>

የጎሳ ፖለቲካ፣ አዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የጎሳ ፖለቲካ፣ አዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም!
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
ኦነጋውያኑ የለማ ቡድን አዲስ አበባን ኦሮሚያ ለሚሉት ክልላቸው ማድረግ የማይችሉ መሆናቸውን ሲያውቁ እንደገና “ሕገመንግሥታዊ የሆነው ልዩ ጥቅምና ልዩ መብታችን!” የሚል ነገር አምጥተዋል፡፡
ይሄ የልዩ መብትና ጥቅም ነገር እንዴት እንደሚተረጎም ትናንት ዐቢይ ሲናገር “አዲስ አበባ ውኃ የምታገኘው ከገፈርሳና ለገዳዲ ስለሆነ በመነጋገር ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ በሚሰጠው በዚህ አገልግሎት ምን ዓይነት ጥቅም ማግኘት እንደሚገባ የመሳሰሉትን ለማለት ነው እንጅ አንድ ኦሮሞ ከአንድ ጉራጌ የተለየ ጥቅም ያገኛል ማለት አይደለም!” ብሎ ለማለባበስ ወይም ለማድበስበስ ሞክሯል፡፡ ልዩ መብት ስለሚለው ነገር ግን ምንም ሳይናገር አልፎታል፡፡ አሁን ላይ እሱ ያድበሰበሰውንና ግልጥ አድርጎ ሊናገር ያልፈለገውን ነገር እኛ ገላልጠን “ይሄ ማለት ይሄ ነው!” ማለት የሚገባን አይመስለኝም፡፡ ግልጽ ሆነው ሲመጡ ያኔ እንገናኛለን!!!
ለጊዜው ግን የክልል ባለቤትነት ለባለክልሎቹ ምን ዓይነት መብት እንዳሰጠና ዜጎችን ለአንደኛና ሁለተኛ ዜግነት ደረጃ እንደዳረገ አሳምሮ ለሚያውቀውና ሲሰቃይበት ለኖረው ኢትዮጵያዊ “…አንድ ኦሮሞና ከአንድ ጉራጌ የተለየ ጥቅም ያገኛል ማለት አይደለም!” ብሎ በመናገር ለማታለል መሞከር ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዐቢይ ልዩ መብትና ልዩ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሕዝቡ የማይገባው ከመሰለው ሕዝብን አለቅጥ መናቁን የሚያሳይ ነው የሚሆነው፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ወያኔ ለስሙ የአማራ ክልል ከሚለው በስተቀር ከመላ ሀገሪቱ “ክልልህ አይደለም!” እየተባሉ ከሥራ ዕድልና ቅጥር እስከ መንግሥታዊ አገልግሎትና የዜግነት መብት መነፈግ ድረስ አለፍ ሲልም ሀብት ንብረታቸውን እየተነጠቁ ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ለ28 ዓመታት አሳራቸውን ሲበሉ ኖረውበታልና ነው፡፡
ለጊዜው አቶ ዐቢይ አዲስ አበባ “የፊንፊኔ ልዩ ዞን” ሲል ከጠራው አካባቢ “ታገኛለች!” ያለውን በምሳሌነት የጠቀሰውን የለገዳዲንና የገፈርሳን ውኃ ጉዳይ ተንተን አድርገን ብናየው ጥሩ ይመስለኛል፡፡
እነ ዐቢይ “አዲስ አበባ የምትጠጣውን ውኃ በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ስለሆነ ልዩ ጥቅምና መብት ለኦሮሚያ መስጠት ወይም መክፈል አለባት!” ብለዋል፡፡ መቸስ ዓለም ይሄንን ጉድ ቢሰማ ስቆ የሚያባራ አይመስለኝም፡፡
እነ ዐቢይ ይሄንን ጥያቄ የምር የሚገፉበት ከሆነ “እናንተ ማን ስለሆናቹህ ነው ባለ ልዩ መብትና ጥቅም የምትሆኑት?  ከመቸ ጊዜ ጀምሮ ተቆጥሮ ወይም ታስቦ ነው የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሰፍራቹህ ያላቹህበት መሬት ባለቤት ልትሆኑ የቻላቹህት ወይም ባለቤት እንደሆናቹህ እንድትቆጠሩ የምትፈልጉት? ይሄ የእኛ ነው የምትሉት መሬት ከእናንተ በፊት የሌላ ያልነበረ ለመሆኑ በበቂ ማስረጃ ማስደገፍ ትችላላቹህ ወይ? በማስረጃ ማስደገፍ ካልቻላቹህና እናንተ እዚህ መሬት ላይ ከመስፈራቹህ በፊት መሬቱ የሌላ ከነበረስ አሁን ላይ መሬቱን የእኛ ነው ለማለት የሚያስችላቹህን መብት ማግኘት ትችላላቹህ ወይ?” ወዘተረፈ. የሚሉ ጥያቄዎች ሊሰነዘሩባቸው እንደሚችልና ጥያቄዎቹንም ያለ አንዳች ማድበስበስና ዕብለት በአግባቡ ለመመለስ እንደሚገደዱ ሊያውቁት ይገባል!!!
አንድ አካል በሚገባው ወይም በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ቢያነሣ ምንም ላይመስለን ይችላል፡፡ “የኔ ነው!” ብሎ ለማለት የሚያበቃ የታሪክም ይሁን የሕግ የምንም መብት ሳይኖረውና የራሱ አለመሆኑንም አሳምሮ እያወቀ ግን “የኔ ነው!” ብሎ የሚደርቅ ከሆነ ይሄ ድርቅና የሞራል ዝቅጠት ከመሆንም አልፎ አሳፋሪ ሌብነት፣ ውንብድናና ዝርፊያ ነው የሚሆነው፡፡
በእርግጥ እነ ዐቢይን ወይም ኦነጋውያኑን ይሄ ሁሉ ነገር ግድ ላይሰጣቸው ይችላል፡፡ ባይሰጣቸውም ነው እውነቱን እያወቁት መድረቃቸው፡፡ ማወቅ የሚገባቸው ቁም ነገር ቢኖር ግን እነሱ በዚህ ደረጃ ዘቅጠው ዓይናቸውን በጨው አጥበው ሲደርቁ ሌላውም በመጡበት መንገድ ለማስተናገድ የሚገደድ መሆኑን ነው!!!
ከዚህም ባሻገር እነ ዐቢይ “አዲስ አበባ እንደ ውኃና የመሳሰሉት የተፈጥሮ ሀብት ከኦሮሚያ ታገኛለችና ለዚህም ለኦሮሚያ መክፈል አለባት!” የሚለው ጥያቄያቹህ ፈጽሞ አግባብነት የሌለው ጥያቄ እንደሆነ የሚያረጋግጠው ይሄ ማለት የአማራ ክልል የምትሉት ትግራይ ክልል ከምትሉት ለተከዜ ውኃ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ከምትሉት ለዐባይ፣ ለበለስና ለደንከር ውኃ፣ የአፋር ክልል ከምትሉት ለሚሌ፣ ለቦርከናና ለቆሊና ውኃ ይክፈል፡፡ ኦሮሚያ ክልል የምትሉት ደግሞ አፋር ክልል ከምትሉት ለአዋሽ፣ ሱማሌ ክልል ከምትሉት ለዋቢሸበሌ ውኃ ይክፈል ማለት ስለሆነና በአንድ ሀገር ሕዝብ መሃል እንዲህ ዓይነት ነገር መተሳሰብ አግባብነት ስለሌለውና አደገኛም ስለሆነ ነው፡፡
ምክንያቱም እንኳን እኛ ለእኛ ይቅርና እኛ ለባዕዳኑ ለሱዳንና ለግብጽ እንኳ አላስከፈልንምና ነው፡፡ በመሆኑም ይሄ ክልል የሚባልና “አዲስ አበባ የእኛ ናት!” ወይም “ልዩ ጥቅም ልዩ መብት!” ምንንትስ የሚባል የጎሳ ፌዴራሊዝም (ራስ ገዝ) ጣጣ ሀገር ቢያደኸይ፣ ቢያቆረቁዝ፣ ቢያብጥ እንጅ ነጻ ዝውውርን፣ ነጻ ንግድን፣ ነጻ የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) ፍሰትን ወይም እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉልና የሚኮደኩድ በመሆኑ ማሰብ የምትችሉ ከሆነ ያለ ኢትዮጵያ በስተቀር ሌላ ሀገር የማይከተለውን ይሄንን እጅግ ኋላ ቀር የጎሳ ፖለቲካንና የጎሳ ፌዴራሊዝምን እንደሌሎች ሀገራት ሁሉ ከፖለቲካው (ከእምነተ አሥተዳደሩ) አስወግዳቹህ ወይም በሕግ ከልክላቹህ ድንገት በዱብዕዳ እንዳመጣቹህትና እንደጫናቹህብን አድርጋቹህ አሁንም ድንገት ከዚህች ሀገር አጥፉልን አስወግዱልን???
የልባቸውን በልብ አድርገው “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፣ ሉዓላዊ ሀገር እንጅ ሉዓላዊ ክልል የለም፣ ከጎጥ አስተሳሰብ ውጡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕኩል ነው፣ አንድነት ይሻለናል መከፋፈል ይቅር….!” ምንትስ ቅብርጥስ እያሉ ሕዝብን ሲያጃጅሉ የነበሩት ዐቢይና ለማ አሜሪካ ጉብኝት ላይ በነበሩ ጊዜ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እነ ዐቢይ ለሚሉት ለዚህ ነገር ቁርጠኛና ታማኝ ከሆኑ ሀገሪቱን ከከፋፋዩና የአንድነት ጠንቅ ከሆነው ከጎሳ ፖለቲካና ከጎሳ ፌዴራሊዝም እንዲያወጧት በጠየቋቸው ጊዜ ዐቢይ ሲመልስ “አንድ ትውልድ እንዳለ በጎሳ ፖለቲካ ከመመረዝም በላይ እከሌ ጠላትህ ነው እየተባለ ያደገ ስለሆነ ከዚህ ነገር በአንዴ ለመውጣት መሞከር ሊከብድ ስለሚችል የቤት ሥራውን ይዘን ቀስበቀስ በምንሠራው ሥራ እንድንወጣ ብናደርግ ነው የተሻለ የሚሆነው!” የሚል የብልጠት መልስ እንደመለሰ ይታወሳል፡፡
ዐቢይ ሆይ! ስትጭኑብን ጊዜ ያልጠየቀውን ነገር አንሡ አስወግዱ ስትባሉ “ጊዜ ይጠይቃል አዲሱ ትውልድ በዚህ ተመርዞ የወጣ ነው፣ ትውልዱን ከጎጠኝነት አስተሳሰብ ለማላቀቅ ጊዜ ይጠይቃል!” ምንንትስ ካላቹህ ጎሰኝነት ተጨማሪ ጊዜ አግኝቶ እንዳይነቀል ሆኖ ስር እንዲሰድ ከመፈለግ ካልሆነ በስተቀር ወይም ወደሀገር ውስጥ የገቡት ጽንፈኛ ጎሰኞች እንዳይነቀል አድርገው እንዲተክሉት ጊዜ እንዲያገኙ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር አንድን ያልተፈለገን ተክል ለመንቀል ከችግኝነት ዘመኑ ይልቅ ፈጽሞ የዛፍነት ዘመኑ ሊቀል አይችልምና ምላሻቹህ “ሆድ ሲያውቅ ድሮ ማታ!” እንዲሉ ሸፍጥ ያዘለ መሆኑን ማንም ሊገነዘበው የሚችለው ነውና ማንንም ልታታልሉ አትችሉም!!!
በጀርመን የናዚ ደጋፊዎች የሌሉ ስለሆነና ተደራጅተው የመንቀሳቀስ ፍላጎት ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም በሕግ የተከለከሉት፡፡ አደገኛና ለሀገር ለሕዝብ እንደማይጠቅም ስለታመነበት እንጅ፡፡ በጣሊያንም የፋሽዝምና የሞሶሎኒ ደጋፊዎች ስለሌሉና ተደራጅተው መንቀሳቀስም የሚፈልጉ ስለሌሉ አይደለም በሕግ የተከለከሉት፡፡ ለሕዝብም ለሀገርም እንደማይጠቅም ስለታመነበት እንጅ፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በዓለማችን እንደማይጠቅምና አደገኛ መሆኑም ታውቆ የትኛውም ሀገር የማይከተለውን የጎሳ ፖለቲካ እና መገለጫው የጎሳ ፌዴራሊዝም ለሀገርና ለሕዝቧ እንደማይጠቅም ከገባቹህ እንደሌሎቹ ሀገሮች ሁሉ በሕግ ከልክሎ የፖለቲካ ሜዳውን እንደ የሠለጠነው ዓለም የሠለጠነ ወይም ዘመናዊና ዘር ላይ ሳይሆን ሐሳብ ላይ ብቻ የተመሠረተ በማድረግ፣ ዜጎች በዕኩልነት የሚታዩበት፣ በብቃት ችሎታቸው ብቻ የሚመዘኑበትና የሚስተናገዱበት፣ ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያለ አንዳች አድሎና ልዩነት የሁሉም ዜጋ የሆነበት እንዲሆን አድርጉ???
ይሄንን የምለው ትናንትና ጎሳ ተኮር ፓርቲ መመሥረትን እንደ መብትና ችግር እንደሌለው ቆጥረው ከጎሳ ፓርቲዎች ጋር አንድ ላይ እየተሰለፉና እየተጎዳኙ በመሥራት ጠንቀኛውንና ኋላቀሩን የጎሳ ፓርቲዎችን ወይም ፖለቲካዊ አደረጃጀትን ሲያበረታቱ እንደኖሩትና ድንገት ዛሬ ተነሥተው “የዜግነት ፖለቲካ ብቻ!” እንዳሉት እንደ ዘገምተኛ ፖለቲከኞቻችን ድንገት ዛሬ ተነሥቸ ሳይሆን ይሄንን የምለው ገና ድሮ ከዓመታት በፊት ጀምሬ የጎሳ ፖለቲካ የትም ሀገር እንደሌለና እንደ እኛ ዓይነት ውጥንቅጡ የወጣና የተሳከረ የጎሳ ፌዴራሊዝምም እንዲሁ የትም ሀገር እንደሌለ፣ ፀረ ሰብአዊ መብት፣ ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ፣ እጅግ ኋላቀርና አደገኛ መሆኑን በዚህም ምክንያት በሠለጠነው ዓለም ጨርሶ የሌለ መሆኑን በርካታ ሰፋፊና ጥልቅ ትንታኔዎችን በመስጠት እንደሠለጠነው ዓለም መወገድ ወይም በሕግ መከልከል እንዳለበት ስሞግት ስለፍፍ መኖሬ ይታወቃል፡፡ ይሄ እስካልሆነ ድረስ ይህችን ሀገር መቀመቅ ለማውረድ ካልሆነ በስተቀር ለመታደግ ልትሠሩ አትችሉም!!!
ይሄ ከጎሳ ፖለቲካ ላለመውጣት የምትሰጡት ተልካሻ ምክንያት ግን መስረቅ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች አሉና ተብሎ ስርቆትን “ወንጀል ነው!” ብሎ መደንገግ አይገባም፣ ሱሰኛ መሆን የሚፈልግ በርካታ ሰው አለና ተብሎ ሱስ አማጭ ነገሮችን መጠቀም “ወንጀል ነው!” ብሎ መደንገግ አይገባም እንደማለት ነው፡፡ ይሄም ደግሞ የመሀይም አመክንዮ ነው፡፡
አንድ ነገር እንደማይጠቅም ከታወቀ ወዲያውኑ ቆራጥ ውሳኔ ወስኖ ያለውን አደጋ ሊገባው እንዲችል አድርጋቹህ ለመረዛቹህት ትውልድ በመግለጥ ከዚያ መውጣት ነው እንጅ አመክንዮአዊ ያልሆነ ሰበብ በመስጠት ጊዜ ለመስጠት መሞከር ውሎ ሲያድር ለሞት የሚዳርግን አገደኛ ሕመም በጊዜ በማከም ማዳን ሲቻል ጊዜ በመስጠት ለሞት እንዲያበቃ የማድረግ ሥራን ነው እየሠራቹህ ያላቹህት፡፡
ይሄንን ተልካሻ ምክንያት ጠቀሳቹህ እንጅ ዋናው ምክንያታቹህ በጎሰኝነት የተመረዛቹህ ስለሆናቹህና ህልውናቹህ ከጎሳ ፖለቲካ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ከጎሳ ፖለቲካ ወጣቹህ ማለት ከባሕር እንደወጣ ዓሣ ሕይዎት አልባ ስለሚያደርጋቹህ ነው ሌላ አይደለም!!! የኢትዮጵያም ሕዝብ ይሄንን ጠንቅቆ ያውቃል!!! ለዚህም ነው “ተዋሕደን የአንድነት ፓርቲ ለመመሥረት ተዘጋጅተናል!” ብላቹህም እንኳ የጎሳ ፌዴራሊዝሙን ግን እንደማትተውትና እንደሚቀጥል የተናገራቹህት፡፡
ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይገባቹሀል??? ሁለት የተለያየ ቋንቋን የሚናገሩ የማይተዋወቁና የማይግባቡ ግለሰቦችን አንድ ሥራ እንዲሠሩ ማስገደድ ማለት ነው፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል??? ውጤታማ ሥራስ ሊሠሩ ይችላሉ??? ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተን ከማብሰል ድንጋይ ቀቅሎ ማብሰል ይቀለዋል፡፡ እናንተን ከስር ነቅሎ ያለማጥፋት ሌላ ምንም መፍትሔ የለም!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ
Filed in: Amharic