>
8:01 am - Saturday December 10, 2022

የኦዴፓ ግርግር እቃ ለማንሳት ነው!  (ቴዎድሮስ ሀይለ ማርያም)

የኦዴፓ ግርግር እቃ ለማንሳት ነው!
ቴዎድሮስ ሀይለ ማርያም
         የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “ዜጎች በመላ ሀገሪቱ እየተፈናቀሉ ነው። በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚደረገው የደሃ ጎጆ ማፍረስ ድርጊት  ኢሰብአዊ ነው። ድርጅቱ አካሄዱን ካላረመ ለለውጡም ሂደት ለሀገራችንም ህልውና  አደጋ አለው” ብለን መጮሃችን ክፉኛ አስቆጥቶታል።
      ሌላው ቀርቶ ኦዲፒና ኦነጋውያን  በገዛ ሀገሩ ተመልካችና ተቆርቋሪ አጥቶ ለእልቂት የተዳረገውን  የጌድኦ ህዝብ  ለመታደግ የተካሄደውን የበጎ አድራጎት ጥረት “በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተከፈተ ዘመቻ” ሲሉ ኮንነውታል። ኦዲፒ በፌዴራልም ፣ በክልልም ከፍተኛ ሃላፊዎችና በኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን በኩል እንዴት ተደፈርኩ የሚል ዛቻና መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል። ነገሩ ወዲህ ነው!!
       ኦዲፒ አሳዳጊው ህወሃት ወልቃይትን ፣ ራያንና መተከልን ከአማራው በነጠቀችበት ስልት በዚህ የሽግግር ወቅት ግርግር ፈጥሮ  አዲስ አበባን በኦሮሚያ ለመዋጥ አቆብቁቧል። ይህ ራሱ ሊደብቀው ያልቻለው የአደባባይ  ምሥጢር ነው።   ሀገርን የሚያህል ሃላፊነት በአደራ የሰጠነው ድርጅት እንዲህ በራሱ ጊዜ አልጋ ሲሉት ዓመድ ሲሆን ያሳዝናል።
—————————
     አዲስ አበባ የማናት? የመላው ኢትዮጵያዊያን ናት። ኦዲፒ ይህቺን በጋራ ጥረት የተገነባች የአፍሪካ መዲና በህግ አግባብ  የሚወስድበት ቅንጣት እድል የለውም። “የራሴን እድል እወስናለሁ” ፣ “ፓርላማ አላደርሰውም” ምንትሴ እያለ እንደሚፎክረው በነውጥና በጉልበት ነጥቄ  እኖራለሁ ማለት ደግሞ የወፈፌ ምኞት ነው።
      የኦዴፓ “አርባን ፖለቲክስ”  የወቅቱን የሃይል አሰላለፍ  ፣ የራሱን ድክመትና ጥንካሬ ፣  የኢትዮጵያን ህዝብ የለውጥ መንፈስ በቅጡ ያልመዘነ ነው። ኮንዶሚኒየም በቄሮ ዱላ መንጠቅ ይቻል ይሆናል። ያም ቢሆን  ሌላው  አብሮ ለመኖር ፣ ለሀገር ህልውና ሲል ከተወው።
      አዲስ አበባን የምታህል ቁልፍ  የፖለቲካና ኤኮኖሚ እምብርት  በአጠና ወይም በልዩ ሃይል አስፈራርቼ ልንጠቅ  ማለት ግን አጉል መንጠራራት ይሆናል።   ኦሮሞውን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ከእንግዲህ  አምባገነኖችንና በህዝብ ህልውና የሚቀልዱ ዘረኞችን የሚሸከምበት ትዕግስት  ምን ያህል እንደተሟጠጠ ያለመገንዘብ ነው።
————————
     ኦዲፒ— አነጋውያን! “መካሪ የሌለው ንጉሥ ያለአንድ ዓመት አይነግስ” ነውና ለጋራ ደህንነታችን ሲባል ለህዝብ ጆሮ ስጡ።  አዲስ አበባን በነውጥ እንወስዳለን የሚል እብደት ሳይረፍድ አስወግዱና   ታሪክና ህዝብ የጣለባችሁን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ተሰለፉ።
       አሁን ተራው የእኛ ነው ካላችሁ ዘንድ ቅርፊታችሁን ስበሩና ሀገር አስተዳዳሪ ምሰሉ። የጥላቻና የዘረኝነት ግንብ አፍራሸ ፣ የፍቅርና አንድነት ድልድይ መሆናችሁን አስመስክሩ።
       ይህ ታላቅ ሃላፊነት የሚጠይቀው  ትዕግስትን ፣ አስተዋይነትን ፣ ፍትሃዊነትን ስለሆነ አልቃሻነትን ፣ አኩራፊነትን አድሏዊነትን አስወግዱ።  ከአጉል ፍረጃ ፣ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨትና የጀብደኝነት አባዜ ይልቅ  የመፀፀትና የይቅርታ መንፈስ አሳዩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእውነታው ታረቁ።
—————————
       የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በአስቸኳይ ወደ ቀልቡ ካልተመለሰና  በሰሞኑ የጠብ አጫሪነት ፣ የማናለብኝነት ፣ የተደፈርኩ ዛቻና ፉከራ ከቀጠለ  አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተስፋ ያደረገበት የለውጥ ሂደት ቀንደኛ እንቅፋትነቱን ያረጋግጣል። ህዝብን ማንም ወደማያተርፍበት የእርስ በርስ መተላለቅ በመማገድ ሀገር ያፈርሳል። ፈጣሪያችን ከዚህ መቅሰፍት ይታደገን!
Filed in: Amharic