>

አዲስ አበቤዎችን ያላካተተው ለአዲስ አበባ የወደፊት ዕድል መፍትሔ አቅራቢው ኮሚቴና እንድምታው (ኤፍሬም የማነብርሐን)


አዲስ አበቤዎችን ያላካተተው ለአዲስ አበባ የወደፊት ዕድል መፍትሔ አቅራቢው ኮሚቴና እንድምታው

ከኤፍሬም የማነብርሐን

ሕውሓት ሥልጣን ከያዘ ከቀን አንድ ጀምሮ ለ27 ዓመታት፣ የሕውሓትን አስከፊ አገዛዝ ገርስሶ ለመጣል ያላሰለሰ ትግል ያደረገው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፈው አንድ ዓመት ብዙ መልካም ነገሮችን አይቷል። በመጨረሻዎቹ ሰዓቶች ላይ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ኢሕአደግ መግባቱን የተገነዘቡ የኦሮሞና የአማራው ጥገኛ ደርጅቶች፣ ሕወሐትን ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ አውርደውታል። ለዚህም ትልቅ አስተዋጽኦ ጠ/ሚ አቢይ ዋና ተዋናይ መሆናቸው ብዙም አከራካሪ አይደለም።

ነገርግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተለይም አዲስ አበቤዎች ምንም በነ”ቲም ለማ” ፍቅር ናውዘው የነበረ ቢሆንም፣ የኦዴፓና ኦነግ ደጋፊ የሆኑ ቄሮዎች በአዲሳበባ ጫፍ ዙሪያ፣ በተለይም በቡራዩ፣ በለጋጣፎ፣ ወዘተ በሜንጫና ምስማር ጫፉ ላይ በተሰካበት ዱላ በመረዳት አረመኔያዊ እንቅስቃሴ አያደረጉ መሆኑን በመሸበር መመልከቱን ግን አላቆመም። አዲሳበቤው ይሕንን በመቃወም ሕጋዊና ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ቢያካሂድም፣ የኦሮሞው መንግስት ጡንቻ በሱ ላይ፤ በራሱ ከተማ፤ ከአካባቢው ከራቀ ቦታ ቢመጡም በኦሮሞነት ደም ትሥሥር ሳቢያ ማዕከላዊ መንግስቱን በተቆጣጠሩ የኦሮሞ ኃይሎች በጣም በከበደ አኳኃን ጥቃት እንደሚሰነዘርበትና እንደሚወርድበት በተደጋጋሚ በተፈጸመበት እሥራትና የመብት ረገጣ ሳቢያ በበቂ መጠን ተመልክቷል።

በኦዴፓ የሚመራው የፌደራል መንግስትም በሕዝብ ያልተመረጡትንና በነኦነግና ኦዴፓ ጡንቻ በጉልበት የተሾሙትን የሱሉልታ የቀድሞው ከንቲባና አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚለውን ትርከት የሚያቀነቅኑትን ታከለ ኡማን ከጫንቃችን ላይ ያወርድልን ይሆናል ብሎ በሚጠብቅበት ሰዓት፣ እንዲያውም ይባስ ተብሎ ሰሞኑን ታከለ ኡማን እንደ “ኦዲሰስ” (Odysseus) በውስጡ ያስገባ አንድ የኦዴፓ/ኦነግ የትሮይ ፈረስ የአዲስ አበባን ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የሚል ስም ሰጥቶት አሁንም የሕዝቡን ፍላጎት በሚቃረን መልኩ አቋቁሞታል። ጥሩነቱ አዲሳበቤዎች እንደትሮይ ከተማ ነዋሪዎች ሳይሞኙ ይሕንን የኦዴፓ የትሮይ ፈረስ እንዳይገባ አግተውታል። ይህንንም የኦዴፓ የትሮይ ፈረስ ከአዲስ አበባ በራፍ እንዲያነሳ በባልደራስ አዳራሽ በጊዚያዊ የሕዝብ ስብስብ በተመረጠው በአስክንድር ነጋ የሚመራ አስተባባሪ ጊዜያዊ የሕዝብ ወኪል ኮሚቴ አማካኝነት አዲሳበቤዎች በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ለኦቦ ለማ መገርሳ ደብዳቤ በደረሰኝ በተደገፈ ደብዳቤ ጥያቄ አቅርበዋል።

እርግጥ ውዱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቅማቸው ውስንና ምናልባትም በአጥፊዎቻቸው ተከበው ከባድ ግፊት ያለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን መናገር በሚገባቸው ሰዓት ዝምታን በመምረጣችው ሰውን ግራ እያጋቡ መገኘታቸውንና፤ ባለፈው አንድ ዓመት ከልባቸው ተናግረዋል ብሎ ሕዝብ ያመነባቸውን የኢትዮጵያዊነት ተውፊትና በሥራ እንዲተረጉሙትም የሚያስችላቸውንና የሚያጎናጽፋቸውን ወገን በጣም ቸል ማለታቸውን መገንዘብ ብዙም አያዳግትም። ቢያውቁት (እርግጥ ተቸግረውም መሆኑን ሳንረሳ) ይሕ ወገን የኦሮሞ ጽንፈኛ ኃይል ሊሰጣችው ከሚችለው በላይ እጥፍ ድርብ ኃይል ሊሰጣቸውና ቅቡልነታችውን ሊጨምር የሚችል፣ ቸል ካሉት ግን ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ሊከታቸው የሚችል ኃይል መሆኑን ሊዘነጉ አይገባም። ይህም ኃይል በሙሉ ፍላጎቱ እሳካሁን ሲደግፋቸውና አሁን ለደረሱበት ዓለማዊ ገናናነት ምክንያት እንደሆነም ሊገነዘቡ ይገባል።

ለነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ አማርኛ ተናጋሪው ላይ የበለጠ ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸውና አሁንም በዚሁ አካሄድ እየሄዱ ያሉ መሆኑ ተደጋግሞ ይታያል። በመሆኑም አንዳንዴ እውነተኛው የትሮይ ፈረሱ “ኦዲሰስ” (Odysseus) እሳችው ይሆኑ ይሆን የሚል ፍርሐት እየመጣብን “እርኩስ መንፈስ ከአእምሮ ጥፋ” እያልን በጭንቀት ላይ እንገኛለን። ለምሳሌ ሰሞኑን የዶክተር አምባቸውን የፕሬዝደንትነት መሾም የክብር ሥነሥርዓት ላይ በዶክተር አምባቸው ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራና በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ችግር ዶ/ር አምባቸው መቀሌ ድረስ ሄደው እንዲፈቱ የጫኑባቸውን ኃላፊነት ስናይና፤ ትላንትም ብዙም በማያሻማ አኳኃን “ለአንድ ክልል ጥያቄ ስንል ሕገመንግስቱን አንቀይርም” ብለው ሕገ መንግስትን መቀየር በሕዝብ ምርጫ ሳይሆን በእሳቸው ጡንቻ ሊያቆሙት እንደሚተጉ ብመኢመስል መልኩ ሲናገሩ ለሰማ ትንሽ የደበቁንን ማንነታቸውን እያሳዩን መጡ ይሆን ወደሚል መላ ምት እንድንገባ ግድ ሆኖብናል። አሁን ዶክተር አምባቸው ራሱን መቀመቅ እንዲከት ካልሆነ በቀር ወልቃይትና ራያ ላይ ከሕዝብ አቋም የትለየ ምን ሊያቀርብ ይቻለዋል? እሳቸውስ ምን ያህል ጊዜ ያንን ወነጀለኛ ወርቅነህ ገበየሁንና ብዛት ያላቸው ጥፍር ነቃዮችንና ገራፊዎችን እሹሩሩ እያሉ እስካሁን በአካባቢያቸው እንዳቆዩ እንዴት ማየትይሳናቸዋል አሁን ዶክተር አምባቸው ላይ ከትግራይ ጋር ስላለው ግንኙነት ጉዳይ ይህን የሚያክል ትልቅ ጫና የሚጭኑበት።

አንድ ግልጽ መሆን የሚገባው ነገር መለስ ዜናዊና ሕውሐት፣ ኢትዮጵያዊነትን በትግራይ የበላይነት ለመተካትና የወልቃይትና ራያን ሕልማቸውን እውን ለማድረግ በተለየ በማነጣጠር በአማርኛ ተናጋሪው ላይ ከሌላው ብሔር ብሔርሰብ ላይ ከተደረገው በማይመጣጠን መልኩ ላለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ ጫና አድርገው ብዙ ሰቆቃ ፈጽመውበታል። እርግጥ ብዙ ኦሮሞዎችን ለስር ዳርገዋቸዋል። ነገርግን 14 ሚሊዮን የሚደርስን አማርኛ ተናጋሪ ያለክልል በማስቀረትና 
“መጤ” ኢንዲባል በማስደረግ ከጥቅም ውጭ ባደረጉበትና፣ በወልቃይትና ራያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን መሰል የዘር ማጥፋት ሙከራ ግን በሌላ ብሔር ላይ አላደረጉም። እንዲያውም ሌሎጭ ብሔር ብሔረሰቦች የሚሏቸውን የጠቀሙ መስሏቸው የለበጣ ክልል አየፈጠሩ የቋንቋ ወሰን ከልለው ላሁኑ ብጥብጥ ዳርገውታል። ይሕ ሐቅ በሆነበት ሁኔታ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከመቶ ሁለት መቶ ዓመታት በፊት ብዙ ግልጽነት የሌለውን ትርከት በማንሳትና (በወቅቱም ማንኛውም ቦታ አገር ለመመስረት የሚደረገውን አሰራር የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ለምን በኢትዮጵያ ተጠቀሙበት ሚል በሚመስል አግባብ በሌለው ክርከር) በማነጻጸር ይህንን በአማርኛ ተናጋሪው ላይ የተፈጸመውን ደባ በተቃራኒ ቆመው መከራከር ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ታይተዋል። የመቶ ሁለት መቶ ዓመት ታሪክን ባለፉት ሃያ ዓመታት ከተፈጸመ ወንጀል ማመሳሰል ፍርደ ገምድላዊና ወገንተኛዊ ዳኝነት ነው። ሌላው ቢቀር እስከ 14 ሚሊዮን የሚደርስ በየከተማው የሚኖር አማርኛ ተናጋሪ በመለስ ዜናዊና በዚህ የተበላሸ ሕገ መንግስት መብትና ክልል የለሽ መደረጉና በነኦዲፒ አሻጥር ወደመጤነት ኢንዲካለል ከፍተኛ ጥረት እየተደረግ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር መሆኑ አሁን የሚታይና አገሪቱም አሁን ለደረሰችበት የዘረኝነት ውጤት አንዱ ዋና ምክንያት መሆኑን መገንዘብ ብዙ የሚያስቸግር እሳቤ አይደለም። ይሕንን ሐቅ እንኳን ማየት እንዴት ያቅታል። የአዲስ አበባ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በታከለ ኡማ ሊወከል እንደማይችል የዲሞክራሲ መሰረታዊ ሕግጋቶች ይገቡኛል ለሚል መሪ እንዴት አይታይም። መጀመርያ ተሳሳቱ ቢባል እንኳን እንዴት የኦዲፓን የትሮይ ፈረስ አዲስ አበባ ላይ አምጥተው እንዴት ይገትሩብናል።

አዎ መለስ ዜናዊ የትግራይን የበላይነት ለማረጋገጥና 14 ሚሊዮን የሚሆን በኢትዮጵያ የተበተነው አማርኛ ተናጋሪ የሚፈጥረውን ችግር በአንድ ምት ለመምታት ድሮ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ሸዋና ውሎ አማራ የሚል ግዛት ፈጠረ። በፍጹም የማይታወቅ ኦሮሚያ የሚባል ክልልም እንዲሁ ቀድሞ ሸረኝነት በሌለው መልክ በወንዝ ክፍፍል መልከአ ምድር ላይ በተመሰረቱ ክፍላት ሀገራትን በመፍጠር ለተመሳሳይ ኢትዮጵያን በሚበትን አከላለል አስቀመጠ። በዘመነ መሳፊንትም ሆነ ከዚያ በፊት ኦሮሞ የሚባል አንድ አገር አልነበረም። ከመቶ ዓመት በላይ የነበረን አዲስ አበባን ወደታከላካይነት ደርጃ ዝቅ አድርጎት ቁጭ ብሏል። የኦሮሞ መንግስት አዲስ አበባ ስትመሰረት አልነበረም። እንዴት ሆኖ ነው ባንዴ እንዲህ ተነስቶ በእድሜ አራት አምስት እጥፍ የሚበልጠውንና ከመንገስት ምሰረታ አንጻር ሲታይ ደግሞ አራት መቶ አምስት መቶ አመታት ታሪካዊ መሰረት ያለውን ነባራዊ ዕውነታ እንዲገዳደረው የሚያደርገው? ደግሞም እኮ ይህን የመሰለ ጉዳይኮ መወሰን ያለበት በሁሉም ሕዝብ ፍላጎት ነው እንጂ በጥቅት የዘውጌ ኤሊቶች የጉልበት አካሄድ መተግበር ያለበት ጉዳይ አይደለም። ይህ የጥቂት የዘውግ ኤሊቶች ፍላጎትና አካሄድ የዲሞክራሲና የብዙሃንን የበላይነት መሰረተ ሀሳብ ይቃረናል።
ለማንኛውም አዲሳበቤ አዲስ አበባ ላይ የተቀመጠውን የአዲሳበባ ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በተባለው የኦዴፓና የኦነግ የትሮይ ፈረስ የነሱን ዓላማ እንዲያስፈጽሙ በውስጡ የተሰገሰጉትን እነታከለ ኡማን “እባካችሁ ነቅተንባችሗል፣ የራሳችንን ወኪሎች እኛው እራሳችን መርጠን ስለምናቀርብ አንፈልጋችሁም” በማለት አዲሳበባን በድብቅ እንዳይዙ አጥብቆ ዘብ በመቆም ይህ ፈረስ ካዲሳበባ ላይ እንዲነሳላት ባለማሰለስ ማሳሰብ ይኖርበታል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤

ኢትዮጵያም ለዘላለም ትኑር

Filed in: Amharic