>

ኦዴፓም እንደ ህወሓት... (ዳንኤል ደምሴ)

ኦዴፓም እንደ ህወሓት…
ዳንኤል ደምሴ
ህወሓት ኢትዮጵያን 27 አመት “ቀጥቅጦ” ቢገዛም ህዝቡም ሆነ ህወሓት ራሱ የህወሓትን መንግስትነት እርግጠኛ ሳይሆኑ ከስልጣን መንበሩ ተገፍትሮ ተንደባሏል።
ለዚህ ችግር አንዱ ምክኒያት ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የሚያስችል መንግስታዊ ባህርይ መላበስ አለመቻሉ ነበር። በድንገት ከጫካ ወጥቶ ከተማ እንደገባ አውሬ ደንብሮ ከሁሉም ጋር ሲናከስ መኖሩ ግልፅ ነበር።
ታዲያም ህወሓት ሆዬ በማያርፈው የተንኮል እጁ በሚጭረው እሳት የሚመጣበትን ጣጣ በትግራይ ቀሚስ ውስጥ ተደብቆ ለማምለጥ ይሞክር ነበር፤ ሆኖም ምግባር እንጅ ቀሚስ አያድንምና ክፉ ምግባሩ ከመድረክ ገለል አድርጎታል።
ዛሬም ባለተራ ነኝ ብሎ ራሱን እያታለለ ያለው ኦዴፓ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህችን የተነቃባትና ህወሓትን ለውድቀት የዳረገች ስልት አቧራዋን አራግፎ ወደ መድረክ ያመጣት ይመስላል።
ከሰሞኑ ኦዴፓ ተደጋጋሚ በሚሰራው ስህተት የሚመጣበትን ናዳ በኦሮሞ ቀሚስ ውስጥ ተከልሎ ለማለፍ እየሞከረ ስለመሆኑ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ላይ ለመታዘብ ችለናል። ቃል በቃል ከህወሓት ኮርጆ “በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት” ማለት ጀምሯል።
ከጅምሩ ኦዴፓም ሆነ ህወሓት ያልተገነዘቡት ጉዳይ ቢኖር የፌደራል ቁልፍ የስልጣን ወንበሮችን ተቆጣጥሮ ለአንድ ብሔር ብቻ መስራት እንደማይቻል ነው። የብሔር ፌደራሊዝሙን ወዶና የፌደራል ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን አግበስብሶ ለብሔሬ ብቻ እሰራለሁ ማለት አይቻልም። በፍፁም። ስልጣን ስታግበሰብስ ተጠያቂነትንም እያግበሰበስክ መሆኑን ልብ ልትል ይገባል።
ሲቀጥል የህዝብን ችግር በዘላቂነት መፍታትና እድገቱን በፅኑ መሰረት ላይ መገንባት የሚቻለው ከታች ማህበረሰቡን ባለበት ቦታ (በክልሉ) በትምህርት፣ በስነልቦናና በመሳሰሉት ማዘጋጀት ሲቻል ብቻ ነው።
እናም ኦዴፓ ሆይ ስምን የሚያጠፋው ምግባር እንጅ ሰው አይደለምና ህወሓታዊ አመልህን ተው አይጠቅምህም።
Filed in: Amharic