>

ጠ/ሚ ዐቢይ ሆይ! የሚያሸብርዎ ህሊናዎት ነው! (ጌታቸው ሽፈራው)



ጠ/ሚ ዐቢይ ሆይ! የሚያሸብርዎ ህሊናዎት ነው!
ጌታቸው ሽፈራው
ጠ/ሚ ዐቢይ  በፌስቡክ የሚደርስባቸውን መጠነኛ ትችት “ሽብር” ብለውታል! የሀሰት ወሬ ሲሉ ደጋግመው መልዕክት አስተላልፈዋል! ሀሰት የትኛው ነው?
~ለኦሮሞ ብቻ መታወቂያ መታደሉ ሀሰት ነው?
~እነ ለማ መገርሳ የአዲስ አበባን ሕዝብ አሰፋፈር እንቀይረዋለን ማለታቸው ሀሰት ነው?
~የለገጣፎው ሰቆቃ ሀሰት ነው?
~ታከለ ኡማ አዲስ አበባን ፊንፊኔ ለማድረግ መስራቱ ሀሰት ነው?
~የጌዲኦ ሰቆቃ ሀሰት ነው?
– ድሀው ልብን ጠፍ አድርጎ የሰራውን ኮንዶምኒየም ለኦ.ኤም.ኤን ሰዎች ማደልዎስ ሀሰት ይሆን?
~ኦህዴድ ስልጣን ማግበስበሱ፣ ብዙዎችን መግፋቱ ሀሰት ነው? የትኛው ነው ሀሰት? የትኛው ነው ሽብር?
_
ሽብር እየተፈጠረ ያለው ፌስቡክ ላይ ሳይሆን ኦሮሚያ ውስጥ ነው።  ሽብር የሚፈፀመው በእርስዎ አስተዳደር ነው።
–  ሽብር የተፈጠረው  ቡራዩ ላይ ነው፣ እሱን በሚገባ አላወገዙም።
– ሽብር የተፈጠረው ለገጣፎ  ላይ ነው። እሱን አልሰማሁም ብለዋል።
  – ሽብር የተፈፀመው  የእርስዎ ፓርቲ ድጋፍ ባላቸው አካላት ኮዬ ፈጬ ላይ ነው። እሱን እንዳላዩ አልፈውታል።
– ሽብር የተፈፀመው ወለጋ ላይ ነው። ትናንትም ተፈፅሟል። ሰው ተገድሎ አስከሬኑ እየተቃጠለ  ነው ያለው “መሄድ አልችልም” ያሉበት ስፍራ ወለጋ ላይ ነው።
– ለመሆኑ ያንን ሁሉ ባንክ የዘረፈው ፣ ዜጎችን ሲሻው ገድሎ ሲሻው አፍኖ የሚወስደው ማህበራዊ ሚድያው ይሆን?
– “ያልታወቁ አካላት” እየተባለ ወንጀሉ የሚድበሰበስለት ኦነግ ሸኔ በወለጋ እየፈጸመ ያለውን ሽብር ለማስቀየስ ጉዳቸውን ፍርጥርጥ የሚያደርገውን ማሕበራዊ ሚዲያ መክሰስ ተገቢ አይደለም። እውነት ሲመስለው ማሕበራዊ ሚዲያው በእነ አብይ ፎቶ ተጥለቅልቆ ነበር። አጨብጭቦ ነበር። አሁን ሲነቃ መጠነኛ ትችት እያደረገ ነው።
ጠ/ሚ ሆይ! እያሸበረዎት ያለው ፌስቡክ አይደለም። ህሊናዎ ነው! ትናንት ጥሩ እንደሚሰሩ ተናገሩ። ማሕበራዊ ሚዲያው በድጋፍ አደመቀዎት። ዛሬ እየነቃ ነው። ትችት ጀመረ። የሚያሸብርዎት የትናንቱ እና የዛሬው ዕውነት ተጋጭቶ ነው! የሚያሸብርዎት ህሊናዎ ነው። ወይ ወዳሉት መመለስ አሊያም የሚተቹበትን ማመን ነው። የሚያንኑበትን እየሰሩ፣ በቃል የሚነግሩትን  ሕዝብ እንዲያምን ከጠበቁ ገና ይሸበራሉ። በመጠኑ ፌስቡክ ላይ እየተፃፈ ያለው እየተሰራው ካለው በጭልፋ ነው።  እውነታውን ታውቁታላችሁ። ለራሳችሁ የፃፋችሁት ሀቅ እንጅ ፌስቡክ ላይ የተፃፈ አይደለም።  ካልተፃፈ እውነት፣ የተፃፈና የምትተገብሩት አላማ እውነት ሆኖ እየፈጠጠ ነው። ፌስቡክ እየፃፈ ያለው ጥቂቱን ነው። ብዙውን እናንተ በድብቅ ተወያይታችሁ፣ ፅፋችሁ እየተገበራችሁት ነው። መሸበር የነበረባችሁ ገና ይህን ክፉ ሀሳብ እያሰባችሁ መልካም መልካሙን ስትነግሩን ነበር። መሸበር የነበረባችሁ መልካም መልካሙን እየነገራችሁን የራሳችሁን እውነት፣ ማድረግ የምትፈልጉትን ማስታወሻችሁ ላይ ስትፅፉ ነበር እንጅ  ከምታደርጉትና ማድረግ ከምትፈልጉት መካከል ትንሿ እውነት ፌስቡክ ላይ ስትወጣ አልነበረም!
የሚያሸብርዎት ፌስ ቡክ ላይ የተፃፈው አይደለም። የሚያሸብርዎት ለህሊናዎ የነገሩትና ለሕዝብ የሚነግሩት ስለተጋጨ ነው። የሚያሸብርዎት ሕዝብ ከሚነግሩትና ከማያደርጉት ይልቅ ህሊናዎ ላይ ያሰፈሩትን መስራት የሚፈልጉትን በጥቂቱ ስላወቀብዎት ነው።  የሚያሸብርዎት እውነት ነው! የሚያሸብርዎት ሀቅ ነው! እውነትን እየተናገሩ እውነትን መካድ ያሸብራል። ከፈንጅም በላይ ነው። የሚያሸብርዎት ህሊናዎ ነው!  ማሕበራዊ ሚዲያውን አይውቀሱ!
Filed in: Amharic