>

"እኛ ቤተመንግስት አንገባም፤ መግለጫም የምንሰጠው ህዝብ መሀል ነው!  (ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ  በቢሮው በሰጠው መግለጫ)

“እኛ ቤተመንግስት አንገባም፤ መግለጫም የምንሰጠው ህዝብ መሀል ነው! 
ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ  በቢሮው በሰጠው መግለጫ
ዛሬ በሰላማዊና ህጋዊ ትግል እንቅስቃሴ፣ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) እጅግ በጣም የተሳካ ጋዜጣዊ መግለጫ ማድረግ ችሏል፣ በጽናት እና በብርቱ ትግል የተደረገም ነውና ደስ ብሎናል።
በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት /ባልደራስ/በዛሬው እለት አራት ኪሎ በሚገኘው የእስክንድር ቢሮ ውስጥ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ በመግለጫው ላይም በርካታ የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች መገኘታቸው ተመልክቷል።
ባለአደራ ምክር ቤቱን በመወከል ጋዜጠኛ እስክንድር ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄዎች መልስ የሰጠ ሲሆን፣
ለአብነት…
“በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መግለጫ እንድትሰጡ መንግስት ፈቅዶላችሁ ነበር ። ለምን አልተጠቀማችሁበትም?” 
“እኛ ቤተመንግስት አንገባም ። የህዝብ ድምፅ ነን ። ለወደፊቱም ህዝብ መሃል እንጂ ቤተመንግስትም ሆነ ሌላ የመንግስት ተቋም ውስጥ ሆነን መግለጫ አንሰጥም!!! “
ምርጫ የመወዳደር እቅድስ የላችሁም??
በሚቀጥለው ምርጫ የመወዳደር ፍላጎት ፈፅሞ የለኝም እንደ አጠቃላይ እራሱ የባልደራስ ምክር ቤት የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ የለውም ። ባቋራጭ ስልጣን ለመንጠቅ የሚባለው ነገር ከንቱ ውንጀላና የተነሳውን የመብት ጥያቄ ለማዳፈን የቀረበ ምክንያት ነው ።
በመግለጫው ከተካተቱት ሀሳቦች በከፊል
~ በአዲስ አበባባና በኦሮሚያ መካከል ሊደረግ የታሰበ የአስተዳደር ወሰን ድርድር በሁለቱም ክልል በህዝብ የተመረጡ መስተዳድሮች እስኪሰየሙ ድረስ እንዲቆይ፣
~ የከተሞች የብሔር ስብጥር ለመለወጥ ሲባል የተጀመረው የሰፈራ መርሃ ግብር በህዝብ የተመረጡ መስተዳድሮች እስከሚሰየሙ እንዲቆም የሚሉ ሁለት ጥያቄዎችን ለመንግስት አቅርቧል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ በአንድ መድረክ ላይ ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ብለው ስለሰጡት አስተያየት የተጠየቀው እስክንድር መልስ ሲሰጥ “እንቅስቃሴያችን ሰላማዊና ሕጋዊ እንዲሆን ውክልና የሰጠን ሕዝብ ቃልኪዳን አስገብቶናል። ጦርነት ቢከፈትብን እንኳን ምላሻችን ሰላማዊ ነው። የሃሳብ ጦርነት ግን ልንፋለም እንችላለን” ብሏል።
“ባለ አደራው ምክር ቤት /ባልደራስ/ የተሰባሰበው በአስር ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ውክልና ስላለን ሞራላዊና ፖለቲካዊ ሕጋዊነት አለን፤ የከተማው ምክር ቤት ከንቲባውን ጨምሮ ይህ የለውም ብለንም እናምናለን” ሲልም ጨምሮ ተናግሯል።
በዚህ አጋጣሚ፣ በስፍራው የተገኝታችሁ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን እና ባለሞያዎችንን ከልብ ከልብ እናመሰግናለን።
 እንዲሁም ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመታደም የመጣችሁ በርካታ ግለሰቦች፣ መርሃ ግብሩ እንዲሳካ ደፋ ቀና ላላችሁና ሀሳቦቻችንን በመደገፍ ከጎናችሁ መሆናችሁን ገልጻችሁ በአጋርነት ለቆማችሁ በሙሉ [በሀገር ውስጥና ወጪ ሀገራት የምትገኙ ኢትዮጵያውያን] በሙሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ። በቅንም ሆነ በክፋት እሳቤ የነቀፋችሁንም ዜጎች ተጨማሪ ጉልበት ሆናችሁናል!
ሁሉንም ማድረግ ለሚችል ፈጣሪም ይመስገን!
መብትህን ደፍረህና ታግለህ እንጂ ቁጭ ብለህና ፈርተህ አታስከብረውም! ሰላማዊና ህጋዊ የመብት ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል። 
ዴል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ!
Filed in: Amharic