>

ተሳዳቢዎቹ ዲፕሎማቶች ወዴት ገቡ? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ተሳዳቢዎቹ ዲፕሎማቶች ወዴት ገቡ? 
የመንገደኛ ማስታወሻ ከጄኔቭ – ያሬድ ሀይለማርያም
በትላንትናው እለት በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል ውስጥ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ስለምትገመገም ለዛ የቅድመ ግምገማ መድረክ ነበር። ይህ ግምገማ በየአራት አመቱ የሚካሄድ ሲሆን በእንግሊዘኛው Universal Periodic Review (UPR) ይባላል። ይህን ሂደት ተገምጋሚውም ሆነ ገምጋሚዎቹ አገራት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እና ብዙ ገንዘብ አፍሰው የሚሳተፉበት ሂደት ነው። ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን የምትገመገመው ቀደም ባሉት በሁለቱ ግምገማዎች የመሳተፍ እድል ገጥሞኝ ነበር። በቀደሙት ግምገማዎች ወቅትም ሆነ በየጊዜው በመንግስታቱ ድርጅት ውስጥ በምናደርጋቸው የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ላይ ሁሉ በስድብ የሰለጠኑ እና የዲፕሎማትነት ክህሎት እንጥፍጣፊው እንኳ የማይታይባቸው ተሳዳቢ ካድሬዎች በየመድረኩ እየመጡ ስለመብት ጥሰት እንናገር የነበርነውን ሰዎች፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን እና ተወካዮቻቸውን ሙልጭ አድርገው ሰድበውን እና ስብሰባውንም እየረገጡ ይሄዱ ነበር። እኛ መብት በገፍ ተጥሷል ስንል እነሱ አይናቸውን በጨው አጥበው የፈጠራ ወሬ ነው ብለው ተሰብሳቢውን አዋክበው፣ ሌሎች ዲፕሎማቶችን አንጓጠው፤ እራሳቸን አዋርደው እና ኢትዮጵያንም አርክሰው ይሄዱ ነበር።
ትላንት ለመጀመሪያ ጊዜ እኛም በአገሪቱ ውስጥ የታዩትን አንዳንድ በጎ መሻሻሎች ስንገልጽ እና በአፋጣኝም መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች በገለጽንበት መድረክ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንኳ የሚመሰክር ካድሬ ድፕሎማት አልተገኘም። ከ50 በላይ የሌሎች አገሮች ዲፕሎማቶች በተገኙበት መድረክ በጄኔቫ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሽን አንድም ሰው ዝር አላላም። ከዛ ይልቅ የገረመኝ ከስብሰባው ስንወጣ ሁለት የሚሽኑ አባላት እዛው በራፉ ላይ ካለ ካፍቴሪያ ቁጭ ብለው ቡናቸው እየጠጡ ወጋቸውን ሲጠርቁ ማግኘቴ ነው።
ዲፕሎማቶቹ ካድሬዎች ስድብ ብቻ ነው እንዴ የሰለጠኑት? የመሳደቢያ መድረክ ሲጠፋ የዲፕሎማቲክ ስራቸው አበቃ ወይ? ብዮ እንዳስብ አደረገኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን በስብሰባው ላይ የነበሩ ታዳሚዎችም የተገምጋሚዋ አገር ተወካዮች ባለሞኖራቸው ሲደመሙ አስተውያለሁ። ለአገር እና ለሕዝብ ጥቅም የሚሰራ የዲፕሎማሲ ስራ በክቡር አምባሳደር አክሊሉ አብተወልድ ጊዜ ያከተመለት ይመስላል።
Filed in: Amharic