>

"ሃገሬን የገደላት በረካ እውቀት ነው!!!"  (መስከረም አበራ)

“ሃገሬን የገደላት በረካ እውቀት ነው!!!” 
መስከረም አበራ
ከጠ/ሚው ንግግር ውስጥ ያላደናገረኝ ነገር ባይኖርም በጣም የደነቀኝ ግን ከሶማሌ ክልል አምጥተው አዲስ አበባ ስላሰፈሯቸው ኦሮሞዎች ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ነው፨ “ሁሉም ፓርቲ አዴፖም ፣ህወሃትም ፣ደኢህዴንም የሚሰራው የቆመለትን ዘር ከተሜ ለማድረግ ነው፨ ስለዚህ ምንም የሚገርም ነገር የለውም” አሉ ጠ/ሚው፨
በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ማፈናቀሎች የእርስበርስ ግጭቶችና ሌሎች ችግሮች አገዛዙ ወይም ወያኔ/ኢሕአዴግ ለራሱ ርካሽ ፖለቲካዊ ዓላማ እና ጥቅም ሆን ብሎ እንደሚፈጽማቸው እሙን ነው፡፡ ይሄ መሆኑንም ዐቢይ ዛሬ ከጋዜጠኛ ለተጠየቀው ጥያቄ በመለሰው ነውረኛ ምላሽ አረጋግጧል፡፡
ጋዜጠኛው እንዲህ ብሎ ጠየቀ “ሥልጣን በያዙበት በዚህ አንድ ዓመት ከመጋቢት እስከ መጋቢት በተከሰቱ ጉዳዮች ለምሳሌ የጌዲኦን ተፈናቃዮች አያያዝ በተመለከተ ሊሆን ይችላል፣ የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሀገር በማስገባትዎ ሊሆን ይችላል፣ ተከፍተው ወይም አኩርፈው በተቀመጡትን ሊሆን ይችላል በመሳሰሉ ነገሮች ይሄን ባደርግ ኖሮ ወይም ይሄንን ባላደርግ ኖሮ ብለው የሚጸትትዎት ነገር አለ ወይ?” ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ዐቢይ ሲመልስ “ይሄንን ባደርግ ኖሮ የምለው የሚጸጽተኝና የማፍርበት ምንም ነገር የለም!” ሲል አጭርና ግልጽ መልስ ሰጥቷል፡፡
ይታያቹህ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ወይም በዐቢይ አሥተዳደር ዘመን በሕዝብ ላይ በየቦታው ከማፈናቀልና የብዙዎችን ነፍስ ከበላው ከእርስበርስ ግጭት ጀምሮ የአቢያተክርስቲያናት ከካህናትና ምእመናን ጋር መቃጠል ሳይቀር ያልደረሰ ያልተፈጸመ ግፍ የሌለ በሆነበት ሁኔታ ይሄንን ሁሉ ግፍ፣ ጉዳት፣ ጥቃትና አደጋ ያደረሰው ወይም እንዲፈጸም ያደረገው ወያኔ/ኢሕአዴግ ቢሆንም ዐቢይ ይሄንን አምኖ “እንዲህ አድርገናልና በዚህም ይጸጽተኛል አፍርበታለሁም!” ይላል ተብሎ ባይጠበቅም ይሄ ቢቀር እንኳ “እነኝህ ሁሉ ጉዳቶችና አደጋዎች በሕዝብ ላይ ሊደርሱ የቻሉት መንግሥቴ ሕዝቡን ከእነኝህ አደጋዎች ግጭቶችና ጉዳቶች መጠበቅ ባለመቻሉ ነውና በዚህ በጣም ሐዘን ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌም በለገጣፎ እኔ ሳልሰማና ሳላውቅ ያ ሁሉ የነዋሪዎች ቤት ፈርሶ ዜጎች ሜዳላይ እንዲወድቁ በመደረጉም የመንግሥት ሥራ የፌዴራሉንም ሆነ የፓርቲየ የኦዴፓን መዋቅርና የዕዝ ሠንሰለቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሠራ በማድረግ ሥራዬን በአግባቡ ብሠራ ኖሮ ያንን ሁሉ ቤት ከመፍረስና ሕፃናትና እናቶችም ሜዳ ላይ ከመበተን መታደግ እችል ስለነበረ ይሄንን ባለማድረጌ በዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳት፣ እንግልት፣ አደጋና ኪሳራ በእጅጉ ይጸጽተኛል አፍርበታለሁም!” ማለት ሲኖርበት እንዲህ ማለት ያልቻለውና ያልጸጸተው ከላይ እንደገለጽኩላቹህ ማፈናቀሎቹ ግጭቶቹና ጥቃቶቹ ሆን ተብሎ ለርካሽ ፖለቲካዊ ዓላማና ጥቅም ተብሎ እንዲፈጸሙ የተደረጉ ስለሆነ ነው፡፡
ያ ባይሆን ኖሮ ሌላው ሁሉ ቢቀር እንደ ሰው እንኳ “ለእኔ ድጋፍ ለመስጠት ብለው መስቀል አደባባይ ላይ ወጥተው በነበሩበት ሰዓት የቀን ጅቦች ወይም የለውጥ አደናቃፊዎች ባደረሱት የእጅ የቦምብ (ፈንጅ) ጥቃት የሞቱና የቆሰሉ፣ የአካል መጉደል ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ጉዳይ ጥቃቱ ሊደርስ የቻለው ተገቢው ጥበቃና ጥንቃቄ ባለመደረጉ ነውና እንደመሪ ተገቢው ጥበቃና ጥንቃቄ እንዲደረግ ማድረግ ባለመቻሌ ነውና አደጋው ሊደርስ የቻለው ይሄ በጣም ይጸጽተኛል ያሳፍረኛልም!” ይል ነበረ፡፡
ዐቢይ ይሄንን ሊል ያልቻለው በዓመት ውስጥ ዐቢይ ሥልጣን ከያዘ ወዲህም ሆነ በፊት ይሄ በሕዝብ ላይ የተፈጸመው ግፍ ሁሉ ሆን ተብሎ ለወያኔ/ኢሕአዴግ ርካሽ ፖለቲካዊ ዓላማና ጥቅም ሲባል የተፈጸመ በመሆኑ አጭርና ግልጽ አድርጎ እንደተናገረው በሥልጣን ዘመኑ በሆነው ሁሉ ነገር የሚጸጽተውና የሚያፍርበት ነገር ምንም የሌለ ሊሆን ችሏል፡፡ እጅግ አያሳዝንም???
ጠ/ሚው ይህንም ሌላም ብለው አበቃሁ ሲሉ  “ወይ ሃገሬ መከረኛዋ” ማለቴ አልቀረም!
ቀጥሎ ትዝ ያለኝ “ሃገሬን የገደላት በረካ እውቀት ነው ያለው የ”ምን ልታዘዝ?” ድራማ ደራሲ ነው፨ እሱን ደራሲ የምታገኙት ወገኖች ባለህበት ሰላም ሁን በሉልኝ፨በሳምንት አንድ ጊዜ ሁሉንም እንደሚገባው ይነግርልኛል፨ ከበረከት  በላይነህ በተጨማሪ አንድ ሌላ እንዲህ ያለ ሰው በማየቴም ሃገሪቱ ከቆየች በጥበቡ ቀኩል ተስፋ የሚደረግበት አንዳንድ ሰው አይጠፋም ለካ አስብሎኛል፨
በበረካ እውቀት መሰረት ገጠሬን ከተሜ ማድረጊያው መንገድ የመሬት ፖሊሲውን አሻሽሎ የተማረ ዘመናዊ አርሶ አደር መፍጠር ፣ከዛ ኢኮኖሚው ራሱ በጤናማ ተፈጥሯዊ መንገድ  ገጠሩን ከተማ እንዲደያደርግ ማስቻል አይደለም፨ ይልቅስ  አብዲ ኢሌ የሚባል ወፈፌ የሰዎችን ኑሮ እስኪያመሳቅል ጠብቀህ ፣በቆላ ሃገር የኖሩ ሰዎችን ወደ ደጋው የሃገሪቱ ዋና ከተማ አምጥተህ አፍስሰህ ግራ ማጋባት ነው፨ ቅራሪ እውቀት አደገኝነቱ እፍረትን አያሳስብም፨
አቤቱ ህዝብህን ከባለ ቅራሪ እውቀቶች አድን!
Filed in: Amharic