>

የጠ/ሚ አብይ ንግግርና እሚቀጥለው ምርጫ! (ደረጄ ደስታ)

የጠ/ሚ አብይ ንግግርና እሚቀጥለው ምርጫ!
ደረጄ ደስታ
ሰሞኑን በአቶ ለማና ዶ/ር አብይ ንግግር ተደብድበናል።  የጠየቁት ይቅርታና እሱን መሳይ ንግግራቸው ከተጋነነው ጥፋታቸው በላይ የተጋነነ መስሎኛል። ምናልባት ወደፊት ሊያጠፉት ከሚችሉት እሚታሰብ ተቀማጭ አድርገው ካልሆነ መቸም ለማይረኩ ተቃዋሚዎቻቸው ብዙም ባይደክሙ ይሻላቸዋል። እንኳን እሚጠሏቸው እምንወዳቸውም ብንሆን መቸም አንረካባቸውም። ችግሩ ውስብስብና ከአቅማችን በላይ ነው። በዚያ ላይ ደገፍናቸው እንጂ አልመረጥናቸውም። እንኳን ባልመረጡት፣ የመረጡትንም ቢሆን መቃወም የግድ በመሆኑ ነው ምርጫ እሚባል ነገር ያስፈለገው። ስለሆነም፣ አሁን ያለው ምርጫችን እነ አብይ መሆናቸውን መግለጻችን፣ ካሁን በኋላ ያሉትን የመምረጥ መብታችንን ማስከበራችን መስሎ ስለታየን ጭምር ሊሆን ይችላል። ፍሬ ነገሩ እሱ ነው ብዬ አስባለሁ። የፖለቲካ ሥልጣኔ መቋጫውም ሆነ መፋጫው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይመስለኛል። የዛሬ ዓመት ነው የተባለለትና ያልተዘጋጀንበት ቀጣዩ ምርጫችን ምን ይመስላል?
ዶ/ር አብይ በትናንቱ ንግግራቸው እንዲህ አሉ “በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድም በተለይ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ፍጹም ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ዳግም ለአፍሪካ ምሳሌ ለመሆን እንዲበቃ” መንግሥታቸው ይሰራል።  ይህ በመንግሥት ብቻ እሚሠራ ሥራ ይሆን? መንግሥት ትልቁንና ወሳኙን ድርሻ ሊጫወት ይችላል። መንግሥታችን ግን አንድ ለናቱ ፓርቲ ነው። ያውም ውስጡን ያላጠራ፣ በአዲስ ማኔጅመንት መከራውን እሚያይ እና ገና ተቀዶ እየተሰፋ ያለ ፓርቲ መሆኑን ከንግግራቸው ተረድተናል። ያም ባይሆን ደግሞ፣ በቃ ከዛሬ ጀምሮ እኛ ማስተዳደር አቅቶናል፣ ሰልችቶናል፣ ሥልጣናችሁን ተረከቡን …ይለናል ብለን አንጠብቅም። እንኳን ትንሽም ልምድ ያላቸው ቀርቶ፣ እሱን አመራር ለኔ አቀብሉኝ እኔ ልክ አገባዋለሁ እሚሉ ቆፍጣኖች ከየጉያችን ኩፍ ኩፍ ብለዋል። ስለዚህ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ምርጫ ባለመኖሩ ያላየናቸው፣ ብዙ አዋቂና እጅግ የተሻሉ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ግን ፈጥነውና ተቀናጅተው የመሰባሰብ ሳይሆን የመደራጀት ልምድ ያላቸው፣ ወይም የተደራጁ ድርጅቶች፣ ምን ያህል ይሆናሉ ብንባል፣ ምን እንላለን? ከሶስት የኮሚቴ ስብሰባ በኋላ፣ አገር ስጡን እሚሉትን፣ የውህደትና ልዩነት ወይም ውግዘትና መግለጫ እሚያንጋጉትን የገዛ አባሎቻቸውን ጋጠወጥነት እንኳ መቆጣጠር እማይችሉትን ሳይሆን፣ ነፍስ ያለው ሥጋና ተቋም ያላቸውን ደንዳና ድርጅቶችን ማለቴ ነው።
ይህን ጽሁፍ እስካዘጋጅ ድረስ 109 ፓርቲዎች አሉ እሚል ነገር ሰምቻለሁ። እነዚህ ኢህአዴግን ለብቻው ገጥመው ይችሉታል ተብሎ አይታሰብም። ወግ ተይዞ ቢያሸንፉ፣ ጥምር መንግሥት ይመሰርታሉ እንዳይባልም፣ በውህደት መሠረተ ሀሳብ ላይ እንኳ እሚያጠፉትን ጊዜና ዘመን ማየት ነው ። ለማንኛውም 109 ፓርቲ ጥምር ፓርቲ ሳይሆን ክምር ፓርቲ ነው። የእምቧይ ካብ። ከብዛት ጥራት ያልወጣው፣ እድሜ ልኩን ሲናጥ ደጋፊዎቹን አንጀት ሲልጥ እሚኖር አለመታደል ሆኗል። ይህ መሆኑ ሰዎቹ እየቀለዱ በብላሽ እያበዱ ነው ማለት ብቻም አይደለም። ድካማቸው መና የቀረም ብዙ ናቸው። ይህ መሆኑ የድርጅት ምንነትና ጠቃሚነት ያልገባው አባልና ደጋፊም መኖሩ ነው። ድርጅት ሲያጫርት እሚውልና እሚያድር መንጋ በመብዛቱም ጭምር እንደሆን መመርመር ነው። ይህ መሆኑም አንዱ ችግር ይመስለኛል።
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳን አንስተዋል። እሱን ማድረጋቸውና መሾማቸው ከቁርጠኝነታቸው አንዱን እሚያሳይ በጎ ነገር መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ግን  ምርጫው በምርጫ ቦርድ ኃላፊ በእመቤታችን ብቱካን ሚደቅሳ ጥንካሬ ብቻ አይሳካም። ነጻና ምርጫና ብላሽ ተቃዋሚ ብቻ ተደምሮ እሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም። እውነት ነው ነጻነቱን ስጡንና ተቃዋሚው ይቸግረን ይባል ይሆናል። በዚያ ላይ ሁሉም እሚጀመረው ከአንድ እርምጃ ነው። መንግሥትም ደግሞ በዚህ ተጠያቂ አይሆንም። ተቃዋሚዎችህን ኮትኩተህ ለወግ ምርጫም ሆነ ሥልጣን አብቃ ተብሎም አይባልም። ያን ያህል የዋህነት አይጠበቅበትም። ኢህአዴግ ካለው አቅምና አደረጃጃት ያውም፣ እነ አብይና ለማ፣ እንዲሁም አቶ ደመቀ እነ ዶ/ር አምባቸውም ሆኑ፣ ከአዳዲስ ኢህአዴግ አባላት አንጻር ሲታይ፣ ተስፋ እሚጣልበት ድርጅት እየሆነ፣ ራሱን እያፈረጠመ፣ በትችት እተየታከመ፣ በድክመታችን እያገገመ፣ እሚሄድ መለኛ ድርጅት እየሆነ ከሄደም በቀላሉ እማይነቀንቁት መሆኑን አለመጠራጠር ነው። ከጸሎት ሁሉ ግን አገር እሚመራውን ኢህአዴግን አሳስትልን፣ ደካማ ድርጅት አድርገህ፣ በወንጀል ንከርልን ብሎ ጸሎት፣ ይዞት እሚመጣውን ጣጣ ማሰቡ ነው። ኢህአዴግ ንጽህና እንጂ ወንጀል፣ ጥንካሬ እንጂ ድክመት ያነሰው ድርጅት አይመስለኝም። አብይ በንግግራቸው በተሳሳቱልን፣ ለማ በቀባጠሩልን ብሎ ስህተትን እንደ አሳ እያጠመዱ ጊዜ ከማጥፋት፣ መሠረታዊና እንደ ምርጫ ባሉ ትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ይበጅ ይመስለኛል። ውደቀትና ስኬታቸው እሚለካው አንድም በዚያ ነው ብዬ አስባለሁ።
Filed in: Amharic