>

ኦዲፓ/ኦህዴድ በእስልምና እምነት ላይ   ሴራ እየሸረበ ይሆን?!?  ( ዘመድኩን በቀለ)


ኦዲፓ/ኦህዴድ በእስልምና እምነት ላይ 
 ሴራ እየሸረበ ይሆን?!?
ዘመድኩን በቀለ
ለጭካኔ መግለጫዎች ሙስሊም ሴቶችን ያውም ሂጃብ ያጠለቁትን ከፊት አስቀምጦ እስልምና በህዝብ ዘንድ በክፉ እንዲታይ እያደረገ ይመስለኛል።
•••
ኦዲፒ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ ለገጣፎ በሱሉልታ እና በደቡብ በተከሰተው ራብ ላይም ጠንከር ያለ መግለጫ እንዲሰጡ እያደረገ ያለው ሂጃብ ያደረጉ ሙስሊም ሴቶችን ነው። የሚገርመው ከእነዚህ ሂጃብ ካጠለቁ ሙስሊም ከሚመስሉ ሴት የኦህዴድ ባለሥልጣናት መካከል አንዷ የሆነችው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንቷ ወሮ ጠይባ ሃሰን ሙስሊም እንዳልሆነች ብዙዎች ይናገራሉ። ሴትየዋ የፕሮቴስታንት አማኝ ከሆነች ዓመታት የተቆጠሩ እንደሆነና ነገር ግን እስከአሁን ሂጃቧን ሳታወልቅ ሙስሊም መስላ አክት እንደምታደርግ የሚናገሩ አሉ። መስጊድ ለመስገድ ያያት አንድም ሰው እንደሌለም ይነገራል። ነገር ግን እስከአሁን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሂጃቡን አላወለቀችም።
•••
ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው[ ለማ መገርሳ]፣ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞትም ኢትዮጵያ ነን። [ ዐቢይ አህመድ ] ወዘተ የሚል ወርቃማ ቃላትን የሚናገሩት ግን የኦዲፓ ባለ ሥልጣናትና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው። እነሱ አፈ ቅቤ ሆደ ጩቤ ሆነው ሳለ ሙስሊሞቹን የኦዲፒ ሴቶችም ሆነ ወንዶች ባለሥልጣናት በጭካኔ፣ በማፍረስ፣ በማሰደድ መግለጫዎች ላይ ከፊት መደንሰራቸው ዓላማው ለእኔ ግልጽ አይደለም። አልገባኝምም።
•••
ህዝብ የሚጨነቅባቸውን ጉዳዮች በሙሉ ያየን እንደሆነ የአስጨናቂው ፓርቲ ወኪል ሆነው ከፊት መስመር ሲሰለፉና ሲቀርቡ የምናየው የሙስሊም ስም የያዙ ከንቲባዎችን ስም ነው። ለምሳሌ የለገጣፎ ከንቲባዎች የቀድሞዋ ወሮ ጫልቱ ሳኒና የአሁና ሃቢባ ሲራጅ፣ የሱሉልታ ከተማ ከንቲባ ወሮ ሮዛ ሰኢድ፣ አሁን ደግሞ ጴንጤ ሆና ሳለ ሂጃብና ስሟን የሙጥኝ ብላ ያልለቀቀች ናት ተብሎ የሚነገርላት ወሮ ጠይባ ሀሰን ይጠቀሳሉ።
•••
እናም ከዚህ የተነሳ አንዳን ሙስሊሞች ኦዴፓ የሚባለው ፓርቲ ሆን ብሎ የሙስሊሞችን ስም ለማጥፋት እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው ብለው መናገር ጀምረዋል። ምስኪኑን ህዝብ አፈናቅለው አስርበው፣ ሲያበቁ ለምን በሙስሊሞች  መግለጫ እንደሚያሰጥ ምስጢሩ የተገለጠለት ካለ ቢነገረን መልካም ነው የሚሉም ተፈጥረዋል። እኔም የእነዚህ ጠያቂዎች አካል ነኝ። ለገጣፎ ያሁሉ ድሆችን ሲያፈናቁሉ የፈረዳባት ሙስሊሟ ከንቲባ ናት ወጥታ ሂጃቧን እንደለበሰች ያን እልህ የተሞላበት አናዳጅ መግለጫ እንድትሰጥ የተደረገው። አሁንም የሱሉልታን ህዝብ እንደዛው እያስጨነቀች ያለችው እንደተለመደው ሂጃብን መለያዋ የደረገችው ሙስሊም ከንቲባ ናት።
•••
በእስልምና አስተምህሮ መሠረት ሂጃብ ከልብስነት ባሻገር የተከበረ የአማኟ ሴት መገለጫ እንደሆነ ነው የሚነገረው። እናም ይህን ሂጃብ አድርጎ ህዝብ የሚያስለቅስ ሥራ መሥራት ለእምነቱ ተከታዮች ጥሩ ስሜት የሚሰጥ አይደለም። ለሃቀኞቹ ነው ታዲያ። እና እናንተ አሳፋሪ የኦዲፓ ባለስልጣኖች በአስቸኳይ ከእንደዚ ዓይነት ነውረኛና እምነቱን በሌሎች ወገኖች ዘንድ በጭካኔ እንዲታይ ከሚያደርጉ ተግባራት ታቀቡ። እናንተም ሴት ሙስሊም የኦዲፓ ባለሥልጣናት ወይ ሂጃባቹን አውልቃቹ ጣሉ ወይም ደግሞ ለሃቅ ቁሙ። በተለይ እስልምናን ትተው ፕሮቴስታንት ከሆኑ በኋላ ሂጃቡን እና ስማቸውን የሙጥኝ ብለው ላሉት ከንቲባዎች ነው መልእክቱ።
•••
የጅማዋ ተወላጅ ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል በተፈጥሮዋ ርህርህትና ሆደ ባሻ፣ ሆደ ቡቡም ናት ይባልላታል። ባለፈው ጊዜ መቀሌ ለስብሰባ በሄደች ጊዜ ከአዲስ አበባ ሸሽተው መቀሌ የተደበቁ የቀድሞ የትግል ጓዶቿን ባየች ጊዜ መድረኩን በንግግር ለመክፈት በተነሳች ወቅት ንግግር መድረግ እስኪያቅጣት ድረስ በእንባ ስትጣጠብ ታይታለች። በወቅቱ ብዙዎች አብረዋት አልቅሰዋል። ጌዲዮዎች በተፈናቀሉ ጊዜ ለአንዲት አራስ ልብሷን እዚያው ካምፕ ውስጥ አውልቃ ስታለብስም ታይቷል። ያችኑ አራስ ስደተኛ ሴትም ቅቤ ስትቀባ የታየውም እዚያው ካምፕ ውስጥ ነው። አሁን ግን ይህቺ በብዙዎች ቀልብ ውስጥ በመልካም ስም የገባች ሙፈሪያት እንድትዋሽ ተደረገ። እሷ ለጌዲኦ ተረጂዎች ምንም ዓይነት እርዳታ አልተቋረጠባቸውም ብላ እንድትናገር ከተደረገ በኋላ ወዲያውኑ እነ ራዲዮ ፋናና ዋልታ ቴሌቭዥን፣ ቪኦኤና ሌሎችም የስደተኞቹን ብሶትና እርዳታ ካገኙ 6 ወር እንዳለፋቸው እያለቀሱ እንዲናገሩ ተደረገ። በዜና መልክም ተበተነ። ከዚህ ዜና በኋላ ወሮ ሙፈሪያት በብዙዎች ተሰደበች፣ ውሸታም ተባለች፣ ሃቅ የላትም ተባለች። ጨካኝ አረመኔ፣ በረሃብተኞች ሰቆቃ የምትቀልድ ተደርጋ ተወቀጠች። ሂጃቧን እንዳጠለቀች በሁሉም ዘንድ ተወቀሰች። ጉዳዩ የሚመለከተው የክልሉ ፕሬዘዳንት ግን ጮጋ ተባለ። እናም ይሄ ሁሉ ሲታይ ኦፒዲ ምን አስቦ ነው ብለህ ለመጠየቅ ትገደዳለህ።
•••
ተመልከቱ ከዚህ በታች ያማቀርበው ዘገባ EBC ያቀረበው ዘገባ ነው። የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ ለድርድር አይቀርብም ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ሕገ ወጥ ግንባታዎች ከፈረሱባቸው የማህበረሰቡ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል በማለት የቀረበ ዜና ነው። ሪፖርተሯ ጋዜጠኛ አዲስዓለም ተሾመ ናት። ተናጋሪዋ ደግሞ ሂጃብ ያጠለቀችዋና የሙስሊም ስም የተሸከመችዋ ወሮ ጠይባ ሀሰን ናት። ጠይባ እንዲህ ትላለች። የንግግሯን ንቀት፣ ድፍረት፣ ትእቢት ብቻ ተመልከቱልኝ። ልብም በሉልኝ። አሁን ይህቺን ሴት አይቶ እስላም ስለሂነች ነው የሚናገሯት እያለ አንድ ሙስሊም ቢነጫነጭ ማን ይፈርድበታል። ለማንኛውም ወደ ዜናው እንሂድ።
•••
ወ/ሮ ጠይባ ከእነዚህ የማህበረሰብ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፣ መንግስት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት ስላለበት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
•••
ሕገ ወጥ ግንባታዎችን በሕግ አግባብ እየተከላከሉ መሄድ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ስራ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ጠይባ፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑና በፕላን እንዲመሩ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
•••
በዚህ ሂደት ውስጥ ከከተሞች ፕላን ጋር የሚቃረን ሕገ ወጥ ግንባታዎች  ሕጋዊ አግባብ እንዲይዙ እየተሰራ ነው ብለዋል ወ/ሮ ጠይባ፡፡
•••
የኦሮሚያ ከተሞች በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባቸው ከተሞች መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ ጠይባ፣ የከተሞች የልማት ስራ ሲሰራም ሆነ ሕጋዊ እርምጃ ሲወሰድ የብሔር ልዩነት በማድረግ አልተከናወነም፣ ለወደፊትም አይከናወንም ብለዋል፡፡ [ እዚህች ጋር ጣልቃ ልግባ ባለፈው ወሮ ሃቢባ ጃዋር ሚዲያ ላይ ቀርበው ስለለገጣፎው ሲናገሩ የሚጮሁት የሚዲያ አክሰስ ያላቸው ከሁለት ክልሎች የመጡ ናቸው ማለታቸው ልብ ይሏል። ሁለት ለጥቃት የተመረጡ ብሄሮች ማለት ነው።]
•••
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን በእኩል ያገለግላቸዋል፤ የክልሉ መንግስት ብሔር ብሔረሰቦችም በሕጋዊ መንገድ ሰርተው ሀብት ማፍራት እንዲችሉ የማገዝ አቋም እንዳለው ም/ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል፡፡
•••
የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ውስጥ ስህተት የተፈጠረ እንደሆነ የክልሉ መንግስት አጣርቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ጠይባ፣ በቤቶቹ ላይ ሕጋዊ መረጃ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል መረጃውን የማቅረብ ሙሉ መብት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
•••
ሕገ ወጥ ድርጊቶች ከመሰራታቸው በፊት ማስቆም የተሻለ አማራጭ ነበር ያሉት ወ/ሮ ጠይባ፣ በሕገ ወጥ ግንባታ ንግድ ላይ የተሳተፉ የመንግስት መዋቅር አካላት ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡[ ሃቢባ ተይዘዋል ስትል ጠይባ ደግሞ ገና ተጣርተው ይያዛሉ ትለናለች። አልተገናኝቶም። እኩል እንኳ አያስዋሿቸውም።]
•••
አንዳንድ አካላት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ እንዲደናቀፍ ለበርካታ ዓመታት አብሮ የኖሩ ሕዝቦች እንዲጋጩና በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ እየሰሩ መሆናቸውን ወ/ሮ ጠይባ ገልጸው፣ እነዚህ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የክልሉ መንግስት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
•••
በነዋሪዎቹ ላይ የመብት ጥሰት ያደረሱ የጸጥታ አካላት ላይ የማጣራት ስራ ተሰርቶ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል ም/ፕሬዝዳንቷ፡፡ [ ገና ወደፊት ማለት ነው ]
•••
ቤት ከፈረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ማጣራት ተደርጎ የድሃ ድሃ ለሆኑት የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ወ/ሮ ጠይባ፡፡ [ ቀልድ ]
•••
እየተከናወነ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ለማደናቀፍና ለፖለቲካ ፎጆታ ማዋል የሚፈልጉ አካላት ጉዳዩን የብሔርና የሃይማኖት መልክ ለማስያዝ የሚያራግቡት ወሬና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚያካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ተቀባይነት እንደሌለውና የክልሉ መንግስት እነዚህን አካላት ለሕግ ለማቅረብ  ይሰራል ብለዋል ወ/ሮ ጠይባ፡፡ [ በሳቅ ]
•••
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም አስቀድሞ ሕገ ወጥ ግንባታዎች እንዳይገነቡ የማድረግ ስራና ሕገ ወጥ ግንባታዎችንም ሕጋዊ አግባብ እንዲይዙ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ወ/ሮ ጠይባ ገልጸዋል፡፡
•••
የአሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ODP) ማዕከላዊ ጽ/ቤት የገጠር  አደረጃጀት ዘርፍ  ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፣ የተወሰደው እርምጃ በሌሎች ከተሞች ከተወሰደው እርምጃ የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡ አቶ አዲሱ  አክለውም አንዳንድ አካላት ግን ይህንን ሁኔታ ለፖለቲካ ፍጆታ እያወሉት ነው ብለዋል፡፡ [ ጠይባን ብዙ አስለፍልፎ አዲሱ በሁለት ቃል ዜናው ይሠራለታል]
ሻሎም !   ሰላም !
መጋቢት 10/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic