>
5:13 pm - Saturday April 19, 6741

እዚህ ኛው ቤት ቁጭ ብለን ለዚያኛው ቤታችን ዳንቴል መስራቱን ማቆም አለብን! (አብነት አሰፋ)

እዚህ ኛው ቤት ቁጭ ብለን ለዚያኛው ቤታችን ዳንቴል መስራቱን ማቆም አለብን!
አብነት አሰፋ
*  አንቀፅ 39 ልማታችንንም የሚገድብ አንቀፅ ነው። አንቀፅ 39 ሠላማችንን የሚያውክ አንቀፅ ነው። አንቀፅ 39 ነገን በተስፋ ሳይሆን በፍርሃት እንድንጠብቅ የሚያደርግ አንቀፅ ነው። አንቀፅ 39 የዛሬ ሠላማችንን ብቻ ሳይሆን የሚነሳን ነገ እገነጠለላሁ ብሎ የሚነሳ ወገን ጋር የሚኖረን ግንኙነት የጦርነት እንዲሆን የሚበይንብን ነው!!!
የ አዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄን ጨምሮ በሃገራችን ያሉ የመሬት ይገባኛል ጥያቀዎች መነሻቸው አንቀፅ 39 ነው። ሁሉም ስገነጠል ምን ይደርሰኛል ወይም እነ እገሌ ሲገነጠሉ እከሌ የተባለውን ለም መሬት ወይም ከተማ ይዘውብኝ እንዳይሄዱ ምን ማድረግ አለብኝ ወይም ወደፊት ስገነጠል እገሌ የተባለውን ለም መሬትና ከተማ ይዤ መገንጠል የምችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ምን ማድረግ አለብኝ  የሚለውን ስሌት ይዞ ነው የሚቡዋጨቀው ።
 የ አዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄን ጨምሮ  ሁሉም ንጥቂያ ላይ ነው ። ይህ ሊቆም የሚችለው እንደ ሃገር እንደ አንድ ባለ ብዙ ቋንቋ ባለ ብዙ ባሕል እና ባለ ብዙ ሃይማኖት ሕዝብ አብረን ለመኖር  ስንስማማና መፃዒ እድላችንን ማስተሳሰር ስንችል ነው እንጅ ነገ በቀላል የፖለቲካ ነፋስ ልንበታተን የምንችል በካርቶን የተሰራን ስብስቦች እንደሆንን እያሰብን አይደለም ።
ፍትሃዊ ሠላም የምናገኘው እና ከነዚህ የይገባኛል ውዝግቦች ወጥተን ነገን በተስፋ መቀበል የምንችለው የኢትዮጵያ መሬት እና የ ዓየር ክልል የሁላችንም የጋራ ሃብት መሆናቸውን ስንተማመን እና ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል በሙሉ የዜግነት መብት መኖር እሚችልበትን ሕግ አውጥተን ስንተዳደር ነው። ይህን እንዳናደርግ ሕጋዊ እንቅፋት የሆነብን አንቀፅ 39 ነው። በመሰረቱ ይህ አንቀፅ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው መብታችውን በውድም ሆነ በግድ ኣስከብረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ሳይሆን በውሃ ቀጠነ እገነጠላለሁ እያሉ በማስፈራራት ወይም ነገ ስገነጠል ትቼ ለምሄደው ክልልና ሕዝብ ምን አስጨነቀኝ የሚል ከራስ ውጭ ለሌው የ ሃገር ልጅነት እሳቤ እንዳይኖረን ባይተዋር እንድንሆን የሚያደርግ ከ ኢትዮጵያ በቀር በየትም ሃገር የሌለ ነገን በተስፋ ሳይሆን በስጋት እንድንመለከት የሚያደርግ ጨለማ ሕግ ነው ።  አንቀፅ 39 እያለ  በየክልሉ ለጦርነት ያሰለፉን የይገባኛል ጥያዎችም ሆኑ የ አዲስ አበባን ችግር በዘላቂነት መፍታት አይቻልም። ስናስታምመው እንኖራለን እንጅ ተማምነን አንኖርበትም።
አንቀፅ 39 በሸገርም ሆነ በመላው ሃገራችን የልማት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚፈልጉ ዜጎች በነፃነት እንዳይሰሩ የሚያደርጋቸው በነገ ላይ እምነት እንዲያጡ የሚያደርግ ሕግ ነው። በግለ ሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በ ሃገር ደረጃ ይሚታቀዱ እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ የጋራ ፕሮጀክቶች ነገ ቤንሻንጉል እገነጠላለሁ ቢል ግድቡ ላይ ያፈሰስነው ሃብት ይዘው እንዲሄዱ ልንፈቅድላቸው አይገባምና ምን ማድረግ አለብን የሚል የጥያቄ ምልክት እየተቀመጠበት ነው።
ይሕ ችግር ቀጣይ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችም ላይ ማጥላቱ አይቀርም። አንቀፅ 39 ልማታችንንም የሚገድብ አንቀፅ ነው። አንቀፅ 39 ሠላማችንን የሚያውክ አንቀፅ ነው። አንቀፅ 39 ነገን በተስፋ ሳይሆን በፍርሃት እንድንጠብቅ የሚያደርግ አንቀፅ ነው። አንቀፅ 39 የዛሬ ሠላማችንን ብቻ ሳይሆን የሚነሳን ነገ እገነጠለላሁ ብሎ የሚነሳ ወገን ጋር የሚኖረን ግንኙነት የጦርነት እንዲሆን የሚበይንብን ነው። ዛሬ በ አንድ ሃገር ውስጥ እያለን በወንዝና በቁራሽ መሬት የምንገዳደል ሠዎች ነገ እንደ ጎረቤት በሠላም እንኖራለን ብሎ የሚያስብ የዋህ ብቻ ነው።
የሁላችንም የዜግነት መብት እኩል የሚከበርበት ሕግ አብረን አውጥተን ስለመለያየት ሳይሆን ስለ አብሮነት መጭውን ትውልድ እያስተማርን ለመቀጠል የሚያስችል በቂ ትስ ስር አለን። በሃገራችን የነበሩ መንግሥታት የሠሩት ግፍ ሕዝብ ክሕዝብ ጋር እንዲቃቃር የሚያደርግ አልነበረም። ሕዝባችን ዛሬም አብሮ የመኖር ችግር እንደሌለበት ደግሞ ደጋግሞ እያሳየን ነው።
አባቶቻችን በብዙ መከራ ያቆዩልንን ሃገር አፍርሰን ግን የተሻለ ቀን እንደማናመጣ  አፍርሰን መልሰንም ብንገጣጥማት አሁን በሕዝባችን መሃከል ያለውን ስሜት በ እጅጉ ካሻከርነው ብሁዋል ስለሚሆን አሁን ለማስተካከል ከምንችለው ችግር የከፋ ችግር ነው የምንፈጥረው።  የሶሻሊስት ሃገሮች ወድቀው ሶሻሊስት የነበሩ ሃገራት ሁሉ መስመራቸውን ወደ ካፒታሊዝም መስመር ሲያስተካክሉ  ሶሻሊዝም የሚለው ቃል ትርጉም ምንድነው ሲባል ወደ ካፒታሊዝም የሚወስደው ረጅሙ፣ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለው፣ ጠመዝማዛ መንገድ ነው የሚል ትርጉም ተሰጥቶት ነበር።
ተሰርታና ተገጣጥማ ዓለም እንደ አንድ ሃገር  ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ባለ ታሪክና ባለዝና ቅኝ ያልተገዛች ሃገር  የተቀበላት ሃገር ባለቤት የሆንን ሕዝቦች ሃገራችንን ፍትሃዊ እናደርጋለን ከማለት ይልቅ ሃገራችንን በ አንቅፅ 39 አፍርሰን በፍላጎት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ መልሰን እንገነባታለን የሚለው ቂላቂል ወሬ ላይ ተስፋችንን ልናንጠለጥል እና ለዚህ ጨለማ አንቀፅ ጥብቅና ልንቆምለት አይገባም።
አንድ የሆነ ሃገር ፍትሃዊ ማድረግ ነው የሚሻለው እንጅ አፍርሶ መስራቱ የማያዋጣ የእብደት ፕሮጀክት መሆኑ ማንም ሕሊና ያለው ሠው የሚረዳው ሀቅ ነው።
ለሃገራችንና  ለህዝባችን  ሠላምና ብልፅግና ስንል እዚህኛው ቤት ቁጭ ብለን ለዚያኛው ቤታችን ዳንቴል መስራት ማቆም አለብን።
Filed in: Amharic