>
4:01 am - Monday July 4, 2022

የአፄ ምኒሊክን ቤተ መንግስት በብዙ መገረም ጎብኝተናል - ግርምቴን ላጋራችሁ!!! (ኤልያስ መሰረት ታዬ)


የአፄ ምኒሊክን ቤተ መንግስት በብዙ መገረም ጎብኝተናል – ግርምቴን ላጋራችሁ!!!
ኤልያስ መሰረት ታዬ
ከፍተኛ አዳዲስ ግንባታዎች፣ ከአፄ ምኒሊክ ጀምሮ የነበሩ ህንፃዎች ላይ እየተካሄዱ ያሉ እድሳቶች፣ የጠ/ሚሩ ቢሮን አዳዲስ ገፅታዎችን እንዲሁም በግቢው ውስጥ አዲስ የእንስሳት ፓርክ፣ የህፃናት መጫወቻ፣ ከመሬት በታች ያለ የመኪና መተላለፊያ፣ የቀድሞው ጠ/ሚር መለስ ዜናዊን ቤት ወደ እንግዳ መሪዎች ማደሪያ እየተደረገ ያለ የግንባታ ስራ ወዘተ አይተናል።
ግንባታው ሲያልቅ ዜጎች እና ቱሪስቶች ትኬት እየቆረጡ በመግባት መጎብኘት ይችላሉ ተብሏል።
ግቢው በግምት ወደ 50 ሄክታር ይደርሳል ተብሎ የሚገመት ሲሆን እያንዳንዷ ሜትር ግንባታ ላይ ነች ማለት ማጋነን አይሆንም። እኔን ከደነቁኝ መሀል:
– አፄ ምኒሊክ ግብር ያበሉበት የነበረው ግዙፍ አዳራሽ እንደ አዲስ ታድሷል። ይህንን አዳራሽ ለማያያዝ 8,000 ኪሜ ገደማ የከብት ቆዳ ጥቅም ላይ ውሏል ይባላል (ከአዲስ አበባ ደቡብ አፍሪካ ደርሶ መልስ እንደማለት ነው)። አዳራሹ ጠ/ሚሩ ላሰቡት የአምስት ሚልዮን ብር እራት ፕሮግራም ይውላል ተብሏል። ሰርገኞችም ልክ እንደ ሆቴል አዳራሽ እየተከራዩ መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።
– የቀድሞው ጠ/ሚር መለስ ዜናዊን መኖርያ ቤት ሶስት የሀገር መሪዎችን በአንዴ ማስተናገድ እንዲችል ሆኖ እየተሰራ ነው። እኛ ዛሬ ስንጎበኘው ሶፋ እና አልጋ እየገባለት ነበር።
– በአፄ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት የልኡላን ቤተሰቦች ይኖሩበት የነበረው እና በሁዋላም ግራውንዱ እነዚሁ ቤተሰቦችን እና የአፄውን ሚኒስትሮች ለማሰቃያ ይውል የነበረው ህንፃ ከፍተኛ እድሳት ተደርጎለት እጅግ ትላልቅ ስክሪኖች እና ሳውንድ ሲስተሞች ተገልፀውለት በጊዜው የነበረውን ታሪክ ለጎብኚዎች በዲጂታል መንገድ ለማስጎብኘት ዝግጅቱ ተጠናቋል ተብሏል።
የግቢው አዳዲስ ግንባታ እና ወጪ በ “ወዳጅ ሀገር” እንደተሸፈነ ጠ/ሚሩ በቅርቡ መግለፃቸው ይታወሳል።
አዲሱ ጠ/ሚር ስልጣን ሊይዙ ሰሞን ከግቢው ውስጥ መኪኖች እንደጠፉ ሰምቼ ስለነበር አንዱን የጉብኝቱ አካል የነበረ የፀጥታ አካልን ስለጉዳዩ ስጠይቀው “ልክ ነው! ሁለት መኪኖች ከግቢ ውጪ ተወስደው እና መሬት ውስጥ ተቀብረው በጥቆማ የዛሬ ሁለት ወይም ሶስት ወራት ገደማ በቁፋሮ ተገኝተዋል” አለኝ። የቀድሞው ጠ/ሚር መለስ ተመራጭ የነበረች አረንጓዴ ቅብ ቼቭሮሌት መኪና ግቢ ውስጥ ትታይ ስለነበር “እሷን ጨምሮ?” ስለው “በል በል! ፈጠን ፈጠን እያልክ ጎብኚዎቹን ተቀላቀል” ብሎ ወደፊት መራኝ።
ከዛም ልብ ያልኩት ነገር እጅግ ብዛት ያላቸው የባንግላዴሽ፣ የፓኪስታን፣ የህንድ ወይም የኔፓል ዜጎችን የሚመስሉ ሰዎች በብዛት በግቢው ስራ ላይ እንደነበሩ ነው። ሁኔታው ዱባይ ሲኬድ የሚታዩ ግዙፍ ህንፃዎችን የሚገነቡ ሰዎችን ያስታውሳል። ማታ የጠ/ሚሩን ጋዜጣዊ መግለጫ ጨርሰን ስንወጣ እነዚህ ሰራተኞች በብዛት በአውቶቡስ እየተጫኑ ወደ ሌላ ማደርያ ስፍራ ሲወሰዱ ተመልክቻለሁ።
ሌላው ለአስጎብኝዎቻችን ያነሳሁት አንድ ጥያቄ ነበር። እድሳቱ ሲካሄድ ታሪኩን እንደጠበቀ እንዲካሄድ ምን ጥረት ተደርጓል? የተሰጠኝ መልስ “አቅም በፈቀደ መጠን የታሪክ ድርሳናት፣ ፎቶዎች፣ ስእሎች እንዲሁም የታሪክ አዋቂዎች ግብአት ተወስዷል። ከቀለም አቅም እንኳን እራሱኑ አይነት መልክ ለማምጣት ብዙ ሙከራ ተደርጓል” የሚል ነበር።
ከአስጎብኚዎቹ ሌላ የሰማነው ነገር ከአፄ ምኒሊክ ግዜ ጀምሮ አገልግሎት ላይ የዋለው ግቢው አሁን ለግንባታ እና እድሳት ሲቆፈር የሰው አፅም እንደተገኘ ነው።
ለማጠቃለያ፣ ድሮ ግቢ ውስጥ ከነበሩት ህንፃዎች ውስጥ ወደፊት የማይኖረው (የፈረሰው) ህንፃ የቀድሞው መሪ ፕሬዝደንት መንግስቱ በአንድ ወቅት ወደ ሩስያ ለ20 ቀን ጉብኝት ሲሄዱ የደርግ ቤቶች ግንባታ ግብረ ሀይል 24 ሰአት እየሰራ ያጠናቀቀው ቤት ነው። እንደተነገረን “ህንፃው ከ1983 ወዲህ ምንም ጥቅም ሳይሰጥ ስለቆየ እና ምንም እድሳት ስላልተደረገለት ተጎድቶ ስለነበር እንዲፈርስ ተደርጎ በቦታው ሌላ ስራ እየተሰራበት ነው።”
መልካም ቀን!
Note: ካሜራ ይዞ መግባት ተፈቅዶ ስላልነበር ፎቶዎችን ማስቀረት አልቻልኩም።
Filed in: Amharic