[ዶሮ ማነቂያዎች]
ዘመድኩን በቀለ
★ የዛሬ ዓመት ልክ በዚህ ቀን ጠቅላያችን በተሾሙ ዕለት የጦመርኳት ጦማር ናት። በዚህ ጦማር ምክንያት የተሰደብኩትን ስድብ በፌስቡክ ዓለም ቆይታዬ ተሰድቤ አላውቅም። የቅር ወዳጆቼ ሳይቀር “ አበዛኸው ” ብለው በድፍረት እስኪያኮርፉኝ ድረስ ብዙ ጠላት የገዛሁባት ጦማር ናት። በወቅቱ ሁሉ ሰው በጠሚው መልክ፣ ቁመና፣ ንግግር አቅሉን ስቶ በሰከረበት ሰዓት እኔ ለምን በተቃራኒው ብቻዬን ቆሜ ይኽቺን ጦማር እንደጻፍኳት ለእኔም ግልጽ ባይሆንም በወቅቱ ግን “ የጻፍኩትን ጽፌያለሁ” በማለት ምላሽ ሰጥቼ ማለፌን አስታውሳለሁ።
★ እናላችሁ እነሆ አጅሬ ፌስቡክ ዓመቱን ጠብቆ ጦማሩን ጎልጉሎ ቢያስታውሰኝ ጊዜና እኔም መሰደብ አማራኝና ያንኑ ጦማር መልሼ ለጠፍኩላችሁ። ዛሬ ግን ትናንት አይደለም። ስካሩም የበረደ ይመስላል። እንደ አምናው ባልሰደብም የሚንበጫበጭብኝ ግን አላጣም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። መልካም የትውስታ ንባብ ይሁንላችሁ። በነገራችን ላይ ከምር እኔ ዘመዴ ግን ከእስራኤል ዳንሳና ከካራቲስት ኢዩ ጩፋማ ሳልሻል አልቀርም።
★ አሁን አቢቹን ፕሮቴስታንቶች በፍቅር፤ የሥልጣን ፍርፋሪ ፈላጊ የጥንት ተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች በልምምጥ፣ በወጣቶቹ በፋኖና ቄሮ ትግል ሀገራቸው እንዲገቡ የተደረጉትም በውለታም በይሉኝታም፣ ባለ ጊዜ ነን ባይ ጥቂት የነገደ ኦሮሞ አባላት በስጋት እናም በሆዳቸው የሚያስቡ፣ ስለሆዳቸውም ብቻ የሚኖሩ ደገም ለከርሳቸው ሲሉ ይወዱታል፣ ይከራከሩለታል። ውሉደ ህወሓቶች ግን ከበሰለ ማዕድ ላይ ገፍቶ በረሃ ስለጣላቸው አምርረው ይጠሉታል። እኔ ግን አልጠላውም። ለዐቢቹ መስታወቱ ነኝ። መልኩን ከነ ቡግሩ የማሳየው መስታወቱ ነኝ። አከተመ ።
~ ፖለቲካ prostitute ሽርሙ*ና ነው ፤ ሸርሙ* ደግሞ ተኳኩላ፣ ተቀባብታ፣ የሌላትን መልክና ውበት ይዛ ለገበያ መቅረቧ የተለመደ ነው። እናም ነግቶ ስናያት ቋቅ ሊለን በስካር መንፈስ በሸርሙ* ውበት አንሸወድ። ደግሜ እላለሁ አዳሜ ቡረቃሽን ቀንሺ። ፈንጠዝያውም በልክ ይሁን። ራሳቸው ኢህአዴጎቹ ይታዘቡናል። ከምር ይታዘቡናል። እናም ጎበዝ ብዙ ባናሽቃብጥ መልካም ነው።
~ ” የተመረጠው ኢህአዴግ ነው ምንም ለውጥ የለም ” የተከበሩ አረጋዊው ፖለቲከኛ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ። እናም የሽማግሌ ምክር ብንሰማ መልካም ነው ።
#ETHIOPIA | ~ አዲስአበባ ~ ዛሬ በዶክተር ዐቢይ ንግግር ሁሉም ሰው ኤህአዴግ ሆኖ ታየ። ከእኔና እንደኔ ጨለምተኛ የሚል ስያሜ ከተሰጠን ጥቂት ተጠራጣሪዎች በቀር ሁሉም ሰው ዛሬ ኢህአዴግ ሆኗል። በኮሎኔሉ ንግግርም ሰክሯል። የጉሽ ጠላ ስካር በቶሎ ስለሚለቅ ነገን መጠበቅ ነው። ስካሩ እስኪለቃችሁ ግን እቃ አትፍጁ። ቀስ፣ ኧረ ቀስ፣ ራጋ በሉ እንጂ ጎበዝ።
•••
መቼም የማይካደው ነገር ኮሎኔል ዶር ዐብይ ስለ ሀገርና የሕዝብ አንድነት የተናገረው፣ ስለ ፍትሕም የተናገረው የሚደነቅ ነው የሚሉ ሰዎች ግርም ይሉኛል። ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ንግግር ያልተናገረበትን ጊዜ የሚያስታውሰኝ ካለም ይንገረኝ። መለስ ዜናዊ ሎሜ ቶጎ ላይ የማይወዳቸውን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና ግርማዊ አጼ ኃይለሥላሴን በአፍሪካ መሪዎች ፊት በእንጊሊዝኛ አሞግሶ ያደረገው ንግግር ከዛሬው ከዐብይ ንግግር በምን ያንሳል? እውነታው ግን መለስ ኢትዮጵያን ቀብሮ ነው የሞተው ።
★ በ2009 ዓም ኢህአዴግ አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት ዘመን እንደሚመጣ እንዲህ በማለት ነግሮን ነበር።
•••
የዛሬው የኮሎኔል ዶክተር ዐብይ አስደማሚ ንግግር ከመሰማቱ በፊት የዛሬ ዓመት ገደማ ኢህአዴግ እንዲህ ብሎ ነግሮን ነበር ። …”ይሁንናም የሚጠብቀውን ያኽል ጠንካራ የአገር ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ተገንብቷል ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አይገኝም ። በዚህ ረገድ ኢህአዴግና የሚመራው መንግሥት የሠሩት ሥራ ደካማ እንደሆነ ይቀበላሉ ። በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የሥነ – ዜጋ ትምህርት የታሰበውን ያህል ውጤታማ አልሆነም። የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ዜጎች ብሔራዊ ስሜትና የአገር ፍቅር እንዲያጎለብቱ የረባ አስተዋጽኦ አላደረጉም። ይልቁንም አሉታዊ አስተዋጾኦቸው የሚያይልበት ሁኔታ ይታያል ።
•••
በአሁኑ ወቅት በወጣትነት ዕድሜ ያለው በኢህአዴግ የምትመራዋ ኢትዮጵያ ያደገ በመሆኑ በተላላቅ ወንደሞቹና እህቶቹ የነበረውን ብሔራዊ ስሜትና አገራዊ ፍቅር ሊወርስ ዋነኛ ተጠያቂው #ኢህአዴግ እንደሆነ አያከራክርም ። ይኽ እንደተጠበቀ ሆኖ ወጣቱም በአይኑ ከሚያየውና ከነጉድለቱም ቢሆን ተጠቃሚ ከሆነበት አገራዊ ለውጥና እድገት እንዲሁም በቀጣይ ከፈነጠቀው ተስፋ በመነሳት በአገሩ ላይ ፍቅርና እምነት ማሳደር ይገባዋል። ” [ አዲስ ራዕይ መጽሔት መስከረም – ጥቅምት 2009 ዓም ]
•••
ልብ በሉ ይኽን ያለው የዛሬ ዓመት ገደማ #ከኦሮማራ ክስተት በፊት፤ ከለማና ገዱም #የኢትዮጵያዊነት_ሱስ ሰበካ በፊት ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት የቀደው ዕቅድ ነው። ከዚያ የኢትዮጵያ ” የከፍታ ዘመን” የሚል ሰበካም ተከተለ። ከዚያ አሁን ደግሞ በመጨረሻ የአዲሱ ዘመን ትውልድ አካል እንደሆኑ የሚሰማን አንደበተ ርቱዑ ወጣቱ ኮሎኔል ዶክተር ዐብይ አህመድን ኢህአዴግ አሰልጥኖ ፣ ኮትኩቶና አርሞ አሳድጎ ” በአሮጌ አቁማዳ እኛ ዘላለማችንን የምናውቀውን አዲስ የወይን ጠጅ ጨምሮ ሊያጠጣን ፤ አጠጥቶም ሊያሰክረን ይኸው በዕቅዱ መሠረት ሥራውን ዛሬ አሀዱ ብሎ ጀምሯል ።
~ አዳሜ ስካርሽን ቀነሺ። ምድረ ሰካራም ሁላ !
•••
ከ1983 ዓም ወዲህ ከ26 ዓመታት በኋላ ዛሬ መጋቢት 24/2010ዓም በኢትዮጵያ ፓርላማ ታሪክ እነሆ ለመጀመሪያ ጊዜ ግሩም የሥነ ጽሑፍ ክህሎት ባለው ሰው የተዘጋጀ እና ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ የሚለው ከማር ከሶከር ይልቅ የሚጣፍጠው ቃል ከበቂ በላይ የታጨቀበት ግሩም የሆነ ዲስኩር በአዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር በክቡር ኮሎኔል ዶር ዐቢይ መኮንን አንደበት ተነቦ ሰማን።
•••
አብዛኛው ሰው ይኽን የኮሎኔሉን ንግግር ሰምቶ እንደ አዲስ ግኝት ሲቦርቅ ሳይ ግን ራሴን መጠራጠር ጀመርኩ። ይኽን ” ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ የሚል ቃል ደጋግመው ስለተናገሩ በዚያችው ምድር በዚሁ አሁን ባለው ሥርዓት ከሞት እስከ ስደት ገሚሶቹም እስከ አሁን በወኅኒ ቤት እንዲማቅቁ፣ እንዲበሰብሱ የተፈርደባቸውን እንዴት ረስተን አሁን ለራሱ ለኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን ጩኸት ቀምቶ መልሶ ስለነገረን ፈዘን ቆመን የምናጨበጭበው?
•••
እርግጥ ነው የዛሬው የኮሎኔሉ ንግግር ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ንግግር ጋር ተመሳሳይ ነው። ወታደር በተፈጥሮው ሀገሩን ይወዳል። እናም ኮሎኔሉ ከtalkshow በዘለለ ዛሬ ያሰሙትን የሹመት አቀበበል ንግግር በራሱ ብቻ ተፈጻሚ የሚያደርግ ቢሆን ኑሮ ምንኛ በታደልን ነበር። ነገር ግን ድርጅቱ #ኢሕአዴግ ነውና በተመሳሳይ መልኩ ይኽን መሰል ብዙ ቃል ኪዳኖችን ቀርጥፎ የበላ ሥርዓት ነውና ለዛሬውም ለኮሎኔሉ ንግግር ቡረቃ አያስፈልግም ።
•••
ለነበረውና ስለሆነው ነገር ትውስታ ከሌለንና የመማር እጥረት ካለብን ከአረንቋው አንወጣም ። መንገራገጭ ብቻ ነው የሚሆነው። ስለወደፊቱ ተስፋ ማድረግ ቢገባንም ያለፈውን በሒሳዊ ትዝታና ትውስታ ማገናዘብ ያስፈልገናል ። የፊት የፊታችንን ብቻ በማየት ቁም ነገር መሥራት አንችልም። አከተመ ።
•••
በተለይ አሁንም ኮሎኔል ዶክተር ዐቢይ በዛሬው ንግግራቸው “አሁንም ኢሕአዴግ ነኝ። በድርጅቴና በጓዶቼ እኮራለሁ እስካሉ ድረስና የድርጅቱ ርእዮተ ዓለምና የአሠራሩ set up እዚያው እስካለ ድረስ ማድረግ የሚመረጠው ዐቢይን ባለበት እንዳለ መቀበል ሳይሆን case by case እንዲል ፈረንጅ ደረጃ በደረጃ አካሔዱንና ውጤቱን እያዩ መፈንጠዝ ይገባል እንጂ በባዶ ሜዳ እንጣጥ እንጣጥ ማለቱ ጉልበት መጨረስና በኃይለኛው መሰበርንም ያስከትልብናልና ምጥንቓቅ ግበሩ ።
•••
የአቶ መለስ ዜናዊን የከበረ ስም ወስደው በቁማቸው ” የቀድሞው ” የሚል ማዕረግ ተጎናጽፈው ተዝካራቸውን እንዲበሉ የተገደዱት አቶ ኃይለማርያም በትምህርት ዝግጅታቸውም የተመሰከረላቸው እንደሆኑ ይነገራል ። የዛሬውን ኮሎኔል ዐብይን ጨምሮ ሌሎችንም ተማርን የሚሉ ሰዎችንም ጠፍጥፈው ሊሠሩት የሚያስችል እውቀት እንዳላቸውም ይነገራል። አቶ ኃይለማርያም ግን ኢህአዴግ ስለሆኑ ብቻ ከድርጅቱ የጋራ ውሳኔና አመራር ውጪ በግላቸው ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው ምንም መሥራት ሳይችሉ ነው 6 ዓመት ከዕድሜያቸው ላይ ቀንሰው የባከነ ዘመን ያሳለፉት። አቶ ኃይሌ ድርጅታቸው የተሳሳተ መረጃና በቤተመንግሥቱ አጥር ውስጥ ቆልፎ ” እንደ አንበሳ የሚወዱትን ጥሬ ሥጋ ” እያቀረበላቸው ነው እንደ አሻንጉሊት ሲጫወትባቸው የኖረው። ዶር ዐቢይስ ከዚህ የተለየ ምንም አይገጥመውም። ኢንዴዢያ ነው ።
•••
አቶ ኃይለማርያም እንደ ኮሎኔል ዐብይ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ እንዲተውኑ አልተፈቀደላቸውም።
• ኔትወርክ የሚጠፋው ፎቆች ስለበዙ ነው።
• ወርቅ በሰፌድ እፈሱ ፣
• ጤፍ የተወደደው የተመጋቢው ፍላጎት ስለተወደደ ነው። • • ስለ አረብ ሐገር ሴቶች፣
• ስለ አውሮፓ ስደተኞች፣
• ስለ አንድ መሣሪያ ስለያዘ ፖሊስና ትእግስቱ የባጥ የቆጡን እንዲያወሩ፣ እንዲዋረዱ፣
• ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ” ለመለስ ዜናዊ ” የሚል ንግግር ጽፈው እንዲቀለድባቸው የተደረጉ ምስኪን ነበሩ። ኃይልሻ የፌስ ቡክ ሠራዊት አልነበራቸውም። ጥሬ ሥጋ እያበሉ መቀለጃ አድርገዋቸው ከረሙ። አንዴ አስፋልት አንዴ ቱቦ ሲያስጠርጓቸውም ከረሙ። እናም እኔ አንጀቴን የሚበሉኝ መሪ ናቸው ኃመደ ።
•••
የፓርላማው አፈ ጉባኤ ፓስተር አባ ዱላ ገመዳ የኮሎኔል ዶር ዐብይ የነፍስ አባቱ ናቸው። ጠፍጥፈው የሠሩት አባቱ ናቸው። ፖለቲካውን ከህጻንነቱ ጀምረው የጋቱት የቀለም አባቶቹም እዚያው ፓርላማ ውስጥ ነበሩ። ሌላው ቀርቶ ኮሎኔል ዶክተር ዐብይ ንግግሩን በፈጸመ ጊዜ ሔዶ የተቀመጠው የህወሓቱ ደብረ ጽዮን አጠገብ ነው። ክፍቱን ጥሎት የሔደውን ውኃ እንኳን አንስቶ ሲጨልጠው ምንም ዓይነት ጥንቃቄ እንኳን አላደረገም። የኦህዴዱ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ በመርዝ መሰናበታቸውን ኮሎኔሉ አሳምሮ ያውቃል። ለመለስ ውኃ ቀድቶ ማን እንደሚሰጠው ሁላችን የምናውቀው ነው። መልእክቱ ግልጽ ነበር። አለቃህ ህዋሓት ነው። የሚሰጥህን ሁሉ ጨልጠህ ትጠጣለህ ያንኑ መልሰህ ታገሳለህ። አከተመ ።
•••
#ህውሓት መራሹ የዓድዋ ቤተሰቦች ስርወ መንግሥት ኢትዮጵያ የምትባለዋን ጥንታዊት ሀገር በእጁ መዳፍ ስር ካስገባት ከ1983 ዓም ጀምሮ እና የሀገሪቱን የመራሔ መንግሥትነት ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጊዜ አንስቶ ” ኢትዮጵያ ” የሚለውን ቃል ሲጠየፉት መኖራቸው ይታወቃል። ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊም ከአፈር ተቀላቅሎ ራሱ #ኢትዮጵያን እስኪሆን ድረስ አፉን ሞልቶ ሳይጠራት ላይመለስ አሸልቧል። መለስ እንደ ኤርትራዊ እና እንደ ትግሬ ኖሮ እንደ የሞተ፣ የሚዘቀዝቃትን ባንዲራ ሳይወድ በግዱ ለብሶ የተቀበረ፣ በኢትዮጵያ ምድር ሞቶ የኢትዮጵያን አፈር የተቀላቀለ ሰው ነው። ለዚህ ነው ዛሬ ኮሎኔሉ ጠቅላያችን ” ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን ያሉት። አፈሯን ነው ኢትዮጵያ ያሉት። መለስ አሁን ምስጥ የጨረሰው የኢትዮጵያ አፈር ሆኗል።
•••
አይተ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ” ሃገሪቱ ” ኢትዮጵያውያንን ” የሀገሪቱ ህዝቦች ” እንዳለ እናት ሀገሬ ኢትዮጵያዬ ሳይል ነው ላይመለስ ያለፈው። በመለስ ዜናዊ ፍልስፍና ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በመንደር፣ በብሔር፣ በዘርና በጎጥ የተከፋፈልነውና ለአሁኑ ትርምስ የበቃነው በዚሁ በ26 ቱ የህወሓት የአገዛዝ ዘመን ነው። መታወቂያ ደብተራችን ሳይቀር ሳንፈልግ፣ ሳንወድም በግድ እስከ አሁን ድረስ ዐማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ በሚል መርዛማ ቃል ተተብትበን የሌለ አዙሪት ውስጥ እንድንወድቅ የተደረግነው።
•••
እርግጥ ነው ባለንበት ዘመን በመታወቂያው ላይ ” ትግሬ ” የሚል ብሔር ስም የተጠቀሰለት ሰው በብዙ ያተርፋል ፣ ይጠቀማልም። ጉምሩክ ቀረጥ አይጫንበትም። ሥራ በመረጠው መስክ አቅም እውቀትና ክህሎት ባይኖረውም እንኳ በትግሬነቱ ብቻ ያለሰቀቀን ሥራ ያገኛል። ባለሥልጣን ይሆናል። ኮንዲሚንየም ሳይወዳደር ይደርሰዋል። ትግሬ ሥለሆነ ብቻ ጳጳስ ፓትሪያርክም ይሆናል ። ሥራ አስኪያጅ የእድር ዳኛ ሳይቀር ትግሬ መሆን መድኅን ነው በዚህ ዘመን። የማኅበራት፣ መሪ፣ የእድርና የጽዋ መሪ እንኳን ትግሬ ካልሆነ ድርጅቱ በቡዳ ይበላል። የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ሳይቀሩ ትግሬ መርጠው ነው መሪ የሚያደርጉት። ትግሬነት የቡዳ መድኃኒት እስኪሆን ድረስ ማለት ነው። የአክስዮን ምሥረታ ላይ ትግሬዎች ወሳኙን ሥፍራ ካልያዙ አከተመ። መታወቂያው ላይ ትግሬ የሚል ከተጠቀሰለት የተዘጋ መንገድ ይከፈትለታል ። ፖሊስ ወታደር መታወቂያውን ባየ ጊዜ ትግሬው ለማኝ የኔ ቢጤ ቢሆን እንኳ የንጉሥ ያህል ይከበራል። እናም ህወሓት ከመታወቂያችን ላይ ብሔር የሚለው አይነሳም የምትለው ወዳ አይደለም ። ብሔሯን በገነባችው የአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የቀረጸችው የፖሊሲዋ አንድ አካል ስለሆነ ነው። እንዲህ ስላልኩ ብዙዎች ቅር ሊላችሁ ይችላል ። እውነታው ግን ይሔው ነው ። እየመረረንም ቢሆን መፍትሔው መዋጥ ብቻ ነው ።
•••
በአንጻሩ መታወቂያው ላይ ዐማራ የሚል ታፔላ የተለጠፈበት ደግሞ ምድሪቱ ሲኦል እንድትሆንበት ይደረጋል። መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በፍርድ ቤት ፍትህ ለማግኘት ዐማራ የሚል መታወቂያ ካለህ አለቀልህ። ይኸው ነው። እግር ይቀጥናታል፣ ጫማህ አልቆ በአንገትህ ትሔዳታለህ እንጂ ዐማራ ከሆንክ ወፍ የለም። ዐማራ ከሆንክ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት አትችልም። ዐማራ ከሆንክ ነግደህ ማትረፍ አትችልም ። ሠርተህ ጥሪት ከቋጠርክ ወይ ከርቸሌ ወይ መድኃኔዓለም ጓሮ ራስህን ታገኘዋለህ። ስታር ቢዝነስ ግሩፕን ያየ ይፍረደኝ። ዐማራ ከሆንክ በፌስቡክ ገጽህ ላይ ሃሳብህን ካካፈልክ ዘብጥያ ትወርዳታለህ። ትግሬ ከሆንክ ግን አይመለከትህም ቢያንስ ቅድም የለጠፍከውን አንሳው ትባላታለህ እንጂ ወላሃንቲ ነገር አይገጥምህም። አይደለም እንዴ ? ዋሸሁ እንዴ ?
•••
ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ለክቡር ዶክተር ኮሎኔል አብይ አሕመድ ” ጊዜ ሰጥተን እንየው ” የሚሉ ምስኪኖችም ገጥመውኛል። 26 ዓመት ጊዜ አልነበረም እንዴ? 26 ዓመት ሙሉ አባዱላም አባይ ፀሐዬም እዚያው ፓርላማ ውስጥ ነበሩ እኮ። ዐቢይም ከ15 ዓመቱ ጀምሮ ኢህአዴግ ሆኖ የኖረ ኢህአዴግ እኮ ነው። እና የምን ጊዜ ነው የሚሰጠው? ጊዜውን ባትሰጡትስ ልትቀሙት ነበር እንዴ ? ጊዜን ማንም አያቆመውም። እኔ ግን ከእባብ ጎሬ የእርግብ እንቁላል አልጠብቅም።
•••
የሚገርመው ነገር በትጥቅ ትግልም በሰላማዊ መንገድም የሚታገሉት አብዛኛዎቹ ታጋይ ተብዬዎች ጭራሽ ኮሎኔሉ የእነሱ ፓርቲ አባል ይመስል ሻምፓኝ ከፍተው ሲቦርቁ እንደማየት የሚያሳፍር ነገር የለም። ኧረ ቀስ የኢህአዴግ መሳቂያ አትሁኑ። እነ ተመስገን ደሳለኝ ኢትዮጵያ ባሉ የሞት አፋፍ ናቸው። እስክንድር ነጋ አንዷለም አራጌ ኢትዮጵያ ባሉ ዘብጥያ ናቸው። ልዩነቱ የኮለኔሉ ኢትዮጵያ አባባል አንድ ፊልም እንደሚሠራ አክተር የትወና ሲሆን፤ የእነ ተመስገን ደሳለኝ ኢትዮጵያ አባባል ግን በገሃዱ ዓለም ያለትወና የምር የሚኖሩት ፣ የሚናገሩለትና የሚሞቱለት እውነት መሆኑ ነው። ኮሎኔል ዐቢይ ኢትዮጵያ ስላሉ ተጨበጨበላቸው እነ እስክንድር ሲሉት ግን ተከረቸመባቸው።
~ ኮሎኔሉ ዛሬም አስረግጠው ተናግረዋል ። ” የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመራችንና ልማታዊ መንግሥታችንም ይቀጥላል ” ። የህዝቡም መከራ እንደዚያው ይቀጥላል ። ፔሬድ አለ ፈረንጅ ።
~ አዲስ ነገር ከመጣ ግን ሂሴን ለመዋጥ፣ ድንጋይ ተሸክሜም ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ። መንጋው ስለተንጫጫ ግን እኔ አቋሜን አልቀይርም። አከተመ።
ሻሎም ! ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ ።
መጋቢት 24/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ ።