በዓፄ ምኒልክ ለመግባባት ኢትዮጵያዊ መሆን በቂ ነው
ዓፄ ምኒልክ ዓድዋ ላይ የተዋጉት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር አይደለም፤ ከትግራይ ሕዝብ ጋርም አይደለም፤ ከአማራ ሕዝብ ጋርም አልነበረም። ዓፄ ምኒልክ ዓድዋ ላይ ተዋግተው ዓለም አቀፋዊ ደማቅ ድል ያስመዘገቡት ከጣሊያን ጋር ነው። በዓፄ ምኒልክ ለመግባባት ኢትዮጵያዊ መሆን በቂ ነው። ዋጋ ከፍለን የለያየንን መጋረጃ መቅደድ አለብን። አየለ ወርዶ ከበደ ይውጣ የኔ ችግር አይደለም ይሄ። ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ «ፀሐዩ ንጉሥ» ይባሉ ነበር። ምክንያቱም ፀሐይ በፈጣሪ ይታዘዛል፣ አምፖል በቆጣሪ ይታዘዛል። እነዚህ ሰዎች የተዋጉትና ያዋጉት ለኢትዮጵያ ነው እንጂ ለአንድ የተወሰነ አካባቢ ወይም ሕዝብ አይደለም። ታዲያ ለምንድነው የታሪክ ሽሚያ የሚያስፈልገው? ለምንድነው በነሱ ህሊና ያልነበረ ማንነት ፈጥረን ባለቤት የምናበጅላቸው?
እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ነበሩ! ለኢትዮጵያ ተዋጉ! ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዎች እንዳትያዝ አደረጉ! የኢትዮጵያ ናቸው! ብሔራዊ ጀግኖቻችን ናቸው፣ የታሪክ ሽሚያው ቆሞ በጋራ እንደብሔራዊ ጀግና እናስባቸው፣ እንዘክራቸው።
እዚህ ሀገር ላይ ስኖር እንደ ሶስት ሰው ሆኜ ነው የምኖረው
እዚህ ሀገር ላይ ስኖር እንደ ሶስት ሰው ሆኜ ነው የምኖረው። እንደ ኢትዮጵያዊነቴ አስባለሁ። እንደ ሰውነቴ አስባለሁ። እንደ እምነት ተቋም ሰውነቴም አስባለሁ። እንደ ሶስት ሰውነት ለማሰብ ግን ሀገርና ህዝብ ያስፈልጋል። ያለ ሀገር መኖር አንችልም። ዓለምን የሚያጠፏት ተስፋ የቆረጡም ገደብ ያለፈ ተስፋ የሰነቁም ናቸው። መንግሥት እንደሁ ተቀያያሪ ነው። በሊቢያ የመጨረሻው ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ጋዳፊ ሆኑ። የኢራቁ ደግሞ ሳዳም ሁሴንን ማስታወስ በቂ ነው።
ሶሪያ የምትባለው ሀገር ለመቀጠሏ ምንም ማረጋገጫ የለንም። ጎረቤቶቻችንም እየታመሱ ነው። እዚህ እየተፈጠረ ያለው ችግርም ከነዚህ ሀገራት ባልተናነሰ አስጊ ነው። ፖለቲካዊ አመለካከትን እንደ መለያያ ምክንያት ማቅረባችን ተገቢ አይደለም። የቋንቋ ልዩነታችንን፣ የሃይማኖት ልዩነታችንን በምክንያት ማቅረብ ለድክመቶቻችን ሽፋን እንደ ማበጀት ነው።
4 ኪሎ ላይ ከሃጎስ ጋር የተጣላ ሰው፤ እስከ አድዋ፣ ሽሬ፣ አክሱም ድረስ መሣደብ፤ ከሁሴን ጋር የተጣላ እስልምናን መስደብ ነውረኝነት ነው። በአንድ ቶሎሳ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞ መስደብ፣ በአንድ ሃጎስ ምክንያት ሙሉ ትግሬን መስደብ፣ በአንድ የጎንደር ተወላጅ ምክንያት ሚሊዮን ጎንደሬን መስደብ ያልተገረዘ አንደበት ውጤት ነው።
ሰው ብቻ አትሁኑ
እንደኔ እንደኔ የዚህ ሀገር ችግር ከፖለቲከኞቹ በላይ ሃይማኖቶቹ ናቸው ብዬ አስባለሁ። የእምነት ተቋማት መስራት ያለባቸውን ስራ አልሠሩም። መንግሥት ልማት ሲል እኛም ልማት እያልን ነው የምናስተጋባው። ሃይማኖቶች ለአገሪቱ የለማ ጭንቅላት ነው ማፍራት ያለባቸው እንጂ መንግሥት ዶማ ሲያነሳ ዶማ እያነሱ፣ ህንጻ መገንባት አይደለም ድርሻቸው። ሁሉም ሃይማኖቶች ድህነትን ከመቀነስ ይልቅ ሃጢአትን መቀነስ ላይ ቢተጉ መልካም ነው። እነሱ የሃይማኖት ሥራቸውን አለመስራታቸው ነው ይህቺን ሃገር ለዚህ ችግር ያጋለጣት። ድሮ እርቅና ሠላም ለማምጣት ሃይማኖቶች ወሳኝ ነበሩ።
«ፍቅር እስከ መቃብር» ላይ እንኳን ሁለቱ ፊትአውራሪዎች ሲጣሉ ካህናት ናቸው ያስታረቁት።
ይሄ የቀድሞ ጊዜ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው። ዛሬ የእምነት ተቋማት በዚህ መደብ ውስጥ የሉበትም። ራሳቸው የሠላምና የእርቅ ተቋም መሆን ስላልቻሉ ነው፤ አጥፊን መገሠፅና መቆጣት ያልቻሉት። የመንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሲከሽፍ፣ የፓትሪያርኩ ሚና ወሳኝ ነበር። ወታደሩ መሳሪያውን የዘቀዘቀው በፓትሪያርኩ ተግሣፅ ነበር። አሁን ግን ተቋማቱ በራሳቸው ቅቡልነት የሌላቸው ሆነዋል። የራሳቸውን ስራ ትተው የመንግሥት ስራ እንስራ እያሉ ነው።
ልማት ሲባሉ ሰው ማልማት ትተው፣ ሱቅና ህንፃ የመገንባት ፉክክር ውስጥ ነው የገቡት። እንደ እኔ የእምነት ተቋማት፤ ድንጋይ መቆለልና ሲሚንቶ ማቡካታቸውን አቁመው የሰው ጭንቅላት እናልማ። ለዚህም ነው በሌላ ሀገር ትንሽ ወንዝ ካለ መዝናኛ አድርገው ይዝናኑባታል። እኛ ሀገር ትንሽ ወንዝ ካለ የመለያያ ድንበር አድርገን የምንጋጭበት።
ሰው ብቻ አትሁኑ…ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው? ብዬ ሳስብ፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና፣ የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው? እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው? እንደ እንስሳ። …ታላቁ ሊቅ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል «ሰው እግዚአብሔር ሲለየው ፤ ጠባዩ እንደ አራዊት፤ አመጋገቡ እንደ እንስሳ፣ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሔር ሆኖ ይቀራል»
በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው። ጥሪ የማይቀበል፤ ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሰራም ጆሮ አለ።…እኔ በዕውነቱ ከተማው ፈርሶ እየተሰራ ነው እየተባለ ዐይናማዎቹ ሲያወሩም ሲያስወሩም እሰማለሁ። ፈርሶ መሰራት ያለበት የሰው አስተሳሰብ ነው። የሰው አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሰራ፤ የተሰራ ከተማ ይፈርሳል።
ጃፓንና ቻይና ሀገራቸውን ያለሙት መጀመሪያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው። አስተሳሰቡ ያልለማ ሕዝብ የለማውን ያወድማል። ቤታችሁ ገብታችሁ እንድታጤኑት ነው። እነዛ (ምንትስ) የምንላቸው ክርስቲያኖችን አርደዋል… ምዕራባውያኑ ደግሞ ክርስትናን እራሱን አርደውታል።…ወንድ ለወንድ፣ ሴት ለሴት፣ በቤተክርስቲያናቸው እያጋቡ፤ ክርስትናን አጋድመው ያረዱ ምዕራባውያን ናቸው። ይህን ሁሉ ያመጣውም የምዕራባውያን ልክ ያጣ ነጻነትና ገደብ ያለፈ ዝርክርክነት ነው።
ማንም ዐይኑ እያየ የተቀበረ የለም
እንደምታዩት እኔ ዐይነ ስውር ነኝ። ቀላል አይደለም…እንኳን ዘወትር ዓይን አጥቶ አንድ ቀን መብራት ሲሄድ ስንት እንደምታማርሩ ታውቅታላችሁ። አንድ ቀን ግን አልቅሼ አላውቅም። ከሞት ወዲያ መብራት አለ። ከመቃብር በላይ መብራት አለ። … ወደ መቃብር ሲወርድ ማንም ዓይነ ስውር ነው። ማንም ዐይኑ እያየ የተቀበረ የለም። ተስፋችን ግን ምንድን ነው? ከሞት ወዲያ ሕይወት አለ።
…አንድ አንድ ጊዜ እመኛለሁ። የማይረባ ነገር ስናይ (ዓይናችንን) የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር ብየ እመኛለሁ። መልካም ነገር እስክናይ ድረስ ለጊዜው የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር። አሁን እንደው ጆሮ በካርድ የሚሰራ ቢሆን ሐሜት እንሰማ ነበር? የምንፈልገውን (ብቻ) አውርተን (ስዊች ኦፍ) እናደርገው ነበር። ስንት ዞማ ጸጉር ይዞ አስተሳሰቡ የከረደደ አለ።
ከጥላቻ ነጻ ውጡ
ጀርመን ሀገር ሄጄ ሲነግሩኝ፤ ባለ አምስት ኮከብ የውሻ ሆቴል አለ ተባለ። እኛ ሀገር አምስት ኮከብ ሆቴል ገብተው የሚበሉ ትንሽ ዝና (ሀብት) እና ትንሽ ሥልጣን ያላቸው ናቸው። ማን ይገባል ከነሱ ውጪ። ግን ሰዎች ነን። የጀርመን ውሻ ዛሬም ውሻ ነው። ለዘላለምም ውሻ ነው። እኛ ግን ሰው ነን። እንደ ሰው አስቡ (ምዕመናን) በማርያም። የንጉሠ ነገሥቱ የክርስቶስ አልጋ ወራሾች ነን… የደስታችሁ ልኬት የደስታችሁ ሚዛን ምግብና መጠጥ አይሁን፤ መኪናና ቤት ዝናንም አታርጉ። እኛ መለኪያችን ጽድቅ ነው። መለኪያችን መንግሥተ ሰማያት ነው። ያ የምንገባበት ቤት ደግሞ የተዋበ፣ የደመቀ፣ መብራት ውሀ የማይሄድበት፤ … 24 ሰዓት የሕይወት ውሀ የሚጠጣበት፤ ሀብታም፤ ደሀ፣ ተራ ሰው የማይባልበት፣ እገሌ ግባ እገሌ ውጣ የማይባልበት ቦታ ነው።
እንኳንስ ሚሊዮኖች ይቅርና አዳምና ሄዋንም በገነት ውስጥ አልተስማሙም ነበር።…ልባሞች ሁኑ፤ ከጥላቻ ነጻ ውጡ፤ ከተራ አመለካከትና ከጎጠኝነት ነጻ ውጡ፤ የሌላ ችግር ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ የራሳችሁ ችግር አራግፋችሁ ታጠቡ። የባሰውን እንዳይመጣ ጸልዩ። የተሻለውን ስጠን እንጂ እገሌ ይውደም እገሌ ይሁንልን አይባልም።