>

ላይኛው ግቢ (ያሬድ ጥበቡ)

ላይኛው ግቢ
ክፍል 3
ያሬድ ጥበቡ
(ክፍል 1 እና 2 “ደመቀ ያቺን ሰአት” በሚል ርእስ ሥር ተተውኖ ነበር። ላይኛው ግቢ የዚያ ተውኔት ተቀፅላ ነው ። ላይኛው ግቢ ዱሮ በንጉሱ ዘመን የምንሊክ ቤተመንግስት መጠሪያ ነበር ። ደመቀ ያቺን ሰአት ላይ የተጠቀምኩበትን እውነተኛ የባለሥልጣናት ስም በፈጠራ ስም መለወጥ ይሻላል በሚል ተስተክክሏል)
—-
ለሜሳ፣ ደምመላሽ፣ ዘቢባና አንዳርጌ ከስብሰባው አዳራሽ ተቀምጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ነቢይን እየጠበቁ ነው ። በመሃላቸው ያለው ፀጥታ መርፌ ቢወድቅ እንኳ የሚሰማበት አይነት ነው። ከደቂቃዎች በኋላ የክፍሉ በር ሲከፈት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ መካከለኛ እድሜ ላይ ያለ ፣ የለበሰው ገበርዲን ከሩቅ አለሁ አለሁ የሚል ቁመቱ ሜትር ከ75 የሚሆን ሰው አስከትለው ገቡ ። “ለምን ይዞት መጣ ይሆን” በሚል ጥያቄያዊ ገፅታ ሁሉም ከመቀመጫቸው ተነስተው ቆሙ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብሯቸው የመጣውን ሰው “ጀሚልን አብራችሁት ሠርታችሁ ባታውቁም ፣ ያው ኢትዮጵያችን ያላት ትልቁ ኢኮኖሚስታችን መሆኑን ታውቃላችሁ። እንግዲህ ከአሁን በኋላ ወርቅነህን ተክቶ አብሮን ይሠራል” ብለው ካስተዋወቁት በኋላ ወንበራቸውን እየሳቡ ሁሉም እንዲቀመጡ ጋበዙ።
ደመላሽ፣ ጀሚል እንኳን ደህን መጣህ። (ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተመለከቱ) አብሮን ይሠራል ስትል ግልፅ አይደለም፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ያማክረናል ማለትህ ነው ወይስ ወርቅነህን ተክቶ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናል ነው የምትለው እስቲ ግልፅ አድርገው።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ በአንድ በኩል ልክ ነህ በኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮችም ያማክረናል፣ ሆኖም መጀመሪያ እንዳልኩትም ወርቅነህን ተክቶ የቲም ለሜሳ አባል በመሆን አብሮን በቅርበት ይሠራል ማለቴ ነበር ። የውጪ ጉዳይ ቦታማ ያው እንደምታውቀው በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ በሚደረግ ድርድር የሚሾም ነው። ባለፈው እዚህ እኛ የተስማማንበትን ያ የተቀናቃኝ ፓርቲውን የሚመራውን ፕሮፌሰር እጩነት ለነደብረፂ ባቀርብላቸው ሞተን እንገኛለን፣ በኛ ላይ ያለው ጥላቻ ሥር የሰደደ ስለሆነ እርሱን እሾማለሁ ካልክ ህወሓትን ከግንባሩ ገፍተህ እንዳስወጣኸው ቁጠረው ብለው ግግም ብለዋል።
ደመላሽ፣ እኔም በወሎዬነት ቀርቤ ላነጋግረው በሚል ጌታቸውን አነጋግሬው ነበር፣ ግን ካንተ የተለየ መልስ አላገኘሁም ። “ሞት ያስፈረድንበትንና ንብረቱን ያስወረስነውን ሰው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አድርጋችሁ ስትቀርቡ አታፍሩም?” ብሎ በሃይለቃል ነው ያናገረኝ። እናንተስ ማንን ታቀርባላችሁ ስለው ማን ቢለኝ ጥሩ ነው?
ዘቢባ፣ የኦነግን ሊቀመንበር ቢልህ አይገርመኝም።
ደመላሽ፣ በምን አወቅሽ?
ዘቢባ፣ የሠላም ሚኒስትር መሆኔን ትዘነጋለህ ልበል? ኢንሳ እኮ በእኔ ሥር ነው። ስቀልድህ ነው፣ የጌታቸውን ሽሙጥ ስለምረዳ ነው የገመትኩት።
ለሜሳ፣ የሹመቱን ጉዳይ ኋላ እንመለስበታለን። እስቲ አዲሱን የቲማችንን አባል ማንነት ትንሽ ለማወቅ እድል ቢሰጠን ።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ ልክ ነህ ለሜ፣  (ወደ ጀሚል ዘወር በማለት) ከፅንስህ እስከ አሁኗ ቅፅበት ያለህን አስገራሚ ታሪክ እስኪ ንገራቸው፣ ሁለት ደቂቃ ሰጥቼሃለሁ)
ጀሚል፣ አመሰግናለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በሁለት ደቂቃ ምን ያህል እንደሚነገር ባላውቅም ልሞክር ። የ41 ዓመት ጎልማሳ ነኝ። እናቴ ከሱማሌ፣ አባቴ ከትግራይ ናቸው። አባቴን በወሬ እንጂ በዓይነሥጋ አላውቀውም። ቀብሪደሃርን ከዚያድባሬ ጦር ያስለቀቀው ክፍለጦር ውስጥ መቶአለቃ እንደነበርና፣ በኢህአፓ አባልነት ተጠርጥሮ መረሸኑን ብቻ ነበር የማውቀው። አሁን በቅርቡ ነው ከውጪ ከተመለሱት ኢህአፓዎች እውነተኛ ታሪኩን የተረዳሁት። አባቴ ተወልዶ ያደገው አዲግራት ከተማ ነው። ጎበዝ ተማሪ ስለነበር እዚያ ያሉ የካቶሊክ ሚሽነሪዎች ለውጪ ትምህርት ወደ ጣሊያን ይልኩታል። በጣሊያን ቆይታው የኢህአፓ መረብ ውስጥ ይጠለፋል። ፍልስጤም ውስጥ ልዩ ስልጠና ይሰጠውና ወደሃገር ቤት ይመለሳል። በ1969 የሱማሌ ወረራ ሲመጣ ደርጉ የሐረር ጦር አካዳሚን በር ብርግድ አድርጎ ሲከፍት ኢህአፓ ጦሩን ለመቆጣጠር በነበራት ስልት ብዙ አባሎቿን የመኮንነት ሥልጠና እንዲወስዱ ትመድባለች። አባቴም ከነዚህ ሰልጣኞች መሃል ነበር። ሥልጠናውንም ጨርሶ ቀብሪደሃርን የተቆጣጠረውን የዚያድ ባሬ ጦር ለማስለቀቅ ተልእኮ ይሰጠዋል። ግዳጁንም ይፈፅማል። ከእናቴም ጋር የተዋወቁት በዚያን ወቅት ነበር። ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። አባቷ ሱቅ ስትሰራ እቃ ለመግዛት መጥቶ የተዋወቃት ወጣት ጋ በፍቅር ከነፈች። ከዚያ ፍቅር እኔ ተፀነስኩ። እናቴ በእርግዝና ላይ እያለች ቀብሪደሃር የሰፈረው ጦር ውስጥ በተካሄደ “አናርኪስቶችን  የማጋለጥ” ዘመቻ አባቴ የኢህአፓ ሰርጎገብ ነህ ተብሎ ተያዘ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሊቀመንበሩ በተገኙበት እንዲረሸኑ ተደረገ። “ወንድ ልጅ ከወለድሽ ስሙን ጀሚል በይልኝ፣ ሴትም ከሆነች ጀሚላ በያት” ብሎ መናዘዙን ጓደኞቹ ነግረዋት ስወለድ ጀሚል ብላ ጠራችኝ። በፍቅረኛዋ መረሸን የተደናገጡት አባቷ አዲስ አበባ አምጥተው ወንድማቸው ቤት ደበቋት ።  የተወለድኩት እዚህ አዲስ አበባ ከአሜሪካ ላይብረሪ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የአትክልት ተራ አካባቢ ነው። የእናቴ ዘመዶች ሃብታሞች ስለነበሩ እናቴን ለማቋቋም ጊዜ አልወሰደባቸውም። የአምስት አመት ልጅ እያለሁም እናቴ ሃብታም ነጋዴ አገባች ። ትምህርቴን የተከታተልኩት ሳንፎርድ የእንግሊዝ ትምህርትቤት ነው። ኮሌጅ ያጠናቀቅኩት ለንደን ስኩል ኦፍ ኢክናሚክስ ነው። ላለፉት ሃያ አመታት ሃገሬን በሙያዬ በማገልገል እስከ ረዳት ሚኒስትር ደረጃ ደርሻለሁ። ዶ/ር ነቢይ ለከፍተኛ ሃላፊነት ሲያጨኝም ሃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም ለቲማችሁ ይዤው የምመጣው እሴት ስላለ በታላቅ ደስታ ነው የተቀበልኩት።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ ትምህርትህ፣ አስተዳደግህ፣ ከሱማሌና ትግራይ የቢዝነስ ኤሊት ጋር ያለህ ትስስር፣ ከውጪ ኢንቬስተሮችና የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ጋር ያለህ ትውውቅና መረብ ለቡድናችን የሚጠቅም አሴት ወይም ተጨማሪ እሴት ሰለሆነ ነው እኔም ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት ያጨሁህ፣ አንተም እንደማታሳፍረኝ እርግጠኛ ነኝ፣ የቡድኑም አባላት እንደሚደሰቱ አምናለሁ።
ለሜሳ፣ ነብ፣ ጥሩ ምርጫ አድርገሃል። በአባቱ የትግራይ ሰው መሆኑም፣ “እኛ ተገለልን” እያለ ለሚያለቃቅሰው የመቀሌ ቡድን ይጠቅማል።
ዘቢባ፣ እኔም እንደ ባልደረቦቼ የቡድናችን አባል በመሆንህ ደስተኛ ነኝ። አንድ ምናልባት ቅር የሚለኝ አሁን ግለታሪክህን በአጭሩ ስትነግረን አባትህ ሃገሩን ከወረራ ሊታደግ ወጥቶ በራሱ መንግስት አመራር በረሃ ላይ መቅረቱ በእድገትህና ሥነልቦናሀ  ላይ ያሳደረው ጠባሳ ካለ የሚል ስጋት ብቻ  ነው ያለኝ ። ያው እንደምታውቀው በእኔ ሥር የደህንነት መረባችን አለ። አሁን ሽግግሩን በሃሳብ የሚገዳደሩ ወጣቶች፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች ወዘተ እነማን እንደሆኑና በጋራስ የሚያስተሳስራቸው ምን እንደሆን ጥናት አስደርገን (የውጪ ሃገር   ባለሙያዎችን ያካተተ ጥናት) ብዙዎቹ አባቶቻቸው በሱማሌ፣ በኤርትራ ወዘተ በረሃዎች የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ተዋግተው የወደቁ ጀግኖች ልጆች መሆናቸውን ተረድተናል ። አባቶቻቸው የወደቁላትን ኢትዮጵያ ሊሞቱላት የተማማሉ ነው የሚመስለው። የአርበኝነት ስሜታቸው ሰማይ የነካ ነው። አንተም አባትህን ስትራብ የኖርክ ሰው ልትሆን ስለምትችል አርበኝነትህ ችግር እንዳይሆን በሚል ነው ይህን ማንሳቴ።
ጀሚል፣ ልክ ነሽ የወላጅ ነገር የማይጠፋ ቁስል ነው። ይዳፈናል እንጂ አይከስምም። አባቴን ስፈልገው ነው የኖርኩት። ሆኖም ሩጫዬን ጨርሻለሁ።  ሱማሌዎች መሃል ሙስሊም ማህበረሰብ ውስጥ ማደጌም የአባቴ ረሃብ ላይ የራሱን ልጓም ሳያደርግ ይቀራል ብለሽ ነው? አሁን ደግሞ ይህን ለውጥ በዴሞክራሲያዊ ግብ ካጠናቀቅነው፣ ከዚያ የተሻለ ስጦታ ለአባቴ የማበረክትለት አይኖርም ብዬ አስባለሁ፣ የጠቅላያችንንም ጥሪ የተቀበልኩት በዚያ መንፈስ ነው ።
ዶ/ር ነቢይ፣ በጀሚል ትውውቅ ላይ በቂ ጊዜ ያጠፋን ይመስለኛል፣ እስቲ አሁን ወደ እለቱ አጀንዳ እንሸጋገር። የለሜሳ ታሪካዊ ንግግርና የቲም ለሜሳ ቁመና ፣ የባለ አደራ ጉዳይ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሹመት ሌላ አንገብጋቢ አጀንዳ ካላችሁ እድላችሁ አሁን ነው።
አንዳርጌ፣ የሰጠኽን ከበቂ በላይ ነው። እንደ ኢንፎርሜሽን እነዚያ ባህርዳር መሳሪያ ታጥቀው የፕሮፌሰሩን ስብሰባ የረበሹ ወጣቶች ጉዳይ እየተጣራ ነው ። እነማን እንደሆኑ ታውቋል። ለጊዜው የክልሉ ፀጥታ እንዳይያዙ ያደረገው ከዚያ ቀን በፊትም ሆነ በኋላ የነበሯቸውን የስልክና የአካል ግንኙነቶች እስክናጣራና በተለይ በህጋዊ ከተደራጁ አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ፍንጭ እስክናገኝ እየጠበቅን ነው እንጂ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወሰድ ተነግሮኛል።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ ግሩም። ያ በብርሃን ፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው የተባለው የቲም ለሜሳ ሁኔታ ከእኔና ከለሜሳ ንግግሮች በኋላ በምን ላይ ይገኛል?
ደመላሽ፣የለሜ “አሁንም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ንግግር ተወዶለታል። በተደጋጋሚ የሰማሁት ያንን ነው። በግሌም በንግግሩ እጅግ በጣም ደስተኛ መሆኔን መግለፅ እወዳለሁ።
ዘቢባ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን ለመገምገም እንዲያስችለን ከየማህበረሰቡ ከህዝቡ ስብጥር ጋር የሚመጣጠኑ የማህበራዊ ሚዲያ ፊታውራሪዎችን መርጠን የነርሱን ትችት የምንለካበት ሜትሪክስ አዘጋጅተናል ።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ ጀሚል ለምታወሪው ነገር አዲስ ስለሆነ ትንሽ ስለሜትሪክሱ ዘርዘር አድርገሽ ንገሪን እስቲ፣ ለኛም ማስታወሻ ይሆነናል።
ዘቢባ፣ እሺ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ሆኖም በፓወር ፖይንት ካልተደገፈ በዝርዝር ለማውራት ስለማይመች በደምሳሳው ለማቅረብ እገደዳለሁ ። ይሄውልህ ጀሚል፣ ጉዳዩ እንዲህ ነው። የውጪ ኤክስፐርቶች ታክለውበት የሠራነው ሜትሪክስ ነው። ከ20 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸውን የማህበራዊ ሚዲያ ፊታውራሪዎች ቀስመን አወጣንና፣ እያንዳንዳቸውን ባላቸው  የተሰሚነት ደረጃ 1ኛ 2ኛ ወዘተ እያልን መደብናቸው። ለምሳሌ ጃዋር መሃመድ ከአንድ ሚሊዮን ተከታዮች በላይ ስላሉት አስር ከአስር ሰጠነው። የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ተፅእኖ እንደሚያደርግ ደግሞ ስንመዝን በዋና መልኩ ቄሮ ላይና የኦሮሞ ብሄርተኝነት ላይ ነው ተፅእኖው። እንደ ጃዋር ሚሊዮን ተከታዮች ባይኖሩትም ከሩብ ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያለው ልበ ብርሃኑ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ደግሞ አለ። ቴዎድሮስ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አቀንቃኝና የወያኔ ነው የሚለውን ህገመንግስት ለመደምሰስ የሚሟገት ነው። የቴዎድሮስ ተከታዮች አነስተኛ ቢመስሉም፣ የአዲስ አበባ ጉዳይን በሚመለከት ግን ያለው ተፅእኖ ከጃዋር ቢበልጥ እንጂ ያነሰ ስላልሆነ፣ እርሱንም አስር ከአስር እንሰጠዋለን ። እንዲህ እያልን በብሄረሰብ ማንነታቸው፣ ወይም በሚሟገቱለት ዓላማ እየለየን የተለያዩ ሜትሪክሶች ዲቨሎፕ አድርገን፣ ከዚያ በሚለጥፏቸው ሃሳቦች ተከታዪቻቸው የሚሰጧቸውን ድጋፎችና ተቃውሞዎች እንመዝናለን። በጣም ሳይንሳዊ የሆነ የሃሳብ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ሜትሪክስ ነው የፈጠርነው።
አንዳርጌ፣ አምጪዋ ታዲያ፣ ሜትሪክስሽ ምን ይላል ስለቲም ለሜሳ ቁመና?
ዘቢባ፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የአቶ ለሜሳ ንግግር ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅእኖ ፈጥሯል ። ሆኖም በተመሳሳይ የህዝብ ግንኙነቶች ካልተደገፈ እንደገና ሊያሽቆለቁል ይችላል የሚል ማጠቃለያ ላይ ነው ያደረሰን። ዝርዝር ሪፖርቱን በነገው እለት እናደርሳችኋለን።
አንዳርጌ፣ የአማራ ክልል ደህንነት ባደረገው ትንተና ለዶክተሩ ንግግር ከፍተኛ ድጋፍ ቢያሳይም፣ አቶ ለሜሳ “ከአውድ ውጪ ተወስዶብኝ ነው” ብሎ ያቀረበውን አልተቀበሉትም ። የቪዲዮ መረጃውም በሁሉም ስልክ ላይ ስላለ ለሜሳ በደምሳሳው “ሳንረዳዳ ቀርተን እንጂ መልእክቴ ያ አልነበረም” ብሎ ቢተወው የተሻለ ነበር።
ጀሚል፣ እኔም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተጠና የህዝብ አስተያየት መመዘኛ መንገድ ባይኖረኝም፣ እንደምታውቁት አፋን ኦሮሞ የሚናገረውም ሶማሌ በተለይ ቢዝነስ ውስጥ ያለው ብዙ በመሆኑ፣ “አቶ ለሜሳ ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው” የሚለው አስተያየት የሚያመዝን መስሎ ተሰምቶኛል። በአዲስ አበባ መታወቂያ ጉዳይም ወይዘሮዋን ውሸታም ከማስመሰል፣ ግድፈቶች ከነበሩ እየተጣራ ነው፣ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በአነስተኛና ጥቃቅን መሥራት ለጀመሩ የተወሰኑ የኦሮሚያ ወጣቶች ግን የከተማዋ ነዋሪዎች ባይሆኑም ወደፊት ቋሚ ነዋሪ መሆናቸው ስለማይቀር በጠራራ ፀሃይ መታወቂያ ሰጥተናል፣ የተላለፍነው የከተማዋ ቻርተር ካለ ህግን ተከትለን እርማት ይደረጋል ማለቱ የተሻለ ነበር ። ወንድሞቼ፣ ለትምህርት ለንደን በኖርኩባቸው ጥቂት አመታት ከፈረንጆቹ የተማርኩት ነገር ቢኖር፣ ፖለቲካ ስለ እውነትና ሃሰት አይደለም ። ፖለቲካ የማኔጅመንትጉዳይ ነው። የህዝቡን ተስፋውን፣ ፍርሃቱን፣ ቅሬታውን የማስተዳደር ጉዳይ ነው። በነገራችን ላይ በመንግስታችን ባለሥልጣናት ሁሉ ከክልል እስከ ወረዳ ማህበራዊ ሚዲያን የማይሰጠን የማጥላላት ነገር አለ። ለድህረ ምረቃ በሄድኩበት ወቅት ለሁለት ሳምንታት ዋሽንግተን ዲሲ ሄጄ ነበር ። ባረፍኩበት ጓደኛዬ የተነሳ ስለ ኢሳት ጋዜጠኞች የማወቅ እድል ነበረኝ ። ከእጅ ወደአፍ በሆነ ደሞዝ ነው  የሚተዳደሩት። አሁን ከመሃላቸው አንዱን ኤርምያስን ብንወስድ፣ የመጀመሪያውን መፅሃፉን ካሳተመ በኋላ ባገኘው ገንዘብ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በመከታተል፣ በዓመት ቢያንስ 70 ወይም 90 ሺህ ዶላር የሚከፈለው የሂሳብ መምህር መሆን ይችል ነበር ። ግን ያንን አልመረጠም። ድምፅ ላጡ ድምፁን ማዋስ ከግል ኑሮው መደላደል ይበልጥ የከበረ አድርጎ ስላመነ ነው፣ ለኢሳት የፖለቲካ ተንታኝነቱ ሙሉ ጊዜውን የሰጠው። ይህን ሁሉ የምዘበዝበው፣ የሰላ ሂስ ወይም ትችት ሲያደርጉብን ስለሚጠሉን፣ ወይም ስልጣናችንን ስለሚፈልጉ አድርገን ባናየውና፣ ማህበራዊ ሚዲያን ከማይሰይጠን፣ ጊዜው እንደመጣለት ሃይል ተቀብለን አብረነው ለመስራት እንድንወስን አቤቱታ ለማቅረብ ነው።
አንዳርጌ፣ የጀሚልን አለባበሱን አይቼ ይሄን ከተሜ ከየት አመጣብን ብዬ ነበር፣ ለካስ መፅሃፍ በሽፋኑ አይመዘንም የሚባለው እውነት ነው ። ከለመድነው የቡድን አስተሳሰብ እንድንወጣ ሳይረዳን አይቀርም ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለምርጫህ አመሰግናለሁ።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ እረ አይገባም፣ ሥራዬ አይደል እንዴ! ታዲያ አሁን ምን ብናደርግ ይሻላል ትላላችሁ?
ጀሚል፣ ህዝቡም ጋ ሆነ ማህበራዊ ሚዲያው ጋ ያለውን ቅሬታ በግልፅ መመለሱ የተሻለው መንገድ ይመስለኛል።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ ልክ ነህ ጀሚል። ነገ በሚሌኒየም አዳራሽ በሚደረገው የአንደኛ አመት በአል ላይ “የሚሠራ ይሳሳታል፣ የተሳሳተ ደግሞ ይቅርታ ይጠይቃል፣ ባለፈው ዓመት ብዙ ጠብቃችሁ ያልደረስኩበት ወይም ያላሟላሁት ነገር ቢኖር ለጎደለው ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብዬ ብናገር የሃገሬውን ቀልብ ይሰበስበው ይመስለኛል። ምን ይመስላችኋል?
ደመላሽ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ መሃሪ ህዝብ ነው፣ ደግሞም ይቅርታ እንድትጠይቅ ይጠብቅሃል፣ ፍርሀቴ ነገ ያንን ስትናገር በጭጨባ ብዛት የአዳራሹ ምሶሶዎች መነቃነቅ እንዳይጀምሩ ነው።
ዘቢባ፣ የእኔም አስተያየት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ነው።
ለሜሳ፣ ይሁን ግድ የለም ። እስማማለሁ፣ ሆኖም ለስህተታችን ይቅርታ የሚል ቃል መጠቀም የለብንም፣ ደካማ አስመስሎ ያቀርበናል ። አላማችን የህዝቡን መንገድ ተከትለን ለመሄድ ስለሆነ፣ ስለ ስህተት ሳናነሳ እንዲሁ በደምሳሳው “አምርራችሁ የምትተቹን ስለምትወዱን መሆኑን ስለምንረዳ ከሰቀላችሁን ማማ ላይ ገና ባለመድረሳችን ይቅርታ፣ በእናንተ ድጋፍ ግን ከዚያ ማማ ላይ እንወጣለን” በሚል መልክ ንግግሩ ቢቀረፅ ጥሩ ይመስለኛል።
አንዳርጌ፣ እኔም የለሜሳ አቀራረብ ይስማማኛል ። የከተሜውን ጥያቄ ለማሟላት ስንል የገጠሬውን እሴት እንዳናፈርስ መጠንቀቅ አለብን። አሁንም በወግአጥባቂ ባህል የተቀፈደደ ሃገር የምንመራ መሆኑን መርሳት የለብንም። ደካማ መስለን ከቀረብን ይንቁናል፣ ሚዛኑን መጠበቅ የግድ ነው።
ጀሚል፣ ሰናይ ቃላት ብቻቸውን ግን በቂ አይመስሉኝም። በተግባር መደገፍ ያለባቸው ይመስለኛል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የመጀመሪያው ፈተናቸው ከነገ ወዲያ በባለአደራ ምክርቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተገቢውን ጥበቃ አስደርገው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ መቻላቸውን ህዝቡ አተኩሮ የሚከታተለው ጉዳይ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ከዚህ በፊት ለእስክንድር ጋዜጣዊ መግለጫዎች መሰረዝ የደህንነት ስጋት ስለነበር ነው ብለን ለዓለሙ በመግለፃችን፣ አሁን እስክንድር የኛ ችግር ሆኗል። የእስክንድር ህይወት የኛ ሃላፊነት ሆኗል። ሳናስብበት ትልቅ ሃላፊነት እንደወደቀብን ልናውቅ ይገባል።
ጠ/ሚ ነቢይ፣ የባለአደራን ጉዳይ በሌላ ቀን እንወያይበት፣ አሁን ለነገው የአንደኛ ዓመት በአል የማደርገውን ንግግር ለማዘጋጀት ጊዜ ያስፈልገኛል ። የቀሩትን አጀንዳዎች ነገ ከበአሉ በኋላ እንወየየይባቸዋለን ። ስብሰባችንን ጨርሰናል፣ ደህና አምሹ ወዳጆቼ!
ክፍል አራት ከ21 ቀናት ፅሞና በሁዋላ ይቀጥላል ።
Filed in: Amharic