>

የነህ አይደለሁም- ፖለቲካ! (ደረጀ ደስታ)

የነህ አይደለሁም- ፖለቲካ!
ደረጄ ደስታ
የፖለቲካ ዶክተሮች ጋር ብትሄድ የዜግነት ፖለቲካ ይዞሃል ይሉህ ይሆናል። ማን ያውቃል ይሆናል! ሲያራምዱትም ሲያወግዙትም ሲታገሉትም ጎሰኛ ከሚያደርግ የዘርን በዘር መንጥር ፖለቲካ ብቸኝነት በስንት ጣዕሙ!!
ኦርሞ ነኝ አማራ ነኝ ወይም ትግሬ ነኝ እሚባባሉ ሰዎች መካከል ያለው ግርግር አያስፈራም። ያ መቸም እማይቀር፣ ሁሌም እሚሽከረከር ፍርጃ ነው። ችግሩ የዚያ ሰፈር ወዳልሆነው ወደሌላውም ዞሮ አንተ አማራ ነህ ኦሮሞ ነህ እሚል ነገር እንዳያመጣ ነው። እስካሁን ነኝ ያላለ ሳይሆን ነህ ያልተባለ ካለ ማለት ነው። ያስፈራል።
ኢትዮጵያዊነት ብቸኝነት ሊሆን ትንሽ ቀረው ልበል!? ሁሉም ወደ ዘር ጉድጓዱ ሲገባ፣ ከተንጣለለው አገር ብቻህን ትቀራለህ። ያን ጊዜ ካዐይን ይሰውርህ። የአይደለሁም ዘመን እያበቃ ይመስላል። ነኝ ባትልስ – ነህ መባልህ ይቀራል? የኛ አይደለም ያለህ ግንባርህን ይልሃል። ለይ ተብለሃል። ብቸኝነት፣ ገለልተኝነት፣ ጸረ ቡድናዊነትና ያልተነካካ ኢትዮጵያዊነት ራሱ እማያድን ሆኖ ሊያርፈው ትንሽ የቀረው ይመስላል።
ከኢትዮጵያዊነት አንዲት ስንዝር እንኳ ካነሰች ማንነት ጋር ተዳብለህ ከምትኖር ብቸኝነቴን ታቅፌ መሞትን እመርጣለሁ እማትልበት ዘመን እየመጣ ይሆን? ማንነትህን ተገደህና ተሰናክለህ ከመምረጥስ ብትሞት ይሻልሃል። ሲሆን ሲሆንማ ማንነቱ ራሱ ቀርቶብህ ፈጣሪህ እንደፈጠረህ ሰው ብቻ በሆንክ።
 ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያዊነት ብቸኝነት እንዳይሆን ያስፈራል። የፖለቲካ ዶክተሮች ጋር ብትሄድ የዜግነት ፖለቲካ ይዞሃል ይሉህ ይሆናል። ማን ያውቃል ይሆናል! ሲያራምዱትም ሲያወግዙትም ሲታገሉትም ጎሰኛ ከሚያደርግ የዘርን በዘር መንጥር ፖለቲካ ብቸኝነት በስንት ጣዕሙ
Filed in: Amharic