>

እናንተም አበዛችሁት! (ደረጀ  ደስታ)

እናንተም አበዛችሁት!
ደረጀ   ደስታ
ጃዋርና እስክንድር እንነጋገራለን አሉ ተብሎ ሰሚ ተገረመ። ወይ ጉድ! የአማርኛውን ጉድ ማለቴ ነው። እንገዳደላለን ተባብለው ነበር እንዴ? ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና እስክንድር ነጋ ሲገናኙ ምን እሚባባሉ ይመስላችኋል? ኢሳቶቹ ኤርምያስና አበበ ገላው ከውይይታቸው በኋላ ሰይፍ ይማዘዛሉ ብላችሁ ጠብቃችኋል? ዶ/ር አብይ ጦርነት ይሆናል ሲሉ መትረየሳቸውን ደግነው ሲሮጡ የታያችሁ ነገ ተቃቅፈውና ተሳሳቀው ብታዩ የት ትገባላችሁ? ታስረው እንኳ ያሉት ፣ አቶ በረከት ነገ ከእስር ቤት ቢወጡ ከዶ/ር አብይ ጋር ተሳስቀው ሰላምታ እማይለዋወጡ ይመስላችኋል? እውነት ነው አንዳንዶች ለጊዜው ይኮራረፋሉ አጋጣሚ መልሶ እስኪያገናኛቸው ነው። ወዲያው ይታረቃሉ። ባይታረቁም አይጋደሉም። ፖለቲካ ነዋ! ተከታዮቻቸው ግን ሊገዳደሉ ይችላሉ።  ባገራችን እንኳን ሊጋደሉ ተገናኝተው ተደባደቡ የተባባሉ ፖለቲካ መሪዎችን ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?
በዚያ ላይ ደግሞ ጓደኝነት የሚያየው የግል ባህርይ አለ። ብሔርተኛ ሆኖ ጥሩ ደግና ርህሩህ ሰው ሊኖር ይችላል። ኢትዮጵያ ወይ ሞት እያለ ደግሞ ክፉና መሰሪ ሰው ሊኖር ይችላል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነትም ሆነ ብሔርተኝነት ሁለቱም ሀሳቦች ናቸው። ሌሎችን በሚያገዳድሉ ራሳቸው በማይገዳድሉ ሰዎች የሚወጡ ሀሳቦች ሊሆኑ ይችላሉ። በኛ ቤት ግን ፣ ይሄኔ እኮ፣ በዶ/ር አብይ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት እንኳ የተኳረፉ “አስተዋዮች” ይኖሩ ይሆናል። ፖለቲካና የግል ባህርይ ተጽእኖ አይደራረጉም ባይባልም ግንኙነታቸው እኮ የግድ ላይሆን ይችላል።
ሌላው ግን ያው መቸም እንደ አቅሚቲ ጋዜጠኞች አይደለን። በምርጥነታችን ሳይሆን በሥራችን ጠባይ እማናውቀው ታዋቂ ሰው የለም። ድንገት ካጠገባችን ቱር ብለው ተወንጭፈው፣ ስማቸው ተቆልሎ፣ አገር በነሱ ምሎ ሲገዘት የምናያቸው ሰዎች አሉ። ህዝቡ ላይ በሲያንሰኝ ነው ዓይነት እየፎከሩ፣ እኛ ዘንድ ደግሞ ተሳቀው እያፈሩ እሚሽኮረሙም እንዳሉም እናውቃለን። ልንወሻሽ በማንችልበት ደረጃ እንተዋወቃለና!!! በጓደኝነት ቅርበታችን ግን ስለአገራችን ስንከራከርም ሆነ ስንነታረክ ቀርቦ ላየን ሰው ነገ ተመልሰን እምንገናኝ አንመስልም። ግን አብረን ነን። በጣም እሚደንቀው ግን ያን ለየብቻ የተሟገትንበትን ተመሳሳይ ነገር አደባባይ ይዘነው ብንወጣ እሚያመጣው ጣጣ ነው። እንኳን አገር፣ ጓደኞቻችን ራሳቸው ሁሌም እምናወራበትን ነገር፣ ለመጀመሪያው ጊዜ እንደሰሙት ሆነው ገርሟቸው፣ ባልንጀርነታችንንም አስረስቷቸው፣ በጠላትነት ሲወቅሱንና ሊከሱን እንደሚችሉ ሳስብ ነገሩ ይገርመኛል። በዚያ ላይ ደግሞ አንተ ማን ነህና ነው እሱን እምትናገረው እሚባለውን ፈንጂ ሁሉ እያሰብን ምክር፣ ሂስና ተቃውሟችን ሁሉ በእጅና ጆሮ ብቻ እሚሰጥ ግልጽ ደብዳቤ ሆኖ መቅረቱ ያሳዝነኛል።
የኛስ ይሁን ግድ የለም፣ እነዚህ አገርና ዘመን ያተለቃቸው ፖለቲከኞችና የሚዲያ ሰዎች ግን፣ እርስ በርሳቸው ሲገናኙ ከሚባባሉት ቅንጣቷን ያሃል አምልጧቸው አደባባይ ሲያወጧት፣ አገር ተገርሞና ታሞ ሲያወግዛቸው፣ ጓደኞችና ወዳጆቻቸውን አሳልፈው እየሰጡ ዝም ብለው ማየታቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ኧረ ባካችሁ እናንተም አበዛችሁት፣ እኛ እኮ እንቀራረባለን፣ እኔና እሱ እኮ ከዚህም በላይ እንባባላለን፣ እገሌ እኮ ከምንም በላይ ለኔ ወዳጄና እማከብረው ሰው ነው፣ ብሎ እየተሳሳቁ ነገር ማብረድ ቢኖር ምን አለበት? ኢትዮጵያዊነትም ሆነ ብሔርተኝነት እኮ ሀሳብ ነው ሌላ ነገር አይደለም። የሁለቱም ሰፈር ሰዎች ለየብቻ ስንገናኝ ተሳሳቅና ተነፋፍቀን እምናወራውንና የፍቅር ያህል እምንቧቀስበትን ፖለቲካ አደባባይ ስናወጣው ጦርነት እየሆነ እሚያንቀጠቅጠን ለምንድነው? በተለያየ ነገር ልዩነትን ማሳየት ለሀሳብ ነጻነት ሲባል መደረግ ያለበት ቢሆንም በከረረውም ነገር ተናንቆ ሳይሆን ተሳስቆ መነጋገር ደግሞ አንድነትን ያመጣልና ነገር አብርዱ! ወዲህ ደግሞ ማንትስ ማንትስን እንዲህ አለ ብላችሁ አገር አታርበድብዱ! ፖለቲካችንን እንጫወትበት እንጂ አንጋደልበት።
 (አመራር ሰጭ የመሰለው አጻጻፌን ታዘብኩት። አሁን ስደልዘውም አልገኝ። የተራረፈቻችሁ ይቅርታ ካለች ጣሉብኝ። ደህና እደሩ!)
Filed in: Amharic