>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8367

ብሔር እንጂ ህዝብ በሌለበት አገር ማንን ለመቁጠር ነበር "ደረሰ" "ተራዘመ" የምትሉን?!? (ታምራት በቀለ)

ብሔር እንጂ ህዝብ በሌለበት አገር ማንን ለመቁጠር ነበር “ደረሰ” “ተራዘመ” የምትሉን?!?
ታምራት በቀለ
እንደሚገባኝ ህዝብ:- አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ሰዎች(ዜጎች) ድምር ውጤት ነው።በህገ መንግስቱና የህገ መንግስቱ ፍሬዎች ከሚያሳዩት አንጻር  ካየን ደግሞ በኢሃዴጓ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ እንደ
ግለሰብ አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ሰዎች  መሬቱ
ላይ የሉም።ስለዚህ መንግስት መቁጠር ካለበት እውቅና
የሰጣቸውን ብሔር፥ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነው መሆን ያለበት፤እንደ ስነፍጥረት ብዙን አንድ በማለት።
ብሔሮቹም ቢሆኑ ከአራት የማይበልጡ አበይት ብሔራትና  ሌሎቹ ለብሔር ብሔረሰቦች ጭፈራ ካልሆነ በስተቀር  ለሌላ ነገር ብዙም ቦታ የማይሰጣቸው ደቂቀ ብሔራት  ስብስቦች ናቸው።
ህገ መንግስቱ እስካልተቀየረ ድረስ ወደፊት የህዝብ ቆጠራ አይደለም ህጻናት ሲወለዱ የተጽዖ ስም ማውጣት ራሱ ላያስፈልግ ይችላል። ምክንያቱም አብዛኛው ሰው ራሱን የሚያስተዋውቀውና ማንነቱን የሚገልጠው እሱ ብቻ በሚጠራበትና ወላጆቹ ባወጡለት ስሙና በድካሙ በገነባው ማንነቱ ስላይደለ።
ከዛ ይልቅ ማን ልበል ሲባል ጎሳውን ፥ ምንድነህ ሲባልም ጉሳውን  የት ትኖራለህ ሲባል በጎሳው የተሰየመ ክልሉን  እንጂ እናትና አባት በሰጡት ስሙና በትምህርትም ሆነ በልምድ በብዙ ድካም በገንባው ማንነቱ ራሱን ሲገልጥ አይታይም።
ለምሳሌ ሰው ተጎዳ ሲባል ለተጎዳው ሰው ከማዘንና ጉዳቱንና ጎጂውን  ከማውገዝ በፊት የጎጂውንና የተጎጂውን ማንነት ይጠይቃል፣ተጎጂው የኔ የሚለው ጎሳ አባል ከሆነ ጉዳቱን የሱን ዘር ለማጥቃት(ለማጥፋት) ሁን ተብሎ የተሰነዘረ ጥቃት እንደሆነ በጩኸት ያስተጋባዋል፤ወገኔ ብሎ የሚያስበው ጎጂውን ከሆነ ደግሞ ግፉ የቱንም አይነት የአረመኔ ተግባር ይሁን ቢቻል የጎጂው ማንነት እንዳይታወቅ ያልታወቀ ሃይል የፈጸመው ጥቃት እንደሆነ እንጥሉ እስኪወርድ ላንቃው እስኪቀደድ ድረስ ይሰብካል፤ያ ካልተሳካና ያገጠጠና ሊደበቅ የማይችል ነገር ከሆነበት ደግሞ የተፈጸመውን ድርጊት ግፍ ሳይሆን ፍትህን ለማምጣት ወይም ራስን ከጥቃት ለመከላከል የተወሰደና ትክክለኛ ድርጊት  መሆኑን በምክንያት ለማስረዳት ደክሞት ራሱን እስኪስት ድረስ ሲንፈራገጥ ይውላል ።
ከዚህም እንግዳ ጸባይ የተነሳ ሰው ሰውነቱን ይተውና ብሔር(ጎሳ) ብቻ ሆኖ ይቀራል።
 ፌስ ቡክ ላይ ያኋትን  አንድ ቀልድ ትሁን እውነታኛ ነገር ያላወቅኋትን ጨዋታ እዚህ ጋር ባመጣት ከላይ የዘበዘብኩትን ሁሉ ባጭሩ ላመስረዳት የምታግዘኝ ይመስለኛል።
ቦታው አፋር ክልል ነው፤የብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ ናቸው። ያው እንደሚታወቀው በጭፈራ ማለት ነው።አፋር ሞቃታማ ከመሆኗ አንጻር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆቹ በር የላቸውም ይህንን የሚያውቁት አላፊ ዝግጅቱን ምክንያት በማድረግ የባጃጅ ባልቤቶችን ለባጃጆቻቸው በር እንዲያስገጥሙ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፣ከሙቀቱና እናድርገው ቢሉም እንኳን  አቅማቸውም እንደማይፈቅድ ወደ ሃላፊው ቀርበው የባጃጆቹ ባለቤቶች ቅሬታ ያቀርባሉ ።ሃላፊው ከሰማቸው በኋላ ያላችሁት ሁሉ ሳይገባን ቀርቶ አይደለም ግን በር በሌለው ባጃጃችሁ ላይ አንድ ከሌላ አካባቢ የመጣን  ሰው ጭናችሁ ስትከንፉ አንድ ሰው ከባጃጁ ላይ ቢወድቅ ሰው ወደቀ  ሳይሆን ብሔር ወደቀ ነው የምንባለው በማለት ጉዳዩ እነሱ ከዘረዘሯቸው ችግሮች በላይ መሆኑን ነግረው አሰናበቷቸው።
እያየን ያለነውም ይህንኑ ነው የግድይና የበላይ ጠብ በደቂቃ ውስጥ የትግራይና የአማራ ህዝብ ጉዳይ ይሆናል። የሁለት ኩታ ገጠም ክልል ነዋሪ ግለሰቦች በግጦሽ ምክንያት የሚነሳ  አለመግባባት በሁላት አገሮች መካከል በድንበር ምክንያት የተነሳ ግጭት ይመስል የጦርነት ነጋሪት ሊጎሰምበት ይችላል።
የዚህ ሁሉ ምክንያት ዜግነትን አግልሎ ቡድናዊነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስሪት ይመስለኛል፣ መፍትሄው ተቃራኒውን ማድረግ ነው።
Filed in: Amharic