>

ሁሉም የሀገር ባለቤት ነው!!  (አቤ ቶኪቻው)


ሁሉም የሀገር ባለቤት ነው!!
 አቤ ቶኪቻው
ሙሉ ኢትዮጵያ የአንተ ናት የተባለ ሰው “ፊንፊኔ ኬኛ” ብሎ አንዷን ቦታ ለይቶ ሙጥኝ ማለት፤ ሙሉ ኮምፒውተር የአንተ ነው ተብሎ ኪቦርዱ የኔ ነው ብሎ እንደማልቀስ ነው!!!
አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? እኔ አዲስ አበባ የሁሉም ናት ስል የኦሮሞም ናት ማለቴ ነው። የኦሮሚያ ክልል ዋና ቢሮው አዲስ አበባ መሆኑንም አልቃወምም። ክልሉ ከተመቸው መቀሌ ወይም ባህር ዳር ላይ ዋና ቢሮውን ቢያደርግም መብቱ ነው ሁሉም ሃገሩ ነው።
#ኦሮሞ እንኳንስ ዛሬ እና ያኔ ድሮ… አድዋ ድረስ የዘመተው እዛም ድረስ ሃገሩ ስለሆነ ነው። ሙሉ ኢትዮጵያ የአንተ ናት የተባለ ሰው “ፊንፊኔ ኬኛ” ብሎ አንዷን ቦታ ለይቶ ሙጥኝ ማለት፤ ሙሉ ኮምፒውተር የአንተ ነው ተብሎ ኪቦርዱ የኔ ነው ብሎ እንደማልቀስ ነው። የምሬን ነው የምለው የተግባባን አልመሰለኝም። ኢጆሌ ኦሮሞ ፈታ በል አቦ ፊንፊኔን ለይተህ የኔ ናት አትበል። ሙሉ ኢትዮጵያ የአንተ ናት!
#ትላንት OMN ላይ ኦሮሞ ወጣቶችን አንድ ጋዜጠኛ ስለ አዲስ አበባ እየጠየቃቸው ነበር። ወጣቶቹ በጣም ስሜታዊ ሆነው እንዴት አዲስ አበባ የኦሮሞ አይደለችም ይባላል… ብለው ሲናገሩ አሳዘኑኝ… የሆነ ያልተግባባነው ነገር አለ እንጂ አዲስ አበባ የሁላችንም ናት ማለት ምንም የሚያስከፋ ነገር የለውም። የሁላችንም ማለት ኦሮሞንም ጨምሮ ነው!
#አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ሙሉ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው! በሃገራችን ላይ እኩል ባለቤትነት ከሌለን እና ከዚህ መልስ የአንተ ከዚህ መልስ የኔ ከተባባልን ብዙ ነው መዘዙ ብዙ ነው።
በአንድ ቦታ ላይ ወገቤን አስሬ እየሰራሁ እና እያለማው፣ ግብር እየከፈልኩ፣ ዜግነት እያለኝ፤ ይሄ ቦታ የአንተ አይደለም የሚባል ከሆነ ምን በወጣኝ አለማለሁ… ? ምን በወጣኝ ግብር እከፍላለሁ…? ምን በወጣኝ ክልሉን በቀናነት አገለግላለሁ? ሰዎች ወረዳቸውን፣ ዞናቸውን፣ ከተማቸውን፣ ክልላቸውን እና ሃገራቸውን በቀናነት እንዲያገለግሉ እና ለትውልድ የሚተርፍ ልማት እንዲሰሩ የወረዳው፣ የዞኑ የከተማው የክልሉ እና የሃገሩ እኩል ባለቤት መሆናቸው ሊረጋገጥላቸው ይገባል።
እና ወዳጄ እደግመዋለሁ ለአስተዳደር ሲባል የተሰመሩ ክልሎችን እንደ ግዛት ማየት መቆም አለበት። በመላው ኢትዮጵያ ላይ ሁላችንም ባለቤት ነን…  ወሰን አይወስነንም ፤ ድንበር አይገድበንም!
Filed in: Amharic