>
4:18 pm - Tuesday July 5, 2022

የኤርሚያስ እይታና የአድርባዮች ጫጫታ !!! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

የኤርሚያስ እይታና የአድርባዮች ጫጫታ !!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ኤርሚያስ ለገሰ የ27 አመቱን የሸፍጥ ፖለቲካ በትኖ በማሳየት የፈጠረው እውቀትና ንቃት አምሳያ የለው:: የሕወሃትን ገበና ገልጦ የአውሬነቱን ልክ እንድናይ በማድረግ ያደረገው ጥረት ከቃላት በላይ ነው::
ኤርሚያስ ደራሲ ተንታኝና ብቁ አሰላሳይ ፖለቲከኛ በመሆን ብዙ አስተዋጽዖ ለትግሉ እበርክቷል:: በስህተት ጎዳና የጀመረው ፖለቲካ በግዜ ተለውጦ ወደ ሕዝባዊና ሃገራዊ የፖለቲካ ማማ ጫፍ አድርሶታል:: በዚህም ጉዞው እንደ ወንድማማችነታችን እየተስማማንም እየተጋፉንም የቃሉን ትምህርት ሰምተን የአይምሮውን ጭማቂ አንብበን ብዙ ተምረናልና አውቀናልም::
የኤርሚያስ የቀድሞ ጏዶች ዶር አብይና የቲም ለማ ቡድን የሕዝብን ትግል ተጠቅሞ ላስገኛቸው በጎ ውጤቶችና በስልጣናቸው ማግስት ባሰሟቸው ተስፋ ሰጪ ንግግሮች መላው ሕዝባችን መሪ አርጎ በፍቅር ለመቀበል ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታና  ያለፈ ታሪካቸው ላጣራ አላለም:: ለማወቅም አልፈለገም::
ከግዜ በሗላ በኦሮሞ የፖለቲካ ሰፈር የታየው እግላይ ጠቅላይ ፀረ ሕዝብ አካሄድ የፈጠረው ቅሬታና መጠራጠር ሕዝባችን ድጋፋን  እንዲያነሳና የተቃውሞ ድምጹን እንዲያሰማ አስገድዶታል::
በሞቀ የሕዝብ ፍቅርና ድጋፍ ወራት የተሻገረው የዶር አብይ አመራር የተቃውሞ ድምጾች ሲያሸብረው ግራ የተጋባና የተሳከረ መግለጫና ማብራሪያ በመስጠት የደረሰበትን ተቃውሞ ለመከላከል በሄደበት አቅጣጫ ሌላ የውዝግብ እጀንዳን ፈጥሯል::
ይሄውም ዶር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በሰሩበት ስመ ጥፉው ኢንሳ የሚባለው ተቋም ውጤታማና ለሃገር የሚጠቅሙ ስራዎችን እንደሰሩ በገጽታ ግንባታ መልክ ፊልሞችን ማውጣት ጀመሩ::
ጋዜጠኛ ኤርሚያስ ይህን መሰሉ የገጽታ ግንባታ ሞራል የጎደለው ሙሉ እውነት ያልሆነ ፕሮፓጋንዳ የሚያቀርቡት ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ካልሆነ ግን የዶር አብይን ገበና የሚገልጥ መረጃ ለመልቀቅ ኢሳት እንደሚገደድ አሳወቀ :: በዚህም ከያቅጣጫው ተቃውሞና ድጋፍን ቀሰቀሰ::
ዲሞክራሲ ያልገባቸው የሚድያን ሚና ያልተረዱ በስሜት የሚጏዙ የአብይ ደጋፊዎች በአደባባይ ኢሳትን ለቆ እንዲወጣ ከመጠየቅ እስከ ስድብና ዛቻ ደረሱ::
ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ግን ኤርሚያስ ትላንት የነጻ አውጪውን ጦር እንመራለን ይሉ ለነበሩት የአየር ባይር የሕልም አለም ሠራዊት አዛዦች የስብሰባቸው ማድመቂያ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻቸው አውራና የፕሮፓጋንዳ ስራቸው ማጣቀሻ ነበረ:: እነዚሁ ነጻ እውጪዎች ሚናቸውን ስተው ትጥቃቸውን ብቻ አይደለም ሱሪያቸውን አውልቀው ሕዝብ ሲፈናቀል ምንም ያላሉትን ዛሬ ላደሩለት ቡድን ጠበቃ ሆነው የትላንት ልሳናቸው ሆነው ያገለገሉትን በያዙት የተለየ አቋም ብቻ ነጥለው ለመከራከርና ለማስተባበል ሲሞክሩ በማየታችን ለነሱ እኛ አፈርን::
ኢንሳ  ሕወሃት ሃገር ሊያፍን ያቋቋመው የጭለማ ተቋም ነው:: እንኳን በፖለቲካው መስመር ለቆየው ይቅርና ማንም ተግባሩን የሚረዳው የአፈና ተቋም ነው: ምንም ለበጎ አላማ የሚጠቅሙ ውስን ተግባሮች ቢኖሩትም ዋናው ግቡ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ማጥመድ ለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም:: ይሄን መካድ ቄራ እየሰሩ ምንም እርድ አይካሄድም ብሎ የመከራከር ያህል ነው::
ተቋሙ የአፈና ጠቅላይ ሚንስትሩና ቡድናቸውም ሕዝብን ሲዘርፍና ሲጨፈጭፍ የኖረው ኢሕአዴግ ተብዬው የሕውሃት ኩባንያ ነባር አባላት ናቸው:: ይሄ ሃቅ ማንም አልጠፋውም :: ጉዳይም አድርጎ አልያዘውም:: ትላንትን ለታሪክ ትቶ ነገን የተሻለ ለማድረግ ከይቅርታ በብዙ ማይል እርቆ ፍቅሩን መቀበሉን ከመግለጹ በላይ ከሰማይ የወረዱ የድህነት መሪዎች አድርጎ  አብይና ቡድኑን ተቀብሏል::
ማናቸውም ስለ ትላንት ሊነግሩን የሞራል ብቃት የላቸውም:: ትላንትን ሕዝባችን የሚያስብበት ምንም ትዝታ የለውም::  ሕዝባችን ከመሪዎች የሚጠብቀው ለቃላችሁ መታመንን ለአቋማችሁ በጎነትና ለተግባራችሁ ቁርጠኝነትን እንጂ ያለፈ ማንነታችሁ አይደለም:: አሁንም ግራና ቀኝ መርገጣቸውን አቁመው መስመራቸውን ካስተካከሉ ሕዝብ ፍቅርና ድጋፋን ለመስጠት ዝግጁ ነው::
እንዲያውም ዶር አብይና ኦቦ ለማ ቢችሉ በግቢያቸው ያሉትን ከደርዘን በላይ  የስብስቴ ዘመን
ትላንት ላይ የተቸከሉ የታሪክ እስረኞችና ሕዝብን ለማፉጀት መቃብር የሚምሱ ጨለምተኛ የፖለቲካ ነጋዴዎች የፖለቲካ ተሃድሶ ጸበል አስረጭተው ከቆሙበት 18ኛው ክፍለ ዘመን ወደ 21 ክ/ዘ እንዲሸጋገሩ ቢረዷቸው እነሱም የሚቸገሩበት ወጥመድ ይሰበራል:: ሃገርም ከጭለማ ሃሳብ ትፈታለች::
ኤርሚያስ ለገሰ ባነሳህው ሃሳብና ባሳየው አቋም ጸንተህ የስርአቱን ጉድፍ እየነቀስክ የሕዝብ እገልጋይነትህን ቀጥል:: የያዝከው መንገድ ካድርባዮች ይልቅ ትችትህ ለመሪዎቹ ንቃት ያለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው:: ቢዘገይም እውነተኛ ሕዝባዊነት መሪዎቹ ካላቸው እንደሚያመሰግኑህ አልጠራጠርም::
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
Filed in: Amharic