>

ከ56 ሺ ሰዎች በላይ ተፈናውለው በየቀኑ እንደቅጠል ስለሚረግፉበት ድብቅ አረንጓዴ ረሃብ !!! (ዘመድኩን በቀለ) 

ከ56 ሺ ሰዎች በላይ ተፈናውለው በየቀኑ እንደቅጠል ስለሚረግፉበት ድብቅ አረንጓዴ ረሃብ !!!
ዘመድኩን በቀለ 
* ይድረስ ለእነ ታማኝ በየነና 
ለእነ ያሬድ ሹመቴ ባላችሁበት
             *★★★*
★ በዚህ ጦማር የጠሚዶ ዐብይ መንግሥት አልተወቀሰም። አንዳቸውም ስሙን በክፉ አላነሱም። እንዲያውም እሱ ቢሰማ ከመከራ ያላቅቀናል ባዮችም ናቸው። ለእውነትና ለማዕተቤ ስለምሠራ በዚህ ጉዳይ አቢቹ አይወቀስም። አከተመ።
★ ከነገ ሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ በእነ ያሬድ ሹመቴና መሀመድ ካሳ አማካኝነት የሚደረገው የእርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
#ETHIOPIA | ~ ለሁለታችሁም በያላችሁበት ይድረስልኝ።
በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ።
እንደሚታወቀው ሁለታችሁም እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆናችሁ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያዊነትም ጭምር ዋጋ እየከፈላችሁ የምትገኙ ወንድሞች መሆናችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ የተረዳ ነው። እዚህ ላይ ስለዚህ ማንነታችሁ ስዘበዝብ አልውልም።
•••
ባለፈው ጊዜ የሚጮህላቸው አክቲቪስት፣ የሚከራከርላቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በማጣታቸው ምክንያት በጅምላ እንደ ቅጠል በረሃብ ሊረግፉ የነበሩትን በደቡብ ክልል የሚገኙትን ጌዲኦዎችን ለመታደግ ኃላፊነት ወስዳችሁ እርዳታ ለማሰባሰብ መነሳታችሁ ይታወሳል። በዚሁም መሠረት በተለይ በእነ ታማኝ በኩል በተደረገው የእርዳታ ማሰባሰብ ከ 1. 2 ሚልየን ዶላር በላይ በአጭር ቀን መሰብሰቡም ይታወሳል። በእነ ያሬድ በኩል ደግሞ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በመላዋ አዲስ አበባ ይፋ በሚሆኑ ሥፍራዎች እርዳታ ይሰበሰባል። እናም እዚህ ላይ ነው እኔ ማነልከቻ ለማቅረብ ነጠላዬን አጣፍቼ፣ ዶሴዬን በክላሰር በቴምብር አሽጌ ደጅልጠናችሁ ብቅ ያልኩት።
•••
ጉዳዪም ወዲህ ነው። እንደሚታወቀው የገዲኦ ጉዳይ አሁን ልደብቅህ ቢባል እንኳ መደበቅ ከማይታሰብበት ደረጃ መድረሱ ይታወቃል። ዓለም እየተረባረበም ነው። እኔ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንዲታይልኝ የምፈልጋቸው አቤቶታዎችም አሉኝ።
★ ወድ ታማኝ በየነና – ያሬድ ሹመቴ
የምነግራችሁ ታሪክ እዚያው ደቡብ ክልል ውስጥ ስላለ አስከፊ መፈናቀልና ከ56 ሺ ሰዎች በላይ በየቀኑ እንደቅጠል ስለሚረግፉበት ድብቅ አረንጓዴ ረሃብ ታሪክ ነውና ጫ ብላችሁ ስሙኝ። ብዙዎች ለመነካካት ሞክረዋል። ነገር ግን አላደሙትም። ነገሩ አድካሚ ቢሆንም እንድሜ ለ Ha እና ለ En  ለተባሉ ወዳጆቼ አስቸጋሪውን በረሃ እያቆራረጡ በመሄድ መረጃውን አድርሰውኛል። የመፈናቀሉ መነሻ ታሪኩ እንዲህ ነው።
•••
ከአንድ አመት በፊት በደቡብ ክልል በባስኬቶ ልዩ ወረዳ እና በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ መካከል የሚገኙ 11 ቀበሌዎች ወደ ባስኬቶ ተጠቃለን ዞን እንሆናለን የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። ይሄ ነው እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ህዝብ መፈናቀልና መሞት መነሻ ምክንያት የሆነው።
•••
ፖለቲከኞቹ በፈጠሩት የግጭት ጦስ ምክንያት ንፁሐኑ ዜጎች የአብርሃም የመስዋዕቱ በግ ሆነው ተገኙ። በዚህ መሃል ለሚነሱ ግጭቶች እና ጥቃቶች የልዩ ወረዳ እና የወረዳዎቹ አስተዳደሮች እንዲሁም የደቡብ ክልል አስተዳደር ያሳዩት ቸልተኝነት ደግሞ ችግሩን የበለጠ አስከፊ አርጎታል።
•••
ይሄ ማለት እንግዲህ ባለፈው ሰኔ ወር አዋሳ እና አዋሳ ዙሪያ ለተነሱ ጥቃቶች ትኩረት ላለመሳብ የሚደረጉ የክልሉ መንግሥት የቸልተኝነት ማሳያ አንዱ አካል ተደርጎ ይነሳል። ምክንያቱ ደግሞ በወላይታና በሲዳማ መካከል መስመር የሳተ ግጭት ተከፍቶ ወደለየለት የዘር እልቂት ሊያመራ ሲል ለማስቀየሻ የጦስዶሮ ሲፈለግና ግጭቱ በሁሉም የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ውስጥ ነው ለማስባል እነዚህ ምስኪኖች ተመረጡ።
•••
አሁን ግጭት ከተከሰተባቸው 11 ቀበሌዎች መካከል በ4ቱ ቀበሌያት ማለትም
• 1ኛ፦ ማሻራ
• 2ኛ፦ በረዳ
• 3ኛ፦ ብራ ሹማ
• 4ኛ፦ በልታ … ከሚባሉት አካባቢየዎች የተፈናቀሉት 20,101 ሰዎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ተፈናቃዮች በአሁን ሰዓት በምግብ እና ውኃ  እጦት ከመርገፋቸውም ባለፈ …ህፃናቱ እና ወላድ እናቶች በአስከፊ ችግር ለይ ወድቀው ይገኛሉ።
•••
በቀሪዎቹ 7ቱ ቀበሌያት ደግሞ የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር ከ25,000 በላይ ተፈናቃዮች በባስኬቶ ይገኛሉ። በቅርቡም #10 ህፃናት በምግብ እና ውኃ ጥም ወላጆቻቸው እያዩ ሞተዋል።
•••
መንግሥት ባመነው ብቻ #12 ሰዎች በቅርብ ግዜ በግጭቱ ሞተዋል። ነገር ግን ይሄ የሟቾች ቁጥር መንግሥት ያመነው ስለሆነ ቁጥሩን ትንሽ ከፍ ማድረግ ነው። መንግሥት 10 ካለ እውነታው 20 ነው ማለት ነው። ይሄ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠባይ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እቅጩን የሚናገረው በእጁ ላይ ያጠለቀውን ሰዓት ብቻ ነው። እናም የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ነው ይላሉ የችግሩ ሰለባዎች። ምክንያቱም በየቀበሌዉ የሚሞተው የዜጎች ቁጥር በመንግሥት አካላት ስለሚደበቅ በይፋ አይነገርም ይላሉ።
•••
ህፃናት፣ እናቶች እና አዛውንት በየ ዕለቱ እየሞቱ ነው። በየቀኑ ሰው ይሞታል። አምስት ቦታ ላይ ከ36,000 በላይ ህዝብ ያለምግብ፣ ያለመድኃኒት፣ ያለውኃና ለሎች መሠረታዊ ቁሶች በድንኳንና ኮባ ስር በተንተራሰበት እስከወዲያኛው እያሸለበ ነው።
•••
ተፈናቃዮቹ በሚከተሉት ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ። እነርሱም፦
1ኛ፦ ቦላ (‘ቦ’ ላልታ ትነበብ)፣
2ኛ፦ ኦብጫመንዲታ፣
3ኛ፦ ቡኒባሳ፣
4ኛ፦ ዋዳ ባልአሳ፣
5ኛ፦ ቦላ ጋባላ(‘ቦ’ ትጠብቃለች) ናቸው።
•••
ያሬዶ ፤ በአካባቢው ስላለው ሰቆቃ የሚደርሱኝ ምስሎች እንቅልፍ የሚያሳጡና የሚዘገንኑ ናቸው። እባክህ ዘመዴ ለጌዴዮዎች እንደጮኽከው ጩኽልን። ከእግዚአብሔር ጋር ይኼንን ታሪክ ማድረግ ትችላለህ። Zemde የተፈናቃዮቹ ያሰቅቃል። በላኩልህ ዛፍ ስር ኑሩዋቸው በዚያው የሚገፉ አሉ። የሚገርምህ ነገር ዘመዴ ማታ ማታ ዛፏ ስር ለማደር የሚታየው ሽሚያ ያስለቅስሃል። በላክንልህ ፎቶ ላይ የምታያቸው ህፃናት በሙሉ ከነ ቤተሰቦቻቸው ከሰንበሌጥ በተሠሩ መኖሪያ ውስጥ ነው የሚያሳልፉት።
•••
አስከፊው ነገር አፈናቃዮቹ በድንገት ይመጡና ትሄንኑ የሰንበሌጥ ቤት እሳት ይለቁበትና  ቢያንስ፣ ቢያንስ የ10 በተሰቦች የሰንበሌት ዳስ ጋይቱ ሜዳ ላይ ይበተናሉ። በተለይ ቦናሬ ማርቃና በተባለው ካምፕ ላይ ያለው ሰቆቃ አይነግርም ይባላል።
•••
ተመልከት ዘመዴ እነዚህ ሰዎች የተፈናቀሉበት ምክንያት እኮ በመሎ ኮዛ ወረዳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 11 ቀበሌያት ውስጥ ያሉ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአነዋኗዋር ዘይቤያቸው የባስኬቶ ልዩ ወረዳ የሆኑ ናቸው። አሁን የለውጡን መምጠት ተከትሎ የማንነት ጥያቀያቸውን በማንሳት ወደ ባስኬት ብሔረ እንግባ የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ነገር ግን ለውጡ እንደ ኤሊ ስለሚጓዝና ደእህደንም ስማይመለከተው ሰዎቹ መፈናቀል ነበረባቸው። እናም የ11ቀበሌ ህዝብ በአንድ ሌሊት ቤቴን፣ጨርቄን፣ ማቄን ሳይል ወደ ባስኬቶ ልዩ ወረዳ ቀበሌያት በሦስት አቅጣጫ ተፈናቀሉ። ዛሬ ከስድስት ወር በላይ ሆናቸዋል። ቤት የለም። ምግብ የለም። መድኃኒት፣ ህክምና፣ እርዳታ ምንም ነገር የለም። በቃ የሆነ ጊዜ ላይ የተወሰነ መኪና ስንዴ ይመጣ ነበር አሁን ግን ወፍ የለም።
•••
ህዝቡ ስራስር እየበላ ይኖራል። እናት ሸራ ስር ትወልዳለች። ህፃናት በብርድና ሙቀት በተለይ ደግሞ አካባቢው ወባ፣ ታይፎድና ታይፈስና ሌሎችም ውኃ ወለድ በሽታዎች ስላሉ ለህክምና እንዳይደርሱ እንኳን ከቦታው ርቀት የተነሳ ምንም ሳይፈጠር ይሞታሉ። ሌላው አስራሚ ነገር ያለችን አንድ አምቡላንስ ነች። አንዷ አምቡላንስ ስንት ቦታ ትድረስ? የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ብዙ ድጋፍ አድርጓል ግን ከአቅሙ በላይ ሆኗል። የክልሉ መንግሥት ግን የባስኬቶ አመራሮች አፈናቅላችዋል በሚል ሰበብ ክልል ላይ ያላቸውን የስልጣን የበላይነት በመጠቀም ማለት ብዙ መሎን የሚያስተዳድረው ዞን ተወላጆች ክልል ላይ ተሿሚ ስለሆኑ በዚያ አቅማቸው የምግብ፣ መጠጥና መዲኃኒት ሌሎችም ሰብአዊ እርዳታዎች እንዳይመጡ አስደርገዋል ነው የሚሉት ጉዳዩን እንዲያጣሩ ወደ ስፍራው የላኩዋቸው የመረጃ ምንጮቼ።
እናም ውድ ያሬድ ሹመቴና የተከበርከው ታማኝ በየነ በእርዳታ በመጣችሁ ጊዜ ይሄንን ምስኪን ህዝብ ታስታውሱትና ትጎበኙት ዘንድ ከነፍሳችሁ በላይ በምትወዷት ኢትዮጵያችን ስም እግራችሁ ስር ድንጋይ ተሸክሜ በመውደቅ እማጸናችኋለሁ። በመድኃኔዓለም ይዧችኋለሁ፣ እንዲያው በወላዲተ አምላክ ይሁንባችሁ ከሚገኘው እርዳታ ላይ አካፍሏቸው። አደራ በሰማይ አደራ በምድር።
•••
ይሄም እንደ ጌዲኦው መስመር ከያዘልኝ ደግሞ ሌላ በአሰቃቂ ሆኔታ ተርበውም ከህዝብና ከእርዳታ ሰጪዎች ተገልለው በበረሃ ስለወደቁ ዜጎቻችን ጀባ እላችኋለሁ። መረጃዎቹ ተጠቃለው የሚገቡልኝ ከሆነ ምንአልባትም በነገው ዕለት ጀባ እላችኋለሁ።
አመሰግናለሁ። አመልካች ዘመዴ ነኝ ከሀገረ ጀርመን።
•••
ሻሎም  !   ሰላም  !
መጋቢት 14/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic