>

አንድም ንጹህ በሌለበት ሁሉም ከሳሽና ወቃሽ መሆኑ ለአገር አይበጅም!!! አማረ ተግባሩ (ዶ/ር)

አንድም ንጹህ በሌለበት ሁሉም ከሳሽና ወቃሽ መሆኑ ለአገር አይበጅም!!!
አማረ ተግባሩ (ዶ/ር)
አቶ ለማ መገርሳ ተናግረዋል።  ይህንን ልብ የሚነካ  ንግግራቸውንም አዳምጠናል። ቀደም ሲል በኦሮምኛ የተናገሩትንና “በድብቅ የተቀዳ” ተብሎ የአማርኛ ትርጉምም አብሮት የተለቀቀውንም አዳምጫለሁ። በይዘት አንድ ሲሆኑ ሁለቱም ልብ የሚነኩ ነበሩ። ትንሽ ቀደም ቢሉ ጥሩ ነበር። በቃል አቀባይ መግለጫ መስጠት ይበልጥ ጥርጣሬን ከማማባሱም ያለፈ  የቃል አቀባዩም መግለጫ እንደፉከራ ይከጅለው ስለነበር አቶ ለማ ላይ  የተሰነዘረው ቁጣ እንዳውም ይብሱን እንዲያሳምማቸውና አንዲጎዱበት ከማገዝ ያለፈ  ብዥታውን በማፅዳት ቅቡልነታቸው ለማደስ የረዳቸው አለመሰለኝም።
 ያስታወሰኝ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አፍ እላፊ ይናገሩና የዋይት ሃውስ ቃል አቀባያቸው ሳራ ሳንደርስ ብቅ ብላ በጋዜጣዊ መገለጫ ከማስተባበል ያለፈ ሜድያውን ስትወርፍና  ፕሬዝደንቱ የታወቁበትን alternative fact የምትተችበትን አጋጣሚ ነበር።  አሁን ግን እሳቸው ራሳቸው ተናግረዋል። ለማሰላሰል ጊዜ አግኝተው በርጋታና በሚገባ ተዘጋጅተው ጉዳያቸውን ለህዝብ ለማቅረብ  የረዳቸው ይመስለኛል።
በራሱ ህሊና ብቻ እየተመራ ነገሮችን ለመገመት ለሚሞክርና ለምንም አይነት political correctness ለማይጨነቅ፣ ማን ወደደኝ ማንስ ጠላኝ ብሎ ለማያሳስበው ወገን  ንግግራቸውም የሚያረካ አይደለም ማለት የሚቻለ አይመስለኝም። በበኩሌ ርካታ ብቻ ሳይሆን ተነክቻለሁ።
አቶ ለማ መገርሳ ላይ ይህ ነው የማይባል ተፅዕኖ በማሳደር እሮሮውን ያሰማው ወገንና እሳቸውም የህዝብ እሮር በመስማት አጥጋቢ መልስ ስለሰጡ ደስ ሊላቸውና ተንፈስ ሊሉ ይገባል። ልብ በሚነካ ንግግራቸው ያላነሱትና ስሜትና እምነታቸውን ያልገለፁበት ጉዳይ የለም። በተለይም ከህፃን እስከ ወጣትና ጎልማሳ ዕድሜ ድረስ የሚደረሰውን ያገራችንን ትውልድ በጥላቻ መርዝ ተኮትኩቶ እንዲያድግ የተሰራውን ጥፋት አንድ ባንድ ዘርዝረዋል። አልፈው ተርፈው ያልሆነና ያልተደረገ ጡት ቆረጣ ድረስ የሚደርስ ታሪክ እየተፈጠረ፣ ለቂምና ጥላቻ ሃውልት ድረስ የቆመለትን ጉዳይ በጋለ ስሜት በማውሳት ከዚህ ለመውጣትና በዚህም በጥላቻ ስሜት የሚገፉ ወገኖችን በጥንቃቄ በመያዝ በኩል ዋጋ የተከፈለበት እንደነበር ነግረውናል። ማንም የማንንም ኢትዮጵያዊነት የማፅደቅም ሆነ የመግፈፍ መብት ሊኖረው እንደማይችል፣ የሳቸው ኢትዮጵያዊነት የግድ የሌላው ዜጋ ቀጥታ ግልባጭ ሊሆንም እንደማይገባው በሰፊው ዘርዝረዋል። መልሰውም መላልሰውም  ከኢትዮጵያዊ ሱሳቸውን ማንም ሊያላቅቃቸው እንዳምይችልና የማንንም አወንታም ሆነ አሉታ የሚጠይቁበት ጉዳይ እንዳልሆነ ደጋግመው አስምረውበታል።
 ከዚህ በኋላ የሚከተለው ተግባር ነውና ይህኑኑ  በሚችሉት ሁሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በጥሞና መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። የህዝብን ጩኸት ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ጊዜያቸውን ወስደው ለማሰላሰልና በዚህ መልክ ምላሽ በመስጠት በመድፈራቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
አላጠፋሁም ወይም አላጠፋም አለማለታቸው ትልቅ ነገር ነው። ሰው ነኝና የመሳሳት መብቴ ሊከበርልኝ ይገባል ብለዋል። “አንድ ሺህ ጊዜ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ብዬ አንድ ጊዜ ብሳሳት እንዴት አንድ ሺው በዜሮ ተባዝቶ ዜሮ” ተብዬ እረገማለሁ ማለታቸውን የመፀፀት እንጂ በመከላከያነት የቀረበ አድርጎ ለመውሰድ ተገቢ አይመስለኝም።
 በእኔ አስተያየት ከዚህ በኋላ ወደኋላ በመመለስ “ሌላም መረጃ አለን” ፣ “በዚህ ጊዜ ከእከሌ ጋር ይህን ብለሃል” ወዘተ እየተባለ ወደትናንት በመመለስ መወነጃጀል ምንም ጠቀሜታ እንደሌለው መገንዘብ አስተዋይነት ነው። በኢትዮያ የፓለቲካ ታሪክ ውስጥ እጃችንን ለአንድ ሰሞን ያስገባን ማንኛችንም ብንሆን የሕይወት ታሪካችን እንደበረዶ የነፃ ነው ብሎ ማለት ሃቀኝነት የጎደለው ሸፍጠኘነት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በኢህዴግ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ሃላፊነት ከተረከበ አንስቶ እስከወረዳና ቀበሌ ድረስ ትንሽም ብትሆን በነበረው ስልጣን ሲያስርና ሲገርፍ የነበረው፣ በመነካካት ሱቅ የከፈትና ፎቅ የገነባ፣ ያለምንም ተፎካካሪነት ጨረታ ሲያሸንፍ የኖረ፣ ጉቦ እየተቀበለ የድሃ ገበሬና ከተሜ ቤትና ቦታ የቸበቸበ አንዳቸውም ቢሆኑ የህይወት ታሪካቸው ሆነ የብሔር ማንነታቸው ቢመረመር አንድም ንፁህ ይገኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
  ዘመኑ በፈጠረልን ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም መንግስትን ተጠያቂ በማድረግ የሚደመጠውም ወገንም መካከል ቢሆን  ዛሬ በሚሰራው  ስራ ይመሰገን እንደሆን እንጂ በትላንቱ ታሪኩ መኩራራት የሚችል ሁሉም እንዳልሆነ የሚታወቅ ይመስለኛል።    የአቶ ለማ ተፅዕኖ ፈጣሪነትና ስልጣናቸውን ታች ድረስ ለማውረድና ለመደመጥ ከቻሉ ውሎ አድሮ የምናየው ጉዳይ ነው። የማፈናቀሉና ህዝብን፣ ታሪክና ባህልን የማፅዳቱ ጉዳይ ይሰክናል ብዬ ተስፋ በማድረግ አቶ ለማ ቃል እንደገቡት ሰላማዊውና ደምራሲያዊ ሽግግሩ የተሳካ በማድረግ በታሪክ የሚታውሱ ጀግና ከመሆን ወደኋላ እንዳይሉ፣ ሸርተት ያሉም እንደሆነ ሜዲያው ምህረት የለሽ መሆኑን እንደተገነዘቡት አምናለሁ።
የጠ/ሚ  አብይም አረመመድ ከመወለጋገድ ይልቅ ሚዛኑን ጠብቆ በሰከነ መንፈስ ሽግግሩን ለመራት የአቶ ለማ መገረሳ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትና የመደመጥና የመከበር ሃይል ያስፈልገዋል። የለማ ድካም ማለት በብዙ መንገድ የአብይ መወላውል ማለት ይመስለኛልና አቶ ለማ የተናገሩትን በተግባር ሳይውል ሳያድር እንዲተረጉሙ  ብርታቱን ይስጣቸው። እኛም ድጋፋችን አየለየትም።
  ለሰላም አኩልነትና የህግ የበላይነት የታዩትም ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ለምንም የማይንበረከኩ ሆነው እንዲለመልሙ እርሶም ሊያግዟቸውና እንደ ባለድርሻ አካል እያቀረቡ በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ቢያነጋግሯቸው ችግሮቹ ከመካረራቸው በፊት ማብረጃውን ቀድሞ ለማግኘት የረዳል የሚል ሃሳብ አለኝ።
Filed in: Amharic