>
5:13 pm - Saturday April 19, 7119

በየቦታው እየተፈጸመ ያለው ሕዝብን የማፈናቀሉና የማጋጨቱ ሦስተኛው ዓላማ!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

በየቦታው እየተፈጸመ ያለው ሕዝብን የማፈናቀሉና የማጋጨቱ ሦስተኛው ዓላማ!!!
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ማሳሰቢያ
የተሻለ ነገሮችን የመረዳት አቅምና ጭንቅላት የሌለው ሰው ጽሑፉን እንዲያነብ አይመከርም!
በተደጋጋሚ እንደነገርኳቹህ ሕዝብን የማፈናቀሉና የማጋጨቱ ዓላማ ሁለቱ ምክንያቶች፦
1ኛው ወደ እነሱ ያነጣጠረውን ችግር መልሶ ወደ ሕዝብ ዳይቨርት በማድረግ (በማስቀየስ) ከሕዝቡ ከራሱ ከጉያው ችግር፣ ቀውስ፣ አለመረጋጋት በመፍጠር በራሱ ችግር ጠምዶ በመያዝ ወደ አገዛዙ እንዳያፈጥ እንዳያነጣጥር ለማድረግ ሲሆን፡፡
2ኛው ደግሞ እንዲህ እያደረጉ ተፈናቃዩን ላጣ ለነጣ ድህነት በመዳረግ የተቀረውን ሕዝብ ደግሞ በመዋጮ ብዛት ሕዝብን በተለይ ባለሀብቱን እየዘረፉ ሕዝቡን አቅም ለማሳጣት ለማዳከም ነው ዓላማው፡፡ ማለቴን ታስታውሳላቹህ፡፡ ዛሬ ደግሞ ሦስተኛውን ዓላማ እነግራቹሃለሁ፡፡
በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚደረግ ሕዝብን የማፈናቀሉና እርስበእርስ የማጋጨቱ ተንኮል፣ አሻጥር፣ ሴራ፣ ደባ የሚፈጸመው በኢሕአዴግ መዋቅር እንደሆነ ከተፈናቀሉና እንዲጋጩ ከተደረጉ ወገኖቻችን የሚወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ይሄንን ነገር ያዙልኝ፡፡
በቀኝ ጆሯችን ሰምተን በግራ ጆሯችን እያፈሰስነው ካልሆነ በስተቀር ቢያንስ በአሁኑ ወቅት ይሄንን እውነት የማያውቅ ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነገር ግን “ለምን?” ብላቹህ ታውቃላቹህ ወይ??? “ከዚህ ተግባር ጀርባ ያለው ዓላማ ምንድን ነው???” ብላቹህ ታውቃላቹህ ወይ???
ጉዳዩን ጠበብ አድርጌ በብአዴን ዙሪያ ላሳያቹህና ወደሌሎቹ አልፋለሁ፡፡ ብአዴን ሁልጊዜ አማራ በየትም ቦታ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል ድምፁ የማይሰማውና ነገሩ ካለቀ በኋላ ሰነባብቶ “ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍና እርዳታ አድርጉ?” እያለ ብቅ የሚለው ለምን ይመስላቹሃል???
ብአዴን ድሮም ሆነ አሁን በታሪኩ ነገር ካለቀ ከተጠናቀቀ በኋላ ብቅ ይላል እንጅ ለወገን ደርሶ አያውቅም፡፡ ለወያኔ ፖለቲካዊ (እምነተ አስተዳደራዊ) ጥቅም ሲባል ለዓመታት ቅማንትና አማራ እያለ አንዴ “የቅማንት ኮሚቴ መቀሌ ጽ/ቤት ከፍተው የወያኔ ቅጥረኞች ሆነው እየተንቀሳቀሱ ነው!” ሲል ሌላ ጊዜ “ቅማንቶች ከወያኔ ጋር በመተባበር ምሽግና ሦስት የጦር ካምፕ ገንብተው በአሸባሪነት እየተንቀሳቀሱ ነው!” እያለ ሕዝብን ሲያሸብርና ሲያባላ ቆይቶ አሁን ወደ መጨረሻ በክልሉ የብዙኃን መገናኛ ወጥተው “በቅማንት መንደሮች የተገነባ ምሽግም ሆነ የጦር ካምፕ የለም፣ መቀሌ የተከፈተ የቅማንት ኮሚቴ ጽ/ቤትም የለም!” ብለው ለአራት ዓመታት ሲያኪያሒዱት የቆዩትን በጦር ሠራዊቱ የታገዘ የእርስበርስ ግጭት ምን እየተካሔደ እንዳለ ምንም የማያውቁ የበርካታ ንጹሐንንና የዋሐንን ነፍስ በልቶ አንድንም ሰው ተጠያቂ ሳያደርጉ ቋጭተውታል፡፡
ምክንያቱም ግጭቱ ሕዝብን ለማሸበር፣ እረፍት መረጋጋት ለመንሳትና ለማደህየት ወይም ለወያኔ ፖለቲካዊ ትርፍ ሲባል ሆን ተብሎ በአሻጥር የሚፈጸም ግጭት ነውና ተጀምሮ እስኪጨረስ ግጭቱን ያኪያሒዱ የነበሩ ከጦር ሠራዊቱም ሆነ ከኢሕአዴግ አካላት ተጠያቂ ስለማይሆኑ፡፡
ብአዴን በየጊዜው እየወጣ ከሠራዊቱም ሆነ ከአካባቢው የብአዴን አካላት ተጠያቂ የሆኑትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ይናገራል፡፡ ለዓመታት ያ ሁሉ እልቂት ተፈጽሞ ለአንድም ቀን ግን አንድንም ሰው ተጠያቂ አድርጎ አያውቅም፡፡ ይሄንንም የሚያደርገው ሠራዊቱንም ሆነ የአካባቢውን አመራሮች ተጠቅሞ በግጭቶቹ በሕዝብ ላይ ከሚያደርሱት አካላዊ ጉዳት ኪሳራ በተጨማሪ በሕዝብ ላይ የሥነልቡና ጥቃት በማድረስ ሕዝብን ማሳረር፣ ማቃጠል፣ ማበሳጨት፣ ማሳበድ ስለሚፈለግ ነው፡፡
እንደምታስታውሱት ባለፈው ሳምንት የብአዴን ባለሥልጣናት በቴሌቶኑ ዝግጅት ወቅት “ከዚህ በኋላ መፈናቀል አይኖርም!” ብለው ነበር፡፡ በአደባባይ ወጥቶ ከሚናገረው የሚቃረን ነገር በመፈጸም በአማራ ላይ የሥነልቡና ጨዋታ በመጫወት ወይም የሥነልቡና ጥቃት በመፈጸም አማራን ለማሳረር፣ ለማብገን፣ ተስፋ ለማስቆረጥ ብሎም ለማሳበድ በዕድሜ ዘመኑ ለቁጥር በሚያታክት ደረጃ ተደጋጋሚ ጥረት በማድረጉ የምናውቀው ቀንደኛው የአማራ ጠላት ነቀርሳው ብአዴን በባለሥልጣናቱ በኩል በቴሌቶኑ ዝግጅት ላይ ከላይ የጠቀስኩትን ነገር ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆን ገብቶኝ ስለነበረ ያፎደፍድ የነበረውን ነፈዝ መንጋ “አትጃጃሉ የልቅስ ሌላ የወገን መፈናቀል ጠብቁ!” ብየ ነበር፡፡
ያልኩት አልቀረም ሳምንት እንኳ ሳይሞላ አማራ አዲስ የሚፈናቀልበት ግንባር ተፈጥሮ በምንጃር ሸንኮራና በመተሐራ ከተማ በወለጋም እየተገደለና እየተፈናቀለ ይገኛል፡፡ ፀረ አማራው የወያኔ ባሪያ ብአዴንም እንደ ልማዱ ድምፁን አጥፍቷል፡፡ ጥቃቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አሁንም እንደልማዱ ይወጣና “በምንጃር ሸንኮራና በመተሐራ…. ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርጉ?” እያለ ቢዝነሱን ሲሠራ ታዩታላቹህ፡፡
ነገ ደግሞ ይሄው ደባ በሌላ ቦታ ሲደገም ይታያል፡፡ የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስ ይሄው ነገር እየተደጋገመ ይቀጥላል፡፡ እጅግ የሚገርመው ነገር ግጭቱን የሚቆሰቁሱትና የሚያቀጣጥሉት የአገዛዙ አካላት እንደሆኑ ከሰለባዎቹ ወገኖች እየሰማና እያየ በሚፈጸምበት አሻጥር ላይ በተገቢው ደረጃ ሕዝቡ አለመንቃቱ ነው፡፡
ይህ በየቦታው በስፋት የሚፈጸሙ ዜጎችን በኃይል የማፈናቀል፣ እያፈናቀሉ የመግደልና የመዝረፍ ግፍ ለ27 ዓመታት ሲፈጸም የቆየው በዋናነት በአማራ ላይ ቢሆንም ከሁለት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በተለይም ለውጥ ካሉት የወያኔ ድራማ (ትውንተ ሁነት) ወዲህ ግን ለፖለቲካዊ (ለእምነተ አሥተዳደራዊ) ዓላማ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና በተለያዩ ብሔረሰቦች ላይም እየተፈጸመ ይገኛል፡፡
ለውጥ የተባለው የወያኔ ድራማ ከተጀመረ በኋላ በኦሕዴድ፣ በደኢሕዴን፣ በብአዴን፣ በሕወሓት መዋቅሮች አቀናባሪነትና ፈጻሚነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ብሔረሰቦች ላይ እየተፈጸመ ያለው ይህ የማፈናቀልና የእርስበርስ ግጭት ዓላማ ሌላ ምንም ሳይሆን ሕዝቡ “ወያኔ ይማረን ከዚህስ የወያኔ አገዛዝ ይሻለናል!” እንዲል ለማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው ዓላማ ይሄው ነው፡፡ ሕዝቡ እንዲህ እስከሚል ድረስም “እዚህ ቦታ ያለው ችግር ተፈታ!” ሲባል እንደገና ሌላ ቦታ እየቀሰቀሱ የኦሕዴድ፣ የደኢሕዴን፣ የብአዴን፣ የሕወሓት ባጠቃላይ የኢሕአዴግ መዋቅር ሕዝቡን በእርስበርስ ግጭትና በማፈናቀል የማስመረር ተግባርን አጠናክረው ይቀጥሉበታል፡፡
ወያኔ የሌለ ለመምሰል ለጊዜው ዞር አለ እንጅ የትም አልሔደም፣ ምንም የሆነው ነገርም የለም!!! አልቆሰለም፣ አልተቆረጠም፣ አልተፈለጠም፣ አልተፈጀም፡፡ ተመልሶ ለመምጣትም ሕዝብን በየስፍራው እርስበርሱ በማጋጨትና በማፈናቀል የማስመረርና “ወያኔ ይሻለናል!” እንዲል የማድረግ ሥራ በደንብ በተጠናና በተቀናጀ፣ ተጠያቂም በሌለበት መልኩ በሀገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች አጠናክሮ እየሠራ ይገኛል፡፡
ምድረ ዘገምተኛና ነፈዝ ግን ወያኔን ወግተህ፣ አሳደህ፣ ፈጅተህ መቀሌ እንዲወተፍ እንዲወሸቅ ያደረክ ይመስል “ወያኔ ዳግም ላይነሣ ተንኮታኩቶ ወድቋል!” እያልክ በቁምህ በመቃዠት እራስህን ታጃጅላለህ፡፡ ሲያምርህ ይቀራል!!! እንዲህ ብለህ የምታምን በቁም ቅዠት ላይ ያለህ በድን ካለህ ተበልተሃል፡፡ ወያኔንም ፈጽሞ አታውቀውም!!! የወያኔን የሕይዎት ዘመን የሥልጣን ፍቅርን ወይም ወያኔ “ሥልጣን ወይም ሞት!” ባይ መሆኑን ወይም ሥልጣንን ፈጽሞ ለድርድር የማያቀርብ መሆኑን የማያውቅ ሰው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እንግዳና ፈጽሞ የማይገባውም ነውና አርፎ ቢቀመጥ ሕዝብን ከማስበላት ይታደጋል፡፡
ወያኔ ለውጥ ብሎ በሚያላግጥበት ድራማ በፌዴራሉ መንግሥት (በማዕከላዊ መንግሥት) እና በሠራዊቱ ሥልጣን የተባለን በሙሉ ኦሮሞ እንዲይዝ በማድረግ ቀደም ሲል ወያኔ የሆነ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር “ለጋላ ሰጥቸልህ ነው የምሔደው አርፈህ ብትቀመጥ ይሻልሀል!” እያለ ሲዝት የነበረውን ዛቻ ተግባራዊ ያደረገ በመምሰል ሕዝብ እንዲጨነቅ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው የሚገኘው፡፡
ወያኔ ኦሕዴድን ወይም ኦዴፓን በቡራዩ በለገጣፎ በስሉልታ ባጠቃላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ዘር ለይቶ የማፈናቀል ሥራ እንዲሠራና በአዲስ አበባ ላይም የባለቤትነት ጥያቄ እንዲያነሣ ያደረገው ሕዝቡን በማስጨነቅ በማሸበር “ኧረ ከዚህስ ወያኔ ይሻለናል!” እንዲል ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ “ኦዴፓ በራሱ የሚመራና መንግሥት የመሆን ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ ገና ተደላድሎ ሳይቀመጥ እነኝህ እያደረጋቸው ያሉትን ነገሮች በማድረግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ለመጠላት ጥረት ያደርግ ነበር ወይ?” ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡
ወያኔ ሰዓረን ከላይ በማስቀመጥ የተቀረውን የሠራዊቱን ሥልጣንና የማዕከላዊ መንግሥትን ሥልጣን ጠቅልሎ ለኦሕዴድ ወይም ኦዴፓ ማስያዙን ብአዴንና ደኢሕዴን የማያውቁ ሆነው አይደለም ጭጭ ያሉት ወይም ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል በማዕከላዊ መንግሥትም ሆነ በሠራዊቱ እንዲደረግ ያላደረጉት፡፡ ነገር ግን እነሱም እንደ ኦሕዴድ ወይም ኦዴፓ ሁሉ “አድርጉ!” የተባሉትን ያደርጋሉ እንጅ በነጻነት የሚያስቡና የፈለጉትን የሚያደርጉ፣ “እንወክለዋለን!” ለሚሉትም ሕዝብ የሚያስቡ የሚቆረቆሩ አይደሉምና “ለምን እንዴት?” ብለው አልጠየቁም ሊጠይቁ የሚችሉበት ዕድልና ተፈጥሮም የላቸውም፡፡
ወያኔ ኦሕዴድን፣ ብአዴንን፣ ደኢሕዴንንና አጋር ፓርቲዎችን ዲዛይን አድርጎ (ተልሞ) ሲፈጥራቸው የሕሊና፣ የዜግነት ግዴታ፣ የሞራል (የቅስም) ጥያቄ እንዳያነሡ አድርጎ ሆዳቸውን ብቻ እያሰቡ እራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው እስኪያጡ ድረስ እሱን በታማኝነት እንዲያገለግሉ አድርጎ ስለሆነ የፈጠራቸው ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ብለው “ለምን? እንዴት? መቸ? የት?” የሚል ጥያቄ ጭንቅላታቸው ፈጽሞ ማንሣት አይችልም!!!
እናም ፖለቲከኛ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ነኝ፣ ምሁር ነኝ እያልክ ይሄንን ማስተዋል፣ መረዳት፣ መገንዘብ፣ ማወቅ ተስኖህ የምትጃጃል ምድረ ነፈዝና ዘገምተኛ ሁሉ እፍረትን (ሼምን) የምታውቁ ከሆነ እፈሩና አርፋቹህ ተቀመጡ??? እራሳቹህ ተጃጅላቹህ ሕዝባችንን አታጃጅሉ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic