>
5:13 pm - Friday April 19, 5957

የቲም ለማ ቅቡልነት በብርሃን ፍጥነት እያሽቆለቆለ መምጣትና፣ የሃገራዊ ደህንነት ሥጋት!!! (ያሬድ ጥበቡ)

የቲም ለማ ቅቡልነት በብርሃን ፍጥነት እያሽቆለቆለ መምጣትና፣ የሃገራዊ ደህንነት ሥጋት!!!
ያሬድ ጥበቡ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ ወግ ስብሰባ መዝጊያ ላይ ያደረጉት ንግግር የሚደመጥ ነው። ብዙ ቁምነገሮችን አንስተዋል፣ የመጨረሻ ማሰሪያ ቃላቸውም በኢትዮጵያ ቀጣይነት ላይ መሆኑ ደስ የሚል ነው። ሆኖም ፣ ፓርቲያቸው ኦዴፓ በአዲስ አበባ ላይ የወሰደውን አቋም፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚያደርገውን ማፈናቀል፣ እርሳቸው በተገኙበት ስብሰባ የህዝብ ስብጥርን ስለመለወጥ ጓደኛቸው አቶ ለማ ስላደረጉት ንግግር ምንም ሳይተነፍሱ ቀርተዋል።
በአንፃሩ የባልደራሱ ስብሰባ ውጤት የሆነውን የነእስክንድር ነጋን የባለአደራ ኮሚቴ መደራጀትና እንቅስቃሴ አምርረው አውግዘዋል። ለምን ለማውገዝ እንደመረጡ ዘርዘር አድርገው በተናገሩ ጥሩ ነበር ። ሆኖም ያን ለማድረግ አልደፈሩም ፣ “ወዮላችሁ” ብለው አዲስ አበቤውን ማስፈራራት ነው የመረጡት። በምርጫ ቢሸነፉ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን በጣም በርግጠኝነት የተናገሩ መሪ፣ አዲስ አበቤው ከአብራኩ ባልወጡ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከሚገዛ፣ በየቀበሌው ተሰብስቦ ከጎረቤቶቹ፣ ክፉ ደጉን ከሚያውቁለት ወገኖቹ መሃል የቀበሌና የወረዳ መሪዎቹን ቢመርጥ ለምን ዶክተር አቢይን ከነከናቸው?
እንደሚናገሩት ለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ራሳቸውን ተገዢ የሚያደርጉ ከሆነ፣ የአንድ የአዲስ አበባ ቀበሌ ነዋሪ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያደርገውን ጥረት ለመኮነን ለምን ጨከኑ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣  ይህ አዲስ አበባ ውስጥ የሚደረግ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ጥረት፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሞ ክልል ከተሞች ፍላጎት ጋር የሚቃረን አስመስለውም አቅርበዋል ። ሆኖም ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ለምሳሌ ሱሉልታን ወይም ለገጣፎን ብንወሰድ፣ ለምንድን ነው የሱሉልታ ወይም ለገጣፎ ነዋሪ የአዲስ አበባ ቀበሌዎች በሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና ግልፅ መንገድ ጊዜያዊ ህዝባዊ አስተዳደሮችን ቢመሠረቱ የሚከፉት? የጠቅላይ ሚኒስትሩ አረዳድ የተሳሳተ ነው።
አዲስ አበባ ውስጥ የሚደረግ ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የህዝብ አቅም ግንባታ፣ ሱሉልታንና ለገጣፎን ለተመሳሳይ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ ያነሳሳቸዋል እንጂ፣ እንዴት አዲስ አበባ በነፃነት ይተዳደራል ብለው ቅር አይሰኙም። በእርግጥ በአዲስ አበባም ሆነ በሱሉልታ ወይም ለገጣፎ ኢህአዴግ ከባሌ ወይም አርሲ ወይም ጎንደር አምጥቶ የጎለተበት ካድሬ ቅር መሰኘቱ አይቀርም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በዚህ ሥልጣን ላይ ያሉት የካድሬያቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን፣ ሃገራችንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ ለማሸጋገር በመሆኑ ፣ በአዲስ አበባ የተጀመረውን ለውጥ አንዲት ጋትም ቢሆን ወደፊት የሚያራምድ እንቅስቃሴ በበጎ ዐይን ማየት እንጂ ዛሬ በካድሬያቸው፣ ውሎ አድሮ በራሳቸው ሥልጣንም ላይ የሚመጣ አድርገው ማየት አልነበረባቸውም።
ይህንን ለማለት ያስገደደኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምርጫው እስኪጠናቀቅ ከአቢይ በቀር ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሌለ መታወቅ አለበት” ብለው በአፅንኦት መናገራቸው ነው። ሃቁ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ የሚሠራ እንኳንስ እንቅስቃሴ ሃሳቡ እንኳ ያለው የለም ። ከዚህ በፊት በግሌ ለሽግግር ምክርቤት ምሥረታ ጥሪ አድርጌያለሁ። ይህንንም ሃሳብ ሳቀርብ ከምክርቤቱ የተውጣጣ የሥራአስኪያጅ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትላቸውን በምክር እየረዳ ሽግግሩን በዴሞክራሲያዊ ተስፋ እንዲያጠናቅቅ ለማገዝ ነው። ወደዚህ እሳቤ የመራኝም፣ የቲም ለማ ቅቡልነት በብርሃን ፍጥነት እያሽቆለቆለ መምጣትና፣ የሃገራዊ ደህንነትና መረጋጋት በዚያው ፍጥነት እያሽቆለቆለ መምጣት ነው። ቲም ለማን የሚተካ፣ ሆኖም የሃገሪቱን እምቅ ሃይል የሚያንፀባርቅ የሽግግር ምክርቤት መኖር ፖለቲካ አመራሩን ስለሚያጎለብተውና፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ከኦዴፓ ተፅእኖና እስር ነፃ አድርጎ ፣ ያቺ የጌዶዎ እናት እንዳለችው “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆኑ የጌዶዎም መሆናቸውን” ለዓለሙ በማረጋገጥ፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ተአማኒነት ያለው የፖለቲካ አመራር ማእከል ቢኖረን የተሻለ አማራጭ ነው በሚል ያቀረብኩት እሳቤ ነው። አሁንም ከዚህ የተሻለ ምርጫ ያቀረበ ፖለቲከኛ ወይም አሳቢ አላየሁም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ሃሳብ ሊጠሉትና ሊያጣጥሉት አይገባም ። ኢትዮጵያን የሚያህል የመቶ ሚሊዮኖች ሃገር በሳቸው ትከሻ ላይ ብቻ የተተወ እንዲሆን መፈለግ የለባቸውም። ቢያንስ የተቋም መልክ ካላቸው ሃገራዊ ሃይሎች የተመረጠ የሽግግር ምክርቤት ተቋቁሞ በሥራ ሊያግዛቸው ይገባል። ለዚህ ሃሳብ ፈፅሞ እምቢተኛ ከሆኑና ፣ የለውጥ አመራሩ ከኢህአዴግ ምክርቤት መውጣት የለበትም ብለው ካመኑ፣ ምክርቤቱን ስብሰባ ይጥሩና ሽግግሩን የሚመራዉ አካል እንዲመሠረት አድርገው፣ እነዚህም መሪዎች እነማን እንደሆኑ ህዝብ አውቆት፣ በአፋጣኝ ሃገሪቱ የምትፈልገው ሰላምና መረጋጋት ይመሥረት ።
“ሽግግሩን ግዴለም ለእኔ ተውት፣ እኔ አሻግራችኋለሁ” ብለው ቃላቸውን አምነን በተግባር የሆነው ግን ዛሬ የምንገኝበትን አዘቅት ስለፈጠረ፣ ዶክተር አቢይ አሁን የቀረቻቸውን ቅቡልነት አሟጠው ሳይጨርሱ፣ ራሳቸውን ከኦዴፓ እስርና እግረሙቅ አላቆ ነፃ በማውጣት በመከላከያውና ደህንነቱ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር አጥብቆ ኢትዮጵያን ወደተረጋጋ የዴሞክራሲ ተስፋ ሊያሻግር የሚችለውን የሽግግር ምክርቤት እሳቤ እድል ቢሰጡትና፣ ለዚህም ያላቸውን ድጋፍ በነገው ዕለት የተጠራውን የቀበሌዎች ስብሰባ ባለመተናኮልና፣ የሚገባውን የደህንነት ጥበቃ በመስጠት፣ ነፃ የወጣ ህዝብ ሊሠራ የሚችለውን ተአምር ለማየት ቢተባበሩ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል።
ቢያንስ እንደ ምሁር፣ በተለይም ስለደህንነት አጥብቦ የሚያጠና ሰው በመሆናቸው፣ የአንድ ቀበሌ ህዝብ ነፃ ሲሆንና ራሱን ማስተዳደር ሲጀምር ከኢህአዴግ የተሻለ አመራር የመስጠት አቅም ይኑረው አይኑረው ለማየት ይችሉበት ይመስለኛል። በእኔ እምነት የሰፈሬ የአራዳ ሰው ተሰብስቦ ኢህአዴግ ከፋርጣ ካመጣውና “መኪና እንዳይበላው” መንገድ አሻጋሪ ከተመደበለት ካድሬ ይልቅ፣ የሰፈሩ ሰው ተሰብስቦ ከመሃሉ የሚያወጣው መሪ የተሻለ ብቻ ሳይሆን ማወዳደር እንኳ ሃጢያት እንደሚሆን ለዶክተር አቢይ ስናገር በልበሙሉነት ነው። ቦሌም፣ ለገጣፎም፣ ሱሉልታም ተመሳሳይ ነፃ ህዝባዊ ምርጫዎች ቢካሄዱ ከጥሙጋ፣ አርሲና ባሌ ከመጡት ካድሬዎችና ጨካኝ ከንቲባዎች ይልቅ፣ የነዚህ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎች ከመሃላቸው ብሶታቸውን፣ ፍርሃታቸውን፣ ተስፋቸውን የሚያውቅ መሪ የመምረጥ አቅማቸው የትዬለሌ ነው። የነገ ሰው ይበለን! ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! የነገዎቹን ስብሰባዎች ለማገድ ወይም ለመተናኮል አስበው ከሆነ እባክዎ ከፈጣሪዎ ጋር ሲያለቅሱበት ይደሩ! እባክዎን! በህዝብ ነፃነት የተጎዳ ሃገር የለምና! ፈጣሪ ቀናውን ያሳይዎ!
Filed in: Amharic