>

በዘረኝነት፣ በጥላቻና በመንጋ እየተናጠች ያለች ሀገር!!!  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

በዘረኝነት፣ በጥላቻና በመንጋ እየተናጠች ያለች ሀገር!!!
 (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
አዲስ አድማስ
ዛሬ ሀገራችን “መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለቺው” የሚለውን ሃሳብ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋግሞ ሲነገር እሰማለሁ፡፡ በአባባሉ እኔም እስማማለሁ፡፡ እናም፤ ፋታ ወስደን፣ አውጥተን አውርደን፣ አመዛዝነን ቀጣዩን ጉዞ ካልጀመርን ልንወጣው የማንችለው አዘቅት ውስጥ የመዘፈቅ እጣ ፋንታ በእጃችን ላይ ነው። መደማመጥ ከቻልን እጣ ፋንታችን የተቃና እንዲሆን ማድረግ እንችላለን፡፡ በመጣንበት መንገድ የምንቀጥል ከሆነ ግን ሀገራችንንም ራሳችንንም አጥፍተን፣ ከወራት በኋላ በፍርስራሽ ስር ተቀምጠን በፀፀት መቆዘማችን ጥርጥር የለውም፡፡ ከወራት በኋላ በፍርስራሽ ስር የመቀመጡን እድል የምናገኘውም በህይወት ከሚተርፉት ውስጥ መሆን ከቻልን ብቻ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ ለማንሳት የፈለግኩት፤ ነዳጅ ሆነው ወደ አዘቅት እያንደረደሩን ባሉ “ዘረኝነት፣ ጥላቻና መንጋነት” በተባሉ ጽንሰ ሃሳቦች ዙሪያ ላይ ይሆናል፡፡ እነዚህ ቃላት ሲያነቧቸው ወይም ሲሰሟቸው ቅልል ያሉ፣ ትርጉም ያላቸው የማይመስሉ ናቸው፡፡ ግን ከኒኩሌር ኃይል በላይ ሀገር የማፍረስና ህዝብ የመጨረስ ጉልበት ያላቸው በመሆኑ፣ ዛሬ ሀገራችንን አጣብቂኝ ውስጥ ከተው እየገዘገዟት ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ቃላት ተያያዥና ተመጋጋቢ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡ ለየብቻ፣ በተናጠል ውጤታማነታቸው ደካማ ነው፡፡ ሲጣመሩ ግን ጥፋትን ያሳልጣሉ፣ ያፋጥናሉ፡፡ ዘረኝነት ጥላቻን ይወልዳል፡፡ ዘረኝነትና ጥላቻ የመንጋ ጉልበት ካገኙ፣ እንደ ደራሽ ውሃ ያገኙትን ነገር ሁሉ እየጠራረጉ ይነጉዳሉ፡፡ “ዘረኝነት፣ ጥላቻና መንጋነት” ያላቸውን ትርጉምና በተለያዩ ሀገሮች ያላቸውን አንደምታ በአጭር በአጭሩ ካየን በኋላ ወደ ሀገራችን እንመለሳለን፡፡
ዘረኝነትና ጥላቻ
አንዳንድ ሰዎች ዘረኝነት ማለት “ጭፍን ጥላቻ፣ መድልዎና ማግለል” ማለት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ዘረኝነት ማለት “አንድን ሰው ወይም ቡድን በዘሩ፣ በጎሳው፣ በቆዳው ቀለም፣ በሃይማኖቱ ወይም በብሔሩ ምክንያት ከፍተኛ ጥላቻ ማሳየት ወይም ማግለል ወይም አለመውደድ” ማለት ነው ሲሉ ይደመጣሉ። አንዳንዶች “ዘረኝነት ማለት የራስን ወገን በማሰባሰብ ከእነሱ የተለየውን ማግለል ነው” ይላሉ፡፡ ይህንን ጽሁፍ ከማዘጋጀቴ በፊት ያነጋገርኳቸው የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች ደግሞ ዘረኝነት “ከእኔ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ጎሣ፣ ብሔር፣… ውጪ የሆኑ ባዕዳን ‘ያለኝን ያሳጡኛል፤ ይወስዱብኛል’ የሚል ስጋት የሚወልደው ስግብግብነት ነው” ብለውኛል፡፡
ትርጉሙ ይሄ ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄ፣ ሰዎች ለምን ዘረኛ ይሆናሉ? የሚል ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡ በርግጥ ሰዎች ለምን ዘረኛ እንደሚሆኑ ትክክለኛውን ምክንያት ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ፤ ማናችንም ብንሆን ከእናታችን ሆድ ስንወጣ ማንበብን ወይም መዝፈንን ወይም ጋዜጠኛነትን… ተምረን እንደማንወጣው ሁሉ፣ ‘ማንም ሰው ዘረኛ ሆኖ አይፈጠርም’ ብሎ መደምደም ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። በመሆኑም ልክ እንደ ሌሎች የሰው ልጅ ባህሪያት፣ ዘረኝነት “ከሌሎች የምንማረው እኩይ ባህሪ ነው” ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰዎች በማያውቁት ባህል ወይም ዘር ወይም ሃይማኖት ወይም ጎሣ… የተጠቁ፣ የተገፉና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው ሆኖ ሲሰማቸው ወይም ስጋት ሲያድርባቸው “የራሴ፣ ወገኔ” የሚሉትን አጥር ገንብተው እዚያ ውስጥ በመደበቅ “ዘረኛ” እንደሚሆኑ በመስኩ የተመራመሩ ሊቃውንት ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ሰዎች የማያውቁትን ነገር ቀረብ ብለው ለማወቅ፣ ለመገንዘብና አቃፊ ለመሆን ጥረት ማድረግ ሲገባቸው “አደጋ ያደርስብኛል” ብለው በመፍራትና በመሸሽ፣ ስጋትና ጥላቻቸውን ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ዘረኝነትን እንዲፋፋና እንዲስፋፋ ያደርገዋል፡፡
በእንግሊዝኛ “Xenophobia” (ዜኖፎቢያ) የሚለው ቃል ወደ አማርኛ ሲመለስ “ባዕዳንን መፍራት ወይም በጥርጣሬ ማየት” የሚል ትርጉም እናገኛለን፡፡ በአንዳንድ መዝገበ ቃላት ደግሞ “መጤዎችን/ባዕዳንን መጥላት” የሚል ትርጉም ተሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው “Xenophobia” የሚለው ቃል “ባዕድ ወይም መጤ የሆነን ግለሰብ ወይም በርከት ያሉ ሰዎች በጥላቻ ዓይን ማየት፣ ማግለል፣ መጠራጠር፣ መፍራት እና እምነት ማጣት” የሚል ትርጉም እንዳለው ከተለያዩ ሰነዶች ላይ ያገኘኋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
የጥላቻ ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ብዙዎች ከሚስማሙባቸው ጥላቻን የሚፈጥሩ ምክንያቶች ውስጥ፡- “ጠባብ አስተሳሰብ፣ ጭፍንነት፣ ተጠራጣሪነት፣ በስሜታዊነት ሌሎችን መከተል፣ መገናኛ ብዙሃን ስለ ስደተኞች የሚናገሩትን ነገር በተሳሳተ መንገድ መረዳት፣ የዘረኝነት መንፈስ ያደረበት መሆን፣ ከራስ ወገን ውጪ ያለን ነገር አለመቀበል፣ አለመቻቻል፣ የብዝሃነት ልምድ አለመኖርና የማያውቁትን ነገር በሩቁ መፍራት” የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። “ለአገሩ ባዳ፣ ለሰው እንግዳ” የሆነ ግለሰብም ይሁን በርከት ያሉ ሰዎች በቡድን ወደ አንድ አካባቢ መጥተው፣ የተለየ ቋንቋ እየተናገሩ፣ ከአካባቢው ህብረተሰብ የተለየ ባህላዊ ወይም መንፈሳዊ ተግባራትን ሲፈጽሙ፣ በአጭር ጊዜ ሀብት ሲያፈሩ፣ ታዋቂ ሲሆኑ፣… ማየት የቅናት ስሜትን ሊፈጥር፣ ሊያስደነግጥ፣ ሊያስፈራ፣ ሊያጠራጥር ወይም ጥላቻን ሊያጭር ይችላል፡፡
ዘረኝነትና ጥላቻ በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚገኙ ሀገራት ባሉ ማህበረሰቦች የሚፈጸም እኩይ አስተሳሰብ የወለደው እኩይ ተግባር ነው፡፡ በአሜሪካ፣ በብራዚል፣ በካናዳ፣ በሜክሲኮ፣… የቆዳ ቀለምንና አልፎ አልፎም ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥላቻና ማግለል ይታያል፡፡ በአውሮፓ በቤልጂየም፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በሀንጋሪ፣… በቆዳ ቀለምና በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ማንነትን መሰረት አድርጎ (ለምሣሌ፡- ጂብሲ፣ አይሁድ) የማግለል ሁኔታ ይታያል፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በፈራረሰቺበት ወቅት በቦስንያ በተደረገ ዘርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ 100 ሺህ ሰዎች አልቀዋል፣ 2 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል፡፡
በኢስያ በቡታን የኔፓል ጎሣ አባላትን፣ በብሩኒ የማላይ ጎሣዎችን፣ በኢንዶኔዥያ የቻይና ዝርያ ያላቸውን ሰዎች በፖለቲካ፣ በትምህርትና በውትድርና እንዳይሳተፉ ገደብ ጥለው ያገሏቸዋል፡፡ በአንዳንዶቹ ሀገሮች በገጠር ከያዙት መሬት ተነቅለው ወደ ከተማ እንዲሰደዱ የሚደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ በማሌዥያ ፔናን በተባለ ግዛት፣ የውጭ ሀገር ዜጎች ምንም ዓይነት ባህላዊ ምግብ እንዳያዘጋጁ፣ ሪፈረንደም ተደርጎ፣ እገዳ ተጥሎባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡
በአውስትራሊያ በነባሮቹ የኦቦርጂን ጎሣ አባላት ላይ ቅኝ ገዢዎቹ የእንግሊዝ ሰፋሪዎች እስከ አሁን ድረስ የሚፈጽሙት መድሎና ማግለል የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ በግብጽና በጆርዳን፣ በአይሁዶች ላይ ከፍተኛ የጥላቻና የማግለል ተግባር ይፈጸማል። በአፍሪካ በአይቮሪኮስት፣ በሞሪታንያ፣ በኒጀር፣ በሱዳን፣ በዚምባብዌ፣… ልዩ ልዩ ማንነቶችን መሰረት ያደረጉ የጥላቻና የማግለል ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ በዘመነ አፓርታይድ የነበረው የአናሳዎቹ ነጮች መንግስት፣ በብዙሃኑ ጥቁሮች ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት ዓለም ያወቀው ነው፡፡ በሩዋንዳ በሁቱና በቱትሲ ጎሣዎች መካከል በተቀሰቀሰ ዘርን መሰረት ያደረገ ፍጅት፣ በአንድ መቶ ቀናት አንድ ሚሊዮን ቱትሲዎች ተጨፍጭፈዋል። በቡሩንዲ የነበረው ብሔርን መሰረት ያደረገ እልቂትም በዘግናኝነቱ የሚዘከር ነው፡፡
በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል ያለው ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ማግለልና መድሎ ለየት ያለና ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ተቋማዊ የሆነ፣ የህግ ሽፋን ጭምር የተሰጠው ነው። እስራኤል የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣… ብዝሃነት ያለባት ሀገር ብትሆንም ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ መድሎና ማግለል ጣሪያ የነካባት ሀገር ናት፡፡ የአይሁዶች ግለሰባዊ ባህሪ፣ የአይሁድ ሚዲያዎች፣ ትምህርት፣ የኢሚግሬሽን ህግ፣ የመኖሪያ አካባቢን መለየት የመሳሰሉት በእስራኤል ላለው ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ መድሎና ማግለል መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በእስራኤል ያሉ ፍልስጤማውያን፣ በእስራኤላውያን ዓይን “ትምህርት የማይገባቸው፣ ዘላኖችና አመጸኞች” ተደርገው ነው የሚታዩት፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት ፍልስጤሞች በአይሁዶች ላይ የበላይ ነበሩ፡፡ የዐረብ ብሔርተኛነት፣ ፍልስጤማዊነትና ፀረ-ጽዮናዊነት የገነነ ነበር፡፡ ፍልስጤሞች ከጀርመኑ የአዶልፍ ሂትለር ናዚ ፓርቲ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውም ይነገራል፡፡ ናዚ ጀርመን ይከተለው የነበረውን ፀረ-ሴማዊ (ፀረ-አይሁድ) አቋም ይደግፉ ነበር – ፍልስጤማውያን። ሂትለር በአይሁዶች ላይ የፈጸመውን የዘር ፍጅት (Holocaust) “አይሁዶች የፈጠሩት ቴአትር ነው” ይሉ ነበር ፍልስጤሞች፡፡ “ከናዚ ጭፍጨፋ በስተጀርባ ያሉት ራሳቸው አይሁዶች ናቸው፡፡ ያለቁትም አይሁዶች ቁጥር 6 ሚሊዮን ሳይሆን ከአንድ ሚሊዮን በታች ነው…” ይላሉ ፍልስጤሞች፡፡ እስከ አሁንም በዚህ አቋም እንደ ጸኑ ናቸው፡፡
አይሁዶ ራሳቸው በውስጣቸው ሰፊ ልዩነት ስላለ አንዱ ሌላውን የማግለልና እኔ የበላይ ነኝ የማለት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ዘራቸውን ከወደ አውሮፓ የሚቆጥሩ ነጭ አይሁዶች አሽከናዚ (Ashkenazi Jews) የበላይነት ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ አሽከናዚዎች ከኢትዮጵያ፣ ከየመን፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣… ሀገሮች የተመለሱ አይሁዶችን ማዝራሂ ወይም ሰፋርዲክ (Mizrahi or Sephardic Jews) ይሏቸዋል፡፡ ያገሏቸዋል፡፡ ይንቋቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል እስከ አሁን ድረስ የዘለቀው ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ መድሎና ማግለል ዓለም ሊያስቆመው ያልቻለው፣ በዘግናኝነቱም ወደር የሌለው ነው፡፡ መነሻው ላይ የበላይነትን ይዘው ግፍ ይፈጽሙ የነበሩት ፍስልጤሞች ነበሩ፡፡ እስራኤል ሀገር ሆና በዓለም መዝገብ ላይ ስሟን ካሰፈረቺበት እ.ኤ.አ ከ1948 ጀምሮ ግን የጥቃቱ ሰለባዎች ፍልስጤማውያን ሆነዋል፡፡ እስራኤል ሀገር ሆና የቆመቺው ከፊሉን የፍልስጤሞችን መሬት በግዢ፣ ከፊሉን በህገወጥ ሰፈራ ወርራ በመያዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ (ኢህአዴግ መሬት መሸጥ መለወጥ የለበትም የሚለው ብሔር ብሔረሰቦች እንደ ፍልስጤም እንዳይሆኑ በመስጋት ነው)
መንጋነት
አንድ አሜሪካዊ የስነ-አእምሮ ምሁር “ሁሉም ሰው ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያለው ከሆነ፣ የማያስብ ሰው አለ ማለት ነው” ይላል፡፡ ሰዎች ስንባል ማህበራዊ እንስሳት ነን፡፡ እናም አንዳንድ ጊዜ እንስሳነታችን ግለሰባዊ ማንነታችንን ያዳክመውና ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትን በደመነፍስ እናደርጋለን፡፡ የሥነ ልቦና ሐኪሞች ይህንን “የመንጋ አስተሳሰብ” ይሉታል፡፡ የመንጋ አስተሳሰብ “የመከተል ዝንባሌን” ይፈጥራል – መከተሉ አስከፊ ውጤት የሚያመጣ ቢሆንም እንኳ ዝም ብለን እንከተላለን፡፡ ለምሣሌ፡- ከስፖርታዊ ጨዋታ ተከትሎ የሚፈጠርን ሁከት አስቡት፡፡ ጓደኞቻችን ሲጮሁ እንጮሃለን። ድልድይ ሲዘሉ ብናይ ተከትለን ልንዘል እንችላለን፡፡
የመንጋነት አስተሳሰብ ምንጩ ማህበራዊ ግፊት ነው፡፡ ሁላችንም በህብረተሰባችን ተቀባይነት ለማግኘት እንፈልጋለን፡፡ ይህ የሰዎች ባህሪ ነው፡፡ ተቀባይነት የማግኘት ጫና ሲበዛብን፣ ግፊቱ ይበልጥ ኃይለኛ ይሆንብናል። ሰዎች የመንጋ ስብስብ ውስጥ ሲቀላቀሉ የግል አስተሳሰባቸው እልም ብሎ ይጠፋል፡፡ ግላዊ ስሜታቸው ይታፈናል፡፡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት፤ የመንጋ ስብስብ ውስጥ የተቀላቀሉ ሰዎች ጥፋተኛነትን የሚያሰላስለው ስሜታቸውና ሚዛናዊነታቸው ስለማይኖር፣ አጠገባቸው ያሉ የመንጋው አባላት የሚያደርጉትን ለማድረግ ይገፋፋሉ፡፡ ብቻቸውን ቢሆኑ የማያደርጉትን ያደርጋሉ፡፡ ይሳደባሉ፣ ይጮሃሉ፣ ይወረውራሉ፣ ያቃጥላሉ፣ ያወድማሉ፣…አንዴ የመንጋ ስብስብ ውስጥ ከገቡ ህሊና ብሎ ነገር የለም፡፡ መንጋ የሚፈጥረው ጫና በጣም ኃይለኛ ነው፡፡ የመንጋ ጉልበት ግላዊ፣ ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰባችንን ይቀማናል፡፡ ሰዎች ግላዊ አስተሳሰባቸውን ሲያጡ በመደበኛ ህይወታቸው የነበረው እነሱነታቸው ይጠፋል፡፡ በመንጋ ስብስብ ውስጥ የገባ ሰው ሥልጣኔ ካስገኘለት ማማ ላይ ተምዘግዝጎ በመውረድ ትቢያ ላይ ይፈጠፈጣል፡፡ በመልካም ስነ ምግባር ተኮትኮቶ ያደገ ጨዋ፣ የተከበረ ግለሰብ መንጋ ውስጥ ሲቀላቀል አረመኔ፣ ጨካኝ፣ ይሉኝታ ቢስ፣… ይሆናል፡፡
ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ መቀመጫቸው ላይ ብቻቸውን ቢሰየሙም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከተሰለፉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ስለሚያደርጉ ለመንጋ አስተሳሰብ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ግለሰባዊ አስተሳሰባቸውን ያጣሉ። ለዚህም ነው በማህበራዊ ሚዲያ አንድ ሰው “LIKE” ያደረገውን ሃሳብ ሳያመዛዝኑ እነሱም “LIKE” በማድረግ ድጋፋቸውን የሚገልጹት። መንጋው የደገፈውን መደገፍ ወይም መንቀፍ ታዋቂ የሚያደርግ የሚመስላቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይህን ባያደርጉ የመንጋው መሪዎች የሚያዩዋቸው የሚስላቸውም አይጠፉም፡፡ (ለኢንተርኔት ምስጋና ይግባውና በዓለም አቀፍ የመንጋ እንቅስቃሴ የመሳተፍ እድል ይህን ያህል የቀለለ ሆኗል)
የጋራ ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ዘረኝነት፣ ጥላቻና መንጋነት ያላቸውን ትርጉምና ምንነት በተለያዩ ሀገሮች ከታዩ አስከፊ ሁኔታዎች ጋር በማቆራኘት ከላይ በአጭሩ ለማሳየት ተሞክሯል። አሁን ደግሞ ወደ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እናምራና አንዳንድ ተጨባጭ ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የዓለም አካል እንደመሆኗ በዓለም ላይ ከተከናወኑ በጎም መጥፎም ሁኔታዎች ነፃ ልትሆን አትችልም፡፡ እንደ ማህበረሰብ በኛም ሀገር ዘረኝነትና ጥላቻ ነበር፣ አሁንም አለ፡፡ በኛም ሀገር የመንጋነት አስተሳሰብ ነበር፡፡ አሁንም ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ አለ፡፡ በእኛዋ ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ብቻ ሳይሆን ጎጠኛነትና መንደርተኛነት ነበር፣ ዛሬም መናኸሪያ ናት፡፡ የሃይማኖትም፣ የቋንቋም፣ የብሔርም፣ የባህልም፣… ብዝሃነት ማዕከል በሆነቺው ሀገራችን፤በዚህ ዘመን ያለው ዓይነት ጎጠኛነት መቼም ቢሆን ኖሮ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ የታሪክ ምሁራን የሚነግሩንም ይህንኑ ነው፡፡
በዘር በተሸነሸነቺው ኢትዮጵያ ዛሬ “አንተ መጤ ነህና ካጠገቤ ሂድልኝ” የሚል በዘረኝነት የተሸፈነ ጥላቻ፣ የእለት ከእለት ተግባር ከመሆን አልፎ በአፈናቃዮች በኩል እንደ መብት ማስከበር እየታየ ነው፡፡ በዚህም ሰበብ በጂግጂጋ፣ በሞያሌ፣ በሐረርጌ፣ በአሶሳ፣ በወለጋ፣ በጎንደር፣ በሻሸመኔ፣ በሐዋሳ፣ በጌዴዎ፣… ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ የህዝብ እልቂትና መፈናቀል ተከስቷል፡፡ በመንጋ የሚጋልቡ ሰዎች፣ ወገናቸውን ገድለው ዘቅዝቀው እስከ መስቀል ደርሰዋል፡፡
የሚገርመው ነገር ትናንት አፈናቃይ፣ ውጣልኝ ባይ፣ የነበሩት “ዘረኞች”፤ ዛሬ ተፈናቃይና የእለት እርዳታ ጠያቂ መሆናቸው እየታየ ነው፡፡ በአሳዛኝ መልኩ ትናንት ተፈናቃይ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ (የተደላደለ ህይወት ሳይጀምሩ) በሌሎች ላይ የማፈናቀል መሐንዲስ የሆኑበት አጋጣሚም በዚቺው ሀገራችን ታይቷል፡፡ ነገሩ እዚያ ላይ ቢቆም መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬም እየቆየ ማገርሸቱ ቀጥሏል፡፡ በአንዱ አካባቢ ያለው ጋብ ሲል በሌላ አካባቢ ይፈነዳል፡፡ በመንጋ መንፈስ የሚነዳ ዘረኝነትና ጥላቻ እንደ ቋያ እሳት ሀገሪቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ እየለበለባት ነው፡፡ በታላቅነቷ፣ በአኩሪ የታሪክ ባለቤትነቷ የምትታወቀው ሀገራችን፤ የዘረኝነትና የጥላቻ መናኸሪያነቷ ጎልቶ እየተደመጠ ነው፡፡
ሀገራችን ዛሬ ከመቼውም በበለጠ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ዜጎች የዘረኝነትና የጥላቻ ፈረስ እየጋለቡ፣ በመንጋ እየተመሙ በሚወስዱት እርምጃ ሀገራችን እየተናጠች ነው፡፡ ሰርቶ መኖር አዳጋች መሆኑ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሥራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ሊተገበርና የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ባለመቻሉ፣ የህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መልፈስፈስ እየተስተዋለ ነው፡፡ ክልሎችና ፌዴራል መንግስቱ ያላቸው ግንኙነት ከመላላቱም በላይ የተኳረፉ ባልና ሚስት መስለዋል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ የሀገሪቱን ገጽታ ያበላሻል፡፡ ኢንቨስትመንት ይጎዳል፡፡ የቱሪዝም ፍሰቱን ያስተጓጉላል፡፡ የሰርቶ በሌውን ህዝብ እንቅስቃሴ ይገታል፡፡
አበው “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” እንዲሉ፤ አንዳንዱን ነገር እየሸፋፈንን ብናልፈው፣ ቆይቶ በሽታ የሚሆነው ለእኛው ነው፡፡ እንደ ሀገር ወይም እንደ ማህበረሰብ እያየን እንዳላየ፣ እየሰማን እንዳልሰማ ሆነን ማለፍ የሚገቡን ነገሮች ሊኖሩ እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ይህ ግን በሁሉም ነገር ላይ ተፈጻሚ መሆን የለበትም፡፡ በታሪክ ፊት ተጠያቂነትም አለና በሀገራችን ተንሰራፍቶ እየፈጀን ያለውን ዘረኝነት፣ ጥላቻና የመንጋ እርምጃ በስሙ እየጠራን፣ ልናወግዘውና ልንዋጋው ይገባል እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ የተንጸባረቀው ሃሳብ የሚወክለው የጸሃፊውን ብቻ ሲሆን ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡March 23, 2019
Filed in: Amharic