አቶ ነዓምን ዘለቀ በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከድርጀቱ አገለሉ
(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 9/2011)
የአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልና የንቅናቄው የውጭ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነዓምን ዘለቀ በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከድርጀቱ ማግለላቸውን አስታወቁ።
አቶ ነአምን ዘለቀ ለኢሳት በላኩት መግለጫ እራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከንቅናቄው ያገለሉት ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉትን የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ታጣቂዎች በተገባላቸው ቃል መሰረት ምንም አለመደረጉና ሂደቱ መጓተቱ እንቅልፍ ስለነሳኝ ነው ብለዋል።
እናም ከካምፕ ውጭ በዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግሮች የሚገኙ የሰራዊቱ አባላት ቃል በተገባላቸው መሰረት እርዳታ እንዲደርሳቸው ፣ የመልሶ ማቋቋሙ ሂደት በቶሎ እንዲጀመርም አሳስባለሁ ብለዋል።
አቶ ነአምን ዘለቀ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንን(ኢሳት) በማቋቋም፣ በመገንባት ሂደትና እስከ 2015 ድረስም በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከመሰራታቸው ሌላም እስካሁኑ ድረስም በቦርድ ስራ አስፈጻሚ አባልነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ ግን ከአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነትና ከንቅናቄው የውጭ ዘርፍ ሃላፊነቴ መልቀቄን ለድርጅቱ አባላት፣ ደጋፊዎች፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ የትግል መድረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማሳወቅ እወዳለሁ ብለዋል አቶ ነአምል ዘለቀ ለኢሳት በላኩት መግለጫ።
ከዚህ ሃላፊነታቸው ለመልቀቅ የተገደዱትም ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉትን የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ታጣቂዎች በተገባላቸው ቃል መሰረት ምንም አለመደረጉና ሂደቱ መጓተቱ እንቅልፍ ስለነሳኝ ነው ብለዋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልና የንቅናቄው የውጭ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነዓምን ዘለቀ ለኢሳት በላኩት መግለጫ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዴሞክራሲና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ የበኩሌን አስተዋጽኦ ሳደርግ ቆይቻለሁ ብለዋል።
በአለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ በውጭው አለም በተደረገው ትግል ልዩ ልዩ የትግል መድረኮችን በመስራችነት፣በአባልነት፣በአስተባባሪነት፣እንዲሁም በአመራር ሃላፊነቶች የዜግነት ግዴታዬን ከሚጠበቅብኝ በላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ለ26 አመታት ያልተቋረጠ የትግል አስተዋጽኦ አድርጌያለሁም ነው ያሉት።
በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ ከመጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ንቅናቄው የፓለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን ስምምነት በተደረሰ ጊዜ የፓለቲካ ፓርቲ አመራርም ሆነ አባል ሆኜ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለኝ በአመራሩ ላይ ለሚገኙ ሁሉ በተላያዩ ጊዜያት ገልጬ ነበር።
እስካሁንም ድረስ የቆየሁት ከመሪዎች አንዱ ሆኜ እንዳገለግል ለመረጡኝ አባላትና የሰራዊት አባላት ባለኝ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ስል ነው ብለዋል።
እናም መልቀቂያዬን ያዘገየሁት በኤርትራ በርሃና በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነው በጨለማው ዘመን ለኢትዮጵያ አንድነትና ለህዝብችን ነጻነት ህይወታቸውን ለመገበር ለቆረጡ በአሁኑ ጊዜም በካምፕ ውስጥና ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሰራዊት አባላትና ታጋዮች ህይወት ተገቢውን መስመር እስኪይዝ ነበር ሲሉም ነው የገለጹት ።
ቀደም ሲል መልቀቂያ አስገብቸ የነበረ ቢሆንም የንቅናቄው ዋና ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የተለያዩ የንቅናቄው አመራሮች በሀላፊነቴ እንድቆይ በነበራቸው ፍላጎት፣ እኔም ከነሱ ጋር ባደረኳቸው ውይይቶች በቦታው መቆየቴ ሰራዊቱን ይጠቅማል ብዬ ስላመንኩ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
በዚህ መሰረትም እስካሁን ድረስ በተሰጠኝ የሃላፊነት ቦታ ላይ የምችለውን እያገዝኩ ቆይቻለሁ።
ሆኖም ለቆሙለት አላማ ፣ ለንቅናቄያቸውና ለሃገራቸው ክብር መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ለመክፈል የቆረጡ የትግል ጓዶቸ ላለፉት 7 ወራት በከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ማየት ለኔ እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ሆኖብኛል ብለዋል።
አቶ ነዓምን እንዳሉት ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉትን የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ሰራዊት አባላትና እና የሌሎች የፓለቲካ ድርጅቶች ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ያለመ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ከ 7 ወራት በፊት ተመስርቶ ነበር።
ከውጭ ሀገራትም በተለይ የጀርመን መንግስት ለዚሁ የሚውል ገንዘብ ለመስጠት ከበርካታ ወራት በፊት ተስማምቶ ቆይቷል ብለዋል ።
ሆኖም ከተቋቋመው ጽሕፈት ቤት አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ እና ጉዳዩ ተገቢውን ውሳኔ ሳያገኝ እየተጓተተ በመቆየቱ የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት አባላት በተለይም ከካምፕ ውጪ እንዲቆዩ ተደርገው መልሶ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲጠብቁ የተነገራቸው ጭምር ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ለህሊና እረፍት በሚነሳ ሁኔታ ውስጥ እራሴን እንዳገኝ አድርጎኛል ነው ያሉት።
ይህንንም ከልዩ ልዩ የመንግስት ሃላፊዎችና ከመንግስት መዋቅር ውጭ ከሚገኙ በተለይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚቀርቡ ግለሰቦች በማስረዳት ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ ጥረቶች ባደርግም በሚፈለገው መንገድ ሊራመድ አልቻለም ብለዋል።
ይሕም ሆኖ ግን ጥረት ላደረጉ የመንግስት አካላትና ጉዳዩ ላሳሰባቸው ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በአንጻሩ ትላንት ከለውጡ በፊት እነሱን ደጅ ልንጠና ቀርቶ አጠገባቸው ለመድረስ እንኳን የምንጸየፋቸው፣ የተቀመጡበት የሃላፊነት ቦታ የሀገርና የህዝብ ችግሮች ለመፍታት መሆኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው የማይመስሉ፣ ራሳቸውን የኮፈሱ ከንቱዎችና ግብዞችን በዚህ ሂደት ለመታዘብ ችያለሁ ሲሉም ነው የገለጹት።
እናም የሰራዊቱ አባላት ቃል የተገባላቸው እርዳታ እንዲደርሳቸው ፣ የመልሶ ማቋቋሙ ሂደት በቶሎ እንዲጀመር፣ የንቅናቄው የስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች የሚያስፈልገው ያልተቋረጠ ትኩረትና ክትትል እንዲያደርጉ በድጋሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ ብለዋል።
ለአገራችን ሕልውና፣ ለሕዝባችን ሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚያስችል የፓለቲካ ስርዓት እንዲረጋገጥ የሚጨነቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እልህ አስጨራሽ ሁኔታ ውስጥ ብንገኝም ከዚህም ከዚያም የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙ አክራሪና ጽንፈኛ ብሄረተኞችና የለውጥ ቅልበሳ ቡድኖች ወጥመድ ሰላባ ላለመሆን በስልት፣ በሰከነ ጥበብና በሃገራዊ ሃላፊነት መንቀሳቀስ የግድ ነው ብዬ አምናለሁ።
ንቅናቄው በዜግነትና በማህበራዊ ፍትህ ላይ የቆመ የፓለቲካ ፓርቲ የምስረታ ሂደት ወደ ማገባደጃው በመድረሱ በአዲሱ ፓርቲ ለሚመረጡ አመራሮች እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ያለኝን ጽኑና መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።
በንቅናቄው አጠቃላይ የፓለቲካ ራዕይና ተልእኮ፣ በሚመሰረተው የፓለቲካ ፓርቲ አላማና ተልዕኮ፣ እንዲሁም ከማንም የንቅናቄው አመራር አባላት ጋር በግልም ሆነ በፓለቲካ ምንም አይነት ቅራኔ የሌለኝ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ ማለታቸውን አቶ ነዓምን ዘለቀ ለኢሳት የላኩት መግለጫ ያመለክታል።