>

«ኢትዮጵያዊነቴን ከኦሮሞነቴ ልነጥለው አልችልም!!! » (አቶ በቀለ ገርባ)

«ኢትዮጵያዊነቴን ከኦሮሞነቴ ልነጥለው አልችልም!!! »
አቶ በቀለ ገርባ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር
በእፀገነት አክሊሉ አዲስ ዘመን
.
የኦሮሞ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ማግሥት በሽብር ተጠርጥረው ከዓመት በላይ የታሰሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ቀጥለዋል። አዲስ ዘመንም በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮ ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርጎላቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ 
አዲስ ዘመን:- ከእስር ከወጡ በኋላ ያለዎት የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ይመስላል? 
አቶ በቀለ:- ከእስር ከወጣሁ በኋላ መጀመሪያ ወደ ውጭ አገር ነው ያቀናሁት፤ በዚያም አገሪቱ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምን እንደሚጠበቅ ከተለያዩ ኢትዮጵያውያንና ከአንዳንድ ተቋማት ተወካዮች ጋር ተነጋግሬያለሁ። ከዚያም ወደ አገር ቤት በመመለስ መደበኛ ስራዬን ጀምሬያለሁ፤ መደበኛውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመጀመሪያና በፊት የነበሩ ቢሮዎቻችንን በማንቀሳቀስ እንዲሁም አዳዲሶች የመክፈት ስራ ተከናውኗል።
በወጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አባላትን መመልመል ህዝቡን የማነጋገር ስራዎችም ተሰርተዋል። በሌላ በኩል በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍል የነበሩትን አለመረጋጋቶች ለማብረድ ከተሰማሩት ሰዎች መካከል አንዱ ሆኜም በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍሎች፣ እንዲሁም ነገሮች በጣም በተካረሩ ጊዜ በአባ ገዳዎች አማካይነት በተቋቋመው ካውንስል ላይ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል በመሆን የኦነግ ሰራዊት ያለበት ቦታ ድረስ በመሄድና ወደ ሰላማዊ የትግል መንገድ እንዲመለሱ የማድረግ ሚናም ተጫውቻለሁ። በአጠቃላይ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ አቅሜ የፈቀደውን ያህል በመሳተፍ ላይ ነኝ።
አዲስ ዘመን:- የብሔር ፖለቲካ ላይ ያለዎት አቋም ምን ይመስላል? 
አቶ በቀለ:- የአገራችን ፖለቲካ ህዝቦችን በአንድነት አቅፎ የመሄድ ባህል ያለው አይደለም። በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የሚካሄዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ በመካከል የሚረሱ የሚዘነጉ ችግራቸው በአግባቡ የማይደመጥ ጥያቄያቸው የማይሰማ የህብረተሰብ ክፍሎች ይፈጥራል፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ በብሔር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ማካሄድ መጥፎ ነው ብዬ አላስብም። ምክንያቱ ህብረ ብሔር ነን በሚል ስም የሚቋቋሙ ፓርቲዎች ነን የሚሉት ነገር በስራ የማይገልጹ ናቸው። በመሆኑም አሁን ያሉ ህብረ ብሔር ፓርቲዎች ሁሉንም ያቀፈ በትክክል ለሁሉም እኩል ተቆርቋሪ መሆን እስከሚችሉ ድረስ በብሔር የተመሰረተ ፓርቲ ወይም ፓለቲካ ስርዓት ይቀጥላል። ማንም ቢፈልግም ባይፈልግም የሚቀር አይደለም። ህዝብ ድምጹ እንዲሰማ ይፈልጋል፤ ይህንን የሚያደርግለት በሚጠፋበት ጊዜ ደግሞ የግድ ከውስጡ የፈለቁ ሰዎች ያስፈልጉታል።
አዲስ ዘመን:- እዚህ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ የለም ማለት ይቻላል? 
አቶ በቀለ:- እውነት ለመናገር ከሆነ ህብረ ብሔር ፓርቲ አለ ብዬ ለመውሰድ አቸገራለሁ፤ ምናልባት አሉ የሚባሉት ከአንዳንድ ብሔሮች የተውጣጡ ጥቂት ሰዎችን በአባልነት ይዘው ሊሆን ይችላል ሆኖም የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ሊያነሱና ሊያስተጋቡ የሚችሉ ሆነው ግን አላገኘኋቸውም። ስለዚህ የዘውግ ፖለቲካ ይቀራል የሚል እምነትም የለኝም። መቅረት አለበት ብዬም አላስብም።
አዲስ ዘመን:- ድምጻቸው አልተሰማም የሚባሉት ብሔሮች የትኞቹ ናቸው? 
አቶ በቀለ:- ብዙ አሉ፤ ሸኮ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እንዲሁም ክልሎች ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ፓርቲዎቹም ህብረ ብሔር ነን ይላሉ እንጂ በነዚህ ክልሎች ውስጥ ሆነው ድምጻቸው የታፈኑ ወገኖችን ችግር የሚያነሱ አይደሉም። ለምሳሌ የሸኮን ህዝብ ጥያቄ እንደ ጥያቄ አድርገው የሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው አላውቅም፤ የቅማንት ህዝብ ችግር አልፎ አልፎ ይነሳል እንጂ ያን ያህል ጉዳዬ የሚለው የለም፤ በሌሎችም ክልሎች ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች በየጊዜው የተለያዩ መድሎዎ ሲፈጸሙባቸውና ጭቆና ሲደርስባቸው ይታያል፤ ግን ከተወሰኑ ትላልቅ ከሚባሉት ብሔሮች አልፎ ወይም ደግሞ ትንንሽ የሚባሉትን ለማጥቃት ከመጠቀም ያለፈ የእነሱን ችግርና ብሶት የሚያስተጋባ ፓርቲ አልተፈጠረም። በመሆኑም የብሔር ፖለቲካ አስፈላጊና መቅረት የሌለበት ነው።
አዲስ ዘመን:- የብሔር ፖለቲካ እርሶ እንዳሉት አስፈላጊ ቢመስልም ግን አገርን በማፍረስ ደግሞ ሚና አለው ይባላል?
አቶ በቀለ:- አገርን የሚያፈርሰው ሰዎች በብሔር መደራጀታቸው ሳይሆን የህዝብ ጥያቄ የማይመለስ ከሆነ ነው። ፓርቲው በማንኛው መልኩ ተደራጅቶ የህዝብን ብሶት ማድመጥ በዛውም መመለስ ከቻለ እኩልነትን ማስፈን ከተሳካለት፣ ኢ- ፍትሀዊነትን እንዲሁም ኢ- ዴሞክራሲን የሚዋጋ ከሆነ እንኳን አገር ሊበትን በተቃራኒው ገንቢ ነው የሚሆነው። ግን ዛሬ ይህ ነገር ጠፋ ነው እያልን ያለነው። አንድ ብሔር በቁጥር እንኳን አናሳ ሆኖ እያለ የሚጮህለት ካለው ይደመጣል አንዳንዱ ደግሞ ብዙም ቢሆን ድምጹን የሚያሰማለት ስለሌለ ከምንም የማይቆጠር ይሆናል። በመሆኑ አገር የሚያፈርሰው እኔ ብቻ ነኝ ለአገሬ የማስበው እኔ ከማስበው ውጪ ሌላ አስተሳሰብ የለም ብሎ ከማሰብ እንጂ ይህ ሁሉ የህዝብ ብሶት ባለበት አገር ላይ የብሔር ፖለቲካ አገር ያፈርሳል ወይም እያፈረሰ ነው የሚለው ተገቢነት የሌለውና እኛም የማንቀበለው ሀሳብ ነው።
አዲስ ዘመን:- እስር ቤት ሆነውም ሆነ ከወጡ በኋላ ኢትዮጵያዊነትን በጣም ያቀነቅኑ ነበር፤ አሁን ግን ይህንን አስተሳሰብዎን የተዉ የሚያስመስሉ አንዳንድ ተግባሮች ይታይቦታልና በዚህ ላይ ያልዎት ሀሳብ ምን ይመስላል? 
አቶ በቀለ:- እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ላይ ተደራድሬ አላውቅም። ኢትዮጵያዊነቴን የማምነው ለፖለቲካ ስልጣን አልያም ሰው እንዲያወድሰኝና እንዲያሞግሰኝ ብዬ ሳይሆን ማንም የሰጠኝ ደግሞም የሚከለክለኝ ባለመሆኑና እኔም ስለምፈልገውና ስለምወደው ነው። እኔ እኮ ኢትዮጵያዊም ሆኜ ሌሎች ብዙ ማንነቶች ያሉኝ ሰውም ነኝ። ለምሳሌ በብሔሬ ኦሮሞ ነኝ፣ ከተማሩት ውስጥ እመደባለሁ፣ በሙያዬ መምህር ነኝ እነዚህ ሁሉ ግን ኢትዮጵያዊነቴን የሚያስረሱኝ ወይም ደግሞ ወደኋላ የሚመልሱኝ አይደሉም። አስተማሪን የሚነካ ነገር ባገኝ ከእነሱ ወገን ሆኜ እታገላለሁ፤ ይህንን ሳደርግ ደግሞ ሀኪሞችን ወይም ኢንጂነሮችን ለማጥፋት አይደለም፤ የኦሮሞ መብት በሚነካበት ጊዜ እናገራለሁ ይህም ሲሆን ደግሞ ሌሎቹን ብሔሮች ለማጥፋት አይደለም።
በኢትዮጵያዊነቴ ሲመጣብኝ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ለአገሬ እቆማለሁ። ግን ሰዎች ኢትዮጵያዊነትን ራሳቸው ሰጥተው መውሰድ ይፈልጋሉ፤ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሰው ኢትዮጵያዊ ነው ብለው አያስቡም ይህ ግን ስህተት ነው። ኢትዮጵያዊ መሆን የሌላውንም መብት ማክበር ነው። የማያከብረውንም ደግሞ ምክንያቱን በመጠየቅ መዋጋት ነው፤ እኔ የማደርገውም ይህንኑ ነው። አሁን በኦሮሞ ፓርቲ ውስጥ ተደራጅቼ ስላለሁ ስለ ኦሮሞ እንዳወራ አይፈልጉም ማንነት ግን ማንነት ነው፤ ሰው ወንድ ሆኖ ሴት ነኝ ሴት ሆኖ ወንድ ነኝ ማለት እንደማይችል ሁሉ ኢትዮጵያዊነቴን ከኦሮሞነቴ ልነጥለው አልችልም።
ሌላው ኢትዮጵያዊ እንደዛው ነው አንዱ ያለአንዱ መኖር አይችልም ምክንያቱም ተጋብተናል፣ ተዋልደናል፣ በንግድ፣ በስራ፣ በትምህርት በተለያዩ መንገዶች እንገናኛለን፤ ይህ ደግሞ ወደፊትም የሚቀጥል ነው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ የያዙትን ማንነት ይዘው የጋራ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር አገራቸው ናት። እዚህ ላይ ኢትዮጵያዊነት ማለት አማርኛ ማስተማር ብቻ ከሆነ ትክክል አይደለም። በኢትዮጵያዊነት ስም ሌላ ነገር ለመጫን የሚፈልጉ ሰዎች በሚኖሩበት ጊዜ አምቢ ማለት ኢትዮጵያዊነታችንን መካድ አድርጎ ማቅረብ በዛ መልክ ሰዎችን መሳል ትርጉም የሌለው ነገር ነው።
አዲስ ዘመን:- በቅርቡ ግን ከ ኦ ቢ ኤን ቴሌቭዥን ጋር በነበርዎት ቆይታ የኦሮምኛን ቋንቋ ለማሳደግ ይጠቅማል በሚል የሰነዘሩት ሀሳብ በጣም መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ አሁን ከላይ የነገሩኝን ነገር የሚያፈርስ ሆኖብኛልና እንደው በዚህስ ላይ ያልዎት ሀሳብ ምን ይመስላል? 
አቶ በቀለ:- በኦሮሚኛ ቋንቋ እድገት ዙሪያ የተናገርኩት ወይም የሰጠሁት ሀሳብ በትክክል ለህዝብ አልደረሰም። የተረጎመውም አካል በትክክል አልተረጎመውም፤ የተተረጎመበት አውድም ሙሉ ሀሳቡን የሚያንጸባርቅ አይደለም። ይህ በመሆኑ ደግሞ በእኔ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ተከፍቶብኛል። እኔ ያልኩት « ቋንቋን ለማዳበር ኢኮኖሚ ወሳኝ ነገር ነው ። ስለዚህ ቋንቋ እንዲያድግ ከተፈለገ አንድ ህዝብ በሚኖርበት መልከአምድራዊ ቦታ በራሱ ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኝ የመጠየቅ መብቱ ህገ መንግሥታዊ ከመሆኑም በላይ ማንም ሊከለክለው የማይችል ነው።
በመሆኑም የምታስተምረኝ ከሆነ በራሴ ቋንቋ፣ የምታገለግለኝም በራሴ ቋንቋ መሆን አለበት ለእኔ ልትሸጥ የምትፈልገው ነገር ካለ እኔ በምሰማው ቋንቋ ሽጥለኝ ነው ያልኩት»። ይህ ደግሞ ጤነኛ የሆነና ማንኛውም ህዝብ ቋንቋውን ለማሳደግ የሚጠቀምበት አካሄድ ነው። ሌላው አገልግሎት በመስጠት ገንዘብን ወይም ደግሞ ሀብትን የሚፈልግ ካለ ቋንቋውን ሳይወድ ገንዘቡን መፈለግ አግባብ አይደለምና ሀብቱን እንደሚፈልግ ሁሉ ቋንቋውንም ማወቅ አለበት እርሱ በያዘው አገልግሎት እኔ ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር እኔም ቋንቋውን እንድሰማ እርሱም እንዲሰማ አደርጋለሁ ማለት ነው ።
 ይህ ደግሞ ጤነኛ ውድድር ነው። በሌላ በኩልም እኔም ከብሔሬ ውጪ ሌላውም እንደዛው ቋንቋን መስማትና መግባባት እንዲችል ዕድል ይፈጥራል፤ ይህ ደግሞ ለልጅ ልጆቻችን መልካም ከመሆኑም በላይ ከአንድ በላይ ቋንቋን የምናውቅ ያደርገናል። የአንድ ቋንቋ የበላይነት ቀርቶ የተመጣጠነ የቋንቋ እድገት እንዲኖርም ያስችላል። የማንም ቋንቋ ከማንም አይበልጥም፤ አያንስም። አንዱ የአንዱን ቋንቋ ማወቁ ይጠቅመው ይሆናል እንጂ አይጎዳም፤ ይህንን አድርገን ደግሞ አገራችንን ያለ ሁከት ወደፊት ማራመድ እንችላለን። አዲስ ዘመን:- አንዳንዶች ይህንን ሁኔታ ግን ከአማራ ጥላቻ ጋር ያያይዙታልና ምን ይላሉ? አቶ በቀለ:- በምን መንገድ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል? ድሮም ሆነ አሁን በርካታ የአማራ ጓደኞች አሉኝ።
አዲስ ዘመን:- ባለቤትዎም አማራ ናቸው? 
አቶ በቀለ:- አይ እርሷ እንኳን አማራ አይደለችም። ኦሮሞ ናት። ይህ እንደተባለ አይቻለሁ ሰምቻለሁ፤ ግን ባለቤታቸው ተብለው የተለጠፉት ሴት ከእኔ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የማላውቃቸው ሴት ናቸው። በመሆኑም እኔ ያልኩት ቋንቋችንን እናሳድግ እንጂ የሌላውን ቋንቋ እንደፍጥጥ፣ እንጥላ ወይም አንናገር አይደለም፤ እዚህ ላይ ግን ቋንቋው የእኔ ይበልጣልና ልጫን ከተባለ ያኔ ጦርነትም ሊመጣ ይችላል። በመሆኑም ይሄኛውም ለመማር ይሞክር ያኛውም ለመማር ይሂድ ነው ሀሳቡ፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ግንኙነታችን ይጠናከራል፣ በሰላም አብረን ለመኖር ምቹ ሁኔታን እንፈጥራለን።
አዲስ ዘመን:- የሀሰት ወሬ እያናፈሱ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨትን ስራ ላይ ስላለው የማህበራዊ ሚዲያ ምን ይላሉ? 
አቶ በቀለ:- ማህበራዊ ሚዲያው የማይለው ነገር የለም፤ እዛ ላይ ያሉ ሰዎች ከዚህ ቀደምም የኦሮሞ ፓርቲዎች ሆነን መግለጫ አወጥተን በነበረበት ወቀት መግለጫውን ያነበብኩት እኔ ነበርኩና የመግለጫው ይዘትና ሀሳቡ ላይ ሳይሆን በእኔ ማንነትና ስብዕና ዙሪያ ብዙ ነገር ተናግረዋል፣ ጽፈዋል፣ ተሳድበዋል፣ አስፈራርተዋል። ይህ አላማው በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውይይትና ክርክር አደርጎ ልክ የሆነና ያልሆነን ነገር የማጥራት ሳይሆን ግለሰቦችን በተለይም ሰው ይሰማቸዋል የሚባሉ ሰዎችን ስም በማጥፋትና ከፖለቲካ አለም ውጪ አድርጎ ለመተካት ያለመ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን:- በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢሳት አገሪቱን አንድ የማድረግ ሚና እየተጫወተ አለመሆኑን ተናግረው ነበር፤ አሁንስ በዚህ ላይ ያለዎት አቋም ተቀይሯል? ሚዲያውስ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል? 
አቶ በቀለ:- አሁን ላይ በቀለ እንዲህ በማለቱ አገር ሊያፈርስ ነው እያሉ ከሚያናፍሱት ወሬ በላይ አገር ሊያፈርስ ተዘጋጅቶ ያለው ኢሳት ነው። አሁንም እምነቴ ወደፊትም ዞር ብሎ ኢሳት የሚያስተላልፈውን ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚተነትኑ ሀሳቦችን የሚያይ ቢኖር አገር እያፈረሰ ያለ ተቋም መሆኑን ይረዳል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን የእነሱን ሀሳብ የሚጋሩት በፖለቲካው በኢኮኖሚው አቅምና እውቀት ያላቸው በመሆናቸው እስከ አሁን ሳይነኩ ለፍርድም ሳይቀርቡ እያመሱና እያተራመሱ ያሉ ነው የሚመስለኝ በእኔ እምነት። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች እየቆዩ ሲሄዱ ተተንትነው ለፍርድና ለታሪክ ይቀርባሉ የሚል እምነትም አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ መፈናቀሎች እዚህም እዚያም ግጭቶች እየበዙ ነውና እነዚህን ነገሮች ለማስቆም ከመንግሥት ምን ይጠበቃል? 
አቶ በቀለ፡- በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ አለመረጋጋቶች እውነት ለመናገር የሚያሰጉ ናቸው። በሁሉም ክልል በሚባል ደረጃ ያለመረጋጋቶች አሉ፤ እነዚህ ደግሞ በጊዜ መፍትሔ እየተሰጣቸው ካለመሆኑም በላይ የተለያዩ ጥፋቶችን ያጠፉ አካላት ያለማንም ጠያቂነት ደረታቸውን ነፍተው እየኖሩ ነው፤ በመሆኑም ህግ የማስከበር ስርዓት የማስጠበቅ ስራው በጣም የላላ ነው የሚመስለኝ። ሁኔታው ደግሞ በዚሁ ከቀጠለ መቆጣጣር ወደማንችልበት ደረጃና አገርን ሊያፈረስ በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ እንገባለን የሚል ስጋት አለኝ። በመሆኑም ከሚገባው በላይ ዝም ማለት አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ለትልቅ ችግር የሚዳርገን በመሆኑ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ቶሎ ማስተካከል አለበት።
አዲስ ዘመን:- ከፊታችን ምርጫ እየመጣ ነው፤ እርስዎ ደግሞ በአንድ ወቅት በሌሎች አገሮች እንደሚታየው አይነት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ እንዲመጣ እታገላለሁ ብለው ነበርና፤ እንደው ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚመጣበት ይሆናል ብሎ ተስፋ ማድረግስ ይቻላል?
 አቶ በቀለ:- እኔ አሁን የማውቀው በራሳችን በፓርቲያችን በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ነው፤ እኛ ከዚህ በፊትም ስናደርግ እንደነበረው ምንም ነገር ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ምርጫው እንዲካሄድና እንዲጠቃለል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ምርጫው በምንም ዓይነት መንገድ ቢሄድም ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ከተቻለ ስልጣን ለመያዝ ካልሆነም ደግሞ ተቃዋሚ ሆነ ለመቀጠል፣ ችግሮች የሚከሰቱ ከሆነ ደግሞ ተቃውሟችንን ለአለም ህዝብ ማሳወቃችንን መቀጠል አቋማችን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በግሌ የምረዳው መንግሥት ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ፍላጎቱና አቅሙ እንዳለው ነው።
አሁን ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በምርጫ ከተሸነፉ በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ዝግጁ እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው፤ ይህም ተገቢ ከመሆኑም በላይ በቃላቸው ይጸናሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ምርጫ ቦርዱም ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ሊታመኑ የሚችሉ ሰዎች የአመራር ቦታውን ይዘውታል፤ ወደፊትም ሪፎርሙ እንደሚቀጥል ሳስብ የተሻለ ምርጫ ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ከአሁኑ እኛ እናሸንፋለን ሳናሸንፈም ስልጣን ይዘናል የሚሉ አካላት ችግር ይፈጥሩ እንደሆነ አላውቅም አንጂ በሌሎች ፓርቲዎች በኩል ያለው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ምርጫው ችግር ያለበት ይሆናል ብዬ አንዳላስብ ያደርገኛል።
 አዲስ ዘመን:- የለውጡ ኃይል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ አንድ ዓመት አስቆጥሯልና ይህንን ጉዞ እርስዎ እንዴት ያዩታል? 
አቶ በቀለ:- ከሁለትና ሶሰት ዓመት በፊት ከነበረው ዛሬ የተሻለ የነጻነት አየር ያለ ይመስላል፤ በውጭ አገር በስደት የነበሩ በርካታ ሰዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ ችለዋል፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ወደ አገርህ አትገባም የሚባል ዜጋ የለም። ስለዚህ ይህ ትልቅ እመርታ ነው። በፖለቲካ ጉዳይ አስር ቤት የነበሩ ሰዎች በሙሉ ተፈተዋል፤ ይህም ትልቅ ጉዳይ ነው። አሁን በሚሄድበት ቦታ ላይ ማን ይከተለኛል? ምን ይፈጠራል? እያልን እየሰጋን እየፈራንና እየተባን ጥላውን እየሸሸ የሚሄድ ሰው የለም፤ እንደ ልብ ወጥቶ መግባት ተችሏል። በሌላ በኩል ግን በቶሎ የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው ሲገባ ያልተወሰደባቸው፤ መሻሻል ሲገባቸው ያልተሻሻሉ ጉዳዮች አሉ።
ኢህአዴግ ውስጥ ስልጣን ላይ የነበሩ በብዙ ሙስናና ኢ-ፍትሀዊ ድርጊቶች ሲጠረጠሩ የነበሩ ግለሰቦች እስከ አሁን ያለመያዛቸውና አሁንም በብዙ ቦታዎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ሊታይ የሚገባው ሲሆን ወደፊትም ለመንግሥት ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት አለኝ። የህዝቦች መፈናቀልና እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶች ትኩረት ባለማግኘታቸው አሁንም ቀጥለዋል፤ የመንግሥት ድክመት ነው ብዬ አስባለሁ፤ አሁንም በተለይም በምዕራቡና በደቡቡ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከኦነግ ጋር በተያያዘ ሰዎች እየታሰሩ መሆናቸውና አለመረጋጋት መኖሩ ከባድ ነው። በመሆኑም ኢህአዴግ የመጀመሪያ ሰሞን ላይ ቃል ገብቶ እርምጃ መውሰድ እንደጀመረ ሁሉ ታች ባሉ አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው የማስተካከያ ስራ በነበረውና በታሰበው ልክ መሄድ ያለመቻሉ ከባድ ችግር ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
Filed in: Amharic