>

ቤንዚን እያርከፈከፉ ሀገርን ለማንደድ የመራወጥ መጨረሻው ተያይዞ መጥፋት ነው!!!

ቤንዚን እያርከፈከፉ ሀገርን ለማንደድ የመራወጥ መጨረሻው ተያይዞ መጥፋት ነው!!!
መሳይ መካንን
ወደ ሰማይ ኳሷን ልጎ አይኑን ሰቆሎ የእውር ድንብር የሚጓዝ እንጂ ሰከን ብሎ ስለሀገር የሚያስበው ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው፡፡ የላጋትን ኳስ ሰማይ ለሰማይ እያየ መሬት ላይ ሀገር እየፈረሰች መሆኑን ለአፍታም መገንዘብ ያልቻለው የዘመኔ ትውልድ ከዚህም ከዚያም ጭቃ መራጨቱን መፍትሄ አድርጎ ቀንና ለሌት ሲረጋገም ውሎ ያድራል፡፡ ሀገሬ አሁንስ ሰው አለሽ ወይ?!
ማህበራዊ ሚዲያው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ሙቀትና ቅዝቃዜውን የሚወስን መሆኑ ያስፈራኛል፡፡ ጉልበት መፈታተሺያ የሆነበት ማህበራዊ ሚዲያው ከምሁር እስከ ገበሬ አንድ አግዳሚ ወንበር ላይ በእኩል ቁጭ ብሎ ማቆሚያ በሌለው የተኩስ እሩምታ ሲቀጣቀጥ ማየት ለአንዳንዱ ሆቢ፤ ጥቂት ለማይባሉት የገቢ ምንጭ፤ ለአብዛኛው ደግሞ መደበሪያ ከሆነ ሰነባበተ፡፡ አንዳንዱ ስትረስ ማራገፊያ እንደሚያድረገውም አውቃለሁ፡፡ ኮፍያችንን አንስተን ያከበርናቸው የምሁሩ ጎራ ወገኖቻችን መፍትሄ ማፍለቅ፤ ነገን ማመላከት ሲጠበቅባቸው እንደመደበኛ የፌስቡክ እድምተኛ ሙሾ አውራጅ፤ ከሳሽና ወቃሽ ብቻ ሲሆኑ ማየት ያስደነግጣል፡፡ በፌስ ቡክ ጭብጨባው የደራለት ተንታኝ ያለኔ ቅዱስ ከየት አለ በሚል ትዕቢት ተወጥሮ ስታየው የኢትዮጵያ ተስፋ ይርቅብሃል፡፡ ሀገሬ እውን አሳቢ አለሽ ወይ?
ሀገር ቤት ደርሼ ተመልሼአለሁ፡፡ እንደፌስቡኩ ሲዖል ሆና አላገኘኋትም፡፡ እንደእነ ኢቲቪም ገነት ሆና አልጠበቀችኝም፡፡ ኢትዮጵያ በእጅ ላይ ያለች እንቁላል ናት፡፡ ካመለጠች የምትሰበር፡፡ ዘመነ መሳፍንት ዋዜማው ላይ ያለችም ትመስላልች፡፡ የመንደር ጉልቤ በዝቶባታል፡፡ ህወሀት ከ1ሚሊየን በላይ ሚሊሺያ እሰልጥኖ ይፎክርባታል፡፡ ሌላውም ከዚያ በትንሽ ቁጥር ባነሰ መልኩ ሰራዊት እያደራጀ ዘመነ መሳፍንትን ለመቀበል የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ያ የጨለማ ዘመን ከደጃፋችን ተገትሯል፡፡ በራችንን አንኳኩቶ ሊገባ አሰፍስፏል፡፡ ከዚህም ከዚያም የሚታየው ነገር ያንን አስከፊ የታሪክ አሻራ ለመድገም የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ እውን ሀገሬ ከዚህ የሚታደግሽ ማን  ነው?
ትላንት ምርጫ ነበረን፡፡ ህወሀት እኔ ከሌለው ሀገር ትፈርሳለች የሚለው ዲስኩሩ ተራ ፉከራ ነው እያልን ስንታገል የነበረው ቢያንስ ምርጫ ስለነበረን ነው፡፡ ዘንድሮስ? ኢትዮጵያ ከትላንት በከፋ ምርጫ የሌላት ሀገር ሆናለች፡፡ ምርጫ አለመኖሩ አደገኛ ክስተት ነው፡፡ ለምን ምርጫ ላይኖረን ቻለ? እውን ከነችግሩም፤ ከነክፍተቱም ቢሆን አሁን ካለው የለውጥ ሃይል ሌላ ኢትዮጵያን እንደሀገር ይዞ ለማቆየት የሚችል ማን አለ? ምርጫ የሌለው ህዝብ ያለውን ሃይል እየጠረበ፤ እያስተካከለ፤ ቀዳዳውን እያመላከተ፤ መፍትሄውን በጋራ እያስቀመጠ፤ ትግሉን ወደሚፈልገው ግብ ለማድረስ ከመስራት ባለፈ ምን ማድረግ ይችል ይሆን? የፌስ ቡክ ወሬ እየቃረሙ ሀገርን ወደለየለት ቀውስ ውስጥ መክተት ማንን ሊጠቅም? በዕለታዊ ደራሽ ወሬዎች፤ በጥቃቅን መረጃዎች እየተገፉ ሀገርን የምታህል ነገር ህልውናዋን አደጋ ላይ መጣል ከወዴት ያደርሰናል? አብይ ክዶናል፤ ኦነግ ነው፤ ሌላ ተረኛ የዘር ቡድን ኢትዮጵያን ሊሰለቅጣት ነው፤ እያሉ ደምስር እስኪገተር፤ ላብ እስኪያጠምቅ ሙግት መግጠም ከባድ አይደለም፡፡ አውቂነትም ሊሆን አይችልም፡፡ እውነት ከሆነም አብይ እንዳይክደን፤ ኦነግ እንዳይሆን፤ ኢትዮጵያ በተረኛ የዘር ቡድን እጅ ላይ እንዳትወድቅ ምን መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ላይ ያተኮረ፤ መፍትሄ የሚያመላክት ውይይት እንጂ እሳት እያቀጣጠሉ፤ ቤንዚን እያርከፈከፉ ሀገርን ለማንደድ የሚደረግ የ24 ሰዓት ትጋት መጨረሻው ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡
ህወሀት ከ4ኪሎ ቤተመንግስት በተባረረ ማግስት አንድ ስትራቴጂ ነደፈ፡፡ የዶ/ር አብይን መንግስት ማጠልሸት፤ በተገኘው ቀዳዳ ጠ/ሚሩን ማንኳሰስ፤ በሂደትም ቅቡልነትን በማሳጣት ሀገሪቱን ወደለየለት ትርምስና ቀውስ ውስጥ መክተት የበቀል እርምጃው አቅጣጫ አድርጎ አስቀመጠ፡፡ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች፤ ቀለብ በሚሰፍርላቸው የግለሰብ ድረገጾችና የኢንተርኔት ሬዲዮኖች አማካኝነት የዶ/ር አብይን መንግስት ጥላሸት መቀባት በሰፊው ጀመረ፡፡ በዘር ልክፍት ልቦናቸው የተጋረደባቸው፤ አጥንታቸው ድረስ ዘረኝነት ህይወት የዘራባቸው የህወሀት መሪዎች ጠ/ሚሩን በዘረኝነት ሲከሱ መስማት የክፍለዘመኑ ኮሜዲ ሆኖብን ብለን ተቀበልን፡፡ ከጥቂት ወራት ወዲህ ህወሀቶች አጋዥ አግኝተዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ዋጋ የከፈለው የተወሰነው ሃይል ከህወሀት ጋር በአንድ መስመር ተሰልፎ አየን፡፡ ህወሀት ስራ ቀለለት፡፡ ዶ/ር አብይን በተገኘው ወሬ የሚያበሻቅጥ፤ የሚያንጓጥጥ፤ የሚያራክስ፤ አጋር አግኝቷል፡፡ የተጣራም ይሁን ያልተጣራ፤ ብቻ የሆነች መረጃ ይዞ የለውጡን ሃይል ለማብጠልጠል የሚጣደፍ መብዛቱ ለህወሀት ትልቅ ድል ነው፡፡ ያለልፋት የተገኘ ወሳኝ ድል፡፡ እውነት ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያ ይበጃት ይሆን? ዶ/ር አብይን በረባውም ባልረባውም ማንኳሰስ ለኢትዮጵያ ነጻነት ያስገኝ ይሆን? የሚባለው ሁሉ ዕውነት ቢሆን እንኳን በዚህ መልኩ የሚደረግ የማንቋሸሽ ትግል ማንን ይጠቅማል? ከህወሀት ጋር አንድ መስመር ላይ ያሰለፈን የሰሞኑ ግርግር ለህወሀት ሰርግና ምላሽ ሆኖለታል፡፡
ከዚህ ትውልድ ፊት የቀረበ ወሳኝ ፈተና አለ፡፡ አሁን ያለውን የለውጥ ሃይል በውሸትም ይሁን ባልተረጋገጠ መረጃ ቀጥቅጦ ስልጣን እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ ምን ይህናል ብሎ ለአፍታም ተጨንቆ ያውቃልን? የሞኝ ጥያቄ አይደለም፡፡ አንዲት ባለሀብት በአዲስ አበባ በነበረን ቆይታ አግኝተናት በዚሁ ጉዳይ ላይ ከተወያየን በኋላ ጥያቄውን አንስተንላት ነበር፡፡ ‘’የኢትዮጵያ አምላክ ሳያንቀላፋ አያድርም’’ የሚል ምላሽ ሰጠችን፡፡ እንደእምነቷ ያድርግላት፡፡
ግድየለም፡፡ ድንገት የፈረሱ ሀገራትን እናውቃለን፡፡ ዩጎዝላቪያ ወደ ትንንሽ ሀገራት የተቀየረችው በእኛው ዘመን ነው፡፡ በሰማይ ጠቀስ ፎቅችና ታሪካዊ ህንጻዎች የሚታወቁት የሶሪያ ከተሞች ወደፍርስራሽነት የተለወጡት በአይናችን ስር ነው፡፡ አንድ እምነት፤ አንድ ቋንቋ የሚናገሩት ሶማሊያውያን አንድ ሀገር መሆን ካቃታቸው ሩብ ክፍለዘመን አልፈዋል፡፡ ሀገር በሆነች ማግስት 32ቦታ ልትበጣጠቅ ዳር ዳር እያለች ያለችው ደቡብ ሱዳን ጎረቤታችን እኮ ናት?! ጎበዝ፤ ምንድን ነው መፍትሄው? ከእንደገና ጫካ እንግባ? ጦር እንስበቅ? ኢትዮጵያ ችግር የሚያወራላት አላጣችም፡፡ መፍትሄ የሚሰጣትን ግን አምጣ መውለድ ተስኗታል፡፡ ነግቶ እስኪመሽ የችግር መዓት የሚዘከዝክ የትየለሌ ነው፡፡ እሮሮ ቀለባችን ነው፡፡ መርዶ ነጋሪነት መለያችን ነው፡፡ መፍትሄውን ማን ይስጠን? መፍትሄውንም እንደስንዴው import እናስድርገው ይሆን?
Filed in: Amharic