>

ዶር አብይ ነውጠኞችን በጊዜ ካላስቆማቸው ራዕዩ እንደከሸፈና እሱም እንደፖለቲከኛ መክሸፉን ማመንና ማሳወቅ ይኖርበታል!!! (ኤፍሬም ለገሰ)

ዶ/ር አብይ ነውጠኞችን በጊዜ ካላስቆማቸው ራዕዩ እንደከሸፈና እሱም እንደፖለቲከኛ መክሸፉን ማመንና ማሳወቅ ይኖርበታል!!!
ኤፍሬም ለገሰ
ያ እንደዚያ የተጨበጨበለት፣  በኢትዮጲያዊነት ስሜት ያስፈነጠዘን፣ የተሰገደለት፥ የፈጣሪ መልዕክተኛ አድርገን ስናየው የነበር ሰው ምነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠፋብን?
በኔ እይታ ትላንት እንደዚያ ሲናበቡና እጅና ጓንት ሆነው የነበሩት በቲም ለማ ይጠሩ የነበሩት  ዛሬ ሁሉም ወደ ተለያየ አቅጣጫ መጓዝ የጀመሩት ዶ/ር አብይ በብሄር የተደራጀውን ኢህአድግ  የተሰኘውን ድርጅት በማፍረስ ሁሉንም ያቀፈ ኢትዮጲያን ማዕከል ያደረገ ፓርቲ ለመመስረትና የጎጥ ፖለቲካው በአገራችን ቦታ እንዳይኖረውና አገራችንን ለማትረፍ  ሃሳብ ባቀረቡበት እለት ነው።
ለምን ቢባል ይህ አካሄድ  ለጎጠኛው ፅንፈኛውና በበታችነት ስሜት እራሳቸውን ላሳመኑት የኦነግና የኦዴፓ (ኦህዴድ ) አንዳንድ አባላት እንዲሁም ህወሃትና ሌሎችም በብሄራቸው  ስም የስልጣንና የኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ለማርካት ሲሉ የሚነግዱባቸው የቡድን አባላት ስላልተመቻቸው የለውጡን ጉዞ ለመቀልበስ እፍረተ ቢሱን ጃዋርን ከፊት በማድረግ አንዳንድ ዛሬን ብቻ የሚያዩትን  ሆድ አደር  ጅሎችን ከጎኑ በማሰልፍ አገርንና ህዝብን የማመስ ዘመቻውን ተያይዘውታል።
ዶ/ር አብይ እንዳሉን “ስንኖር ኢትዮጲያዊ ስንሞት ኢትዮጲያ” ባሉን ከፀኑ  ከጎናቸው እንደምንሰለፍና ማንኛውንም መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን።
ዛሬ ያለውን የኢፌዴሪ ህገ መንግስት  የፅንፈኞቹና የጎጥ ፓለቲካ ተከታይ ፖለቲከኞች እንዳይነካ የሚሉት ለሰይጣናዊ አላማቸው የሚመቻቸውን አንቀፅ 39 ለማስተግበርና የስልጣን ጥማቸውን ለማርካትና ዘላለማዊ ህይወት እንዳላቸው ቁሳዊ ሃብት ለማከማቸት  ሲሉ እንጂ ለህዝባችን ሰላምና አንድነት አይደለም ቢሆን ኖሮ ዛሬ በጌዴኦ 900000 ህዝብ እንዲሁም የለገጣፎ፣ ለገዳዲ። ሱሉልታ፣ አራት ኪሎ። በአጠቃላይ በተለያዩ የአገራችን ቦታዎች ህዝብ ባልተፈናቀለ፣ ቤት ንብረቱ ባልወደመ፣ ባልተዘረፈ፣ ሰው ባልሞተ ባልተረባ ግፍ ባደረሰበት ነበር። በተጨማሪም
የኢህፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 10፣ 14፣ 15፣ 16፣ 17፣ 24ንዑስ አንቀፅ 3 የሰብአዊና ዲሞክራሲ መብቶች በተከበሩ ነበር። አንቀፅ 25 የእኩልነት መብት፥ አንቀፅ 30 ሰላማዊ ሰልፍ
አንቀፅ 32 በአገር ውስጥ የመንቀሳቀስ ንብረት የማፍራትና የመኖሪያ  ቦታ የመመስረት መብት  እነኚህና ሌሎች የህገ መንግስቱ አንቀፆች  መተግበር በቻሉ ነበር።
አንቀፅ 49 ርዕሰ ከተማዋ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግስት እንደሆነና  እራሷን እንደምታድተዳድር ይደነግጋል እንጂ የማንም ብሄር በሷ ላይ ባለቤትነት እንደሌለው ይገልፃል። ነገር ግን ከመጀመሪያው የኦነግና ስሙን ብቻ የቀየረው ኦህዴድ በጋራ ለመስራት ሲዋዋሉ ዉሉ ሚስጥራዊ በመሆኑ ውስጡን ለቄስ ሆኗል ዛሬ ምናየውም የሚስጥሩ ውጤት ነው።
ተራው የኛ ነው የሚሉ ፅንፈኛ አክራሪና አሸባሪዎች እራሱን ካለ እፍረት አጋኖ የሚቀርበው አጋንታሙ ጃዋር ሞሃመድ የሚመራው የደናቁርት ስብስብ የሚያናፉለትን ህገ መንግስት ጥሰው በዱላ ላይ ሚስማር ሰክተው ፣ ገጀራ፣ ባንጋ፣ ጦር የመሳሰሉትን ይዘው “ሰላማዊ ሰልፍ” እንዲወጡ  ትዕዛዝ እየሰጠ ማየት ያስተዛዝባል ትግስትም ወሰን አለው ይህ በጭፍንነት የሚደረግ ፉከራ መዘዙ  አንዱ አጥፊ እንዲሆን ሌላው ጠፊ ለመሆን አይመቻችም ሁላችንንም ያጠፋናል ሰከን ብለን አዕምሮ እንዳለው የሰው ፍጡር እናስብ። ዶር አብይ በአስቸኳይ ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ቲም ጃዋርን ከሰላምና ከለውጡ እንቅፋት ተግባራቸው ካላስቆማቸው ራዕዩ እንደከሸፈና እሱም እንደፖለቲከኛ መክሸፉን ማመንና ማሳወቅ ይኖርበታል።
ዘላለማዊ ህይወት ለማይኖር ምናለ ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት ጭንቅላታችንና ህብታችንን ብናውል?
ፖለቲከኞች ከህዝባችን ጋር ተናበቡ ህዝባችን የሚፈልገውን የለውጡ ጅማሮ  ወቅት በግልፅ አሳይቷል አሰምቷል ፈጠራውን ተዉት ለማንም አይበጅም ጊዜውንም ታሪካችንንም አይመጥንም።
ለታላቋ ኢትዮጲያና ለህዝቧ ብትሰሩ ህያው ሆናችሁ ትኖራላችሁ!!
ከፈጣሪ ጋር ኢትዮጲያን እንጠብቅ።
Filed in: Amharic