>
5:28 pm - Thursday October 9, 9698

"ምርጥ ዘር ላይ መመራመር ሲያቅታቸው ሰውን በዘር ያባላሉ!!!" (መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ)

“ምርጥ ዘር ላይ መመራመር ሲያቅታቸው ሰውን በዘር ያባላሉ!!!”

 

መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ

በቀደዱልን መፍሰስ የለብንም። እኛ ውሃ አይደለንም። እኛ ሰዎች ነን፤ ልባዊነት (አዋቂነት) በውስጣችን መኖር አለበት። አዋቂነት ማለት ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ ባዮሎጂ ወይም አቋቋም፣ ድጓ፣ ቁርዓን መማር ማለት አይደለም። ይሄ ይሄ ከላይ የሚጨመር ነው። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ማንበብ ያቋረጡ ሰዎች ንግግር የሚያልቅባቸው የተቀባው ድንጋይ ቀለሙ ስለሚለቅ ነው።

አንዳንድ ሕንፃ ዝናብ በጣም ሲበዛበት ቀለሙ ይገፋል፤ ቀለሙ ሲለቅ ድንጋዩ ይወጣል። ማንበብ ስናቆም ወደቀደመ ነገራችን ነው የምንመለሰው፤ ምክንያቱም ርሃብ እንጂ ባህሪያችን ዕውቀት ባህሪያችን አይደለም። ከውስጥ የተቀባ ቀለም ማንበብ ስናቆም ቀለሙ ይለቃል። ለምሳሌ ኮምፒውተር ሳይንስ ላይ የተመራመረ ሰው 15 ዓመት ጎጃም ወይም ወለጋ ከርሞ ቢመጣ ‹‹ኮምፒውተር ምንድነው›› ሊል ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ እኮ የሚገጥመን ነገር ዲግሪው ቤቱ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ዕውቀቱ ግን ጭንቅላቱ ውስጥ የለም። ዲግሪያቸውን ‹‹እዚህ ስመረቅ ነው፤ ከዚህ ቦታ ያገኘሁት ነው›› ይላሉ፤ ዕውቀቱ ግን ከውስጣቸው የለም። ዲግሪው ግድግዳ ላይ ቢሰቀልም ጭንቅላቱ ውስጥ ያለው ዕውቀት ግን በየጊዜው ማሞቅ ያስፈልገዋል።

አባቶቻችን ዓድዋ ላይ እንደዚያ ተግባብተው፣ አርቀው አስበው፣ ጥቁር አፍሪካውያን የሚኮሩበትን የጀግንነት መልስ የሰጡ በልብም በጉልበትም ሲመልሱ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዴት ምን ነካው? ‹‹ምን አገባህ!›› ማለት እንዴት አይችልም?

አባ መላ(ፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ) አንድ ፈረንጅ መጥቶ ሰገሌ(ሰሜን ሸዋ ውስጥ ያለ) የወሎና የሸዋ ነገሥታት ተዋግተው ነበር። ነገር ካለፈ በኋላ አንድ ጣሊያን መጥቶ ‹‹እናንተ የሸዋ ሰዎች እኮ እነዚህን ወሎዎችን ጉድ ሠራችኋቸው!›› አላቸው፤ እሱ ጠብ ለመጫር ብሎ እንጂ አስቦበት አይደለም። ‹‹የወንድማማቾችን ስትል ለምን የዓድዋውን አልነግርህም›› አሉት አባ መላ።

እሱ የነገራቸው የሸዋውንና የወሎውን ነው፤ መጋጨት ደግሞ ያኔም የነበረ ነው። አሁን ሰሞኑን እየሰማሁ ነው፤ እገሌ የሚባለው ክልል ልሁን አለ የሚባል ነው። እነዚህ ዛሬ ክልል እንሁን ክልል እንሁን እያሉ የሚጠይቁ የዛሬ ሰባት ዓመት ዕድሜ ሰጥቶት ያየ መከለያ ይቸግራቸዋል። እርግጠኛ ሆኜ እነግራችኋለሁ መከለያ ይቸግራቸዋል። ሀገር እንደሹራብ በዘዴ የተሠራ ነው። አንዱ ክር ሲመዘዝ ሁሉም ይመዘዛል። እዚህ አገር የወሰን ጥያቄ የሌለበት የለም።

በአማራውና በትግራይ አለ፣ በኦሮሞና በሶማሌ አለ፤ እንደገና ደግሞ ተለጥጦ በአማራና በአማራ መካከል አለ። እሱ ነው እኔ የሚገርመኝ! በኦሮሞና በኦሮሞ፣ በወለጋና በወለጋ መካከል ይቀጥላል ገና! በሶማሌና በሶማሌ መካከል ይደረጋል። ጠብ የሆነ ቦታ ላይ ካልተገደባችሁት ሰውነታችሁን ያበሰብሰዋል።

ይሄን ጥላቻ አሁን መገደብ ካልቻልን በጣም እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ አትራፊ የለም። ልዩነቱ አየለ ሰኞ ይጎዳል፣ ከበደ ማክሰኞ፣ ሥዩም ረቡዕ፣ ተሾመ ሐሙስ፣ እስከ ዕሁድ ድረስ ሁሉም ተጎድተው ጨርሰው ለቅሶ ደራሽም አይገኝም። ይሄንን እርግጠኛ ሆኜ ነው ምናገረው፣ ነብይ መሆን አያስፈልግም።

ወጣቶች በተለይ፤ አዲስ ሃሳብ ምታመነጩ ወጣቶች፤ ይሄን የተከበረ ጭንቅላት፣ እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ጭንቅላት፣ ማፍረስም መገንባትም የሚችለውን ጭንቅላት እስኪ ለበጎ እናውለው!

107 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተዋል እዚህ አገር፤ አሁንም ግን ፈረንጆቹ በበሬ እንደሚታረስ ለማየት ሙዚየም ገብተው ነው የሚያገኙት፤ እኛ አገር ግን ዛሬም በበሬ ይታረሳል። ከአንድ ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቀ ምሁር ገበሬን ወክያለሁ ብሎ ገበሬውን ሲያፈናቅል ከገበሬው ያነሰ ሰው መሆኑን ያሳያል። እንዲያውም እዚህ አገር ገበሬ ውሎ ይግባ! ምሁራኑ ምን አመጡ?

ምሁራኑ ምርጥ ዘር ላይ መመራመር ሲያቅታውቸው ሰውን በዘር ማባላት ተያያዙት! ገበሬው እንዲያውም ምርጥ ዘር እየዘራ ሠርቶ እያበላ ነው። በትግራይ ብትሄዱ፣ በአማራ ብትሄዱ መሬቱ የተበላ ነው፤ ከዚያ ከድንጋዩ ላይ ዘርቶ ግን፣ 24 ሰዓት እየሠራ ከጀንበሯ ጋር ሽቅድምድም ነው። ማታ ሲተኛ አመስግኖ ነው። ‹‹ጌታዬ ያለ እኔ ማንን ፈጥረሃል?›› ብሎ ነው። ሰው ጨረቃ ላይ እንደወጣ አልሰማም፤ ኧረ እንኳን ያልሰማ! እኛም ሰምተን ምንም አልተጠቀምን፤ እብደት ነው ያተረፍንነው!

በዚህ ዘመን የማን አድናቂ ነህ ብትሉኝ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች አድናቂ ነኝ፤ ፖለቲከኞቹን ንቁባቸው! በጣም ነው የገረመኝ። እኔ በ1998 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ቅንጂት የሚባል ፓርቲ አሸንፎ ኢህአዴግ ያልተዘጋጀበት ሽንፈት፤ ቅንጂትም ያልተዘጋጀበት ድል አጋጥሟቸው ሁለቱም ሰክረው ነበር። የቅንጅት የዚያን ጊዜ ችግር ዱብ ዕዳ ድል ወረደበት! ለድልም ለሽንፈትም መዘጋጀት ያስፈልጋል።

ቅድስት ሥላሴ አንድ ዓይነ ሥውር እየለመነ ይኖር ነበር። አንድ ቀን ሎተሪ ይዞ ሰዎች አዩት። ሰው ያነብለትና ‹‹እንዴ! 24 ሺህ ብር እኮ ደርሶሃል›› ብለው ሲነግሩት እዚያው ፍስስ ብሎ ቀረ፤ አልተዘጋጀበትም ነበር ማለት ነው። ሰውየው ሎተሪ ሲቆርጥ ይደርሰኝ ይሆናል ብሎም ማሰብ ነበረበት። ካልተዘጋጁበት ደስታ ይልቅ የተዘጋጁበት ኀዘን አትራፊ ይሆናል።

በ1998 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ሬዲዮ እየሰማሁ ነበር። የዚያን ጊዜ ያመልጠኛል ተብሎ የሚሰማ የሬዲዮ ፕሮግራም ነበር ያለው። ዛሬ እግዜር ይመስገን ያመልጠኛል ብለን አንሰጋም፤ ምክንያቱም ከአንዱ ኤፍ ኤም ቢያመልጠን አንዱ ይደግመዋል። ሁሉም አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ነገር ነዋ የሚያወሩት! የሁሉም ምንጭ ፌስቡክ ነው። ኢንተርኔት ቢዘጋ አብረው የሚዘጉ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች አሉ።

እና በጥቅምት ውስጥ የእስልምና በዓል እየተከበረ ነበር። ስማቸውን የማልጠቅሰው አንድ የፖለቲካ ሰው ‹‹ይሄ ሁሉ ጥረት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አንገት ለማስደፋት ነው›› ሲሉ ሰማኋቸው። አሁን ይቺ ትንሽ ነገር ትመስላለች፤ ግን ሰሚ ብታገኝ ኖሮ እስከ ወሎ እስከ ሀረር አባልታን ነበር። ደግነቱ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰማ ይመስላል እንጂ አይሰማም። አሁን እኛ ሰብከን ሰብከን አይሰማንም፤ የራሱን ነው የሚያዳምጠው።

አንድ ልጅ አማኑኤል ሲሰብክ ሲሰብክ፤ናባል የሚባለው ሰውየ ሦስት ሺህ በጎች ነበሩት፤ እነዚያን ሲያሸልት ዳዊት ድግስ ላክልኝ ብሎ ታሪኩን ሲተርክ ሴትዮዋ ከሦስት ሺህ በጎች ጋር ነው የቀሩት። በኋላ ከስብከት ሲወርድ ምን አሉኝ አለ ‹‹የኔ ልጅ እነዚያ ሦስት ሺህ በጎች የት ገቡ›› ብለው ጠየቁት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስ የሚለኝ ነገር የተነገረውን ሁሉ አይሰማም። የተነገረውን ሁሉ ቢሰማማ ተላልቀን ነበር።

ሰባኪዎች እኮ ጥቅስ ሲያልቅባቸው ፕሮቴስታንቱ ሙስሊሙን ይሳደባል፤ ክርስቲያኑ ግን አይሰማቸውም፤ ሄዶ መሀምድ ጋ ነው ሻይ የሚጠጣው። ፓስተሩ ሃሳብ ሲያልቅበት ‹‹ኦርቶዶክስ እንዲህ አድርጎ!›› ይላል፤ ፕሮቴስታንቱ አይሰማውም፤ ከወልደማርያም ጋር ነው ሻይ የሚጠጣው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይረባን ነገር ወደፊትም አይስማ!

አገራችን ውስጥ የፌስቡክ በላይ ዘለቀዎች፣ የፌስቡክ አጼ ቴዎድሮሶች ናቸው ያሉት። አሜሪካ ቁጭ ብሎ እሱ በርገር እየበላ እዚህ ሰው ያባላል።

የእብድ ገላጋይ ዱላ ያቀብላል አንሁን! ፈረንጆቹ ሆዳቸውን ሞልተው ግብረሰዶም ይፈቀድ ሲሉ የኛዎቹ ከሴት ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ሳይኖራቸው ይፈቀድ ሲሉ ነበር። እንደዚህ ዓይነቶችን አንስማቸው!

እንሰማማ፤ አንድ እንሁን! ከሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ሲባረሩ ከእነ ወለተማርያም ጋር እነ ከድጃም ተባረዋል፤ እናንተ ሙስሊም ናችሁ ቆዩ አልተባሉም። ከእስራኤል እነመሃመድ ሲባረሩ እነወልደማርያም ተባረዋል። ጀርመን ፕሮቴስታንት ስታባርር ሉተርን ስለተቀበልክ አንተማ ተቀመጥ አላለችም፤ ለማመንም ለመካድም አገር ይቀድማል!

Filed in: Amharic