>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3313

"ከ60 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የተሰውበት የካራማራው ድል በየአመቱ ሊከበር ይገባል!!!"  (ሜ/ጀነራል መርዳሳ ሌሊሳ) 

“ከ60 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የተሰውበት የካራማራው ድል በየአመቱ ሊከበር ይገባል!!!”

 

 ሜ/ጀነራል መርዳሳ ሌሊሳ 

 

አዲስ አበባ፡- የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያ ወረራ ለመመከት ያደረገው ተጋድሎ ለመዘከር የካራማራ ድል ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር የቀድሞው ሠራዊት ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች ለም/ጠ/ር ደመቀ መኮንን ጥያቄ አቀረቡ።

የቀድሞው የ18ኛ ተራራው ክፍለጦር አዛዥና በኋላም የሶስተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ምክትል አዛዥ የነበሩት ሜ/ጀነራል መርዳሳ ሌሊሳ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ግዛት ጥሶ የገባው የሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ ጀቶች ታንኮች መድፎችና ሜካናይዝድ ኃይሎችን አቀናጅቶ ሰፊ ወረራ አድርጓል።

የሶማሊያ ወራሪ ኃይል በሀገራችን ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል የሚሉት ጀነራሉ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊትና አየር ኃይሉ በመቀናጀት በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ወራሪውን ጠላት መልሶ በማጥቃት በኃይል ረግጠው ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ ለማድረግ የቻሉት እጅግ የገዘፈ መስዋዕትነት በመክፈል ነው ብለዋል። ይህ ከፍተኛ ብሔራዊ ፍቅር የታየበት ወራሪውን የማስወጣት ጦርነት በትንሹ ከ60 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የተሰውበት መሆኑን ሜ/ጀነራል መርዳሳ አስታውቀዋል።

‹‹ኢትዮጵያን ለዛሬው ትውልድ ደምና አጥንታችንን ከፍለን ያቆየናት፤ ብዙዎች በየጦር ሜዳው ኢትዮጵያ ወይም ሞት ብለው የወደቁላት፤አካላቸውን የገበሩላት ሀገር መሆንዋ መታወቅ አለበት። ቀጣዩ ትውልድ ይሄንን ግዙፍ የአባቶቹን ድል ልክ እንደ አድዋ ድል በየአመቱ ሊዘክረው ሰማእታቱን ሊያስታውስ ይገባል። ዘንድሮ ለማስታወስ ያህል 42ኛውን አመት የካራማራ ድል በዓል ጀግኖቻችንን ለማስታወስ ተሰባስበን ሻማ አብርተን አክብረናል፤የኖርነውም ያለፍነውም ለኢትዮጵያ ስንል ነው›› ሲሉ ሜ/ጀነራሉ ገልፀዋል።

ጀነራሎቹ ከም/ጠ/ሚር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት ከካራማራ ድል ብሄራዊ በዓል ሆኖ መከበር ጋር በተያያዘ ሌሎች ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን ይሄንንም በጽሁፍ እንዳቀረቡ ገልጸው ከዚህ ውስጥ የጡረታ ጉዳይ፤ የቀድሞው ሰራዊት ማሕበር ጽ/ቤትና ፈቃድ ያላገኘ መሆኑ፤ የጀግኖች አምባ ጉዳይ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።

‹‹ም/ጠ/ሚር ደመቀ መኮንን በደምብ አዳም ጠውናል። ተቀብለውናል። ወዲያው የሚሆን ነገር የለም። አጥንተው መልስ ይሰጡናል ብለን እናምናለን። በጽሁፍ ሰጥተናቸዋል። በቃል አስረድተናል።በደምብ ተረድተዋል።ይበልጥ ጉዳያችን የሚገናኘው ከመከላከያ ሚኒስቴር ሲሆን ከመከላከያ ሚኒስትሯ ጋር ቀጠሮ ተይዞልን ወደፊት እንቀርባለን።››

Filed in: Amharic