>

በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ዙሪያ ፍትሃዊ የሆነውን እይታዬ ላካፍላችሁ...!!! (ወንድወሰን ተክሉ - ጋዜጠኛ)

በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ዙሪያ ፍትሃዊ የሆነውን እይታዬ ላካፍላችሁ…!!!
(ወንድወሰን ተክሉ – ጋዜጠኛ)
ይድረስ ለምወዳችሁ ውድ የኦሮሞ ልጆች፣አክትቪስቶችና ፖለቲከኞች በሙሉ
በአዲስ አበባ ላይ ያነሳችሁትን ፍትሃዊ ያልሆነ የባለቤትነት ጥያቄን ታነሱ ዘንድ ትጠየቃላችሁ!!!
—-
**መነሻ- የኦሮሞ ነገድ ተወላጅ የሆኑ በርካታ ወዳጆቼ በአካልም (እንደአጋጣሚ ሆኖ በማህበራዊ ግንኙነታዊ ሰርክሌ ውስጥ የሚበዙት የኦሮሞ ነገድ ተወላጆች መሆናቸውን አሁን በቅርቡ ያወቅኩት እውነታ ነው)በስልክም «ወንዴ በአዲስ አበባ ጉዳይ የምታራምደው አቋም የኦሮሞን ህዝብ ፍትሃዊ ጥያቄ የማይቀበል ነውና አስተካክል » እያላችሁ የኦሮሚያን የአዲስ አበባ ባለቤትነትን እየገለጻችሁልኝ በመገኘቱ እኔም ይህንን አዲስ አበባ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው በሚል ጽኑ አቋም የዶ/ር አቢይ መራሹን መንግስት አካሄድ ለመቃወም የቻልኩበትን ፍትሃዊ የሆነውን እይታዬን ላካፍላችሁ ወደድኩና እነሆኝ ብያለሁ፡፡
ይህን ካልኩ በኃላ በማስቀጠል የምገልጸው ነገር ቢኖር እኔ በግለሰብ ደረጃ ባለኝ ግላዊ አቋም የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያዊያንን ነገዶችን ተፈጥሮአዊ መብቶችን ሳይሸራረፍና ሳይቀናነስ መከበር አለበት ብዬ የማምንና ብሎም ለዚህም እምነቴ ተግባራዊነት ለውጥና ተጽእኖ አመጣ አላመጣምን ምዘና ከግንዛቤ ሳላስገባ ግን የበኩሌን ግላዊ የሆነን አስተዋጽኦን ሳደርግን እያደረግኩም መሆኔን እገልጻለሁ፡፡
በዚሁም አቋሜ የተነሳ በ2016 ላይ ታዋቂውን የኦሮሞ አክትቪስትና ጋዜጠኛ የሆነውን ጁሃርን ስልክ ፈልጌና አስፈላልጌ በማግኘት ህወሃትን መተካት ያለበት የኦሮሞ መር የሆነ ትግል መሆኑን በመግለጽ ጁሃር እራሱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአመራርነት እንዲያዘጋጅና ብሎም የኦሮሞ ኤሊቶች ኢትዮጵያን በመምራት ደረጃ እንዲዘጋጁ እንጂ እራሳቸውን በኦሮሚያ ደረጃ እንዳይወስኑ ሳሳስብና ስገልጽ የነበረ ሲሆን በዚሁ አቋሜም የተነሳ ከ2012 ጀምሮ ኦሮሚኛ የፌዴራሉ መንግስት ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ከአማርኛ ጋር እኩል እንዲያገለግል መታወጅ አለበት ስልና ውስንም ቢሆን በግል አቅሜ ስገልጽ የነበረና እንዲሁም የዶ/ር አቢይ መራሹን የለውጥ መንግስት ከማንም በፊት በፍቅር ከመቀበልም ባሻገር ሰፊ የሆነ የድጋፍ ሽፋን እየሰጠሁ ያለሁ መሆኔንም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
የዶ/ር አቢይ መራሹን የለውጥ መንግስት አፍቃሪና ደጋፊነቴ አንዳችም ቅሬታ ሳይኖረኝ ለመጀመሪያ ግዜ በጽኑ የተቃወምኩት ተግባር ቢኖር የንጹሃንን ቤት በስመ ህገ የማስከበር ስራ የማፍረሱን እርምጃና የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ መንግስት የሚያራምደውን ግልጽ የሆነውንም ሆነ ግልጽ ያላደረገውን ምስጢራዊ አቋምና ዓላማን በእጅጉ ተቃውሜ የግሌን ዘመቻ መክፈቴም እውነት መሆኑን ለግንዛቤ ያህል ከገለጽኩ በኃላ ወደ አዲስ አበባ ጉዳይ ላመራ እወዳለሁ፡፡
***ውድ የኦሮሞ ወዳጆቼ በሙሉ ለምንድነው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ለኦሮሚያ በመስጠት ይጠቃለል የሚለውን አቋማችሁን ፍትሃዊ ያልሆነ ነው ለማለት የቻልኩት?’
1ኛ-አዲስ አበባ በህግ፣በታሪክና በስነምህንድስና ባለቤትነት ብቸኛ የኦሮሚያ ክልል አንጡራ ሀብት አትሆንም፡ አይደለችምም፡፡
ከታዋቂው አክትቪስት ጁሃር ጀምሮ እስከታች ድረስ በርካታ የኦሮሞ ወንድሞቼና ጋደኞቼ አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ውስጥ ያለችና ከተማይቱ በኦሮሞ መሬት ላይ የተቆረቆረች ስለሆነ የከተማዋ ባለቤት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መሆን አለበት ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ለመሆኑ ይህ «በኦሮሚያ መሬት ላይ ነው የተገነባችው » አቋማችሁን በየትኛው መንግስታዊ ህግና ታሪክ ነው እምታስመሰክሩት?በታሪካችን አራት ህገ መንግስታትን አስተናግደናል፡፡ የመጀመሪያው ፍትሃ ነገስት ቀጥሎም ዘውዳዊው ህገ መንግስት ሰልሶም የኢሰፓው የኢህዲሪ ህገ መንግስትና አራተኛው አሁን እየተገዛንበት ያለው የፌዴራሉ ህገ መንግስት ናቸው፡፡ በእነዚህ አራቱ ህገ መንግስታት ውስጥ የአዲስ አበባ ባለቤትነት በኦሮሞ ምድር ላይ የሰፈረች ባለቤትነቱም የኦሮሚያ ነው የሚል አንቀጽ አለን?’ በፍጹም የለም፡፡
2ኛ- አዲስ አበባ ያለችው በኦሮሚያ መሬት ላይ በኦሮሚያ እምብርት ውስጥ ነው የሚለው መከራከሪያ ነጥባችሁ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ያደርጋታልን?
አዲስ አበባ ከዛሬ አንድ መቶ ሰላሳ ሶስት ዓመት በፊት ማለትም በ1879 በወቅቱ ንጉሰ ነገስት በነበሩት ዳግማዊ ምንሊክ  ጭልጥ ባለሜዳ ላይ ተቆርቁራ የከተመች ከተማ ስትሆን ከተማይቱ በተቆረቆረችበት በዚያ ዘመን የኦሮሞ ነገድ ተወላጆች ከሌሎች ነገዶች ጋር ማለትም ከነገደ አማራ፣ነገደ ጉራጌና ወዘተ የሆኑ ስብጥርጥር ነገዶች የሚኖሩበት ምድር እንጂ በዚያን ዘመን የዛሬዋን አዲስ አበባን ግዛት በብቸኝነትና በባለቤትነት የኦሮሞ ገዢ እየገዛው ስለመገኘቱ የሚያሳይ የታሪክ ማስረጃና የህግ ድጋፍም በሌለበት ሁኔታ የዛሬው አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ ያለች ከተማ ስለሆነች በኦሮሚያ ስር መሆን አለበት የሚለው ሙግታችሁን ፍትሃዊነትን ሳጣበት ነው እማየው፡፡
አዲስ አበባን የመሰረተው ዳግማዊ ምንሊክ መሆኑ ቀርቶ የራሷን ግዛት የምታስተዳድር የኦሮሚያ ሀገርም ትሁን ራስ ገዝ ሀገር በኦሮሞ ንጉስና መሪ ተቋቁማ በምንሊክ «ወራሪነት» ወይም ተስፋፊነት ተይዛ ስማ ተቀይሮ አዲስ አበባ የተባለች ብትሆን ኖሮ የዛሬዎቹን የነገደ ኦሮሞ ተወላጆችን የባለቤትነት ጥያቄን ከሞራል አንጻር ፍትሃዊ ነው ብዬ ለመቀበል እገደድ ነበር፡፡
ማለትም አዲስ አበባ ልክ እንደ የአባ ጅፋሩ ከተማ ጅማ በአንድ የኦሮሞ ባላባት በኦሮሞ ግዛት አስተዳደር ስር ተመስርታ ያደገች አይነት ከተማ ብትሆን ከሞራል አንጻር ጥያቄው ፍትሃዊ ነው ልንል እንችላለን ማለቴ ነው፡፡
3ኛ-አዲስ አበባን ቆርቁሮ ያሳደጋት ማነው ?
የአንዲትን ከተማ ሁለንተዋ ባለቤትነት ለመጠየቅ ጠያቂው አካልና ወገን ቢያንስ ቢያንስ የዚያችን ከተማ ብቸኛ ቆርቋሪ፣ገንቢና አሳዳጊ ሆኖ ብናገኘው የባለቤትነት ጥያቄውን ቢያንስ ከሞራል አንጻር አሁንም ፍትሃዊ ሆኖ ልንቀበለው ይቻለን ይሆናል፡፡
ሆኖም ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ከተማዋ የተቆረቆረችው በበርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ጥሩ ስም በሌላቸው የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምንሊክ ሲሆን እኚህ ንጉስ ደግሞ የኦሮሞ ወይም የአማራ ወይም የትግሬም ሆነ የሌላ ነገድ ንጉስ የነበሩ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩ ሲሆን ከተማይቱን ገንብቶ በማሳደግና ዛሬ ያለችበትን ቅርጽና ይዘት እንድታገኝ በማስቻል ደረጃ የኦሮሞው፣አማራው፣ትግሬው፣ኤራትራ ያሉት ዘጠኝ ነገዶች፣የአምስት ዓመቱ ገዢ የነበረው ጣሊያን፣የጉራጌ፣ወላይታ፣ሀዲያው፣አፋሩ፣ጋምቤላው.…ወዘተ የሰማኒያ አንዱ ነገዶች አስተዋጾኦ ማለትም የእነዚህ ሁሉ ነገዶች ሀብት፣እውቀት ጉልበትና ኃይል ከተማዋን ከምንም አንስቶ ለዛሬው ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖሩበት ከተማ ለማድረግ በተቻለበት ሂደት ውስጥ ከምን አንጻር ሆኖ ነው የአንድ ነገድ ባለቤትነት ጥያቄ በእናንተ የኦሮሞ ነገድ ተወላጅ ወንድሞቼ ሊቀርብ የቻለው?? ከዚህም አንግል አንጻር ጥያቄያችሁ ፍትሃዊ አለመሆኑን ነው መረዳት የቻልኩት፡፡
4ኛ-የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ–
የእናንተ የኦሮሞ ወንድሞቼ ሌላውና ዋናው የመከራከሪያ ጭብጥ «አዲስ አበባ የተገነባችው በኦሮሞ መሬት ላይ ነው» በሚለው ነጥብ ሲሆን ከምን አንጻር እንደሆነ ግን በግልጽ ስታብራሩ አልታየም፡፡
በእርግጥ ዛሬ ከአዲስ አበባ ወጣ ስንል በምስራቅም ይሁን በምእራብ በደቡብም ሆነ በሰሜን የምናገኘው የመጀመሪያ ህዝብ የነገደ ኦሮሞ ተወላጆችን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ በኦሮሞ ነገድ ተወላጆች የተከበበች ከተማ አደጓታል፡፡ ያ ማለት ከተማይቱ የተገነባችበት መሬት የኦሮሞ ነው ማለት ነው ? ያ ማለት የከተማይቱ ባለቤት ኦሮሞ ብቻ ነው ማለት ነው?’
ለመሆኑ ይህ መሬት የኦሮሞ ነው፣የአማራ ነው፣የጉራጌ ነው፣ የትግሬ ነው የወዘተ ነው የምንለው ከምን አንጻር ነው?’
እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ የነበረውን ፊውዳላዊውንና ዘውዳዊውን መንግስት የይዞታ ባለቤትነትን መሰረት አድርገን ከሆነ የአዲስ አበባ ባለቤትነት በሚያስደንቅ ሁኔታ ወደ አልተጠበቀ ነገድ ሲወስደን እናገኛለንና ይህን መሰረት አድርጋችሁ እየጠየቃችሁ ነው ብዬ አልገምትም፡፡
በሌላ በኩል ከ1966ቱ አብዮት ወዲህ እስከዛሬው ህገ መንግስት መሰረት አድርጋችሁ የምትጠይቁ ከሆነ የመሬት ባለቤት መንግስት እንጂ ህዝብ አለመሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ሁለቱም ህገ መንግስታት ቁልጭ አድርገው አስፍረዋል፡፡
ስለዚህ ከምን አንጻር ነው የአዲስ አበባ መሬት ባለቤት ኦሮሞ ብቻ ሊሆን የቻለው ??
ሌላው የዚህ የመሬት ባለቤትነት መብት አንድ ነገድ ይሁን አንድ ህዝብ ለስንት ዘመናት በዚያ ምድር ላይ ቢኖር ነው ግዛቱ የእኔ ነው ብሎ እሚጠይቀው የሚለውን አወዛጋቢ ጥያቄን ገና ተወያይተንበት የምንፈታው ነጥብ ሆኖ ሳለና እንዲሁም የነገደ ኦሮሞ መስፋፋት እየበረታ ሄዶ የዛሬዋን አዲስ አበባንና አጠቃላይ ሸዋን እስኪጠቀልል ድረስ ይህንን ክልል ቀደም ብሎ ለዘመናት ሲገዛ የነብረው ነገድ ማነው ?? የነገደ ኦሮሞ ወደ ዛሬይቱ አዲስ አበባ የተስፋፋው በስንተኛው ክፍለዘመን ነው የሚሉትን ወሳኝ ጥያቄዎችን መልስ ሳንሰጥ የዛሬውን አሰፋፈር ላይ ተሞርኩዞ አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ የተቋቋመች ስለሆነ ባለቤትነቷ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መሆን አለበት የሚለው አቋማችሁን ምንም ፍትሃዊነት ላገኝበት እንዳልቻልኩ ነው መረዳት የቻልኩት፡፡
በእነዚህ ወሳኝ ነጥቦች ምክንያት በአዲስ አበባ ላይ በግልና በተናጥል የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የሚችል ማንም ኢትዮጵያዊ ነገድ የሌለ ሲሆን ባለቤትነቷ የመላው ኢትዮጵያዊያን ሆኖ ዛሬ ከምትጎራበታቸው የኦሮሚያ ቀበሌዎች ጋር ግን የሚያዋስኗትን የአስተዳደር ወሰኖችን መካለል እንዳለበት እረዳለሁ፡፡
ይህንን አመለካከቴን በአግባቡ ለሚተችና ለሚሞግትም ቀጣይ መልስ የምሰጥ መሆኔን እየገለጽኩ በአሁኑ ግዜ ሁላችንም በጋራ ማድረግና ማተኮር የሚገባን ጉዳይ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ስኬታማና ውጤታማ ለማድረግ በጋራ እንረባረብ በሚል ወንድማዊ ጥሪ ጽሁፌን እደመድማለሁ፡፡
Filed in: Amharic