>
5:30 pm - Monday November 1, 1976

በቀለ ገርባ መጡብኝ! (ደረጄ ደስታ)


በቀለ ገርባ መጡብኝ!
ደረጄ ደስታ
ጋሽ በቀለ ገርባ ያሉትን በድምጽ ሰማሁት። አፌን ነው እንጂ ጆሮዬን አይዘኝም። ለነገሩማ ኦሮምኛ መናገር ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ መሆን ፈልጌ ተከልክያለሁ። አማራውን ለመጥላት ሳይሆን፣ ተወልጄ ያደግኩበትን ኦሮሞን በመውደድ። ለካ ሳላውቀው አማራና ኦሮሞ “ከተባሉት” ወላጆች ተወልጄና ተገምጄ ኖሯል። ልክ ዛሬ ጋሽ በቀለ ገርባ እንዳደረጉት አፌንም ዘሬንም ያዝ አደረገው መሰል፣ አይ አንተማ አማራ እንጂ የኛ አይደለህም አሉኝ። እንግዲህ አማራውማ አንድም ባጣ ቆይኝ ስላልሆነ ያውም ግማሽ ዘር ይዤ እሱም ዘንድ አልሄድም ብዬ ቀረሁ። በዚያም ላይ ደግሞ ዛሬ ዛሬማ ከሱም ዘር ቆጥሮ አንተማ ያው እነሱን ነህና ወደዚያው ተመለስ እሚል ወገን ተነስቷል ብዬ ተውኩት። ዘር ካየው ምን ለየው። በቃ ዘር ሳትቆጥር ደም ሳትሰፍር እጆቿን ዘርግታ እምትቀበለኝ አገሬ አለች ብዬ እማምዬ አልኳት። ኢሳያስን ኢሱ ያለች አገር የኔማ ምን አላት! ድሮም እኮ የኔው ነህና ወደኔው ትመለሰላሀ አለችኝ። “የአባትህና የእናትህ ወገኖች ሲጣሉ ጥግህን ያዝ!” ብዬህ ነበር እኮ ስትለኝ ተሳሳቅን። ነፍስ እኮ ናት።
እና ወድጄ አይደለም ኢትዮጵያዊ የሆንኩት። ባጣ እምቆይባት፣ ብወድ እምኖርባት፣ ባከብር እምከበርባት ሁለመናዬ ስለሆነች ነው ከዚያ ወዲህ በተድላና በደስታ መኖር ጀመርኩ። ዛሬ ግን ጋሽ በቀለ ገርባ መጡብኝ። ኦሮሞ አማራና ትግሬ እሚባባሉበትን የትንሽ ሰው ፖለቲካቸውን አልፈው ወደኛ ወደ ሀበሾቹ (ቅይጥ ዲቃላ ዥጉርጉር ምንትስ) ወደ ምንባለው ኢትዮጵያውያን መጡ። አገርና ነገር የጠፋው አማራና ኦሮሞ ሆነው የተዋለዱት በመኖራቸው ነው ዓይነት ነገር መናገር ጀመሩ። እና ታዲያ የአባቴና የእናቴ ወገኖች በተጣሉ፣ ጥጌን ይዤ በኖርኩ፣ እነሱ ተዋደው በተጋቡ እኔ ልጠየቅ ነው ማለት ነው? ከትናንት ሌሊት ጀምሮ ምንም እንቅልፍ አልነበረኝም። ጥጌን እንደያዝኩ በቀለ ከምን በቀለ? እንዴት በቀለ? ለምን በቀለ? ወዴት በቀለ? ምኑን በቀለ? ስል አደርኩ።
በቀለ የመከሩት አማርኛ ተናገሪውን ኦሮሞ ነው። አሮምኛ ተናገሩ ሳይሆን አማርኛ አትናገሩ ነው ያሉት። ጥላቻ ይመስለኛል።
ከሁለት ወገን የተወለዱትን ተጠያቂ አድርገዋል። መጋባትና መዋለድን ከሰዋል – ይህ በሽታ ነው።
አማርኛ መናገር ለአማራው እሚዋል ውለታ አይደለም። አማራው በሌለለበት ሐጎስ እና ቶሎሳም ይግባቡበታል። ለራሳቸው ጥቅም ነው።
በአንድ ቋንቋ አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ እየተናገርን መግባባት አቅቶናል፣ እንኳን አብዝተነው። ያልተግባባው ሀሳብና ልብ ነው ቋንቋ አጥሮ አይደለም። ኦሮሞ ራሱ መች ተግባባ?
ሰው ቋንቋ እሚማረው ወይ ካስፈለገው ወይ ከወደደው ወይ ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ነው። በግድ ይዘው እሚግቱት ቋንቋ ውጤት አይኖረውም።
በቀለ በንግግራቸው ሰው እንጂ ሀሳብ አላውሩም። ስለሆነም እምናወራው ሰው እንጂ ሀሳብ እንዳይሆን አስገድደውናል። ስለዚህ በጎሰኞች ወገን ካሉት ሀሳብ አልቋል ለነገሩም ድሮም አልነበረም። ጎሰኝነት የሀሳብ አለመኖር ውጤት ነው። ለማንኛውም የእናትህና የአባትህ ወገኖች ሲጣሉ አንተም አይቀርልህምና ቅይጥ ሆይ ወይ ምረጥ ወይ ጉበጥ ሳትባል ብትነሳ ይሻልሃል።
ዘመኑ የተነስ ከሆነ ቅይጥ ነኝ ያልክ ሁሉ ተነስ! ድል ለቅይጥ!
Filed in: Amharic