>
5:13 pm - Thursday April 19, 1117

ኦዴፓ ኦነግን በአንቀልባ አዝሎ የሚዞረው ለምንድነው?! (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)

ኦዴፓ ኦነግን በአንቀልባ አዝሎ የሚዞረው ለምንድነው?!
ቴዎድሮስ ሀይለማርያም
የለውጡ ፓትረያርኮች አብይና ለማ የገቡበት የኦነግ እንቆቅልሽ የኢትዮጵያዊነት ካርዳቸውን አስበልቷቸዋል!!
         —-
ዛሬ ሀገር የማተራመስ ተግባሩን በግልፅ ያወጀው  ኦነግ በዚያ በአፍላ የመደመር ወረት  የእርቀ ሰላም ጥሪውን ማቄን ጨርቄን ሳይሉ  ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት  ከጎረፉት ተቃዋሚ ታጋዮች ፣ አትጊዎች ፣  ነፃ አውጭ ግንባሮች ፣ ወዘተ አንዱ ነው።
          በወቅቱ በፍቅርና በይቅርታ መንፈስ ብናልፈውም  ኦነግ  ከሁሉ  በተለየ ምሥጢራዊ ድርድር  ብረት ሳያወርድ ሰተት ብሎ የገባ  ብቸኛው ቡድን መሆኑን እናውቃለን። በሀገር ቤትም ኦነግ የራሱ  ግዛት ተቆርጦለት ፣ ቀለብ ተሰፍሮለት ፣ መንግሥት ተካፍሎ ፣ ሲያሰኘው ሺህዎችን አፈናቅሎ ፣  ሲያሻው ባንክ ገልብጦ   እንደ ስለት ልጅ ተቀማጥሎ የሚኖር ብቸኛው አፄ በጉልበቱ ነው።
         ይህም ሆኖ ከማለዳው ለታዛቢ ግራ የሚያጋባው  ኦነግ  በሰው  ፊት እየተገረፈ  ከሚያኖረው ከኦዴፓ ጋራ መዘረጣጠጡና መተባበቱ ነበር።  ኦዴፓ በጭራሽ  የኦነግን ክፉ መስማት አይፈልግም። ጠ/ሚ አብይም ያ ቅቤ የሚያነጥር አንደበታቸው የሚቆለፈው ለኦነግ ሲሆን ብቻ ነው። ከሁለቱ ዓይን ያወጣ ድርጊት ይልቅ  የሚያሳፍረው ደግሞ   እንደ ግንቦት 7 ያሉ  የእንጀራ ልጆች  መድልኦውን በፀጋ ተቀብለው መኖራቸው ነው።
        የለውጡ ፓትረያርኮች አብይና ለማ የገቡበት የኦነግ እንቆቅልሽ የኢትዮጵያዊነት ካርዳቸውን አስበልቷቸዋል!!
 በአሁኑ ወቅት  የኦዴፓ ፅንፈኛ ክንፍ በኦነግ አበጋዝነት ወጣቶችን ሜንጫ አስታጥቆ ሽብር ከመንዛት የሁሊጋን ፖለቲካ አልፎ  በወታደራዊ ኃይል ማህበረሰቦች ላይ ወረራ በመክፈት ለሀገር ደህንነት ትልቅ አደጋ ደቅኗል።
        ኦዴፓ ይህን ያህል ርቀት ኦነግን በአንቀልባ አዝሎ መኖር ለምን መረጠ? ኦነግስ ልዩ ውለታውን ከመጤፍ ሳይቆጥር ለምን  ከመንግሥት በላይ እንደ ልቤ ልፏልል አለ? የሚሉትን  ጥያቄዎች ለመመለስ  ከነገረ ፖለቲካ ጋር የተዛመዱ ሁለት ተጨባጭ የኃይልና የሥልጣን አሰላለፍ መንስኤዎች ይታዩኛል።
   1ኛ-  “ታላቋ ኦሮሚያ”
         ዋነኛው  የኦዴፓና ኦነግ ጥምረት መሰረት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ፖለቲካ አንፃር ያላቸው የጋራ ግብ ነው። ሁለቱም “የታላቋ ኦሮሚያ” ራዕይ አቀንቃኞች ናቸው። ቢቻል የኦሮሞ ልዕልናና  ማዕከላዊ ሚና የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ መፍጠር (የኦዴፓ መነሻ አቋም)  ፣ ካልሆነ ደግሞ የኦሮሚያ ነፃና ሉዐላዊ ሀገረ መንግሥትነት  (የኦነግ መነሻ አቋም) ይሻሉ።
         ኦነግና ኦዴፓ  ልዩነታቸው በማስፈፀሚያ መንገድና ስልት ረገድ ብቻ ነው። የኦዴፓ “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ” ለሥልጣን  የሚያዋጣ ስልት  ነው። ኦነግ በፊናው በኦሮሞ ስም እየማለ ህዝባዊ መሰረቱን ማጥበቅ እንዳለበት ያምናል። ሁለቱም የሚመጋገቡበት ነጥቦች አሉ።
     2ኛ-“የኬኛ ኬኛ ፖለቲካ” 
         ሌላው የኦዴፓና ኦነግ ጥምረት መልክ በውስጣቸው    አንዱ ሌላውን በመዋጥ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ተፈጥሯዊ ሽኩቻ ነው። “የኬኛ” ፖለቲካ ማቆሚያ ስለሌለው  እዚህም እዚያም መናቆር ማስከተሉ አይቀርም።
         በዚህ ረገድ ኦዴፓ በፌዴራልም በክልልም የመንግሥት ሥልጣን ፣ ሀብትና መዋቅር የሚያዝ ነው። ባለፉት 28 ዓመታትም ሰፊ ድርጅታዊ መሰረት  ለመዘርጋት ችሏል። የበላይነት እንደሚሰማው አይጠረጠርም።
        ኦነግ በፊናው የአቅሙ ምንጭ  የኦሮሞን ህዝብ በተለይም የወጣቱንና ምሁሩን ልብና አእምሮ  መግዛቱ ላይ ነው።  በተጨማሪም ኦነግ የአዴፓን መዋቅር  እሰከ አናት  ደረጃ ሰርጎ መግባቱ የተሳካለት ይመስላል።  ይህም ለኦነግ የልብ ልብ ሲሰጠው ፣  በኦዴፓ ላይ ከፍተኛ ስጋት አሳድሮበታል።
        የኦነግ ሠራዊት ባይናቅም ሚዛን የሚደፋ ተፅእኖ የሚኖረው ከሁለቱ ድርጅቶች ውስጣዊ  ትግል ይልቅ ከኦሮሚያ ልዩ ሃይል ጋር ተደምሮ ከሌሎች ተፎካካሪ ክልሎች ጋር ሲናፀር ነው። ይህም ዞሮ በክፉ ቀን  የጋራ ጥቅም የሚያስገኝ እሴት ነው።
የፖለቲካ ተውኔት
        ከዚህ ቀደም ኦዴፓና ኦነግ  በአምቦ አጠቃላይ እርቅና ስምምነት አደረጉ ሲባል ፣ ይሄ  ነገር የፖለቲካ ተውኔት ነው ብያለሁ።  በበኩሌ ሁለቱ ድርጅቶች በአንድ ሳንባ የሚተነፍሱ ፣  ለአንድ ዓላማ በተለያየ መንገድ እየተናበቡ የሚሰሩ ናቸው የሚል እምነት አለኝ።
      ልዩነቱ   ኦዴፓ ሀገር መሪ  ድርጅት  በመሆኑ ይነስም ይብዛ የፓርቲና የህግ ተጠያቂነት አለበት። በሌላ በኩል   ኦነግ ገና ያልተገራና አንፃራዊ የአመፃ ነፃነት ይዞ እንዲቆይ ተደርጓል። በዚህም ብልሃት ኦዴፓ  ህጋዊነቱን አለቅጥ ሳያጣ መፈፀም የማይችለውን ቆሻሻ ሥራ በኦነግ አማካኝነት በአመፅና በሃይል ያከናውናል።
        ሰሞኑን ኦነግ  የአምቦውን  ተውኔታዊ  እርቅ አፍርሻለሁ ሲል ያወጣው መግለጫ በሁለት አንኳር ጉዳዮች ይህንን ሙግት ያጠናክርልናል። አንደኛው  ኦነግ “ትጥቅ ፈታ ፣ ካምፕ ገባ” የሚባለው ነገር የለየለት  ቅጥፈት መሆኑን።  ሁለተኛው ደግሞ ኦነግ በኦዴፓ የይሁንታ ዝምታና ድጋፍ ወደ ቆሻሻ  የሽብር ጥቃት   ሲገባ በአዲስ አበባ ያለውን ጥምር የኦዴፓና—  ኦነግ አመራር ከተጠያቂነት  ነፃ ለማድረግ መፈለጉን።
 
     የሀገር መከላከያ እጣ ፋንታስ?
          እዚህ ላይ አብሮ መነሳት ያለበት በአዲስ መልክ ተዋቀረ የሚባለው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የኦነግ ሠራዊት ግንኙነት ነው። ሲጀመር  በአንድ ሀገር ሁለት ሠራዊት መኖሩ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ጠ/ሚ አብይ መከላከያውን ከላይ እስከ ታች ለመቆጣጠር ያሳዩትና በወጉ ያላስተባበሉት   ጉጉት ነገሩን  የበለጠ አስጊ ያደርገዋል።
         እንደሚታማውም ይህ ሀገራዊ ሠራዊት በኦዴፓ— ኦነግ ቁጥጥር ስር ወድቋል ወይ?  ከሰሞኑ በአማራ ክልል  በኦነግ ሃይል እየደረሰ ባለው ወረራና ጭፍጨፋ የመከላከያ ሠራዊት ሚና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።  የሚፈፀመውን ጥቃት በቸልታ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ለኦነግ ወረራ  የሎጂስቲክ ድጋፍ እየሰጠ ነው የሚሉ ውንጀላዎች እየተሰሙ ነው። መከላከያ በማያገባው  ተሽቀዳድሞ  ያወጣው መግለጫ   የኦነግን ስም ለመጠበቅና እድፉን ወደሌሎች ለማላከክ  መጨነቁን ይጠቁማል። ለምን?
        በእውነቱ  ይህ  የቅጥረኝነት ጥርጣሬ መነሳቱ በራሱ የሠራዊቱን አንድነት ክፉኛ  ማናጋቱ አይቀርም። ኦነግ የመከላከያ ዩኒፎርም ለብሶ በመሪነት ከተሰለፈ ፣  ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ውሃ  በላው ማለት ነው። ሌሎች የሠራዊቱ አባላት በዚህ ሀገር አፍራሽ ተልዕኮ ይተባበራሉ ማለት ዘበት ነው። ቢያንስ ደግሞ  ለየወጡበት ብሄረሰቦችና ለግል እጣ ፈንታቸውም ሲሉ ጥያቄዎች ማንሳታቸውና አጥጋቢ ምላሽ ካላገኙም ወደ አመፅ መገፋፋታቸው አይቀርም።
        በተለይ በተለይ የኦነግ አዲሱ የባለ አራት ዕዝ አወቃቀር ይህን ቢሆን ታሳቢ አድርጎ መከላከያውን ለመተካት የታለመ ከሆነ ጉድ የምናይበት ወቅት ቅርብ ነው። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የብሄራዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ በዚህ ጉዳይ ላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ እንጠይቃለን።
       ፈጣሪ  ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከክፉ ይጠብቅልን!!
Filed in: Amharic