>
5:13 pm - Thursday April 19, 8959

ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከገደል አፋፍ ቢመልሱንም አንዳንድ መስተካክሎች አሁንም ይቀራሉ። (ኤፍሬም የማነብርሃን)

ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከገደል አፋፍ ቢመልሱንም አንዳንድ መስተካክሎች አሁንም ይቀራሉ።

 

ኤፍሬም የማነብርሃን

 

ላንድ ሁለት ሶስት ሳምንታት ያህል የሥራ ባልደረባዎ ኦቦ ለማ መገርሳ፣ እርሶው የሚመሩት ፓርቲ ኦዴፓ፤ በቀጥታ ሊገስጹ የሚፈሯቸው ጃዋር መሐመድና፤ እንዲሁም ቅጥ ያጡ ጥቂት ጽንፈኛ “የኦሮሞ ልሂቃን” በሚያስተዛዝብ ሁኔታ አዲስ አበባን የምትጨምር ፊንፊኔ የኦሮሞ ናት” በማለት ፊን-ፊን እያሉ ሲያቀነቅኑ ከረሙ። ሕዝቡም እርስዎን ስለወደድዎትና ስላከበሮት ቢያንስ ከርሶ መልካም ለመስማት ጆሮዎን ሰብቆ ሲጥብቅ ይባስ ብለው እርሶዎም ተደምረው (ተቀንሰው ልበል?) ብዙ የማይገቡ ንግግሮችን ስላስደመጡትና አይኖ ላፈር ማለት መጀመሩን ስለተገነዘቡ ነው መሰል፣ ትላንት በቢሮዎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሕዝቡን ትንሽ ተንፈስ በረድ እንዲል አድርገውታል። ምንም የማይሳነው አምላክ ይመስገን። ለወደፊቱም ሕዝቡ ከዚህ ልምድ ትምሕርት በመቅሰም “መሪህን እመን ተከተለው ግን ሳትዘናጋ ተቆጣጠረው (trust but verify)” በሚለው መርሕ እየተመራ የለውጡን ጉዞ ከርሶ ጎን በመቆም ይጓዛል ብዬ ገምታለሁ፤ ቢያንስ ሌላ ዱብ እዳ እስከሚሰማ ድረስ። ነገር ግን አንዳንድ በጊዜም እጥረት ወይም መዘንጋት ያላነሷቸውና መነሳት ግን የሚገባቸውን ነገሮችን ማንሳት እፈልጋለሁ።

በመጀመርያ መቼም ያገር መሪ ስለሆኑ፣ እስክንድር ነጋን እግሩ ላይ ወድቀው ይቅርታ ይጠይቁት አልልም። ነገር ግን በንግግሮ በቀታም ባይሆን መንፈሱ “በማንኛውም ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር መነጋገር መወያየት ይቻላል” በሆነ አነጋገር ባሉት መሰረት እስክንድር ነጋን በቢሮዎ ጠርተው የሕዝቡን ብሶት፤ ፍርሓትና ጭንቀት ይጠይቁታል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን አሁንም የሚቀረው ነገር እስክንድር ደግሞ ደጋግሞ፣ የባላደራው ምክር ቤት ሥራው የኦቦ ታከለ ኡማን የማስተዳደር ሥልጣን የመሻማት ፍላጎት እንዳልሆነና ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ኦቦ ታከለ ሕዝቡን ሳያማክር መወሰን እንደማይችል ለማሳሰብ ብቻ አላማ እንዳለው ቢናገርም፣ ይሕንን ግልጽ አባባሉን እንዳልሰማ ሆነው ታከለ ኡማ “ሥልጣኔን ሊነጥቁኝ ነው” ብሎ ስላለ ብቻ በጭፍን መደገፎና በነእስክንድር ላይ ጦርነት ማወጅዎ ዋና መሰረታዊ የሆነ የዲሞክራሲን ሀሳብ ወይ እንዳልገባዎት፤ ወይም አመቺ ባለመሆኑ ወደጎን እንደተውት ሊሰማዎ ይገባል።

ያስታውሱ እንደሆነ ፕሬዝደንት ኦባማ እንደተመረጠ አክራሪ ሪፑብሊካኖች ቲፓርቲ (Tea Party) የሚል ቡድን አቋቁመው ኦባማን ታግለውት ነበር። ኦባማ ግን ሕጋዊ አይደላችሁም ሥልጣኔን ለትነጥቁኝ አሲራችኋል አላለም። ኦባማም ሆነ እስክንድር በአንድ የዲሞክራሲ አገር የአገሩ ዜጎች ምንም መሳሪያ ሳያነሱ የመሰባሰብ መብታቸውን (Right of Association) በሰላማዊ መንገድ ተጠቅመው በመደራጀት የሕዝብ ዘብ ጠባቂ (Public or Citizens’ Watchdog) የማቋቋም መብት እንዳላቸው ያውቃሉ። አሁን እውን እስክንድር ነጋ የከተማ ሽብርና ከበባ (Insurrection) ይፈጥርና ታከለ ኡማን ከሥልጣን ያባርረዋል ብለው ፈርተው ነው ያን ያሕል የጦር አዋጅ ያወጁት? እስክንድር መሰረታዊ መብቱን ተጠቅሞ ነው ይህን ያደረገው፤ ዓላማውም እርሶ እንዳስቀመጡት አይደለም። ከጥቂት ወራት በፊትስ የአዲስ አበባ ኦሮሞ ወጣቶች ማኅበር ሲያቋቁሙና ፊንፊኔን የኦሮሞ እናደርጋታለን አይነት ትርከት ሲያውጁ ምነው ዝም አሉ? በየከትማውስ ካዲስ አበባ ውጭ ሌላ አናስገባም ብለው መሳሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ጠብደል ጎረምሶችን ምን ብለው ያውቃሉ? አሁንም ቢሆን እስክንድርን እና ሌሎች የአዲስ አበባ ዜጎችን ከሕዝብ መሀል የሚያምነውን አስመርጠው ያቋቋሙት የአዲስ አበባ ሀሳብ አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ይጠበቅቦታል። ያኔ እውነትም የሕዝብን ልብ ትርታ ያዳምጣሉ ያስብሎታል። የተናገሩትም እውነት ከልባቸው ነው ያሰኞታል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ስላለው ኦሮሞና “የኦሮሞን በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ጥቅምም” እንዲህ በቀላሉ ሊያመልጡም አይገባም። በአዲስ አበባ ዙሪያ ኢንዱስትሪ ቢገነቡና በዚሕ ሳቢያ ቆሻሻ ቢጠራቀም፤ ከድንጋይና አፈር ቁፋሮ ሳቢያ የኦሮሞ አርሶ አደር መሬት ቢሸረሸር፤ ከአዲስ አበባ የሚወጡ ተስሽከርካሪዎችም የኦሮሞ አርሶ አደሩን ንጹሕ አየር የሚበክሉ ቢሆንም፤ የዚያን አካባቢ ሕዝብ ጥቅም ጉዳይ በጣም ያጋነኑ ይመስላል። በዚህም ሳቢያ ምንም እንኳን አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ መሆኗን ቢያምኑም፣ የከተማዋን አስተዳደር አላግባብ በሆኑ ጥያቄዎች ጋጋታ ቀላል ወደማይባል እሰጥ አገባ ውስጥ እንዲገባ እያዘጋጁት መሆኑንንም አይርሱ። ልክ በአዶላ እንደተከሰተው ዓይነት አደጋ እንዳይደርስ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ባለቤት የአካባቢውን ሕዝብና አየሩን አፈሩን ሁሉ ከሥራው ሳቢያ ከሚመጡ አደጋዎች መከላከል (environmental protection) ይጠበቅበታል። የፌደራል መንግስቱም በክልሎች መሀል ባሉ ጉዳዮች፣ ወሰን ዘለል በሆኑ ኩባንያዎችና ክልል አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ፣ ባጠቃላይ ክልል ዘለል (Interstate) በሆኑ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት ስላለው፣ ጉዳዩ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ “ልዩ ግዴታ” መጫንም ሆነ ለኦሮሞ መንግስት “ልዩ ጥቅም” ፈጣሪ መሆን አግባብ አይደለም። አዲሳበባ የፌደራል ከተማ ስለሆነችና የፌደራል ታክስ ሰብሳቢው የፌደራል መንገስት ስለሆን ለInterstate ጉዳዮች ፌደራሉ መንግስት ነው መጠየቅ ያለበት። የፌደራል በጀቱ ይሕንን ማካተት ይኖርበታል። ታዲያ ለምኑ ነው የፌደራሉ መቀመጫ ነች መባሉ?  አለዚያማ ቀጥሎ ካዲሳበባ ባጀት የተወሰነው ለኦሮሚያ ይሰጥ የሚላ ሊመጣ ነው። በአካባቢው የሚሰሩ ሃብታም ነጋዴዎችም ከየዙሪያ ከተሞች ከንቲባዎች ጋር ተገቢውን environmental protection ስምምነት ማድረግ ይገባቸዋል። ስለዚህ ኦሮሞ በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ጥቅም የሚለው ቅጥል አባባል ከጭቅጭቅ ፈጣሪነት በቀር ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ሊወገድ ይገባል።

የኮዬ ፈጬም ጉዳይ በአስተማማኝና በማያወላዳ መልኩ በንጹሕ የሕግና ውል መስፈርቶች መተግበር የሚገባውን ጉዳይ የልመናና የማባበል አካሄድ ኢየሄዱበት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርቦታል።  ይህ ደግሞ ብሎ ብሎ ለተመሳሳይ የወደፊት የማያልቅ ውጣ ውረድና የሕግ ጥሰት ይዳርጋል እንጂ ለጉዳዩ መፍትሄን አያመጣም።  ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የተፈረሙ ውሎች ሕጋዊ አፈጻጸም እንዲያገኙና መንግስትም በተዋዋይ ወገኖች (contracting parties) መሃከል በሙሉ ፈቃደኝነት የተፈረሙ ውሎችን በሕግ የማስፈጸም ግዴታ አለበት።  ይህንን ውል እንዳይፈጸም ተቃራኒ ድርጊት በሚፈጽሙ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ላይ የሕጉን ሙሉ ኅይል (the coercive power of the state) ተግባራዊ ማድረግም ይጠበቅበታል።  በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቅሱ ወጣቶችን ወደ ቂሊንጦ አስርቤት የወረወረ መንግስት፤ በዜጎች አንጡራ የገንዘብ ቅይይር የተፈጸሙ ሕጋዊ ውሎች እንዳይተገበሩ የሚያደርጉ ወጣቶችና ዋና አስተባባሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ወገቤን ካለ ከጀርባው ያለው ዓላማ አድልዎና ዘረኝነት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው።  ስለዚህ በአስቸኳይ ዕጣ የወጣላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ልክ በአሜሪካ ግዛት አላባማ ላይ የነጭ ዘረኞች ጥቁር አሜሪካውያን ተማሪዎችን ወደ ትምሕርት ቤት አላስገባም ሲሉ የአሜሪካ መንግስት የፌደራል ኃይሉን ተጠቅሞ ለጥቁር አሜሪካውያን ተማሪዎች ዘብና ጥበቃ እንደቆመ ሁሉ፤ የጠ/ሚ አቢይም የፌደራል መንግስት ማንኛውንም ኅይል ተጥቅሞ ባስቸኳይ ይህንን አሳፋሪ ስራ ላንዴም ለዘላለምም ማስቆም ይጠበቅበታል። ለነዋሪዎችም አደጋው እስከሚቆም የ24 ሰዓት ጥበቃ ሊያደርግላቸውና ወንጀለኞች ላይም እርምጃ ሊወስድ  ይገባል።

በመጨረሻም እውነት ነው ብሔረተኛ ነኝ፤ ብሔሬም ኢትዮጵያዊ ነው!! በአዲስ ወግ ሰብሰባ ላይ ኢትዮጵያዊ ብሔር ብሎ ነገር የለም ያሉትን አባባሎን ገና በሰፊው ቀስ እያሉም ቢሆን ማስተባበል ይጠበቅቦታል። የእርስዎን ትውልድ ያሳደገው መለስ ምን ብሎ እንዳስተማረ ይገባናል። “ አንድ መታወቂያ ሊያወጣ የሚጠይቅ ሰው ኢትዮጵያዊ ነኝ ካለ መታወቂያው ላይ ‘አማራ’ ብለህ ሙላው” ብሎ በማስተማር ካድሬዎችን ሁሉ ኮትኩቶ እንዳሳደገና ያንን ትውልድ ጠባብነትን እንዳስተማረው እናውቃለን። በዚህም ሳብያ “ኢትዮጵያዊነት” እንደርሶ ካንዳንድ የዘውጌ ሰፈርና መንደር ለመጣ አንዳንድ የዚህ ትውልድ አባል (ሁሉን አይጨምርም) ስውር ሊሆን ይችላል። አኛ ግን እንሎታለን፤ መለስ ዜናዊ ከ24 ዓመት በፊት ጠፍጥፎ የሰራውን “አማራ ክልል” ተብሎ የሚታወቀውን አንዱንም ቦታ እኛም፣ አባቶቻችንና እናቶቻችንም፣ አያቶቻችን ጭምር አይተውት የማያውቁት አገር መሆኑን ከልባችን እንነግሮታለን። እርግጥ በከተሞች ስላደግንና አማርኛ መግባቢያ ቋንቋ ስለሆነ የምናውቀው አማርኛን ነው፤ የምንሰማው፣ የምንጽፈው፣ የምናስበው፣ ወዘተ በአማርኛ ነው። ምን እናድርግ። ነገር ግን እውነት እሎታለሁ “አማራ ነን” ብለን ግን አስበን አናውቅም። ከጎንደር የመጣውን ጎንደሬ፤ ከጎጃም የመጣውን ጎጃሜ፤ ከውሎ የመጣውን ወሎዬ፤ ከመንዝ የመጣውን መንዜ፤ ወዘተ ብለን፣ ራሳችንን ግን ዘርህ ምንድነው ስንባል ከልባችን “ኢትዮጵያዊ” ብለን ነው የኖርነው። ገና ለገና የነመለሰን አጥፊ ትርከት ተከትለው አንድ ሰው ወዶ ፈቅዶ የሚገልጸውን ማንነቱን አልቀበልህም ባይሉት ይሻላል። እርሶስ ትላንት ከ24 ዓመታት በፊት መለስ ዜናው ጠፍጥፎና በምን መሰረት እንደተሰራ ለአጥኚ ግራ የሚያጋባ “ኦሮሞ” የሚል ክልል ሰጥቶት በእርሱ ተኩራርተው “ኦሮሞ ነኝ” ይሉ የለ? እኛስ ከአጼ ቴውድሮስና ከዚያም በፊት ስትገነባ የነበረች ለሁሉም ታስባ የተሰራች ቢያንስ እስከ 500 ዓመታት ዕድሜ ያላትና በነአጼ ሚኒልክና አጼ ኃይለሥላሴ የተስፋፋች አገር ውስጥ የተፈጠርነው “ኢትዮጵያዊ ነው ዘሬ” ብንል ለርስዎ ፋይዳው ምንድነው? ለምን ያስከፋዎታል? የኔን ውሸት የርሶውን ግን እውነት ያደረገው ማነው? አዎ ለዘረኞች መጤ፤ ባዕድ፤ ሰፋሪ፣ ወዘተ ብሎ ለመለየትና የጥላቻ ግንብ ለመገንባትና የኔ የኔ ብቻ ለማለት፣ ለይቶም ለማጥቃት፣ ለመዝረፍ፣ ለማጥፋት ይመቸዋል። ሌላ ከጀርባው ግን የርሶ አባባል ምንም መልካም (positive) ዓላማ የለውም።

ያለፈውን ስሕተት እንደማይደግሙብንና፣ መስመር ለለቀቁ ጽንፈኛ የኦሮሞ ዘውጌ አባላት ለወደፊቱ ፊቶን ባያዞሩባቸውም ግን ደጃፎቾን በርግደው እንደማይከፍቱላችው እንጠብቃለን። ከዚያ ውጭ ግን በኢትዮጵያ ላይ አርማጌዶን እንዲመጣ መንገድ ማበጀት እንደሆነ ይገንዘቡልን።

አምላክ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይጠብቅ!! ከአርማጌዶንም ይሰውራት! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ኤፍሬም የማነብርሐን

Filed in: Amharic