በቁጥጥሩ እንዳስገባ የጽሁፍ መራጃ አላገነንም።
ምንም እንኳ ቀዳሚ የታሪክ ማስረጃዎች የተጻፉት በንጉሥ ሳህለ ሥላሤ የስልጣን ዘመን ቢሆንም ፊንፊኔ እና እንጦጦ የሚባሉት ስያሜዎች የተጀመሩት ከንጉሱ የስልጣን ዘመን በፊት መሆን አለበት። ፈረንሳዊው የታሪክ ተመራማሪ ፍራንሲስ አንፍሬ እንጦጦ የሚለው የቦታ መጠሪያ ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ እንደነበረ ጽፏል። ከመቸ ጀምሮ የቦታው መጠሪያ እንደሆነ መረጃ ባናገኝም ፊንፊኔ የሚለውን የቦታ ስያሜ የሰየሙት በዚኽው ጌዜ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የቦታ ስያሜ ከመሆኑም በፊት ፊንፊኔ የሚለው ቃል የአማርኛ ቋንቋ ከተፈጠረ ጅምሮ ነበረ። ቃሉ በአማርኛ ቋንቋ በጣም የደረጀ ጽንሰ ሀሳብ ያለው ሆኖ አግኝተነዋል። የአማርኛ መዝገበ ቃላት ይህንኑ ያረጋግጣሉ። አራቱን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከብዙ በጥቂቱ ቀጥሎ አቅርበናል።
የፊንፊኔ የቃሉ ዘር ‘ፊን’፣ (‘ፊን አለ’ ‘ፊን ፊን አለ’ እንደማለት) በአማርኛ ቋንቋ ጽኑ መሰረት ያለው ነው። የሚወክለው ጽንሰ ሀሳብም የምንጭን ውሃ አወጣጥ በሚገባ የሚገልጽ የ‘መፈንጠቅ’፣ የ’መፍረጥ”፣ የ’መፍለቅለቅ’፣ የ’መፍላት’ ስሜት ነው። ‘ፍል ውሃ’ የሚለውም ቃል በቅርጽም ሆነ በጽንሰ ሀሳብ ከ’ፊንፊን’ አንድነው። መፍላት ‘በጠባብ መውጫ በብዙ ቁጥር ተከታትሎ መውጣት’ ነው ልክ ‘አሸን ፈላ’ እንደምንለው። ስለዚህ ‘ፊንፊኔ’ም ‘ፍል ውሃ’ አንድ አማርኛ ናቸው።
በተለያየ ዘመን የተጻፉ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከላይ ያቀረብነውን ገለጻ ይደግፋሉ።እንደ አብዛኛወቹ የአማርኛ ቃላት ሁሉ የፊንፊኔ ስርዎ ቃሉ ሶስት ፊደል ያለው ፈነነ የሚለው ቃል ነው። የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት የሚከተለውን ፍች አስቀምጧል “ ፊን (ፈነነ) ፊር፣ መውጣት፣ መፍሰስ። ፊን አደረገ (በትንሽ በቀጭን ሸና አፈሰሰ)፤ ፊን ፊን አለ (ፊር ፊር አለ፤ ፈረረን እና ፈነነን አስተውል)። ፈነነ (ፊን አለ)፤ ፋነነ (ተነሳ ቀና ተቀሰረ ቆመ)።” በከሳቴ ብርሀን ተሰማ የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፊንፊኔ የሚውን ቃል “ፊን ፊን አለ ፍል ውሃ ከመሬት ሲመነጭ ወደ አየር ፊን እያለ ከመሬት ላይ ዘነበ” የሚል ትርጉም ሰቶታል። በቅርቡ የታተመው የቶማስ ኬን የአማርኛ እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ደስታ ተክለ ወልድ እና ከሳቴ ብርሃን ተሰማ ከሰጡት ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ነው “ፊን አለ ‘to squirt, spurt; ፊን ‘manner of flowing, spurt, jet; ፊንፊን አለ “to flow in spurts or jets, to squirt or spurt up, e.g. geyser; ፊን አደረገ ‘to cause to spurt, squirt (liquid); ፈነነ ‘to spurt, squirt.”
ቆየት ያሉት የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ፊንፊኔ ለሚለው ቃል ከላይ ከተዘረዘረው ፍች ጋሪ ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም ሰተውት እናገኘው አለን። ከነዚህም ውስጥ ጀ. ባይትማን የጻፈው የፈረንሳይኛ አማርኛ መዝገበ ቃል እንዲሁም እኛዚኦ ጉይዲ ያዘጋጀው የአማርኛ የጣሊያንኛ መዝገበ ቃል ተጠቃሽ ናቸው። በግዕዝ የተጻፈው ድርሳነ ራጉኤሉም ፊንፊኔን “ፍሉህ ማይ” ይለዋል፤ትርጉሙም ፍልውሀ ማለት ነው። ከላይ የተዘረዘሩት የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ሆነ ሌሎች ከዚህ ያልጠቀስናቸው ፊንፊኔን ከመሬት ተነስቶ ወደ ላይ የመውጣትን ወይም የመቆምን እንቅስቃሴ ያሳያሉ። ይህ ሁሉ መርጃ ስለ ፊንፊኔ የቦታ ስያሜ አጀማመር የሰጠነውን አስተያየት ያጠናክራል።
በኦሮምኛ መዝገበ ቃላት ግን ፊንፊኔ የሚለውን ቃሉን ማግኘት አልቻልንም። ለምሳሌ ኢ.ሲ. ፉት በጻፈው የእንግሊዘኛ-ኦሮምኛ መዝገበ ቃል ፊንፊኔ የሚለው ቃል አይገኝም። ከዚህ መዝገበ ቃል ያገኘነው ተመሳሳይ ቃል ‘ፊርፊርሳን [Firfirsa] ሲሆን ውሃ መርጨት (ልክ ፀበል እንድሚረጭ ሰው) እና ማጠጣት (ልክ አትክልት ወሀ እንደማጠጣት) የሚል ፊች ሰቶታል። ሥለዚህ ፊርፊርሳ በቅርጽ ከፊንፊኔ ጋር ቢመሳሰልም በጽንሰ ሀሳብ ፈጽሞ አይገናኝም። ዮሀንስ ክራፍ ካሳተመው የኦሮምኛ መዝገበ ቃል ውስጥ ሰለፊንፊኔም ሆነ ሌላ ተመሳሳይ ቃል አይገኝም። ከዮሀንስ ክራፍ መዘገበ ቃላት ውስጥ ፊንፊኔ የሚለው ቃል አለመገኘቱ ትልቅ አንድምታ አለው። ዮሀንስ ክራፍ ፊንፊኔን ከቦታው ድረስ ሄዶ አይቷታል፤ የመፋጀቱንም ነገር ጣቱን ወደላይ ከሚፈላው ውሀ በመክተት ሞክሮታል። በጣም ሰልፈር የበዛበትም ብሎታል። ከላይ እንደተገለጠው ፊንፊኔ የሚለውን ቃል ግን ዮሀንስ ክራፍ ባዘጋጀው የኦሮምኛ መዝገበ ቃላት አይገኝም። ኦሮምኛ ቢሆን ኖሮ ከዮሀንስ ክራፍ መዝገበ ቃል የግድ ይገኝ ነበር።
ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ በ1845 ዓመተ ምህረት ሎውሬንስ ቱሸክ ያሳተመውን የኦሮሞኛ መዝገበ ቃላት እንዲሁም በ2004 ዓመተ ምህረት ጥላሁን ገምታ ባሳተመው የኦሮሞኛ እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ፊንፊኔ የሚል ቃል ወይም በቅርጽም፥ በጽንሰ ሃሳብም በይዘትም ተመሳሳይ ቃል አይገኝም።
 ፊንፊኔ በኦሮሞኛ አይታወቅም ሸገር (ሸጋ አገር?)
አዲስ አበባን ሸገር ማለት የተለመደ ነው። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሸገር የሚለው ቃል በጣም እየተዘውተረ መጥቷል። የንግድ እና የመገናኛ ተቋማትም በመጠሪያነት ይጠቀሙበታል። አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት በፊት የተቋቋመው የሸገር ራዲዮ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ስለ ሸገር ያገኘነው የመጀመሪያው የጽሁፍ መረጃ የዡል ቦሬሊ መጽሀፍ ነው። ዡል ቦሬሊ አዲሱ እንጦጦ ለሶስት ዓመታት ተቀምጦ ነበር። ወደ እንጦጦ የመጣው ከተማው ከተቀረቆረ ከሶስት ዓመት በኃላ ማለትም በ1885 ዓመተ ምህረት ነው። ዡል ቦሬሊ እንደጻፈው አጼ ምኒልክ ከተማው እንዲጸና ሰዎችን ከሌላ ቦታ እያመጡ እንጦጦ ያሰፍሩ ነበር። ሰው የማሰባሰብ ስራ “በኦሮሞዎች ዲልዲላ በአማራዎች ሸገር ጨነቅ ተብሎ ይጠራ ነበር” ብሎ ጨምሮ ጽፏል። ቦሬሊ ሸገር ጨነቅ ለሚለው ቃል ፍች ወይም ማብራሪያ አልሰጠም። ቃሉ ሸገር እና ጨነቅ የሚሉትን ቃልቶች በማጣመር የተፈጠረ ነው።
በስርወ ቃላት ትንታኔ “ሸገር” ስር መሰረቱ “ሠገረ” ነው። የሚወክለው ረቂቅ ጽንሰ ሃሳብም “በመነሻ እና በመድረሻ መካከል ያለን ቦታ ማለፍን፣ መዝለቅን” ነው። ከዚህ ረቂቅ ጽንሰ ሃሳብ የውልድ ቃላቱ ፍቺዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ የሚከተለው የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት የ“ሸጐረ” እና የ“ሻገረ” አፈታት ይህን ጽንሰ ሃሳብ ያጎላል። “ሸጐረ፤(ሠጊር፡ ሠገረ)፤ወረወረ ቀረቀረ፤ዘጋ ደነቀረ። ሻገረ፤ተሻገረ፤በወንዝ በዥረት በዠማ በባህር በጎድጓ ስፍራ ላይ ዐለፈ፤ወዲያ ማዶ ኼደ። ስሩ ሰገረ ነው። (ተረት)፤ይህን ውሃ ማ ይሻገረዋል ቢሉ፤ተዝካር ያየ ተማሪ።” ሃሳቡ ከመያዣው ጋር ከተሳሰሩበት ከአማርኛ ወጣ ብለን ፍችውን በእንግሊዝኛ እና በኦሮምኛ ብንመለከት ነገሩ ለአዕምሮ ብሩህ ይሆናል። የደስታ ተክለወልድ ፍችዎች ከእንግሊዝኛዎቹ “cross” እና “bar” ጋር አንድ ናቸው። ሁለቱም የ”መሻገር፣ መዝጋት፣ ማጐሮ፣ መሸጐር” ሃሳብ አለባቸው።
ጨነቅ የሚለው ቃል ‘አጨናነቀ’ ወይም ‘መጨናነቅ’ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ደስታ ተክለወለድ ‘አጨናነቀ’ ለሚለው ቃለ አጠጋጋ፣አቀራረበ ፣አደራረበ” ይሚል ፍች ሲሰጡት ‘መጨናነቅ’ የሚለውን ቃል ደግሞ ‘መጠጋጋት፥መቀራረብ’ ብለውታል። [612-613] “ሸገር ጨነቅ” የሚለው ስያሜ የከተማዋን መመስረት ተከትሎ ከተካሄደው የሕዝብ ሰፈራ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ፣ ይህ “የመዝጋት”፣ “የማጎር”፣ የ”መሸጐር” አስተሳሰብ ከሃረጉ ቃላት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፤ “ከፍ ያለ የሰው ቁጥር በአንድ ቦታ በመስፈሩ የተነሳ የተፈጠረው “የመሸጐር” እና “የመጨነቅ” ስሜት የወለደው ስያሜ ይመስላል። ሌላ ታሪካዊ ማገናዘቢያ በሌለበት በቃላት ፍች ትንተና ላይ ለሚመሰረት ፍለጋ ስለከተማዋ ስያሜ ይህ ትንታኔ ወደእውነቱ የሚቀርብ መላ ሊሆን ይችላል። የኦሮምኛው “ዲልዲላ” ለሸገር ጨነቅ ተጨማሪ ፍንጭ ይሰጣል። ዲልዲላ የኦሮሞኛው መዘገበ ቃላት ድልድይ የሚል ፍች ይሰጠዋል። ስለዚህ ዲልዲላ “መሻገሪያ”፣ “ድልድል”፣ “ድልድይ” ስለሆነ “ሸገር ጨነቅ” “ጠባብ ድልድይ” እንደማለት ይሆናል።
ከላይ የሰጠነው ትንተና ሸገር ጨነቅ ስለሚለው ቃል እና ስለ እንጦጦ ዳግማዊ ለደት ጥሩ ማብራሪያ ቢሆንም ሸገር ለምን እና ከመቸ ጀምሮ የአዲስ አበባ መጠርያ እንደሆነች መልስ አይሆንም። እኛ ለማግኘት የቻልናቸው የታሪክ መረጃቸው ሸገር የሚለው ቃል ለአዲስ አበባ መጠሪያ እንደሆነ ፍንጭ አይሰጡም። ይህ እንደሌሎቹ አርስተ ጉዳዮች ሁሉ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልገዋል። የማህረሰብ የቦታ ስያሜ ትንታኔ (folk etymology) ስለ ሸገር ክፍተቱን በተወሰነ መልኩ ሊሞላ ይችላል ብለን አናስባለን። እንደሚታወቀው የማህረሰብ የቦታ ስያሜ ትንታኔ ብዙ ጊዜ ታማኘንት የለውም። አንዳንዱ በጣም አስቂኝ ነው። ነገር ግን በዚህ መንገድ የሚሰጡ የቦታ ስያሜ ትርክቶች ብዙዎቹ ታማኘነት ባይኖራቸው አንዳዶች በታሪክ ላይ የተመሰረቱ ነቸው። ስለ ሸገር ቀጥሎ የሰጠነው አስተያየት የማህበረሰብ የስያሜ መነሻ አተናተንን ድክመት ያገናዘበ እንደሆነ አንባቢ እንዲረዳልን እናሳስባለን።
ሸገር “የሸጋ አገር” ከፊለ ስም ወይም ቃል ነው የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህ እውነት ከሆነ በስርወ ቃላት ትንታኔ የሸጋ መሰረቱ ሸገነ ነው። የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሸገነን ‘አማረ፡ ተዋበ፡ አበበ’ ብሎ ተርጉሞታል። ሸገን የሰው የስም መጠሪያም ነው፤ትርጉሙም መልከ ቀና ወይም መልከ መልካም ማለት ነው። ሸገና ላገር መጠሪያነትም ያገለግላል። ደስታ ተክለ ወልድ ሸጋ የሚለውን ቃል “የሸገነ፡ ያማረ፡የተዋበ፡ ውብ፡ ቁንዦ” ብለው ተርጉመውታል። [1215] ከሳቴ ብርሀን ተሰማ ወልደ ሚካኤል በበኩላቸው የሸገነ የሚለውንቃል “የአማረ፥ የተዋበን ኾነ፥ተሽቀረቀረ፥ተሽቀነደረ” ብለው ሲተረጉሙት ሸገገን “በመልክ፥በልብስ፥ሸጋን፥ውብን ኾነ፥ተዋበ፥አማረ፥መልከ መልካምን ኾነ” ብለውታል። [331] የጉይዲ አምራኛ ጣሊያንኛ መዘገበ ቃላትም ተመሳሳይ ፍች አለው። [227-230] የበይትማንም እንዲሁ [285] ስለዚህ ሸገር ማለት የተዋበ ያማረ የአበበ አገር ማለት ነው።
ከላይ እንዳየነው ሸገነ ‘አበበ’ የሚል ትርጉም አለው። በዚህም ምክንያት ሸጋ አገር እና አዲስ አበባ ተመሰሳይ የትርጉም ይዘት አላቸው። ጸሀፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ንግስት ጣይቱ ፍል ውሃ ሳሉ አካባቢውን በአይናቸው ሲቃኙ ባዩት ነገር ሰለተማረኩ የአገሩን ማማር ስላወቁ ከተማ ለመቆርቆር እንደወሰኑ ጽፈዋል። ጸሀፌ ትእዛዝ እንዲህ ይላሉ፣ “በዚያ ጊዜ ወይዘሮ ጣይቱ ከድንኳኑ ደጃፍ ሁነው ሙቀቱን ማማሩን ሀገሪቱን ተመለከቱ።” ከተማውን አዲስ አበባ ያሉበት ምክንያት ፍል ውሃና አካባቢው ለኑሮ ተስማሚ ሸጋ አገር ሆኖ ስላገኙት ነው።
ከላይ የሰጠነው ትንታኔ ትክክል ከሆነ ሸጋ አገር ቀስ በቀስ ወደ ሸገር ተለውጧል። ይህ ደግሞ የሚያስገርም አይደለም። በአገራችን ባህል ሰወችን ውይም የቦታ ስያሜወችን በሙ ስማቸው ከመጥራት ይልቅ በከፊለ ስማቸው መጥራት በጣም የተለመደ ነው። ሸጎሌ የሚለው የአዲስ አበባ የሰፈር ስም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ሸጎሌ የቦታውን ስያሜ ያገኘው ከሸይክ ኮጀሌ ነው። ሸይክ ኮጀሌ የአሶሳ ባላባት ናቸው። ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመነ ምንግስት መጨራሻ አሶሳን አስተዳድረዋል። ሸይክ ኮጀሌ የተወሰኑ ዓመታትን አዲስ አበባ ግዞት በሚመስል ሁኔታ አሳልፈዋል። ወደ አሶሳ ከተመለሱ በኋላ አዲስ አበባ ሰፍረውበት የነበረው ቦታ በስማቸው ሸጎሌ ተብሎ ተሰየመ። የሰውየው ሙሉ ስም ሸይክ ኮጀሌ ቢሆንም ብዙ ሰው የሰፈሩብትን ቦታ የሚጠራው በከፊለ ሥማቸው ሸጎሌ ብሎ ነው። ሰወችን በከፊለ ስማቸው መጥራት በጣም የተለመደ ነው። ለምሳሌ ኢብራሂምን ይብሬ፣ገላውዴዎስን ገላዴ፣ሙሀመድን ማመዴ ውይም አመዴ፣ ቆስጠንጢኖስን ቆስጤ እና ዲሚጥሮስን ዲሞ ማለት በጣም የተለመደ ነበር። ሸጋ አገር ወደ ሸገር የተቀየረበትም ምክንያት በተመሳሳይ ሁኔታ ሊሆን ይችላል።
ሁለቱ እንጦጦዎች
ሰለ እንጦጦ የመጀመሪው የጽሁፍ መረጃ የግራኝ አህመደ የዘመቻ ጸሃፊ አረብ ፈቂህ ነው። አረብ ፈቂህ እንደሚለው እንጦጦ ላይ አጼ እስክንድር በጣም ታላቅ እና ሀብታም ቤተክርስትያን አሰርተውበት ነበር። ቤተክርስትያኒ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ወርቅም እንደተገኘ ጽፏል። እንደሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ንበረቱ ከተዘረፈ በኋላ ጂሃዲስቶች እንጦጦ የሚገነውን ቤተክርስቲያን በእሳት በውስጡ ከሚገኘው ቅርስ ጋር በዕሳት አጋይተውታል። በታሪክ ሁለት እንጦጦዎች ነበሩ።አንዱ እና ብዙ ሰው የሚያውቀው ሰሚነ አዲስ አበባ ያለውን አዲሱን እንጦጦ ነው። የጥንቱ እንጦጦ መገኛ ግን በወጨጫ እና በፉሪ ተራሮች መከከል ከዋደላ ተራራ ነበር።
ዡል ቦሬሊ ከመስከረም 1885 እስከ ህዳር 1888 ለሶስት ተከታታይ አመታት በእንጦጦ ከተማ ቆይታ አድርጎ ነበር። ቦረሊ የጥንቱ እንጦጦ ከአዲሱ እንጦጦ መገኛ በስተደቡብ ምዕራብ እንደሆነ ጽፏል። በ1890 ዓመተ ምህረት ባሳተመው መጽሀፍ ስለዚሁ አርስተ ጉዳይ የሚከተለው መረጃው አስፍሯል፤ “ ንጉሡ ቀደም ብሎ ይኖሩበት የነበረው አካባቢ መጠሪያ እንጦጦ ስለነበረ ይህንኑ ስያሜ ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ። እንዲያውም የቀድሞ መጠሪያው እንዲጠፋ ፍላጎት ነበራቸው። እውነተኛዋ እንጦጦ የምትገኘው ከፊንፊኔ ሁለት ሰዓት በሚያስኬደው ቄስ ቶሪንስ በኦርማ የቤት አሰራር ዘይቤ ካሰሩት ቤተክርስትያን እና ቤት ከሚገኙበት ቦታ ላይ ነው…”
ቦሬሊ ከሰጠው መረጃ በመነሳት እንጦጦ ከፊንፊኔ በስተደቡብ ምዕራብ ሁለት ሰዓት ከተሄደ በኋላ ለሚገኘው አካባቢ መጠሪያ በመሆን ለአንድመቶ ያህል ዘምን አገልግላለች ማለት ነው። አጼ ሚኒልክ ወደ አዲሱ እንጦጦ በሄዱበት ጊዜ ቦታው ዳዋ ውጦት በዱር ተሸፍኖ ነበር። ሰውም አይኖርበትም ነበር። ከተማው እንዲጸና ሰው እየሰበሰቡ ያስፍሩበት እንደነበር ዡል ቦሬሊ ጽፏል። ከላይ እንዳየነው ቦሬሊ የሚኒልክ ሰው የማሰባሰብ ስራ “በኦሮሞዎች ዲልዲላ በአማራዎች ሸገር ጨነቅ ተብሎ ይጠራ ነበር” ብሎ ጨምሮ ጽፏል።
ከቦሬሊ በተጫመሪ ሸዋን በአስራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት የጎበኙ ብዙ የውጭ አገር ሰወች ስለ ጥንቱ እንጦጦ መገኛ ጽፈዋል። ከነዚህም ውስጥ የተወሰኑትን የጽሁፍ ማስረጃውች ቀጥሎ እናቀርባለን። ስለ እንጦጦ ያዩትን እና የሰሙትን ከጻፉት የአውሮፓ ሰዎች መካከል ከሸዋው ንጉስ ከሳህለ ሥላሤ መንግስት ጋር የንግድና የወዳጅነት ውል ለመፈረም የተላኩት የፈረንሳይ መልክተኛ ሮቸት ሄሪኮ፣ የእንግሊዝ መላክተኛ ሻለቃ ሃሪስ፣ ወደሸዋ የክርስትና ሀይማኖት ለማስፋፋት የመጡት የጀርመንና የእንግሊዝ ሚሲዎናውያን አይዘንበርግ እና ዮሃንስ ክራፍ እንዲሁም ፈረንሳዊው አሳሽ ቲዎፍል ሊፈብሬ ይገኙበታል። ከነዚህ ሁሉ ስለ እንጦጦ፡ጥሩ መረጃ ያሰፈረው ዮሃንስ ክራፍ ነው። ንጉስ ሳህለ ስላሴ ወደ ጉራጌ በ1840 ገደማ ሲዘምቱ ዮሃንስ ክራፍ እንዲሁም ሮቸት ሄሪኮ አብረው ሄደው ነበር። ወደ ጉራጌ ሲዘምቱ እንጦጦን በቅርብ እርቀት እንደ ተመለከቱት የቤተ መንግስት እና የቤተ ክርስትያን ፍርስራሽ እንደሚገኝ እና ከግራኝ በፊት አጼ ልብነ ድንግልን ጨምሮ ብዙ የኢትዮጵያ ነገስታት መናገሻቸው እንደነበረ ሰወች የነገሩትን ጽፈዋል። [211-212]
ከዘመቻውም መልስ ወደ አንጎለላ ሲመለሱ በእንጦጦ አድርገው እንደ ተመለሱ ቀጥሎ ያለውን ወሳኝ መረጃ ጽፏል “About twelve o’clock, we entered into the territory of ….Metta Wotsheta (Wotchecha), from the moutnian Entoto, which the Gallas call Wotsheta (Wotchecha). About two o’clock, we encamped at the foot of Entoto, in a plain called Tshaffe holata (Tchaffe Holeta)…” [214] ቀጥሎም ፊንፊኔን ውይም ፍልውሀን አንዳየ እና በአክባቢው ምንም ለአይን የሚማርክ ነገር እንደሌለ የአካባቢው ኗሪዎች ከንጉሥ ሳህለ ስላሴ ጋር ለብዙ ዓመታት የዘለቀ በጣም ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው ጽፏል። [215-216]
በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰሜን ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ያሳለፈው ፈረንሳዊ አሳሺና ተመራማሪ አንቷ አባዲ በ1890 ባሳተመው የኢትዮጵያ መልካ ምዕድር በተሰኘው መጽሀፉ ዮሀንስ ክራፍ ሰለ እንጦጦ በዝርዝር የጻፈውን የሚያጠናክር መረጃ አስፍሯል። ባጭሩ አንቷ አባዲ እንጦጦን ከፉሪ ተራራ በስተሰሜን ከፊንፊኔ እና ከማርያም ጊፍቲ ዋሻ ቤተክርስትያን በስተደቡብ እንደሚገኝ ይገልጻል። ሮቸት ሄርኮ በበኩሉ እንጦጦ በአስራ ስድስተኛው ምዕተ ዓመት በሸዋ አውራጃ የደረሰው ምስቅልቅል ከመፈጠሩ በፊት አጼ ዘርአ ያዕቆብ በእንጦጦ ተራራ ላይ ቤተ መንግስት አሰርተው ይኖሩ እንደነበረ ጽፏል። ሮቸት ሄርኮ ከንጉሥ ሳህለ ስላሴ ጋር በ1841 በሸዋ ያደረገው የጉዞ ማስታወሻ በካርታ የተደገፈ ነው። ካርታውም ፍልውሃን (ፊንፊኔን)፣ ሮጌን፣ የረርን፣ ፉሪን ፣ ወጨጫን እና እንጦጦን ያሳያል። የእንጦጦም መገኛ ከፉሪ በቅርብ እርቀት ከወጨጫ በስተደቡብ ነው። በ1846 ዓመተ ምህረት ድጋሚ ባዘጋጀው ካርታ እንጦጦ ከፊንፊኔ በስተምዕራብ ከፉሪ ተራራ በቅርብ እርቀት አስቀምጧታል።
ቲዎፍል ሊፈብሬ ከላይ የጠቀስናቸው ጸሀፊዎች ሰለ ጥንቱ እንጦጦ የሰጡትን ምስክርነት የሚጠናከር መረጃ በጻፈው ባለሁለት ቅጽ መጽሀፍ አስፍሯል። ቲዎፍል ሊፈብሬ በ1841 ከንጉሥ ሳህለ ሥላሤ ጋር በመሆን ፍልውሀ ወይም ፊንፊኔን አይቷል። ቲዎፍል ሊፈብሬ ከመጽሀፉ ጋር ያሳተመው ካርታ የጥንቱን እንጦጦ አቀማመጥ ያሳያል። በካርታው መሰረት የእንጦጦ መገኛም ከወጨጫ ሰሜን-ሰሜን ምዕራብ ከፉሪ በስተሰሜን ከፊንፊኔ በስተምዕራብ ነው። ወደ ንጉሥ ሳህለ ሥላሤ የተላከው የእንግሊዝ መንግስት መላክተኛ ሻለቃ ሃሪስ በበኩሉ እንጦጦ ከድንጋይ የተሰራ የግንብ ፍርስራሽ እንደሚገኝ ጽፏል። በአጼ ምኒልክ ዘመን ከዘይላ ተነስቶ ደቡብ ኢትዮጵያን ለማሰስ የመጣው ጣሊያናዊው ጉስታቮ ቢያንኪ እንጦጦ አካባቢ ሄዶ ነበር። እርሱም ወጨጫ እንጦጦ ይባል እንደንበር እና ከፉሪ በቅርብ እርቀት እንደሚገኝ ጽፏል።
በአጼ ምኒልክ ዘመን በንጦጦ እና ዝቋላ አካባቢ አሰሳ ያደረገው ጣሊያናዊ ሊዎፖልድ ትራቨርሲ እንጦጦን የጥንቱ እንጦጦ እና አዲሱ እንጦጦ ብሎ ለሁለት ከፍሎ ጽፏል። የጥንቱ እንጦጦም ከወጨጫ በስተደቡብ እንደሚገኝ በጽሁፉ ገልጧል።
የአጼ ምኒልክ ጸሀፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሤ አጼ ምኒልክ ወደፉሪ እና ወጨጫ በኋላም ወደ እንጦጦ የሄዱበት ምክንያት ድርሳነ ራጉዔሉ ላይ የተጻፈውን መሰረት በማድረግ የአጼ ዳዊት ከተማ የነበረበትን ትክክለኛ ቦታ ፍለጋ ነው። ድርሳነ ራጉኤል የዳዊት ከተማ በራራ በግራኝ ከተቃጠለ በኋላ የተጻፈ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በራራ ይቃጠል እንጅ ክአጼ ዳዊት ዘር በቀጥታ የሚወለድ ንጉስ ከተማውን እንደገና የሚመሰረት የሚያድስ በኋላ ዘመን ይነሳል የሚል ትንቢት ደራሲው ጽፏል። በትንቢት ማመን በወቅቱ የተለመደ ስለነበረ የሸዋ መሳፍንት በተለይም አጼ ምኒልክ ትንቢቱን ተቀብለውታል። አጼ ምኒልክ ትንቢቱ በእርሳቸው ዘመን እንዲፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው የዳዊትን ከተማ ትክክለኛ መገኛ በጽናት ይፈልጉ ነብር። ከተማው ያረፈበት ትክክለኛ ቦታ እስከሚገኝ የጥንቱ እንጦጦ ነው ወደተባለው ወጨጫ አጠገብ ክፉሪ በስተቀኝ በጊዚያዊነት የሚያገለገል ከተማ ማሰራት ጀምረው ነበር። ይህ የሆነው በ1879 ዓመተ ምህረት ነው።
ከላይ ከጠቀስናቸው መረጃወች በተጨማሪ አባ ፈርድናንድ የሚባሉ የፈረንሳይ ሚሲዎናዊ ስለ ጥንቱ እንጦጦ ጠቃሚ መረጃ ሰተዋል። አባ ፈርድናንድ መጀመሪያ ፊንፊኔ ቀጥሎም ቢርቢርሳ (የአሁኑ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ) ቤት ሰርተው የተቀመጡት በንጉስ ምኒልክ ዘመን በ1868 ዓመተ ምህረት ነው። ንጉስ ምኒልክም እና ምኳንቶቻቸው ወጨጫ ዳገት ላይ ቤት ሰርተው እንደተቀመጡ አባ ፈርድናንድ ጽፈዋል። በተጨማሪውም በጥር ወር 1880 ዓመተ ምህረት ጎበናን እና ከዚያው ቤት ሰርቶ የሚኖር ሂልግ የሚባል የአውሮፓ ተወላጅ እንዲሁም ጣሊያናዊውን ጉስታቮ ቢያንኪን እንጦጦ በሄዱበት ጊዜ ማግኘታቸውን በጽሁፉ አስፍረውታል። ጎበና ተብለው የተገለጹት ራስ ጎበና ስለመሆናቸው አያጠራጥርም። በመጨረሻም ፈርድናንድ እንጦጦ አንድ ቤተክርስትያን ማሰራታቸውን እና አጼ ምኒልክም የጥንቱን እንጦጦን ለአቡኑ መቀመጫ ይሁን ብለው ሰተው ለራሳቸው ድልድላ ላይ ሌላ ከተማ ማሰራት እንደጀመሩ አክለው ጽፈዋል።
ከላይ በቀረበው መረጃ በመነሳት የጥንቱ እንጦጦ ከወጨጫ ጎን ይገኝ እንደነበር ንጉስ ምኒልክም ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከትመውበት እንደነበረ በፍጹም እርግጠኘት መናገር ይቻላል።
ንጉስ ምኒልክ ጊዚያዊ ከተማ የሰሩበት ለዩ ቦታ ዋደላ እንደሆነ ከ1876 እስከ 1881 ዓመተ ምህረት ሸዋን ተዘዋውሮ ያያወ ጣሊያናዊው አንቶንዮ ቸኪ በካራታ የተደገፈ ዝርዝር መረጃ በመጽሀፉ ሁለተኛ ቅጽ ላይ አስፍሯል። በካርታው መሰረት ከተማው የተመሰረተበት ቦታ በፉሪ እና በወጨጫ መካከል አሁን ዋደላ ተብሎ በሚጠራው ከፍታ ቦታ ነው። ምኒልክ ያሰሩት ከተማ ፍርስራሽ አሁንም በቦታው ከወጨጫ በስተደቡብ ምዕራብ ከአዲስ አበባ በአስር ኪሎ ሜትር እርቀት ዛሬም ይገኛል። ይህ ቦታ አዲስ አበባን ከጅማ ከሚያገናኘው መንገድ በእግር የግማሽ ሰዓት የእግር ጉዞ ይወስዳል። ፈረንሳዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፍራንሲስ አንፍሬ በ1984 አካባቢ ከቦታው ድረስ በመሄድ ሰፊ መሬት ላይ ያረፈ ዙርያው በድንጋይ እድሞ የተከበበ ባለአራት ማዕዘን የቤት መሰረት እና የቤቱ ምስራቃዊ ግድግዳ ስይፈርስ አንዳገኘ በዝርዝር ጽፏል። በተጨማሪም የምኒልክ መኮነን የነበሩት የራስ ለዑል ሰገድ የቤት ፍርስራሽ ቦታውን በጎበኘበት ወቅት ማየቱን የቦታውን ሰዎች እማኝ ጠቅሶ ጽፏል። የዋደላ ማርያም ቤት ክርስትያንም ከጥንቱ እንጦጦ በ600 መትር ዕርቀት ስትገኝ የተመሰረተችውም በ1880 ዓመተ ምህረት ነው።
አጼ ምኒልክ ዋደላ ከጥንቱ እንጦጦ ላይ ያሰሩትን ጊዜያዊ ከተማ ትተው ወደ ድልድላ አዲሱ እንጦጦ የሄዱት በጥር ወር መጨረሻ አካባቢ በ1882 ዓመተ ምህረት እንደሆነ ከላይ ያገኝናቸውን አባ ፈርድናንድ የጻፉትን የጽሁፍ መራጃ በመጥቀስ ፍራንሲስ አንፍሬ በጥናቱ አረጋግጧል። ጸሀፌ ትዛዝ ገብረ ስላሴ በታሪከ ነገስቱ ላይ እንዳሰፈሩት ንጉሡ ወደ አዲሱ እንጦጦ የሄዱበት ምክንያት ሲፈለግ የነበረው የዳዊት ከተማ ፍርስራሽ በቦታው ስለተገኘ ነው። አባ ፈርድናንድ እንደ ጻፉት ከሆነ ምኒልክ ወደ አዲሱ እንጦጦ የመሄዳቸው ነገር ቁርጥ ሲሆን ከጥንቱን እንጦጦ ያስጀመሩትን ጊዚያዊ ከተማ አፍርሰው ነው የሄዱት። ምክንያቱ ባይታወቅም ንጉሱ የጥንቱ እንጦጦ በስሙ እንደጸና እንዲቀጥልም አልፈለጉም። ከላይ ያገኘነው ዡል ቦሬሊ እንደሚለው ከሆነ ንጉሡ የጥንቱ እንጦጦ ስያሜው እንዲጠፋ ፍላጎት ነበራቸው። ፍላጎታቸውም ተፈጽሟል። ብዙ ሰው የሚያወቀው አዲሱን እንጦጦ፡ነው። የጥንቱ እንጦጦ ፈጽሞ ተረስቷል።
ንጉስ ምኒልክ የጥንቱ እንጦጦ ስያሜ እንዲጠፋ የፈለጉት በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው እና ዋናው ምክንያት የአጼ ዳዊት ከተማ ትክክለኛ መገኛ አዲሱ እንጦጦ ነው ብለው ስላመኑ ነው። የፔንታገን ቅርጽ ካለው እድሞ እና አለቱን በመፈልፈል የተሰራ ምሽግ የሚመስል ቁፍር የተከበበ የቤተ መንግስት ፍርስራሽ አዲሱ እንጦጦ መገኘቱ ቦታው የአጼ ዳዊት ከተማ ስለመሆኑ በንጉሡ ዘንድ እንደ ዋና መረጃ ተወስዷል።ሁለተኛው ምክንያት እንጦጦ ለሁለት የተለያዩ የቦታ ስያሜዎች እንዲሆን ስላልፈለጉ ነው። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ንጉሡ መኖርያ ቤታቸውን በ1883 አዲሱ እንጦጦ አሰሩ። ከዚያም በ1885 እንጦጦ ራጉኤልን እና እንጦጦ ማርያምን አስጀምረው ከሶስት ዓመት በኋላ በ1887 አጠናቀቁ።
ነገር ግን ንጉስ ምኒልክ እንጦጦ ከትመው ብዙም አልቆዩም። በ1886 ዓመተ ምህረት በአጼ ምኒልክ ባለቤት በንግስት ጣይቱ አማካኝነት ከተማውን ከእንጦጦ ወደ ፍል ውሀ አዛወሩት።
Filed in: Amharic