>
5:13 pm - Saturday April 19, 8036

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት፤ ወደ ኢትዮጵያ ባለአደራ ምክርቤት ይደግ (ከተክሌ – ቶሮንቶ)

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት፤ ወደኢትዮጵያ ባለአደራ ምክርቤት ይደግ

 

|ከተክሌ – ቶሮንቶ

ኢትዮጵያ ነገ

1- አብይና ጓደኞቹ፤ የዛሬ አንድ አመት ከአዘቅት አውጥተውናል፡፡ አሁንም ከአብይ የተሻለ አሻጋሪ ማግኘት ይከብዳል፡፡ አብይን፤ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ለሰራልን ነገር ሁሉ አመስግነን አንዘልቀውም፡፡ ያመልካም ስራው ግን ወደመቀመቅ እንዲከተን አይፈቅድለትም፡፡ አንደኛ፤ አብይ ኢህአዴግ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ አብይን ጊዜ እንስጠው ብለን፤ ወዲህም አቅም አጥሮን እንጂ፤ ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ይቺን አገር ያለምርጫ ለአንድም ቀን መምራት አይገባውም ነበር፡፡

2- የዛሬው አብይ በእስክንድር ነጋ ላይ የወሰደው እርምጃ፤ ማለትም፤ የአዲስ አበባና የፌደራል ፖሊሶች የእስክንድርን የራስ ሆቴል መግለጫ የከለከሉበት ሂደት፤ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው፤ ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡ ለሕገመንግስቱ ብቻ የሚታዘዝ ፖሊስና ሰራዊት እናፈራለን ብሎ ቃል የገባልን አብይ፤ አመት ሳይሞላው፤ ከቤተመንግስቱ ጥቂት እርምጃዎች ርቀት ላይ፤ እንዲህ አይነት አይን ያወጣ የመብት ጥሰት ሲፈጸም፤ እሱ አያውቅም ማለት ይከብዳል፡፡ አብይ ያውቃል፡፡ የንጉሱ ጥላሁን ቃለምልልስም ያንን ያረጋግጣል፡፡ ባለፈው ሳምንት አብይ የተናገረው፤ ጦርነት እንገባለን ዛቻም ያሳብቅበታል፡፡

3- በዛሬው የአብይ አካሄዱ፤ እስክንድር ነጋ እንደውም የአዲስአበባ ባለአደራ ምክርቤትን፤ ወደኢትዮጵያ ባለአደራ ምክርቤት ማሳደግ አለበት፡፡ ምክንያቱም የዛሬው የአብይ ስራ የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን እጣ ፈንታም እንድንጠይቅ፤ ሰውን ሳይሆን፤ ስርአትን፤ ሰውን ሳይሆን ተቋምን እንድናምን አስታውሶናል፡፡ ምክንያቱም፤ ተቋም እንደሰው አይዋዥቅም፡፡ ተቋም እንደሰው አያኮርፍም፡፡ ተቋምም እንደሰው አይቆጣም፡፡ ተቋም እንደሰው ድርብ ሚዛን አይጠቀምም፡፡ አጠናና ቆንጨራ ታግሰን፤ መሀል አዲስ አበባ ላይ፤ በይረባ ሰንካላ ምክኛት፤ ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከል፤ አይመስጥም፡፡

4- አብይ ወጣት ነው፤ ቅን ይመስላል፤ አፉም ቅቤ ነው፤ ላለፉት ለተሰሩት ጥፋቶች ሀላፊነት ስለተወሰደ፤ እንደገረፉ እንዳሰሩ ስለተናገረ፤ ቢያንስ ቀርቦ ስላዳመጠን፤ አገራችን እንድንገባ ስላደረገ፤ የታሰሩትን ስለፈታ፤ እስኪ ጊዜ እንስጠው ብለን እንጂ፤ ኢህአዴግ ይህቺን አገር ለመምራት ምንም አይነት የሞራልም የህግም መሰረት የለውም፡፡

5- አብይ ካለፈው አዘቅት ስላወጣን ብናመሰግነውም፤ ወደሌላ መቀመቅ ሲከትን ዝም ብለን እንመለከታለን ማለት አይደለም፡፡ የእስክንድር መግለጫ መከልከል፤ ሌላ መቀመቅ አለ የሚል ጥያቄ ይጭራል፡፡ አብይ ብዙ ችግሮችን የመፍታቱን ያህል፤ አንዳንድ ችግሮችን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ባለመድፈሩ፤ ለኢትዮጵያ የሚያሳድራቸው ችግሮች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

6- የእስክንድር ንቅናቄ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ እንደውም ወደኋላ ስቃኝ፤ ያኔ ስድስት ኪሎ እያለን፤ እስክንድር አማራው ታሪክ ይሰራል፤ የአማራው ጉባኤ፤ ምናምን እያለ የሚጽፋቸው ነገሮች አይመቹኝም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ እስክንድር፤ አይደለም በርግጥም ሕገወጥ የሆነውን የታከለ ኡማን መንግስት፤ ራሱንም አብይንም፤ መንግስት ለመሆን ማንዴት የለህም፤ በፍትሀዊና ነጻ ምርጫ አልተመረጥክም፤ ብሎ ለመቃመው መብት አለው፡፡ ባለአደራ ምክር ቤትም ይበለው፤ ባለአደራ ማህበር፤ ለቆመለት አላማ በሰላማዊ መንገድ የመቀስቀስ፤ የማደራጀት፤ የመንቀሳቀስ መብት አለው፡፡ አሁን እንደሚያደርገው በሰላማዊ መንገድ ብቻ፡፡

7- አብይ፤ ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድ፤ ኢህአዴግ ታዛቢ፤ ኢህአዴግ መንግስት፤ ኢህአዴግ ተወዳዳሪ፤ ሆኖ ብቻውን ተወዳድሮ ባሸነፈበት ምርጫ ተመርጦ፤ የእስክንድርን ባለአደራ ምክርቤት የምርጫ ሂደት ሊተች ምንም አይነት ሞራል የለውም፡፡ ለዚያውም ኢህአዴግ፡፡ እስክንድር ትግሉን፤ ሕግን በጠበቀ መልኩ፤ ባሻው መልኩ ሊያዋቅር ይችላል፡፡ በየክፍለከተማው፤ የወረዳው፤ ሀምሳ ኮሚቴ አደራጅቶ፤ የአዲስአበባዊያንን ጥቅም ለማስጠበቅ፤ ታከለን አይደለም፤ ኢህአዴግን ለመገዳደርና ለመጎትጎት ይችላል፡፡ የባለአደራ ምክርቤትን፤ በግድ ጠምዝዞ፤ ባለአደራ መንግስት ብሎ በመተርጎም፤ ለመምታት ማሰናዳት፤ ማምታታት ነው፡፡ ብርሀኑ ነጋም ምን ነክቶት እዚህ ጨዋታ ውስጥ እንደተሰነቀረ እንጃ፡፡ ብርሀኑ፤ አሁን የእስክንድርን ልብ አጥቶት ነው፡፡

8- ይሄ የአብይ የዛሬው እርምጃ፤ እግረመንገድ አንዳንድ ነገሮችን እንድዳስስ አስታውሶኛል፡፡ አብይ፤ እንደመሪ፤ በቀጥታ ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሊቋጫቸው ወይም መፍትሄ ሊያበጅላቸው የሚገባውን ነገሮች፤ በቃላት ሸንግሎ፤ በጸሎት፤ በመልካም ንግግር ለማጥፋት ይተጋል፡፡ ይሄ “prosperity gospel” ተሸንቅሮበት፤ እነዚህ የSelf-help መጽህፍትን ጠጥቶ መሰለኝ፤ ብዙ ነገሮችን በቃል ያድናል ቃል ይገድላል፤ እና በፍቅር ያሸንፋል መፈክር ማለፍ ይፈልጋል፡፡ እንደውም አንዳንዴ፤ አብይ፤ ከመድረክ ላይ በሚለቀቁ ረጃጅም ስብከቶች አገር የሚድን ይመስለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ችግር፤ እንደዚያ ድነሀል፤ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ እንደተባለው የአመታት የአልጋ ቁራኛ የሚፈታ አይደለም፡ አብይ እንደዚያ ያስባል፡፡

9- አንዳንድ ነገሮችን፤ You cannot wish it away. ወይም ድሮ ኢህአዴግ እንደሚያደርገው በግምገማ፤ የተወሰኑ ካድሬዎችን ሰብስቦ በመገሰጽ አይጠፋም፡፡ ችግሩ አለ፡፡ ፊት ለፊት መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡ የጌዴዮ ቀውስ፤ በአማራውና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ውጥረት፤ የአዲስ አበባ ጉዳይም፤ በአፍና መልካም ንግግር ብቻ በመናገር እንደሚጠፉ ማሰብ መሪነት አይደለም፡፡ ፈሪነት ነው፡፡ ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ያደረገው አብይ ትልቁ ድክመቱ፤ አንዳንድ ወሳኝና አጨቃጫቂ ነገሮችን፤ በጸሎትና በመልካም ምላስ ብቻ የምናልፋቸው አድርጎ ማሰቡ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ነገሮች በንግግር ብቻ አያልፉም፡፡

10- አብይ ባለፉት ሁለት ንግግሮቹ ላይ ትልልቅ ፋውሎችን ሰርቷል፡፡ ለምሳሌ ስለጌዴዎ የተናገረው ስህተት ነው፡፡ የራሱ ሚኒስትር፤ ወ/ሮ ሙፈሪያት፤ ምግብ መንገድ ላይ ተዘርፎ ለተጎጂዎች ሳይደርስ ቀርቷል፤ ይመረመራል ብላ አምና፤ እሱም ራሱ ያንን አረጋግጦ ተናግሮ ነበር፡፡ እንደገና ጥቂት ቀናት ቆይቶ፤ አንድ ሰው ነው የሞተው፤ በፎቶሾፕ ምስል ሰርተው እያለ፤ የመቶሺሆችን መፈናቀል ማሳነሱና ስላቅ መናገሩ ትክክል አይደለም፡፡ በእሱ መንግስት ስር ስለተፈናቀሉ ሰዎች፤ የተናገረው ፕሬዚዳንቱ ሙላቱ ተሸመ፤ በ1992 ምርጫ ክርክር ግዜ ይመስለኛል፤ ከተናገሩት ጋር ይመሳሰላል፡፡ አንዱ ተቃዋሚ፤ ኢትዮጵያ በድህነት ከዓለም 177ኛ ምናምን ወጥታለች ብሎ ሲከራከር፤ ማስትካከያ ብለው፤ በግድ እጅ አውጥተው፤ የለም 169 ነን አይነት ነግግር፡፡ (ቃል በቃል አላስታውሰውም) አሁን፤ የተነፋቀለው፤ 3 ሚሊዮን ሆነ 2.5 ሚሊዮን፤ ለውጥ ምን ያመጣል፡፡ እዚህ ላይ አብይን ኢህአዴግነቱ አሸንፎታል፡፡

11- ስለእስክንድር የተናገረውም፤ ያመለጠውና የአብይን ክፉ ጎን ያሳየ የተሳሳተ ንግግር ነው፡፡ ባንድጊዜ ከፍቅር ያሸንፋል ንግግር ወደ ጦርነት እንገባለን ማስፈራሪያና ዛቻ መውረድ አስደንጋጭ ነው፡፡ እስኪ ይሁን፤ ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ እስኪ እድል እንስጠው፤ ከኛ የተሸለ እውቀትና መረጃ አለው፤ ፈረንጆቹ እንደሚሉት The benefit of the doubt እንስጠው ስንል፤ ዛሬ በእስክንድር ላይ የወሰደው እርምጃ አስደንግጦናል፡፡ አስቆጥቶናልም፡፡ መታረም አለበት፡፡ መደገምም የለበትም፡፡ ይባስ ብሎ ደሞ፤ ቃል አቀባዩ ንጉሱ ጥላሁን የሰጠው ማስተባበያ አይሉት ማብራሪያ፤ የበለጠ አናዳጅ ነው፡፡ ራስ ሆቴል የጸጥታ ስጋት ካለ፤ የተቀረው አገሪቱማ በፈጣሪ እርዳታ ነው ያለው፡፡ የንጉሱ ጥላሁን ማብራሪያ፤ ቀሽም ነው፡

12- የዛሬው የአብይ እርምጃ ያሳየን፤ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ባለአደራ ምክርቤት እንደሚስፈልገንም ነው፡፡ አብይ እንደግለሰብ መልካም ሰው ቢመስልም፤ አብይ ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ራሱ እንደድርጅት አደራ የያዘው፤ ላለፉት 28 አመታት አደራውን ቀርጥፎ የበላ መንግስት ወይም ፓርቲ ነው፡፡ እንደታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አብይ የዚያ መንግስት አናት ሆኗል፡፡ ዛሬ በፖሊሶች በኩል የወሰደውና፤ በአብይ ቃልአቀባይ የተረጋገጠው እርምጃ የሚያሳየው፤ አሁንም ቢሆን ስልጣን በሕግና በስርአት ካልተቀየደ፤ ሊያማስን እንደሚችልና፤ የአብይም ኢህአዴግ ያው ኢህአዴግ እንደሆነና ለአደራ እንደማይበቃ ነው፡፡

13- አብይ ሆይ፤ ስላደረግክልን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ከአዘቅት ስላወጣከን ግን ወደ መቀመቅ ስትወስደን እንቀበላለን ማለት አይደለም፡፡ አዲስ አበባ አይደለችም፤ ኢትዮጵያም የምር ባለአደራ ምክር ቤትና ባለአደራ መንግስት ያስፈልጋታል፡፡

 

Filed in: Amharic