>
11:19 am - Wednesday November 30, 2022

አሸባሪውና ተሸባሪውን መለየት አቃተን!!!  (ዘመድኩን በቀለ )

 

አሸባሪውና ተሸባሪውን መለየት አቃተን!!!

 ዘመድኩን በቀለ 
በአዱ ገነት የጠሚዶኮ ዐብይና የእስክንድር ፍጥጫ፣ 
• በባህርዳር የግንቦት ሰባት መበተን፣
• በመቀሌ የዓጋመና የእንደርታዎችን የመገዳደል ወሬን ተሰምቶ ነበር። 

* በህልሜ አቢቹ እንደ መንግሥቱ ኃይለማርያም። ብረቱ ሰው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ደግሞ  እንደ በዓሉ ግርማ ሆነው ድራማ ሲሠሩ ዐይቼ ብንን ብያለሁ። መጨረሻውን አላየሁም። 

አዲስ አበባ ፤ ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድና እስኬው።
•••
በፋና ቴሌቭዥን የዌብ ፔጅ ገጽ ላይ ሸበላው ጠሚዶኮዬ ንግግር ሲያደርጉ አየሁ። ለወትሮው እሳቸው ንግግር ያደርጋሉ ሲባል የሚኮለኮለው መንጋ ሁሉ የት እንደገባ አላውቅም ጥቂት ተመልካቾች ነበሩ የሚያደምጧቸው። እሳት ለብሰው፣ እሳት ጎርሰው ይናገራሉ። ከተሾሙ ጀምሮ እንዲህ ከምር ሳያስመስሉና ሳይተውኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የውስጥ ስሜታቸውን በመደበቅና በመግለጥ መካከል እየታገሉ ሲወራጩ ያየሁት። የመንጌ ግማሽ ከመለስ አነስ ብለው ከኃይለማርያም ግን ከፍ ብለው ነበር ያየኋቸው።  በአንድ ወገን ደርግ ደርግ ሲሸቱ፤ በሌላ በኩል የ11 ወሩ ስብከተ ወንጌል ትዝ እያላቸው አንዴ ደርግ አንደዜ ደግሞ ፓስተር እያደረጋቸው ነበር ሲደሰኩሩ ያመሹት። አታበሳጩኝ፣ ነግሬያለሁ። ወደ ማልፈልገው ጉዳይ አታስገቡኝ ነበር ሲሉ የነበረው ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ።
•••
የእኔው ጠሚዶኮዬ ጌታቸው አሰፋን ፈርተው፣ 18 ባንክ ዘርፎ በቢልየን የሚቆጠር ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ የዘረፈውን የውስጥ ልብሳቸው የሆነውን፣ ከኮት ከሸሚዛቸውም ሥር የተሸሸገውን ኦነግ ልባሻቸውን ፈርተው፣ አንድ ሞት አይፈሬ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ልክ እንደ ኤዲአሚንዳዳ፣ እንደ ሳዳም ሆሴን፣ እንደ ጋዳፊ ሲያደርጋቸው ሳይ ከምር አሳዘኑኝ።
 እሳቸውም እንደ ሌሎቹ አምባገነን መሪዎች ጭምብላቸውን ሊያወልቁ ዳር ዳር እያሉም እንደሆነ ጠረጠርኩ። ከሁሉ ከሁሉ ባለፈው ቤተ መንግሥት ወታደሮች መጡ በታባለ ጊዜና አሁንም በእስክንድር ላይ የዛቻ ሲያዥጎደጉዱ ለገዳዲን፣ ሱሉልታን፣ ቡራዩን፣ ሰበታና ሰንዳፋን እንደማስፈራሪያ መጠቀማቸው የሆነ ያሰቡት ነገር ስለመኖሩ አመላካች ነው ብዬ እንድጠረጥር አድርጎኛል። የሆነ ነገርማ አላ። ዝም ብሎ አስር ጊዜ እነ ሰበታና ሰንዳፋ፣ ሱሉልታና ቡራዩ ተደጋግመው ለማስፈራሪያነት አይጠሩም። በእነዚህ ቦታዎች ኦሮሞ ብቻ አለመኖሩን ግን ዐማራም፣ ጉራጌም፣ ትግሬም፣ ደቡብም መኖሩን ግን የነገራቸው ያለም አይመስለኝ። አሉ። ዐማሮችም አሉ። ዱላ ሲያዩ ክላሽ የሚያነሱም አሉ ይባላል።
•••
ለማንኛውም በህልሜ አቢቹ እንደ መንግሥቱ ኃይለማርያም። ብረቱ ሰው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ደግሞ  እንደ በዓሉ ግርማ ሆነው ድራማ ሲሠሩ ዐይቼ ብንን ብያለሁ። መጨረሻውን አላየሁም። ድንገት ነው የባነንኩት። ምን ዓይነት ዘመን ነው እባካችሁ መሣሪያ ብረት ያለው ተከብሮ ቢክ እስኪሪብቶ የያዘን ሲያዩ መደናበር። ምን የሚሉት ፍርሃት ነው? እስክንድርም ይጽፋል። ገዢዎችም ይባንናሉ። ብትት ብትትም ይላሉ። ሂደቱም ይቀጥላል። እስክንድር ነጋም ለጠሚዶው ከባድ ምላሽ በትዊተር ገፁ አስወንጭፎላቸዋል። “ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ኃይል የእግዚአብሔር ነው” ነበር እስኬው ያላቸው። እንዲህ ብሎ የሚያምን ደግሞ አሸናፊነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።
•••
ባህርዳር እና ግንቦት ሰባት!!
••••
ትናንት ዕሁድ ግንቦት ሰባት በባህርዳር ስብሰባ እንደሚያደርግ በድንገት ተነገረ። ፌስቡክ ድብልቅልቁ ወጣ። ምን ሲደረግ፣ እንዴት ቢደፍረን ነው በሚሉና ምን ታመጣላችሁ በሚሉ ወገኖች መካከል የጦፈ ሙግት ተካሄደ። በተለይ ደግሞ የድርጅቱ የግንቦት ሰባት መስራች የነበሩት አቶ ነዓምን ዘለቀ በባህርዳር ወሮታ ካምፕ የተጠለሉት ወታደሮቻቸው ምንም ድጋፍ ከመንግሥት ሳይደረግላቸው በካምፕ ተቀምጠው አንዳንዶቹም እየለመኑ ህይወታቸውን ሲገፉ ማየታቸው አስቆጥቷቸው መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው ድርጅቱን መልቀቃቸው በባህርዳር የሌለ ሙቀት ጨመሮ ተቃዋሚዎችን አባዘባቸው።
•••
መሸም ነጋም እሁድም ሆነ። ገና ፀሐይ ሳትወጣ ባህርዳር በተቃዋሚ ሰልፈኞች ተጥለቀለቀች። ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ መፈክርና ክላሽም ይዘው ነበር። ወደ ስብሰባው አዳራሽም አምርተው አዳራሹን ተቆጣጠሩት። ዶክተር ብርሃኑም ነጋም ሁኔታው ስላላማራቸው ወረታ ደርሰው በሰላም ወደ አዲስ አበባቸው ተመለሱ። የሆነው ይሄው ነው።
•••
ከሰልፉ በኋላ እጅግ አነጋጋሪ የነበረው በሰልፉ ላይ የጦር መሣሪያ የያዙ ሰልፈኞች መታየት ነበር። ብዙዎቹንም ያነጋገረውም ይሄው ጉዳይ ነበር። ሆኖም ግን እኔም ደርጊቱን ብቃወመውም በዐማራ ባህል መሠረት ግን ለዐብይ ድጋፍ ሰልፍ ጊዜም፣ ለቀብርና ለሠርግ ጭምር ክላሽ ይዞ አደባባይ መውጣት በዐማራ የተለመደ ነገር ነው። ታቦት ሲሸኝ በግራ በቀኝ መሣሪያውን ተሸክሞ ትርኢት የሚያሳይ ነው ዐማራ ማለት። ከተሳሳትኩ እታረማለሁ። ትግሬ በከበሮ፣ ኦሮሞ በክትክታ ዱላው፣ ደቡብ በጋሻና ጦሩ።  አፋርና ሱማሌ በጎናቸው ሻጥ በሚያደርጉት ጎራዴ፣ ቤንሻንጉል በቀስቱ ይታወቃል። ሆኖም ግን የፈለገ ልማድ ቢሆን ትናንት ግን በባህርዳሯ  ዐማራ አጅሬ ክላሽ በፍፁም መታየት፣ አልነበረባትም። በጭራሽ። በፍጡም።
•••
በአንድ በኩል ድርጊቱን ብቃወመውም በሌላ በኩል ደግሞ ሜንጫና ዱላ ይዘው ሰልፍ ለሚወጡት ወገኖች እዚህም ሰፈር ክላሽም ይዞ መውጣት አለና ተረጋጉ የሚል መልእክት ለእነ ሃጂ ጃዋር የሚያስተላልፍ በመሆኑ በመጠኑም ቢሆን ጥሩ ነበር ባይ ነኝ። አሁን ሁሉም በያለበት አቅሙን ማሳየት ላይ ቢሆንም ትንፋሽ ስቦ እንዲያስብ ስለሚያደርገው መታየቱ አይከፋም ባይ ነኝ። ሕግ ወጥቶ ሁሉም ሰይፉን ወደሰገባው እስኪመልስ ትርኢት መሳየቱ ግን ይቀጥላል። በነገራችን ላይ ከዐማራው መደራጀት፣ ከብአዴን ቀበቶውን ጠበቅ ማድረግ በኋላ በእነ ጃዋር ሰፈር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የሌለ የጠባይ ለውጥ እየታየ መምጣቱን እየታዘብኩ መጥታቻለሁ። ጃዋር ነፍሴም አዲስ አበባን በአፋን ኦሮሞም፣ በአፋን ሲዳማም ፊንፊኔ ማለቱን ትታ አዲስ አበባ እያለች መጥራት ጀምራለች። ይሄ ትልቅ ለውጥ ነው። የኃይል ሚዛን ግን ወሳኝ ነገር ነው ማለት ነው። ወጥር ዐማራ አለ ዘመዴ።
•••
የጦር መሣሪያ ይዞ ከመሰለፉ ውጪ ህዝብ ተቃውሞ ማሰማቱ ጤናማ ነው። ድርጅቱ በድሎኛል ያለ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ በደለኝ ያለውን ህዝብ መቃወሙ ጨዋነቱን ያሳያል። ግንቦት ሰባት እንደ ዛሬው ገሌ ሳይሆን በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ በነበረ ጊዜ በአውሮፓና በአሜሪካ፣ በአፍሪካና በአውስትራሊያ፣ በካናዳም ጭምር የተለየ ሃሳብ የያዙ የኢትዮጵያ አገዛዝ ስብሰባዎችን ሲያቋርጥ እንደነበር ይታወሳል። አሁን ከባህርዳሩ የሚለየው መሣሪያ ያለመያዛቸው ብቻ ነው። በምዕራቡ ዓለም እየኖሩ ስብሰባ ሲበጠብጡና ሲያውኩ የኖሩት አንዳንድ ፍሬንዶቼ ዛሬ ተራው በእነሱ ሲደርስ ማለቃቀስ የለባቸውም። መጽሐፍስ “ሰው የዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” አይደል የሚለው። ኢንዴዢያ ነው። ይልቅስ ተነጋገሩ። መፍትሄው እሱ ነው።
•••
መቀሌ ሰብዓ አጋመ እና ሰብዓ እንደርታ !!!
•••
ትናንት እሁድ ሌላ መርዶ በመቀሌ ከተማም ተሰምቷል። በመቀሌ እስታዲየም በነበረ የእግር ኳስ ግጥሚያ የአዲግራት አጋመዎችና እና የመቀሌ እንደርታዎች ተጋጭተው የ5 ሰዎች ህይወት መጥፋቱም ተነግሯል። ወዳጄ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትግራይ ህዝብ የታፈነ ህዝብ እንደሌለ ለማወቅ የግድ ኢዩ ጩፋን መሆን አይጠበቅብህም። የትናንትናውን የመቀሌና የአዲግራቶች ጨዋታ ረብሻ በአንዳቸውም የትግራይ አክቲቪስትና ሚዲያዎች ትንፍሽ አላሉም። ሰናይት መብራቱ፣ ዳዊት ከበደ፣ ዳንኤል ብርሃነ፣ አየሁ ናይና እንኳን ሲሉ አልታዩም። ጭጭ ፣ ምጭጭ፣ ወጥ አድረገው ነው ጮጋ ብለው ለማለፍ የሞከሩት።
•••
የቤታቸውን ኮተት አስቀምጠው ስለ ባህርዳር ሰልፍ ያውም በሰላማዊ ሁኔታ የተጠናቀቀውን ሲተቹ ነው ያመሹት። አቢቹን ሲሰድቡም ነው ያመሹት። የፌስቡክ የኮመንት መስጫዋን በ12 ቁጥር ሚስማር ጠርቅማ የከረመችው ሰናይት መብራቱ እንኳ የኮምንት መስጫ ሳጥኗን ከፍታ አቢቹን በመስደብ አዳሜን ፔጇ ላይ ሰብስባ ልታስቀይስ ስትጋጋጥ አምሽታለች። ነገር ግን ጉዳዩ ከመፈንዳት አላመለጠም።
•••
አሁን በትግራይ ከፍተኛ ራብ እንዳለ ይነገራል። ነገር ግን ታፍኗል። በትግራይ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር እንዳለም ይነገራል ነገር ግን ታፍኗል። በፊት በደጉ ዘመን በመላዋ ኢትዮጵያ በተለይም በዐማራና በኦሮሚያ ተዘዋውሮ እንደ ልቡ ሠርቶ ይኖር የነበረው የትግራይ ህዝብ አሁን አሁን በህወሓት ጦስ የተነሳ በትግራይ ክልል ብቻ ተወስኖ እንዲቀመጥ አድርጎታል። የራብ ዘመን ሲመጣ ወደ ጎረቤቱ ዐማራ ተሰድዶ በዚያ የክፉ ቀንን ያሳልፍ የነበረ ህዝብ አሁን አሁን በህወሓት ጦስ የተነሳ ችግር ላይ ወድቋል። የሥራ አጡ ቁጥር የትየለሌም ነው እየተባለ ነው። ከኤርትራና ከዐማራ ጋር ጠብ ውስጥ የምትገኘው ህወሓት የሌለ ጨንቋታል።
•••
ሥራ የሚያገኙት፣ የሚቀጠሩት የዐድዋ ልጆች ብቻ ናቸው በሚልም ሌሎቹ የትግራይ ልጆች አኩርፈዋል። በተለይም አዲግራቶች ብሶታቸው ከዚህም የከፋ ነው ይባላል። መቀሌዎችም እንዲሁ። ይሄው ብሶታቸው ነው አሁን ሆድ ያባውን ብቅል እያወጣው በየጊዜው በካምቦሎጆ ሲገናኙ የሚያጣላቸው። የሚያገዳድላቸው።
•••
በትግራይ ከተሞች ማጅራት መምታት የተለመደ ሆኗል የሚል ዜና ራሱ የክልሉ መንግሥት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም። በመቀሌና በአዲግራት ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ የተደራጁ ቡድኖች መፈጠራቸውም ይነገራል። ሃገር ስትታመም ሙሉ አካሏ ነው የሚታመመው። ኢትዮጵያ ታማ ትግራይ ጤናማ የምትሆንበት ሎጂክ የለም። ያውም ከዐማራ ጤፍ እንዳይሄድ መንገድ ተዘግቶ፣ ወጣቱ ከትግራይ ውጪ የመንቀሳቀስ መብቱ ታግቶ። እንዴት ነው ትግራይ ጤነኛ የምትሆነው? መመጻደቅ አያስፈልግም። እውነቱን ተነጋግሮ ወደ ሰላም መምጣት ለሁሉም ጠቃሚ ነገር ነው።
•••
ትግራይ ደሴት አይደለችም። መሪዋም ሙሴ አይደለም። መና አውርዶ አይመግባትም። ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ የትግራይ ልጆች በኢትዮጵያ ተዘዋውረው፣ ተወዳድረው፣ ተቀጥረው ሥራ ካልያዙ እንዴት ይሆናል? በየዓመቱ የሚመረቁ ተማሪዎች በትግራይ በተከማቹ ቁጥር፣ ሥራ አጥነት በበዛ ቁጥር ቀጥሎ የሚፈጠረውን አደጋ መገመት አያቅትም። ወዳጄ ትግራይ ሰላም ናት ብለህ በቴሌቭዥን ስለጨፈርክ ያ የተባለው ሰላም በጭፈራ አይመጣም። ችግርን የፈለገ ጎሮቤት ምን ይለኛል ብለህ ብትደብቀው አብጦ መፈንዳቱ እንደሁ አይቀርም። ግመል ሠርቆ አጎንብሶ እንዴት ይሆናል ? በፍፁም አይሆንም።
•••
በዐማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊያ፣ በአፋር፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል የሚፈጠሩ ችግሮችን ቤንዚን እየጨመሩ የሚያርገበግቡት የትግራይ አክቲቪስቶችም ብትጠነቀቁ ለራሳችሁ መልካም ነው። በሌላ ቁስል መሳቅ ግፍ ነው። ይኸው በራስ ሲደርስ መግቢያ ቀዳዳ ነው እኮ የጠፋችሁ። ትንፍሽ ማለት እስኪያቅታችሁ። ደም መቃባት ከተጀመረ ደግሞ በቀላሉ ላይበርድ ይችላልና መሪዎቹን ትታችሁ ከህዝቡ ጎን ቁሙ። የፈሩት፣ ይደርሳል። የጠሉት ይወርሳል። አለ የሃገሬ ሰው።
•••
• ሞቱ የተባሉትን ወንድሞች ነፍስ ይማር። 
• ሰላም ለሃገራችን። 
• ሰላም ለኢትዮጵያ 
•••
ሻሎም !  ሰላም !
መጋቢት 16/2011 ዓም።
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic